የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ

0
4

የጊቤ ሸለቆ  ብሔራዊ ፓርክ በደቡብ ክልል የሚገኝ በተለያዩ ስነምህዳሮቹ እና ከያዘው ብዝሃ ህይወት ብዛት ባሻገር ለቀጣናው በሚደረገው  ጠንካራ ጥበቃም ተጠቃሽ ነው፡፡

ፓርኩ በ2011 እ.አ.አ የተመሰረተ ሲሆን ለምስረታውም በቀጣናው የሚፈሰው የጊቤ ወንዝ ዋነኛ መሰረት ብቻ ሳይሆን የሸለቆው ስያሜ መነሻ መሆኑንም ልብ ይሏል፡፡

የፓርኩ ዋና ጽ/ቤት ከአዲስ አበባ 178 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ወልቂጤ ከተማ አቅራቢያ ነው የሚገኘው፡፡ አጠቃላይ ስፋቱም 360 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ተለክቷል፡፡ በመልካ ምድራዊ አቀማመጡ ዝቅተኛው 1500፣ ከፍተኛው 2500 ሜትር ልኬታ አለው፡፡

በፓርኩ በአካለመጠናቸው ግዝፈት ካላቸው ጠቅላላ  ዝርያዎች ውስጥ 17 አጥቢ እንስሳት እንደሚገኙ የተመዘገበ ሲሆን ከነዚህም ጐሽ፣ ዝሆን፣ አቦሸማኔ፣ ከርከሮ እና ዝንጀሮ ሲገኙ የጊቤ ወንዝም ዓዞ፣ ጉማሬ … የመሳሰሉትን ይዟል፡፡

ከዓእዋፍ 200 ዝርያዎች ተመዝግበዋል- በፓርኩ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ዓሳ በል ጭልፊቶች ተጠቃሽ መስህብ ናቸው፡፡

የፓርኩ ዋና መሰረት በሆነው የጊቤ ወንዝ ዳርቻም በጀልባ ተጓጉዞ ለመጐብኘት የተመቸ ነው፡፡ በዙሪያው የሚገኙ ኗሪዎችን ባህል እና አኗኗር መቃኘትም ያስችላል፡፡

በፓርኩ ቀጣና የዝናብ ወራቶች ከሰኔ እስከ መስከረም ያሉት ሲሆኑ ጭቃ እና ደመና ስለሚስተዋልባቸው ተዘዋውሮ መመልከትን ያግዳሉ ፡፡በመሆኑም ለጐብኚዎች የሚመከረው  ከጥቅምት እስከ ታህሳስ ያሉት ወራት መሆናቸውን ልብ ማለት ተገቢ ነው፡፡

ለፓርኩ ዘላቂነት ስጋቶቹ የእርሻ መሬት መስፋፋት፣ የደን መመንጠር፣ ልቅ ግጦሽ እና አደን ናቸው፡፡ ፓርኩን ለመጠበቅ የተቋቋመውን  የእንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ጥረትም ስጋት ላይ ጥለውታል -ተግዳሮቶቹ፡፡

ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ናሽናል ፓርክ አሶሴሽን፣ አክሽን ቱር ኢትዮጵያ እና ፊልም ፊክስር ድረ ገፆችን ተጠቅመናል፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሰኔ 15  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here