“የአርብ ጠንካራ እጆች…!”

0
65

“የዘመናዊ ሕክምና አባት” ተብሎ የሚጠራው የግሪኩ ታዋቂ ሐኪም ሂፖክራተስ ከ460 እስከ 370 ዓ.ዓ በነበረበት ዘመን የወባን ምልክቶች በዝርዝር መዝግቦ ነበር፡፡ በዚያን ዘመን ግን የበሽታው መንስኤ ምን እንደሆነ ማንም አያውቅም ነበር፡፡ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ሰዎች ወባ ከረግረጋማ   ቦታዎች በሚወጣ የተበከለ አየር ምክንያት እንደሚከሰት ያምኑ ነበር፡፡ ይህን   ተከትሎም ወባ ማላሪያ (በጣሊያንኛ ቋንቋ መጥፎ አየር) የሚል ስያሜ እንደተሰጠው የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ አመላክቷል፡፡

እ.አ.አ በ1880 የፈረንሳይ ወታደራዊ ሐኪም ቻርልስ ሉዊ አልፎንስ ላቨራን በአልጄሪያ ውስጥ የወባ ታካሚዎችን ደም በላብራቶሪ በመመርመር የበሽታውን ጥገኛ ፍጥረት ማግኘት ችሏል፡፡ ይህ ግኝት የወባን ምስጢር የገለጠ ታላቅ የሳይንስ ድል ነበር፡፡ ከ17 ዓመታት በኋላ  በ1897እ.አ.አ ብሪታኒያዊው ሐኪም ሮናልድ ሮስ በሕንድ ያደረገው ጥናት ደግሞ ወባ በሴት አኖፊሊስ በተሰኘች ትንኝ ንክሻ እንደሚተላለፍ አረጋገጠ። ይህም ለወባ መከላከል እና መቆጣጠር አዲስ በር ከፈተ፡፡

ይህ ሁሉ አንድ እውነትን ያስታውሰናል፤ ወባ የትናንት ታሪክ ብቻ አይደለም፤ የዛሬም ፈተና ነው፡፡ በእውቀት፣ በምርምር እና በመከላከል የሰው ልጅ ከጥንት ጀምሮ ከተፋለመው ከዚህ በሽታ ጋር ያለው ጦርነት ገና አላበቃም፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያትተው የወባ በሽታ ስርጭት ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ያለው ቢሆንም በድሃ ሀገራት ችግሩ የከፋ ነው፡፡ ለአብነትም ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት በሽታው በገዳይነቱ ከቀዳሚዎቹ መካከል ተጠቅሷል፡፡

መንስኤ

የፕላዝሞዲየም ጥገኛ ተውሳኮች ወባን ያስከትላሉ፡፡ ሴቷ የወባ ትንኝ የተበከለውን ሰው ስትነክስ ጥገኛ ተውሳኩን (ፕላዝሞዲየም) ትሸከማለች፡፡ በዚህ ወቅት ጤነኛን ሰው ስትነክስ ተህዋሱ ወደ ጤነኛው ይተላለፋል፡፡ ጥገኛ ተውሳኩም በጉበት ውስጥ ተባዝቶ ደም ውስጥ ይሰራጫል፡፡ በዚህ መንገድ የበሽታው ስርጭት በሰውነት ውስጥ ይስፋፋል፡፡

በተጨማሪም በእርግዝና ወይም በወሊድ እንዲሁም በደም ልገሳ ወቅት በሽታው ከሰው ወደ ሰው ሊሰራጭ እንደሚችል የድርጅቱ መረጃ ያመላክታል፡፡ የወባ በሽታ የተለያዩ የወረርሽኝ ወቅቶች እንዳሉት የሚጠቁመው መረጃው ይህም እንደየ ሀገራቱ የአየር ንብረት መለዋወጥ ከወቅቶች ጋር ይወሰናል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ እንዳደረገው ሰዎችን ሊበክሉ የሚችሉ አምስት ዓይነቶች የፕላዝሞዲየም ጥገኛ ተውሳኮች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ፕላዝሞዲየም ፋልሲፓረም (Falciparum) እና ፕላዝሞዲየም ቫይቫክስ (Vivax) በጣም የተለመዱ ሲሆኑ ፋልሲፓረም የተባለው ደግሞ ከባድ ሕመምን በማስከተል በገዳይነቱ ይታወቃል፡፡

ምልክቶች

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመላክተው የወባ በሽታ ከቀላል እስከ ከባድ ምልክቶችን ያሳያል፤ አብዛኛውን ጊዜ ከሰባት እስከ 14 ባሉት ቀናት እና ከእነዚህ  በኋላ  ምልክቶቹ ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ለበርካታ ቀናት ያህልም ምልክት ሳያሳይ ሊቆይ ይችላል፡፡ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ማንቀጥቀጥ፣ ራስ ምታት፣ የጡንቻ ሕመም፣ ድካም፣ የመተንፈስ ችግር፣ ተቅማጥ፣ ማቅለሽለሽ ወይም ማስታወክ፣ የቆዳ ቢጫ ወይም የዐይን ቀለም ነጭ መሆን ዋና ዋና የወባ ምልክቶች ናቸው፡፡ ከዚህም አለፍ ሲል ራስን እስከ መሳት የደረሰ ከባድ የሕመም ምልክት ሊኖር ይችላል፡፡

