“ሦስተኛው ስፍራ”

0
397

ቡና ብዙ ነው፤ ቡና ትንሽ ነው። አንድ ትንሽ ስኒ፤ ብዙ ፋይዳ።

ለብዙዎች ቡና ማለዳን መነቃቂያ፣ የሥራ ድካምን ማስታገሻ ወይም ደግሞ የጣዕም ምርጫ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በጥልቀት ለተመለከተው ቡና ከፈሳሽነቱ ባለፈ የሰው ልጅን ማኅበራዊ መስተጋብር የሚቀይር፣ የሥነ-ልቦና ጤናን የሚገነባና የታላላቅ ሐሳቦች መፈልፈያ መድረክም ነው።

ቡና መጠጥ ሳይሆን መድረክ ነው፤ የልብን የሚያወጡበት፣ ሰላምን የሚዘሩበትና አዲስ ራዕይን የሚቀይሱበት ልዩ የውይይት ዓለም።

በኢትዮጵያ የቡና ሥነ-ሥርዓት ከመጠጣት ድርጊት ያለፈ “ተቋማዊ” ትርጉም አለው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ አንትሮፖሎጂ ተመራማሪ የሆኑት ጌታነህ መሐሪ በ2016 (እ.ኤ.አ) ባደረጉት “የቡና ሥርዐት በከተሞች ማህበራዊ ሕብረትን ለማጠንከር ያለው ሚና” በሚል  ጥናት ቡና በከተማ ነዋሪዎች መካከል ያለውን ማኅበራዊ ትስስር  በማጠናከር ረገድ የማይተካ ሚና እንዳለው አረጋግጠዋል።

ጥናቱ እንደሚያሳየው በተለይም በከተሞች አካባቢ የሚኖሩ ሴቶች በቡና ሥነ-ሥርዓት አማካኝነት የራሳቸውን መደበኛ ያልሆነ የድጋፍ መረብ ይፈጥራሉ። ይህ መድረክ ጎረቤታሞች መረጃ የሚለዋወጡበትና እንደ “እቁብ” ያሉ ማኅበራዊ የኢኮኖሚ ድጋፎችን የሚመሠርቱበት የሰፈር ፓርላማ ነው። እዚህ መድረክ ላይ ችግሮች ይፈታሉ፣ ሰላም ይወርዳል፣ የብቸኝነት ስሜትም ይወገዳል።

በተለይ በደቡብና በምዕራብ የሀገራችን ክፍሎች ቡና ለግጭት አፈታት ትልቅ ሚና አለው። ዳንኤል ደረጄ በ2015 (እ.ኤ.አ) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባቀረቡት ጥናት የቡና ሥነ-ሥርዓት በሲዳማ ማኅበረሰብ ውስጥ ያለውን የማኅበራዊ ካፒታል ፋይዳ በዝርዝር አስቀምጠዋል። በሲዳማ ባህል “ቡና ቃላ” ለምርቃትና ለዕርቅ ዋነኛው መንገድ ነው።

በተመሳሳይ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የሚጠቀሰው የ”ቡና ቅሬ” ሥርዓት ሰዎች በጦፈ ክርክር ውስጥ እንኳ ቢሆኑ ለቡናው ክብር ሲሉ ሐሳባቸውን በለሰለሰ መንገድ እንዲገልጹ ያደርጋል።

ይህ “የቡና ዲፕሎማሲ” ዛሬም ቢሆን በዘመናዊው ዓለም ይሠራበታል። ታላላቅ የዓለም ስምምነቶች በይፋዊው የስብሰባ አዳራሽ ሳይሆን በዕረፍት ሰዓት በቡና ስኒ ዙሪያ በሚደረጉ ከመደበኛ ውጭ ውይይቶች ይቋጫሉ። ምክንያቱም ቡና የሰዎችን የመከላከል ግድግዳ የማፍረስ ተፈጥሯዊ ኃይል አለው፤ ያቀራርባል።

