ዓለማችን የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ብዙ ጥረቶችን አድርጋለች፡፡ ይሁን እንጂ የተደረገው ጥረት አበረታታች ቢሆንም በቂ አለመሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ያብራራሉ፡፡
የአየር ንብረት ለውጡን ለመከላከል ከተከናወኑ ተግባራት መካከል እ.አ.አ በ2015 በፈረንሳይ ፓሪስ የተካሄደው ኮፕ 21 ጉባዔ ይታወሳል፡፡ 195 ሀገራት እና የአውሮፓ ሕብረት የዓለምን የሙቀት ጭማሪ በዓመት ከሁለት ዲግሪ ሴንቲግሬድ በታች ለማቆየት የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት ቃል የገቡበት ዓለም አቀፍ መድረክ ነበር፡፡በተጨማሪም ሀገራት በየአምስት ዓመቱ እየተሻሻሉ የሚተገበሩ ዕቅዶችን ያዘጋጃሉ፡፡
ሀገራት ወደ ታዳሽ ኃይል ሽግግር (የፀሐይ፣ የነፋስ እና የውኃ ኃይል ዘርፎች ላይ) የተደረገው ኢንቨስትመንት በጣም ጨምሯል፡፡ እ.አ.አ ከ2015 ጀምሮ የፀሐይ እና የነፋስ ኃይል ከዓለም የኤሌክትሪክ ምንጮች ውስጥ ያላቸው ድርሻ ከሦስት እጥፍ በላይ መጨመሩን ወርልድ ሪሶርስ ሴንተር አስታውቋል፡፡ ከ10 ዓመት በፊት ከአንድ በመቶ በታች የነበረው የዓለም የመኪና ሽያጭ ድርሻ በአሁኑ ወቅት ከ20 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡በተመሳሳይ በርካታ ሀገራት የደን መልሶ ማልማት ዘመቻዎችን እያካሄዱ ነው፡፡
ኢትዮጵያም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሚል በቢልዮኖች የሚቆጠር ችግኝ ተክላለች፤ እየተከለችም ነው፡፡እ.አ.አ በ2023 የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባዔም የኮፕ28 ተሳታፊ ሀገራት ከቅሪተ ነዳጅ ቀስ በቀስ ወደ ንጹህ ኃይል ለመሸጋገር የሚያስፈልግ ርምጃ እንዲወሰድ ተስማምተዋል፡፡
ቢሆንም ግን የሰው ልጅ ሕይዎቱን በምድር ላይ ለማቆየት በሚያከናውናቸው የዕለት ተዕለት ተግባራት የአየር ንብረት ለውጥ እንዲስፋፋ እና የተፈጥሮ አደጋዎች እንዲከሰቱ እያደረገ ይገኛል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቀው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እ.አ.አ ከ2030 እስከ 2050 ባለው ጊዜ ውስጥ በየዓመቱ በአማካይ 250 ሺህ ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ፡፡በየዓመቱ ሰኔ 05 ቀን የሚከበረው የዓለም አካባቢ ቀን የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን የምንጠብቅበት፣ የአካባቢ ችግሮችን የምንመለከትበት እና ለዘላቂ ልማት ያለንን ቁርጠኝነት የምናረጋግጥበት ዓለም አቀፍ መድረክ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ዘንድሮ ግን ከቀደሙት ዓመታት በተለየ ሁኔታ ዓለም በአየር ንብረት ቀውስ፣ በሙቀት መጨመር፣ በድርቅ፣ በጎርፍ እና በብዝኃ ሕይወት መጥፋት እየተፈተነች ባለችበት ወቅት ተከብሯል፡፡ ዋና መልዕክቱም ”የአየር ንብረት ለውጥ በሰው ልጆች ሕይወት፣ በኢኮኖሚ እና በተፈጥሮ ላይ እያደረሰ ያለውን ተጽዕኖ በመገንዘብ ፈጣን እና ተጨባጭ ርምጃዎችን መውሰድ ይገባል” የሚል ነበር፡፡
“በተፈጥሮ ተነሳስተን፣ ለአየር ንብረት፣ ለወደፊታችን” በሚል መሪ ቃል የተከበረው ይህ ቀን መንግሥታትን፣ ድርጅቶችን፣ የግሉን ዘርፍ እና ዜጎች ይህን አደርጋለሁ ብለው ቃል ከመግባት ባለፈ ወደ ተግባር እንዲሸጋገሩ ጥሪ የቀረበበት ነው፡፡በዓሉን ታሳቢ በማድረግ በዓለም ዙሪያ የተካሄዱ ዋና ዋና ክንውኖችም የዚህን መልዕክት አጠናክረውታል፡፡ በብዙ ሀገራት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዛፎች ተተክለዋል፣ የወንዞችና የሐይቆች ጽዳት ዘመቻዎች ተካሂደዋል፣ ወጣቶች እና የማሕረሰብ ቡድኖች ስለ አካባቢ ጥበቃ የግንዛቤ መርሃ ግብሮችን አካሂደዋል፡፡
