“ፈተና ባይኖር ጠንካራ አልሆንም”

0
38

“የሰው ልጅ ፈተና ሳይኖርበት  ነገሮች አልጋ በአልጋ ቢሆኑለት መማርን፣ መለወጥን.. አያስብም ነበር፡፡ ችግር እና ፈተና ሲበዛ ያንን መሰናክል ለማለፍ እና ተመራጭ ለመሆን ʽእማራለሁ፤ በመማር  መለወጤ ደግሞ ካለሁበት ደረጃ ሁል ጊዜም ከፍ እላለሁʽ ብሎ ያስባል” የሚሉን በወርሀ ሰኔ/2018 ዓ.ም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የመጀመሪያዋ ሴት ሙሉ ፕሮፌሰር ማዕረግ የተሰጣቸው ተመራማሪ  ዶ/ር አቻምየለሽ ገብረጻድቅ ተክሌ ናቸው፤  ይህም በዩኒቨርሲቲው ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ሙሉ ፕሮፌሰር አድርጓቸዋል።

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ ትውልድ እና እድገታቸው በደቡብ ኢትዮጵያ በቀድሞው ሲዳሞ ክፍለ ሀገር ክብረ መንግሥት አውራጃ በአሁኑ ወቅት ደግሞ አዶላ ከተማ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ነው፡፡ እስከ  12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውንም የተከታተሉ በዚሁ ነው፡፡

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ባመጡት ውጤት በ1985 ዓ.ም በቀድሞው ሥያሜው  ጎንደር ህክምና ጤና ሳይንስ በኮምፕረሲን ነርሲንግ በዲፕሎማ ተመረቁ፡፡ በወቅቱ ጤና ጥበቃ ሚኒሥቴር ባደረገው  ምደባ ደቡብ ሲዳሞ ዞን ተመድበው ሥራ እንጀመሩ ለበኵር በስልክ ገልፀዋል፡፡

ጥቂት ጊዜ ወረዳ ላይ እንደሠሩ በዲግሪ ለመማር የሚያስችል ዕድል አግኝተው ወደ ጅማ ዩንቨርሲቲ አመሩ፡፡ “በወቅቱም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከተዋወቅሁት ከትዳር አጋሬ ጋር ትዳር መሰረትሁ፤ በልጅም ትዳራችን ሞቀ፡፡

በሂደትም የትምህርት እድል አገኘሁ፡፡  ሁለት ልጆቸን ትቸም ወደ ዩኒቨርስቲ ገባሁ” የሚሉት ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፤ አንድ ዓመት ተምረው ለእረፍት ወደ ቤተሰብ ሲመለሱ ግን ልጆቻቸው ተመችቷቸው አላገኙም፡፡በዚህም ወደ ነበሩበት ዩኒቨርሲቲ ከመመለስ ይልቅ ከልጆቻቸው ሳይርቁ በአካባቢው ባለ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን መቀጠል ፈለጉ፡፡

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ ያሰቡት ተሳክቶላቸው የተማሩት ኮርስ ተይዞላቸው ትምህርታቸውን ወደ ዲላ (ደቡብ ዩኒቨርሲቲ) በማዛወር የመጀመሪያ ዲግሪ በሕዝብ ጤና አጠባበቅ በ2002 ዓ.ም.ተመረቁ፡፡ ትንሽ ጊዜ ወረዳ ጤና ተቋም ሠርተው ወደ ጤና ቢሮ በሽታ መቆጣጠር ላይ ከሠሩ በኋላ ወደ መምህርነት የመግባት ፍላጎት ስላላቸው ወደ ሐዋሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተወዳድረው ገቡ፡፡ በዛም ሰባት ወር ሠርተው ወደ ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተዘዋወሩ፡፡

በዩኒቨርሲቲው  በማስተማር አንድ ዓመት ከቆዩ በኋላ ደግሞ የማስተርስ (ሁለተኛ ዲግሪ) ትምህርት ዕድል አግኝተው ወደ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በመግባት የህብረተሰብ ጤና ተምረዋል፡፡ አንድ ዓመት ካገለገሉ በኋላ  ደግሞ በሥራቸው ባሳዩት የላቀ አፈጻፀም ሌላ የትምህርት ዕድል አግኝተው ቀጣዩን ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና ከአዲስ ኮንቲኔንታል የሕዝብ ጤና ኢንስቲትዩት የጋራ ፕሮግራም በሕዝብ ጤና የዶክትሬት (Ph.D.) ዲግሪያቸውን በ2007 ዓ.ም አግኝተዋል።

“ምሠራባቸው ቦታዎች ላይ የማልፈልጋቸውን ትግሎች (መሠናክሎች) ለማለፍ ምን ማድረግ አለብኝ? ብዬ ሳስብ  ቶሎ ቶሎ ተምሬ ተመራጭ ሰው መሆን እና ከፍ ማለት አለብኝ ብዬ በማሰብ እየቀደምኩ እገኛለሁ፡፡” የሚሉት ፕሮፌሰር ይህ ማለት  ከሥር ከሥር የሚጎትቱ ነገሮችን ለማለፍ የሚችሉበት መንገድ በመማር ዕውቀት መጨበጥ  እንደሆነ በማሰብ ነው፡፡