የሥነ-ልቦናና የማኅበራዊ ሳይንስ ተመራማሪው ሬይ ኦልደንበርግ  ሦስተኛው ስፍራ የሚል ጽንሰ-ሐሳብ አለው። የመጀመሪያው ስፍራ ቤት ነው። ሁለተኛው ሥራ ነው፤ ሦስተኛው ደግሞ እንደ ቡና ቤት ያሉ ሰዎች ያለ ምንም የሥልጣን ተዋረድ በነፃነት የሚገናኙባቸው ስፍራዎች ናቸው።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የተካሄዱ የጤና ሳይንስ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የቡና መጠጣት ልማድ ከጭንቀት እና ከብቸኝነት ስሜት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። የቡና ሥነ-ሥርዓት ባለባቸው ማኅበረሰቦች ውስጥ ሰዎች ስሜታቸውን በግልጽ የመናገር ዕድል ስላላቸው፣ ይህ እንደ የቡድን ሕክምና ያገለግላል።

የሥነ-ልቦና ተመራማሪው ጆን ባርግ  ባደረገው ጥናት በእጃቸው ላይ የሞቀ መጠጥ የያዙ ሰዎች ለሌሎች ሰዎች ያላቸው አመለካከት ይበልጥ አዎንታዊና “ሞቅ ያለ” እንደሚሆን አረጋግጧል። በቡና ወቅት የሚለቀቀው የደስታ ሆርሞን (ዶፓሚን) ይበልጥ ግልጽና ተግባቢ እንድንሆን ያደርገናል።

በታሪክ ውስጥ የቡና ቤቶች የሐሳብ ገበያዎች ነበሩ። ታዋቂው የታሪክ ጸሐፊ ቶም ስታንዳጅ  “ኤ ሂስትሪ ኦፍ ዘ ወርልድ ኢን  6 ግላስስ” በተሰኘው መጽሐፉ ቡና የአውሮፓን የአብርሆት ዘመን (የተሐድሶ ዘመን) ለማምጣት የነበረውን ሚና ይገልጻል። የለንደን የቡና ቤቶች ባለ አንድ ሳንቲም ዩኒቨርሲቲዎች ተብለው ይጠሩ ነበር፤ ምክንያቱም በአንድ ሳንቲም ቡና ገዝቶ ታላላቅ ምሁራን በሚያደርጉት ጥልቅ ውይይት መሳተፍ ይቻል ስለነበር ነው።

ታላቁ የፈረንሳይ ፈላስፋ ቮልቴር (Voltaire) በቀን እስከ 40 ሲኒ ቡና ይጠጣ እንደነበርና አብዛኛው የጽሑፍ ሥራው በቡና ቤቶች ውይይት የታገዘ እንደነበር ይነገራል።  ቡና የፈጠራና የንግድ መፍለቂያ መሆኑን ያረጋግጣል።

ብዙ ስኬታማ ሰዎች ታላላቅ ሐሳቦቻቸውን ያገኙት በቡና ቤቶች ውይይት ላይ ነው። ደራሲ ጄ.ኬ ሮውሊንግ የመጀመሪያውን የ”ሃሪ ፖተር” መጽሐፍ የጻፈችው በኤድንበርግ በሚገኙ ትናንሽ የቡና ቤቶች ውስጥ ተቀምጣ ነበር።

የስታርባክስ መሥራች ሃዋርድ ሹልትስ ድርጅቱን ዓለም አቀፍ ግዙፍ ኩባንያ ለማድረግ የተነሳሳው በጣሊያን የቡና ቤቶች ያለውን ማኅበራዊ ትስስር ከተመለከተ በኋላ ነው። እርሱ “እኛ የምንሸጠው ቡና ብቻ አይደለም፤ ሰዎችን የምናገናኝበትን ስሜት ጭምር ነው” ይላል። ይህ የሚያሳየው ቡና ለንግድ ስኬት ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች ትስስር ያለውን ዋጋ ነው።