በተጨማሪም በርካታ ሀገራት የፀሐይ፣ የነፋስ እና ሌሎች ታዳሽ ኃይሎችን ለማስፋፋት ያቀዷቸውን ፕሮጀክቶች አስተዋውቀውበታል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ ባስተላለፉት መልዕክት ዓለም የሙቀት መጨመርን በአንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ ሴልሺየስ ውስጥ ለማቆየት የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ያላት ጊዜ እየጠበበ መሆኑን አሳስበዋል፡፡በዓለም ዙሪያ የሚታዩ የሙቀት ማዕበሎች፣ የድርቅ ክስተቶች፣ ከፍተኛ የዝናብ መጠን እና ጎርፍ የአየር ንብረት ቀውስ የወደፊት አደጋ ሳይሆን የዛሬ እውነታ መሆኑን እያሳዩ ነው፡፡
ለአፍሪካ አህጉር ይህ ቀን ልዩ ትርጉም አለው፡፡ አህጉሪቱ ለዓለም የካርቦን ልቀት ትንሽ ድርሻ ብቻ ብታበረክትም የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ክፉኛ እየጎዳት ነው፡፡
ድርቅ፣ የምግብ እጥረት፣ የውኃ ችግር እና የእርሻ ምርት መቀነስ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን እየጎዱ ነው፡፡ኢትዮጵያም ከዚህ እውነታ ውጭ አይደለችም፡፡ በተለይ የደን መመናመን፣ የአፈር መሸርሸር፣ የውኃ ሀብት ላይ እየደረሰ ያለ ጫና እና ተደጋጋሚ ድርቅ ለአካባቢያዊ እና ለኢኮኖሚያዊ ደኅንነት ፈተና ሆነው ቀጥለዋል፡፡በሌላ በኩል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ የዛፍ ተከላ ዘመቻዎች እና በታዳሽ ኃይል ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች ሆነው ታይተዋል፡፡ ለውጥም ተመዝግቦባቸዋል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ እንዴት ይከሰታል?
በአሁኑ ጊዜ በሰው ልጅ የሚመሩ የአካባቢ ለውጦች የአየር ንብረትን በመቀየር፣ ስነ-ምህዳሩን በማበላሸት እና ከፍተኛ የአየር ሁኔታ ክስተቶችን በመፍጠር ምድራችንን በእጅጉ እየጎዱ ይገኛሉ፡፡
የዓለም ሙቀት መጨመር የበረዶ ግግርን ያቀልጣል፡፡ ይህም የባሕርን ከፍታ በመጨመር መኖሪያዎችን ያጠፋል፡፡በተጨማሪም ብክለት እና የደን መጨፍጨፍ የብዝኃ ሕይወት መጥፋትን ያፋጥናል፡፡ ይህም የፕላኔታችንን ጤና የሚደግፈውን ረቂቅ የሕይወት ሚዛን አደጋ ላይ እንደሚጥል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስለ አየር ንብረት ለውጥ ያወጣው መረጃ ያትታል፡፡
የቅሪተ አካል ነዳጆች (የድንጋይ ከሰል፣ ነዳጅ ዘይት እና ጋዝ) ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዙ ሲሆኑ ለአብነትም 68 በመቶው የዓለም ሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን እና 90 በመቶው የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀትን ይይዛሉ፡፡
የምድር በግሪን ሀውስ ጋዝ ልቀቶች መሸፈን ምክንያት ዓለማችን እየሞቀች እና የአየር ሁኔታው እየተቀየረ ሊመጣ ችሏል፡፡ ዓለም አሁን በታሪክ ከየትኛውም ጊዜ በላይ በከፍተኛ ፍጥነት እየሞቀች ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሞቃታማ የአየር ሁኔታውም የተለመደውን የተፈጥሮ ሚዛን እያበላሸ ነው፡፡ ይህ በሰው ልጆች እና በምድር ላይ ባሉ ሌሎች ሕይወታዊ አካላት ላይ ብዙ አደጋዎችን ይፈጥራል፡፡አብዛኛው የኤሌክትሪክ ኃይል የሚመነጨው በከሰል፣ በዘይት ወይም ጋዝ በማቃጠል ሲሆን እነዚህም ካርቦን ዳይኦክሳይድን እና ናይትረስ ኦክሳይድን ይፈጥራሉ፡፡ እነዚህ ጋዞች ምድርን የሚሸፍኑ እና የፀሐይን ሙቀት የሚይዙ ኃይለኛ የሙቀት አማቂ ጋዞች ናቸው፡፡ ኢንዱስትሪዎች ማለትም እንደ ሲሚንቶ፣ ብረትታ ብረት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ፕላስቲኮች፣ አልባሳት እና ሌሎች ሸቀጦችን ለመሥራት የሚያስፈልገውን ኃይል ለማመንጨት በአብዛኛው የቅሪተ አካል ነዳጆችን በማቃጠል ስለሚጠቀሙ ልቀትን ይጨምራሉ፡፡የአምራች ኢንዱስትሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀቶች ከፍተኛ አስተዋፅዖ ካደረጉት መካከል አንዱ ነው፡፡በተጨማሪም እርሻ ወይም የግጦሽ ሳር ለመፍጠር ወይም በሌላ ምክንያት ደኖችን መቁረጥ ልቀትን ይጨምራል፡፡ ምክንያቱም ዛፎች ሲቆረጡ ያከማቹትን ካርበን ይለቃሉ፡፡
እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ በየዓመቱ በግምት 10 ሚሊዮን ሄክታር ደን ይወድማል፡፡ የደን መጨፍጨፍ ከግብርና እና ሌሎች የመሬት አጠቃቀም ለውጦች ጋር አንድ ሦስተኛውን ለዓለም አቀፍ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀቶች ድርሻ አለው፡፡አብዛኛዎቹ ተሸከርካሪዎች፣ መርከቦች እና አውሮፕላኖች የሚሠሩት በቅሪተ አካል ነዳጆች ነው፡፡
በመሆኑም መጓጓዣ ለሙቀት አማቂ ጋዞች በተለይም ለካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀት ዋነኛ አስተዋጽዖ ያደርጋል፡፡ ትራንስፖርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከኃይል ጋር የተያያዘ የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀት አንድ አራተኛ የሚጠጋውን ይይዛል፡፡እንደ መረጃው ከሆነ የአኗኗር ዘይቤያችን በፕላኔታችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡ እንደ ልብስ፣ ኤሌክትሮኒክስ እና ፕላስቲኮች ያሉ ሸቀጦች የዕለት ፍጆታም እንዲሁ ለአየር ንብረት መዛባት አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ በዚህ ረገድ ሀብታም ሃገራት ትልቁን ኃላፊነት ይሸከማሉ፡፡
ለአብነትም 20 ትልልቅ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገራት 80 በመቶ ለሚሆነው የዓለም በካይ ጋዞች ልቀት ተጠያቂ ናቸው፡፡የግሪን ሀውስ ጋዝ ክምችት እየጨመረ በሄደ ቁጥር የዓለም ሙቀት መጠን ይጨምራል፡፡
ያለፉት አሥርት ዓመታት (እ.አ.አ ከ2015 እስከ 2024) የአየር ንብረቱ በጣም ሞቃታማ እና ሙቀቱም እየጨመረ የሄደ ነው፡፡ እ.አ.አ ከ1980ዎቹ ጀምሮ እያንዳንዱ አሥርት ዓመታት ከቀዳሚው የበለጠ ሞቃታማ ነው፡፡በተመሳሳይ የዓለም ሙቀት መጨመር በተደጋጋሚ ድርቅን እያስከተለ መሆኑን መረጃው ጠቁሟል፡፡ ሙቀቱ የውኃ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ይበልጥ አባብሷል፡፡ በየጊዜውም በድርቅ ሳቢያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለረሃብ እና ቸነፈር እየተዳረጉ መሆኑን አመላክቷል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ በመሬት እና በውቅያኖስ ውስጥ ባሉ ዝርያዎች ላይም አደጋን ይፈጥራል፡፡ የሙቀት መጠኑ እየጨመረ ሲሄድም እነዚህ አደጋዎች ይጨምራሉ፡፡ አሁን ላይ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ዓለማችን ከአንድ ሺህ በላይ የእንስሳት ዝርያዎችን እያጣች ነው፡፡
በሚቀጥሉት ጥቂት አሥርት ዓመታት ውስጥ አንድ ሚሊዮን ዝርያዎች ሊጠፉ ይችላሉ፡፡ የደን ቃጠሎ፣ አውሎ ነፋስ፣ ከባድ ዝናብ እና ከየት እንደመጡ የማይታወቁ ወራሪ የሰብል ተባዮች እና የተለያዩ በሽታዎች በየጊዜው የሰውን ልጅ ሕይዎት ፈታኝ አድርገውታል፡፡የአየር ንብረት ለውጥ ክስተቶች መጨመር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለረሃብ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መጨመር ምክንያቶች ናቸው፡፡ እንስሳት ሊሞቱ እና ቢኖሩም እንኳ በሚፈለገው መጠን ምርት ላይሰጡ ይችላሉ፡፡ የሰብል ምርትም እንደዚሁ ሊቀንስ አልያም ጭራሽ ምርት ላይኖር ይችላል፡፡
በአሁኑ ወቅት የውቅያኖስ አሲድ እየጨመረ በመምጣቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚመገቡ የባሕር ሀብቶች ለአደጋ ተጋልጠዋል፡፡
በብዙ የአርክቲክ ክልሎች የበረዶ እና የበረዶ ሽፋን ለውጦች ከውኃ ሀብት የሚገኙ የምግብ አቅርቦቶችን አቋርጠዋል፡፡
በአጠቃላይ የሰው ልጅ አሁን ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቀነስ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ውስጥ ካልገባ ከፍተኛ ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ፕሮግራም አስታውቋል፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የሰኔ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


