በአማራ ክልል በ2018/2019 የመኸር ምርት ዘመን አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል። በዚህም ከ205 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
ለዚህ ደግሞ የአፈር ማዳበሪያን በበቂ መጠን በወቅቱ ከማቅረብ በተጨማሪ ዘመናዊ የእርሻ አሠራሮች እየተተገበሩ መሆኑን ነው የቢሮው መረጃ የሚያመላክተው፡፡ ስምንት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ላይ እንደሚውልም ነው የተነገረው፡፡
ይህን መነሻ በማድረግ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮችን እና ሌሎች የዘርፉን ባለድርሻዎች የዕቅድ ዝጅት ሥራዎችን በተመለከተ በኩር በስልክ አነጋግራቸዋለች፡፡
አርሶ አደር መልኬ መለሰ በፎገራ ወረዳ ሽና ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። አርሶ አደሩ በሁለት ሄክታር መሬት በዋናነት ሩዝ እና በቆሎ ለማምረት ማሳቸውን በማዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አርሶ አደር መልኬ ለበኩር በስልክ እንደተናገሩት ምርታማነትን ለመጨመር የበርሚ ኮምፓስት አዘጋጅተው እየተጠቀሙ ነው፤ ስድስት ኩንታል ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያም አዘጋጅተዋል፡፡ ምርጥ ዘር ለመጠቀም መዘጋጀታቸውንም ነው የተናገሩ።
ሆኖም የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ በነጋዴዎች እጅ እየገባ ላልተፈለገ ወጭ እየዳረጋቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡
ሌላው ሐሳባቸውን በስልክ የሰጡን በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የሰቆጣ ከተማ ወለህ 01 ቀበሌ ነዋው አርሶ አደር አማረ ታደሰ ናቸው። አርሶ አደሩ ለ2018/2019 የምርት ዘመን ማሳቸውን በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን መሬታቸውን በማረስ እና በማለስለስ እያዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አርሶ አደሩ እንዳሉት መሬታቸውን ከማረስና ከማለስለስ ባለፈ በቂ በርሚ ኮምፖስት እና ኮምፖስት አዘጋጅተዋል፤ ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያን እና ምርጥ ዘርን በመጠቀም የማሳቸውን ምርታማነት ለመጨመር ተዘጋጅተዋል።
አርሶ አደሩ አክለውም የግብርና ባለሙያዎች ምክረ ሀሳብ እና ክትትል እንዳልተለያቸውም ነው የተናገሩት።
ሌሎች ከተለያዩ አካባቢዎች ያናገርናቸው አርሶ አደሮችም ተመሳሳይ ሐሳብ ነው ያነሱት፤ የሚጠበቅባቸውን እርሻ ሥራ (ማሳን ደጋግሞ ማረስ፣ አስፈላጊ ግብዓቶችን ማዘጋጀት) እያከናወኑ መሆኑንም ነው የተናሩት።
አቶ ውለታው ተረፈ በደቡብ ጎንደር ዞን የፎገራ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ ናቸው፤ እርሳቸው እንዳሉት በ2018/2019 የምርት ዘመን 113 ሺህ 378 ኩንታል የሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዷል፤ ከዚህ ውስጥ 39 ሺህ ኩንል ያህሉን ማቅረብ ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ 632 ኩንታል ያህል ምርጥ ዘር ለማቅረብ መታቀዱን በማንሳት፣ ከ588 በላይ ኩንታል ወደ ወረዳው ገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሜትር ኩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ለመዘጋጀት ታቅዶ እየተሠራ ነው፤ እስካሁን ደግሞ ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሜትር ኩብ በላይ እንደተዘጋጀ አስታውቀዋል፡፡
በበጀት አመቱም 74 ሺህ 700 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ከአንደኛ እርሻ እስከ አራተኛ እርሻ ድረስ የማሳ ዝግጅት መሠራቱን ነው ለበኩር በስልክ ያብራሩት፡፡
ከዚህም ከስድስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የጽ/ቤት ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ የዋግ ኧምራ ብሔረሰብ አስደተዳደር ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲሱ ወልዴ ከበኩር ጋር ባደረጉት ቆይታ በ2018/2019 የምርት ዘመን 120 ሺህ 638 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን መታቀዱን ተናግረዋል። ከዚህም አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ነው ያሉት።
ለዕቅዱ ስኬት ታዲያ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፤ ከዞን እስከ ቀበሌ ያሉ ፈፃሚዎችን የማዘጋጀት ደግሞ አንደኛው ነው። ለአርሶ አደሮችም በገበሬዎች ማሰልጠኛ ማዕከላት የክህሎት ስልጠና በባለሙያዎች መሰጠቱን ነው መምሪያ ኃላፊው ያብራሩት።