መከላከያዎቹ

የወባ በሽታ መከላከያ ዘዴዎች በዋነኝነት በሁለት ይከፈላሉ፤ በሽታውን አስተላላፊ የወባ ትንኝ መራቢያ አካባቢ በማጽዳት በበሽታው ከመያዝ በፊት መከላከል (Vector control) እና ከተያዝን ደግሞ በሕክምና (Chemoprevention) የመከላከል አማራጮች ናቸው፡፡ በበሽታው ከመያዝ በፊት የመከላከያ አማራጮችን መተግበር ቀዳሚው ተግባር ነው፡፡ በኬሚካል የተቀባ የአልጋ አጎበር መጠቀም፣ የወባ ትንኝ መራቢያ አካባቢን ማጽዳት ማለትም ረግረጋማ እና ውኃ የሚያቆሩ ቦታዎችን ማዳረቅ፣  ውጤታማ የመከላከል ስልቶች ናቸው፡፡ ከዚህ ባለፈ በሕመሙ ከተያዝን ደግሞ በቶሎ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ ይገባል፡፡ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ በወባ መያዛቸውን ያረጋገጡ ሰዎችም የሚታዘዘውን መድኃኒት   በአግባቡ መውሰድ እንደሚገባ የዓለም ጤና ድርጅት በድረ ገጹ ያሰፈረው መረጃ ይመክራል፡፡

የወባ በሽታ ሁኔታ በአማራ ክልል፡-

በክልሉ ጤና ቢሮ የወባ መከላከል እና መቆጣጠር ፕሮግራም አስተባባሪ  አቶ ዳምጤ ላንክር እንደገለጹት በወረርሽኝ ደረጃ የሚገለጽ ክስተት ባይኖርም የዚህ በጀት ዓመት(ከሀምሌ 2017 ዓ.ም ጀምሮ) የወባ ታማሚዎች ቁጥር ከ2016 ዓ.ም እና ከዚያ በፊት ከነበሩ ዓመታት ጋር ሲነጻጸር አሁንም የበሽታው ስርጭት ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይሁንና  ከ2017 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸር ግን ቀንሷል፡፡

እንደ አስተባባሪው ማብራሪያ በተያዝው በጀት ዓመት አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሰዎች የወባ በሽታ ምርመራ ተደርጎላቸዋል፤ ከእነዚህም ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች የወባ ተህዋስ በደማቸው ተገኝቶባቸዋል፡፡ ከጠቅላላ የወባ ሕሙማን መካከል ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት 13 በመቶ ይሸፍናሉ፡፡

የበሽታው ስርጭት በተለይ የክልሉ ምዕራቡ ክፍል  በየዓመቱ 90 በመቶው ተጠቂ መሆኑን አስተባባሪው ጠቁመዋል፡፡ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የተከናወኑ  ሥራዎችን በተመለከተም አስተባባሪው እንዳብራሩት  ላለፉት ሁለት ዓመታት የወባ ሁኔታ በድንገተኛ የክስተት አስተዳደር ሥርዓት እየተመራ ይገኛል፡፡ በ48 ወረዳዎች የመኝታ አጎበር ስርጭት የተካሄደ ሲሆን 18 ከፍተኛ ስርጭት ባለባቸው ወረዳዎች ደግሞ የቤት ውስጥ የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት ተካሂዷል፡፡ በልማት ቀጣናዎች ከ51ሺህ በላይ የጉልበት ሠራተኞች የወባ ቅድመ መከላክል ሕክምና (Seasonal Chemoprevention) ተሰጥቷል፡፡ የወባ ሕክምናን ለማጠናከርና ሕብረተሰቡ ጥራቱን የጠበቀ የወባ ምርመራና ሕክምና እንዲያገኝም ጄኤስ አይ (JSI)  ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር 48  የጤና ባለሙያዎች  የወባ ሕክምና ሥልጠና አግኝተዋል፡፡

መጭውን የክረምት መግቢያ አስመልክቶ የወባ በሽታ የሚጨምርበት ወቅት በመሆኑ በክልሉ ባሉ ሁሉም ዞኖች እና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከፍተኛ ጫና ላለባቸው ጤና ጣቢያዎች ከ900 በላይ ከሚሆኑ ባለሞያዎችና ኃላፊዎች ጋር የምክክር መድረክ (Advocacy Workshop) ተካሂዷል፡፡ ከፍተኛ የወባ ስርጭት ባለባቸው 10 ወረዳዎችም የቤት ለቤት የወባ ሙቀት ልየታ፣ ምርመራና ሕክምና (Mass Fever Testing Treatment) እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የመድኃኒት እጥረት እንዳያጋጥም ከመድኃኒት አቅራቢ ድርጅት (EPSS) ጋር በቅርበት እየተሠራ ነው፡፡ እስካሁን ባለው ጊዜም እጥረት አላጋጠመም፡፡ “የአርብ ጠንካራ እጆች የወባ ወረርሽኝን ይገታሉ!“ በሚል መሪ ቃልም ጤና ጣቢያ በበላይነት የሚከታተለው የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ በየዕለቱ አርብ  እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ሥራውንም ለማጠናከር የተለያዩ የማነቃቂያ መድረኮች ተዘጋጅተዋል፡፡

