ሀሰተኛ መረጃ እንዴት ይለያል?

0
100

ኅብረተሰቡን ለማሳሳት፣ ለማደናገር፣ ማሕበራዊ ውጥረትን ወይም የተሳሳተ ግንዛቤ ለመፍጠር ሆን ተብሎ የሚሰራጭ  መረጃ ሀሰተኛ (የፈጠራ ወሬ)ይባላል፡፡  በጉዳዩ ዙሪያ መረጃ የሠጡን በአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ የሚዲያ ይዘት ማበልፀጊያ እና ስርጭት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክት አቶ ጋርዳቸው አንሙት ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው ማብራሪያ ሀሰተኛ መረጃዎች ወደ ኅብረተሰቡ በፍጥነት በመሰራጨት  በግለሰብ ፣ ማህበረሰብ እና ሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ፡፡  ማህበራዊ፣ ኢኮኖያዊ  እና  ፓለቲካዊ  መናጋትም ያስከትላሉ፡፡

ሀሰተኛ  መረጃ  ከግለሰብ፣ ከድርጅት፣ ከተቋም …ተነስቶ  እስከ ሀገር የነበረን መልካም ሥም እና ዝና  የማጠልሸት ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ የሀሰተኛ መረጃ ሌላው ማህበራዊ ችግር ነው፡፡ ማህበራዊ ችግሮቹ ሰዎች ባገኙት የተዛባ መረጃ ፍርሐት ፣ ጭንቀት እና ውጥረት ይፈጥርባቸዋል፡፡

ያላቸው ጭላንጭል ተስፋ ተሟጦ ወደ ተስፋ መቁረጥ ያደርሳቸዋል፡፡ በአዕምሮ ላይም  ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡አቶ ጋርዳቸው እንደሚሉት የጥላቻ ንግግር መረጃ ውጤት በከፍተኛ ደረጃ ግጭት እና ጥላቻን ማምጣቱ ነው፡፡ ከሀሰተኛ መረጃ በመነሳት የሃይማኖት፣ የዘር፣ የፓለቲካ እና የጎሳ ግጭት ምክንያት በመሆን አንዱ በሌላው  ላይ እንዲነሳ አድርጎ በቀላሉ ወደ ማይወጡት ችግር ያስገባል፡፡ሌላኛው ጉዳት የሕዝብ አመኔታን ሊቀንስ ይችላል፤ ሀሰተኛ መረጃ በበዛ ቁጥር ግለሰቦች በሆነ አካል ያላቸውን እምነት በመሸርሸር እውነተኛ መረጃ ቢሰጣቸው እንኳን ለመቀበል እንደሚቸገሩ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ችግርም ሀሰተኛ መረጃ   የሚያስከትለው ሌላው ችግር ነው፡፡

ለምሳሌ በአሁን ወቅት በአካባቢው  የሚታየው  ”የሆነ አካል  “መንገድ እዘጋለሁ’ ብሏል ብሎ መረጃ ሲያሰራጭ ማኅበረሰቡ ሳያመዛዝን ገበያ ላይ ሸቀጣ ሸቀጥን ጨምሮ ሁሉም ይጠፋል በሚል ስጋት  በሰልፍ ይገዛል፣ ይሸጣል፡፡ ከዚህ በዘለለም  ወዳልሆነ ቀውስ ግለሰቦችን ይከታል፡፡ ሀሰተኛ መረጃ በግለሰቦች ጤና ላይም ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስበት መመንገድ አለ፡፡ ኮሮና ቫይረስ(ኮቪድ) በተከሰተ ጊዜ የነበረው መረጃ የተዛባ መሆኑ ”ክትባት ሲመጣ እንኳን አደገኛ ነው፣ በሽታው የለም፣ ክትባቱ የጤና ቀውስ አለው ..…” በሚል የተለያየ የተዛባ መረጃ በመሰራጨቱ በነፃ የመጣ ክትባትን ሕዝቡ  ለመከተብ ፈቃደኛ እንዳልነበር ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡

በወቅቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዓለም ጤና ድርጅት በሀገራችን ደግሞ ጤና ሚኒሥቴር ከሚያወጣው መረጃ ይልቅ አሉባልታዎች ተዓማኒ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ ምንም እንኳን በዓለም አቀፍ ከደረሰው ጉዳት አንፃር  በሀገራችን ሰፊ ጉዳት ባይደርስም  የተዛባ መረጃ ሕዝቡን ለከፋ የጤና ችግር ሊዳርግ እንደሚችል ዳይሬክተሩ በማሳያ አስረድተዋል፡፡ የሀሰተኛ መረጃ ሌላው ችግር ደግሞ ማህበራዊ መከፋፈልን በመፍጠር አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳ ፣ እርስ በርስ መተማመን  እንዳይኖረው ያደርጋል ይላሉ አቶ አንዳርዳቸው፡፡  ይህ ግጭት  ተባብሶ ደግሞ ጥላቻ እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል፡፡የሀሰተኛ መረጃ በፓለቲካዊ ዘርፍ ደግሞ ሀገር እንደ ሀገር እንዳትቀጥል የሚያደርግበት  ተፅዕኖው ከባድ ነው፡፡  እንደ ማኅበረሰብ ያለው የፓለቲካ ክፍፍል አድጎ በመንግሥት ላይ ያለው ዕምነት ከቀነሰ ሀገር አንድ ሆና እንዳትቀጥል በር የሚከፍት መሆኑን ነው አቶ አንዳርዳታ ያስገነዘቡት፡፡

ዳይሬክተሩ አንደሚሉት  ”በተለይም  ሕዘብ በጉጉት የሚጠብቃቸውን ዝግጅቶች በመለየት  በርካታ  ሀሰተኛ መረጃዎች ይለቀቃሉ፡፡ ለምሳሌ በምርጫ ወቅት ምርጫ በየአምስት ዓመቱ የሚካሄድ፣ ኅብረተሰቡ ይጠቅመኛል የሚለውን ተፎካካሪ ይሆነኛል የሚለውን የሚመርጥበት ሁነት ነው፡፡

በዚህ ሰዓት የሚለቀቅ ሀሰተኛ መረጃ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በራሳቸው ፕሮግራም እና  ፓሊሲ ተመሥርተው ሳይሆን  አንዱ የአንዱን ሥም በማጠልሸት እና በማጥፋት ላይ ያተኩራል፡፡ ይህም ማኅበረሰቡ ቀድሞ ያገኘውን መረጃ ስለሚያምን በምርጫው ቀድሞ ተስፋ ይቆርጣል፤ አስተሳሰቡ ይከፈላል፤  ጥርጣሬ ተፈጥሮበት ’ብመርጥ ባልመርጥ ምን ለውጥ አመጣለሁ’ ወደሚል ይሄዳል” በማለጽ የቅርብ ጊዜ ሁነትን እንደ ማስረጃ አቅርበዋል፡፡

አቶ ጋርዳቸው እንደሚገልጹት የሀሰተኛ መረጃ ችግሮች ይህንን ያህል ከሆነ እንዴት መለየት እና መመርመር እንችላለን? ብሎ ማኅበረሰቡ እራሱንም ሌላውንም መጠየቅ ይገባዋል፡፡ ዳይሬክተሩ ሀሰተኛ መረጃዎችን መለየት የሚያስችሉ መንገዶች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡ የመረጃ ምንጩን አስተማማኝነት ማረጋገጥ ቀዳሚው ነው፡፡

ይህም ሲባል ይላሉ አቶ አንዳርዳቸው መረጃው የተለቀቀበት ሚዲያ ወይም አካል የታወቀ፣ ታማኝ እና ሕጋዊ መሆኑን ማረጋገጥ ነው። መረጃውስ የተሰራጨው  ከመንግሥት ተቋም ነው? ከታዋቂ ግለሰብ ነው? ማን ለቀቀው?…. የሚለውን መመርመር እንዲሁም  አጠራጣሪ መረጃን (ምንጭን) ከመጠቀም መቆጠብ ይገባል፡፡ሌላው መለያ መንገድ ደግሞ ከብዙ ቦታዎች (ምንጮች) ነገሩን ማጣራት ፣ማወዳደር እነማን መረጃውን አጋርተውታል? ብሎ መመርመር እንደ ሚገባ ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል፡፡ አስደንጋጭ እና ስሜት ያላቸው (sensational) ርዕሶች ካሉ ውስጡን ሳይመረምሩ አለማጋራት እንዲሁም  እንደ እውነት አድርጎ አለመውሰድ ሌላው የሀሰተኛ መረጃ ዘዴ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡  ሌላኛው ደግሞ መረጃዎችን ከማጋራት በፊት እውነታውን ማጣራት ራስንም መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡  “ይህንን መረጃ በማጋራቴ እኔ ምን አገኛለሁ? ለሰዎች ምን ጥቅም አለው?” ብሎ ራስን መጠየቅ ይገባል፡፡  በችኩልነት ተገፍቶ የሚጋሩ መረጃዎች  የኋላ ኋላ ችግር እንዳያመጡ   መጠንቀቅ እንደሚገባ ዳይሬክተሩ መክረዋል፡፡