የኢትዮጵያ የቡና ሥነ-ሥርዓት ሦስቱ ዙሮች የራሳቸው የሆነ ማኅበራዊና ፍልስፍናዊ ቅደም ተከተል አላቸው።

አቦል የመክፈቻ ነው። አዳዲስ ዜናዎች የሚሰሙበትና ውይይቱ የሚጀመርበት ነው። ቶና ውይይቱ የሚጠልቅበት፣ ችግሮች የሚፈተሹበትና መፍትሔ የሚፈለግበት ነው። በረካ መጨረሻ ነው። የተደረገው ውይይት ተጠቃሎ፣ በሰላምና በምርቃት የሚለቀቁበት ዙር ነው።

ይህ ሂደት በራሱ አንድን ሐሳብ የመጀመር፣ የማዳበርና የማጠቃለል ሥርዓት ነው። እንዲህ ዓይነቱ የተቀናጀ የውይይት ሥርዓት በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን የመቻቻል ባህል  ያሳድጋል።

ዛሬ በቴክኖሎጂ ተገፋፍተን ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት በስክሪን ላይ ብቻ እየቀረ ባለበት ዘመን የቡና ጠረጴዛ ዙሪያ ውይይቶች ይበልጥ ያስፈልጉናል። በአካል ተገናኝቶ ቡና እየጠጡ ማውራት የሚሰጠው የሰውነት ቋንቋ እና የዓይን ግንኙነት በማኅበራዊ ሚዲያ ሊተካ አይችልም። የቡና ጠረጴዛው ብቸኝነት የሚሸነፍበት የሰው ልጅ መተሳሰብ የሚታደስበት መድረክ ነው።

ቡና ከመጠጥነቱ ባለፈ የሰው ልጅ የማኅበራዊ ኑሮ ቅመም ነው። ሰዎችን ያቀራርባል፣ ሐሳብን ያነቃቃል፣ የሥነ-ልቦና ጫናን ያቃልላል። በአገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎቻችን የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት ቡና ማኅበራዊ ትስስርን የሚያጠናክር፣ የአእምሮ ጤናን የሚጠብቅና ለሰላም ግንባታ የሚረዳ ትልቅ ሀብታችን ነው።

የቡና ስኒዎቻችንን ስናነሳ የምንጠጣው ፈሳሽ ብቻ ሳይሆን ከሺህ ዓመታት በፊት የጀመረውን የታሪክ፣ የጥበብና የማኅበራዊ ትስስር ሰንሰለት መሆኑን ልብ ይሏል። ቡና ማለት የሰው ልጅ ከሰውነቱ ጋር፣ ጎረቤት ከጎረቤቱ ጋር፣ ነጋዴ ከደንበኛው ጋር የሚገናኝበት ታላቁ ድልድይ ነው።

 

 

መረፊያ

በረከት በላይነህ ግጥም

የተራበ ነብር ከሩቅ ተመልክታ

ሚዳቋ ፀለየች….

“አውጣኝ አውጣኝ” አለች ለፈጠራት ጌታ

ነብሩም ተርቦ

ወደ አምላኩ ቀርቦ

ሚዳቆዋን አይቶ – አንጀቱ ከሆዱ እንደተጣበቀ

ፈቅዶ እንዲሰጠው – አምላኩን ጠየቀ

የሁላችን ሰሪ ፀሎታቸውንም – ሰማቸው ፈጣሪ

አምላክም በድምፁ – ሚዳቆዋን አላት

“እሩጠሽ አምልጪ – ከበረታው ጠላት”

ነብሩንም አለው – “እሩጥ ተከተላት

ምግብ አድርገህም ብላት”

ሚዳቆዋ ስትሮጥ

ከነብር ለማምለጥ

ነብሩም ሲከተላት

ሆዱን ሊሞላባት

ቋጥኙን ስትዘል እግሯ ተስፈንጥሮ

ሆዱን ብትረግጠው የተኛው ከርከሮ

ከእንቅልፉ ሲነቃ ልክ ሲደነብር

ጉሮሮውን ያዘው የፀለየው ነብር

አውጣኝ ያለው ወቶ – አብላኝ ያለው በላ

ሳይፀልይ ያደረው – ከርከሮ ተበላ፡፡

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሰኔ 22  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here