ወባን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ያጋጠሙ ችግሮችንም አቶ ዳምጤ ጠቁመዋል፡፡   እነሱም በአንዳንድ ወረዳዎች የአጎበር ስርጭትን  በሚፈለገው ፍጥነት አሰራጭቶ አለመጨረስ፣ ከፍተኛ የወባ ጫና ባለባቸው ወረዳዎች የፀረ ወባ ትንኝ ማጥፊያ  ኬሚካል በበቂ  መጠን ከጤና ሚኒሥቴር አለመመደቡ፣ በቆላማ የልማት ቀጠናዎች ወባ እና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ሥርጭት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የበጀት እጥረት መከሰት፣ ሕብረተሰቡ በወባ መከላከል ሥራ  ላይ ሙሉ ተሳታፊ አለመሆኑ (የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ በየሳምንቱ አለመሥራት፣ ማሕበረሰቡ የተሰጠውን የመኝታ አጎበር በአግባቡ አለመጠቀም፣ ሕመም ሲሰማ ፈጥኖ ወደ ጤና ተቋም አለመሄድ፣ በሃኪም የታዘዘውን መድኃኒት ጨርሶ አለመውሰድ፣ ምርመራ ሳያደርጉ እና የወባ በሽታ ሳይገኝባቸው  በግምት ብቻ መድኃኒት ከፋርማሲዎች ገዝቶ መጠቀም ናቸው፡፡

 

ታዲያ እነዚህን ችግሮች ለመፍታትም በክልሉ በሁሉም ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች የምክክር መድረክ ተዘጋጅቶ ችግሮችን ለይቶ በማውጣት  እንዲፈቱና የመከላከልና የቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ እንዲካሄድ የሚያስችል አሠራር ተዘጋጅቷል፡፡ ከዚህ ባለፈ  የበጅት እጥረቱን ለመቅረፍ ሁሉም ዞኖች ለፕሮግራሙ በጀት እንዲመድቡ እንዲሁም የተገኘን በጀት በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው እቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡

የወባ በሽታን በዘላቂነት ለመፍታት የማሕበረሰቡ ተሳትፎ ቁልፍ ሚና እንዳለው የጠቆሙት  አስተባበባሪው ሕብረተሰቡ በወባ መከላከልና ቁጥጥር ሥራዎች የባለቤትነት ስሜት ኖሮት ሙሉ ተሳትፎ ማድረግ አለበት፡፡ የተሰጠውን የመኝታ አጎበርም በአግባቡ መጠቀም፣  በአካባቢው ያሉ ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ የሆኑ ቦታዎችን በየሳምንቱ ማዳፈንና ማፋሰስ፣ በፀረ ወባ ኬሚካል የተረጩ ቤቶችን ግድግዳ ቢያንስ እስከ ስድስት ወራት ድረስ በጭቃ፣ በእበት፣ በአመድ አለመለቅለቅ፣ ቀለም አለመቀባት፣ በጋዜጣ ወይም በሌሎች ነገሮች አለመሸፈን ይኖርባቸዋል፡፡

የወባ በሽታ ምልክት ወይም የሰውነት ትኩሳት ሲኖርም ፈጥኖ በአካባቢው ወደሚገኝ ጤና ተቋም ሄዶ ምርመራ ማድረግና በሽታው ከተገኘም በሃኪም የታዘዘውን መድኃኒት በሙሉ መውሰድ ወይም ለሌሎች ሰዎች አለማካፈል እና አለማቋረጥ ተገቢ ነው፡፡ ከሕገወጥ የመድኃኒት አዘዋዋሪዎችም መድኃኒት ገዝቶ አለመውሰድም ተገቢ ነው፡፡ ሕክምና ብቻውን ወባን ለመከላከል በቂ ስላልሆነ ህብረተሰቡ በመከላከል ሥራዎች ላይ ተሳታፊ መሆን እና በትኩረት መሥራት  እንዳለበት ምክር ለግሰዋል፡፡

መረጃ

*የዓለም ጤና ድርጅት የ2025 ሪፖርት እንደሚያሳየው  በዓለም ላይ በ2024 ብቻ 282 ሚሊዮን ሰዎች በወባ ተይዘዋል፤ 610ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡

*የወባን በሽታ የምታስተላልፈው ሴቷ አኖፊለስ ትንኝ ሰዎችን የምትነክሰው ከምሽት እስከ ንጋት ባለው ጌዜ ነው፡፡

*በምሽት በተቻለ መጠን ሙሉ ሰውነትዎን የሚሸፍን ልብስ ይልበሱ፡፡

*ትንኞች ጥቁር  ወይም ደማቅ ቀለም ያላቸው ልብሶች ይስቧቸዋል፡፡

ምንጭ፡- የዓለም ጤና ድርጅት ፣የአሜሪካ ሲዲሲ

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here