ሌላው እውነታ ማረጋገጫ ደግሞ ማስረጃ መፈለግ ነው፡፡ ፎቶ ካለ ፎቶውን ፣ ፎቶዎችን እና ቪዲዮ ካለ ቪዲዮዎችን መመርመር፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ሀሰተኛ መረጃዎች ከዐውዳቸው ውጪ የተወሰዱ ምስሎችን በመጠቀም ጥቅም ላይ ስለሚውሉ ማረጋገጥ።

በሌላ በኩል ደግሞ የዲጂታል አጠቃቀምን ማሳደግ አስፈላጊ ነው፡፡ መረጃ በታወቁ፣በተማሩ ሰዎች ሳይሆን በሚጽፉጽ መረጃ ኃላፊነት የማይወስዱ ማንበብ እና መፃፍ የቻሉ ሰዎች ሁሉ የሚለቁት ነገር ስለሆነ የመረጃውን ዓላማ መረዳት፣ መረጃው የተፈጠረበት ዋና ምክንያት ትኩረት ለመሳብ፣ ጥላቻን ለመዝራት ወይስ ሰውን ለመጉዳት እንደሆነ በማጤን እውነታን መለየት ከራስ እንደ ሚጠበቅ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ ከችግሩ ለመውጣት የታወቁ ተቋማትን መረጃ ብቻ መጠቀም ይገባል፤ ምክንያቱም እነዚህ ተቋማት  ኃላፊነት ስለሚሰማቸው የሚያሰራጩት መረጀ ወደ እውነት የተጠጋ ነው፡፡ አቶ ጋርዳቸው እንደሚሉት የሀሰተኛ መረጃ መጠናከር ምክንያት መንግሥት  ሀሰተኛ መረጃን ለመከላከል ያወጣውን ሕግ ማስከበር አለመቻል ያመጣው ጥፋት ነው፡፡ በ2012 ዓ.ም የሀሰተኛ መረጃ እና ጥላቻ ንግግር አዋጅ ወጥቷል፤ ዋናው የአዋጁ አስፈላጊነትም ግጨት እና ብጥብጥን መቀነስ ስለሆነ መንግሥት ይህን አዋጅ ጥቅም ላይ ማዋል እንደ ሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ተጠቃሚነት የመረጃ ነፃነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ተጠያቂነት ከራስ ጀምሮ በሕሊናው ፣ በእምነቱ ፣ የጎረቤቱን ክብር በመጠበቅ መሥራት እንደ ሚገባ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡  ሚዲያውም የተዛባውን አሠራር በማስተካከል ብዙ ሥራ ማከናወን እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡

የህግ አንቀጽ

የጥላቻ ንግግር አዋጅ

  • በዓለም ዓቀፍ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ኮንቬንሽን (ICCPR) ከተካተቱ ሰብዓዊ መብቶች መካከል ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት (freedom of expression) በአንቀጽ 19 ስር ተደንግጎ ይገኛል።
  • በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 ስር እንደተደነገገው ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በማንኛውም መንገድ እና ስልት ማከናወን የሚችል ሲሆን ይህ መብት በሕግ የወጣቶችን ደኅንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ሥም ለመጠበቅ ሲባል ሊገደብ እንደሚችል ተቀምጧል፡፡
  • የጥላቻ ንግግርንና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከልከል በወጣው አዋጅ ቁጥር 1185/2012 መሠረት የጥላቻ ንግግር ማድረግና ሀሰተኛ መረጃን ማሰራጨት በወንጅል እንደሚያስጠይቅ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here