ቻይና “ ቲ 1200” የተሰኘ ጠንካራ የካርበን ፋይበርን በፋብሪካ በብዛት በማምረት ከዓለማችን ቀዳሚ ሀገር ልትሆን መቻሏን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል፡፡
“ቲ 1200” የተሰኘው የ “ካርበን ፋይበር” ከሌሎች ቁሶች ስሪት የተለየ መሆኑን ያስነበበው ድረ ገጹ በ2023 እ.አ.አ በጃፓን ቶሬይ” በተሰኘ ፋብሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ መስራት ቢችልም ሂደቱ አስቸጋሪ፣ ጥራቱም ሆነ ምርቱ በቂ እንዳልነበረ ነው የተገለፀው፡፡
የቻይናው ብሔራዊ የግንባታ ቁሳቁስ አምራች ቡድን “ሲኤንቢኤም” በዓመት 100ቶን ወይም 100,000 ኪሎ ግራም “ካርበን ፋይበር” በማምረት ቀዳሚ ሊሆን መቻሉ ነው የተሰመረበት- በድረ ገጹ፡፡
“ቲ 1200” “የካርበን ፋይበር” በጥቂት የገመዱ ዲያሜትር በሺህ የሚቆጠሩ ቀጫጭን ክሮችን አጣምሮ የያዘ ነው፡፡ ቁሱ ክብደት የሌለው ቀላል ሲሆን ከብረት በተሻለ ተጣጣፊ እና ጥንካሬ እንዲኖረው ታስቦ በቴክኖሎጂ ተጋምዶ በባለሙያዎች ሊሰራ መቻሉ ነው የተረጋገጠው፡፡
የምርቱ ጥንካሬ እና ውጤታማነት በቅርንጫፍ አምራቹ ኩባንያ “ዞንግፉ ሼኒንግ” የተሰራ ባለሁለት ዲያሜትር ስፋት ያለው ገመድን በመገልገል ባለሁለት ፎቅ አውቶቡስ መጐተት መቻሉን ድረ ገጹ ይፋ አድርጓል፡፡
“ቲ 1200” ፋይበር ገመድ ከ200 ዲግሪ ሴልሺየስ በሚልቅ ሙቀት ቀልጦ አላስፈላጊ ውህዶችን በመለየት የቀረውን የነጠረ ቁስ በጥሬ እቃነት በመገልገል የተሰራ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