ከዚህ ጎን ለጎንም የማሳ ዝግጅት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል። ከ307 ሺህ በላይ ሜትር ኩብ ኮምፖስት መዘጋጀቱን የጠቆሙት አቶ አዲሱ “ከዚህ ውስጥ ከ125 ሺህ ሜትር ኩብ በላይ (41 በመቶ) የሚሆነውን ወደ ማሳ የመቀላቀል ሥራ ተሠርቷል” ብለዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ 641 ነጥብ 25 ሜትር ኩብ በርሚ ኮምፖስት በማዘጋጀት ወደ እርሻ ማሳ እየተጨመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለፃ የታቀደውን ምርት ለማግኘት ከተፈጥሮ ማዳበሪያ በተጨማሪ ከ11 ሺህ ኩንታል በላይ ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ብሔረሰብ አስተዳደሩ መግባቱን በመግለጽ 27 ሺህ ኩንታል ያህል የከረመ የአፈር ማዳበሪያ መኖሩን ጠቁመው፣ በአጠቃላይ 38 ሺህ 226 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በማሕበራት እና በዩኒየኖች ለስርጭት ተዘጋጅቶ መቀመጡንም ተናግረዋል። በመሆኑም “በበጀት ዓመቱ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት አይገጥመንም” ነው ያሉት።
ከዚህ በተጨማሪም ሰባት ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለመጠቀም ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም ነው አቶ አዲሱ የተናገሩት። እስካሁን ባለው 2400 ኩንታል የተለያዩ ምርጥ ዘሮች ለአርሶ አደሩ መሠራጨቱን ተናግረዋል።
በአማራ ክልል በ2018/19 የምርት ዘመን ከአምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በማረስ 205 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ ነው፤ ይህንን ግብ ለማሳካት ስምንት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ መታቀዱን የክልሉ ግብርና ቢሮ የግብርና ግብዓት እና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሙሽራ ሲሳይ ለበኩር ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሯ እንዳሉት ሦስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ገብቷል፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ ሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታሉ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል፡፡
በቀጣይ ደግሞ ቀሪውን የአፈር ማዳበሪያ (አራት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል) ወደ ክልሉ በማስገባት ለአርሶ አደሩ በወቅቱ ለማድረስ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ግብዓት በወቅቱ አለማግኘት እና የዋጋ መናር አርሶ አደሮች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ናቸው፤ ይህን በተመለከተ ለወ/ሮ ሙሽራ ጥያቄ አንስተንላቸዋል፡፡
ክልሉ የግብዓት አቅርቦቶችን በወቅቱ ለማድረስ እና ከዋጋ አንጻር የሚነሱ የአርሶ አደሩን ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በትኩረት ሲሠራ መቆየቱን እና እተሠራ መሆኑንም ነው የተናገሩት፤ መንግሥት ከፍተኛ ድጎማዎችን በማድረግ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ መሥራቱን ደግሞ አብነት አንስተዋል፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች የግብዓ ስርጭቱ በቀጥታ ወደ አርሶ አደሩ አይደርስም፤ ይልቁንም በነጋዴ እጅ ገብቶ አርሶ አደሩን ላልተፈለገ ወጭ እያጋለጠ መሆኑን አርሶ አደሮች ያነሳሉ፡፡ በተጨባጭ በማስረጃ በተደረሰባቸው አካላት ላይ እርምጃ መወሰዱን እና ወደፊትም ትክክለኛ መረጃ ከተገኘ እርምጃ እንደሚወሰድ ወ/ሮ ሙሽራ ገልጸዋል፤ ቢሮው ደግሞ በቀጥታ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ 220 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅረብ በዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ ከ99 ሺህ ኩንታል በላይ የተለያዩ ምርጥ ዘሮች ለአርሶ አደሩ ተሰራጭተዋል፡፡ ይህም የምርት ግብዓት አቅርቦቱ ቀድሞ መጀመሩን አመላካች እና አበረታች ተግባር ስለመሆኑ ጠቁመዋል። የምርጥ ዘር ስርጭቱ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ15 ሺህ ኩንታል በላይ ብልጫ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ የስርጭት መጠኑን አጠናክሮ በወቅቱ ለአርሶደሩ ለማዳረስ ተጠናክሮ እንደሚሠራም ነው የተናገሩት።
የአፈር ለምነት፣ የምርጥ ዘር ተጠቃሚነት፣ የእርሻ ሜካናይዜሽን፣ የግብርና ባለሙያዎች ክትትል እና የአርሶ አደሮች ዝግጁነት ለምርታማት ማደግ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው። በተለይም የተፈጥሮ እና የሰው ሠራሽ ማዳበሪያን በማቀናጀት መጠቀም የአፈር ጤናን በማሻሻል ለዘላቂ የምርት ዕድገት ወሳኝ እንደሆነም ተናግረዋል።
(ሰናይት በየነ)
በኲር የሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