የአራት ወንድ እና የስድስት ሴቶች  እናት የሆኑት ፕሮፌሰር አቻምየለሽ ከዲፕሎማ በሥተቀር ሌሎች ልጆቻቸውን በሥራ እና በትምህርት ላይ እያሉ እንደወለዷቸው ተናግረዋል፡፡   “ስለወለድኩ ብዬ ትምህርቴን አላቋርጥም፤ እየተማርሁ ነው በሚልም መውለድ አልተውሁም፡፡ እወልዳለሁ፤ እማራለሁ፡፡ በሂደቱ ነገሮች አድካሚ ቢሆኑ እንኳን ቀን ለልጆች ጊዜ ቢሰጥ ከእንቅልፍ ጊዜ መሥዋት አድርጎ ወደ ሥራ በመግባት ማንኛውም ፈተና ይታለፋል በማለት ጥንካሬያቸውን ገልፀውልናል፡፡

የትዳር አጋራቸው የሚረዷቸው እና በማንኛውም ተግባር አጋዥ መሆናቸው፣ ልጆችም የቤተሰብ አካል ሆነው የሚችሉትን የሚረዱ አድርገው ማሳደጋቸው ለስኬት እንዳበቃቸው ተናግረዋል፡፡ ቤት ሲባል እናት ብቻዋን ዋጋ የምትከፍልበት ሳይሆን በጋራ የሚሠሩበት (የሚካፈሉበት) ሲሆን በመረዳዳት ነገሮች ይታለፋሉ የሚል እምነትም አላቸው፡፡

እንደ ፕሮፌሰር አቻምየለሽ ገለጻ ሴቶች ካገቡ በኋላ ነገሮችን ቀድመው  “አንችለውም” ብለው ያስባሉ፣ፈተናን አግዝፎ ማየት ችግር አለው፣ በርግጥ ነባራዊ ሁኔታውም ሲታይ ብዙ ወደ ኋላ የሚጎትቱ ነገሮች አሉ፤ ወደ ላይ ሲታይ አጠገብ ካለው ጀምሮ ኮርኳሚው ብዙ ነው፡፡ ካሰቡት ዳገት ነው፤ ነገር ግን የሚችሉትን ለማድረግ ጥረትን አለማቋረጥ እና መጠንከር ያስፈልጋል፡፡

“ልጅ መውለድ እንደሚታሰበው ወደ ኋላ የሚያስቀር፣ ድሃ የሚያደርግ ነገር አይደለም” የሚሉት ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፤ “ያለውን እውነታ መካድ የለብንም፤ እኛ ያልፃፍነውን ሳይንስ ተቀብለን ነው የምንታገለው፡፡ ልጅ ሲሠጠን ሽልማት ነው! ያንን ተቀብሎ ጠንክሮ መሥራት መሆኑን እኔ ህያው ምስክር ነኝ!”በማለትም የሕይዎት ተሞክሯቸውን ለሌሎች ጠቁመዋል፡፡

ፕሮፌሰርነት ተመራማሪ እና መምህር ሆኖ በዩንቨርሲቲ ለሚሠራ ማህበረሰብ የሚሠጥ ማዕረግ ነው፡፡ ይህ ማለት ከተመራመሩ፣ ከሠሩ በዩንቨርሲቲ ላሉ ሴት መምህራን ማዕረጉ እሩቅ አይደለም፤ ትግሉ ግን ብዙ፡፡ ይህ ማለት ግን  አይደረስበትም  ማለት እንዳልሆነ አስገንዝበዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሴቶች  መፎካከር  ሳይሆን መነጋገር እና ተባብሮ መሥራት ሲችሉ የልፋቱን መጠን መቀነስ ይቻላቸዋል፡፡

በሕዝብ ጤና፣ በክሊኒካዊ ምርምር እና በአካዳሚክ መሪነት ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በላቀ አገልግሎት ያሳለፉት ፕሮፌሰር አቻምየለሽ በእናቶችና ሕፃናት ጤና፣ በስነ-ምግብ (nutrition) እና የጤና ስርዓትን በማጠናከር ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያተረፉ ባለሙያ ናቸው።  ከኢፌድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒሥቴር ጋር በመሆን ብሔራዊ የስነ-ምግብ መመሪያዎችን እና ስትራቴጂካዊ ሰነዶችን በማዘጋጀትና በቴክኒክ ክለሳ ላይ ግንባር ቀደም ሚና በመጫወት ሥራዎቻቸው በቀጥታ በሀገራዊ የጤና ፖሊሲ ላይ ጉልህ አስተዋፅዖ አበርክተዋል።

በትምህርት እና ምርምር ጉዟቸው ውስጥ ሴት በመሆናቸውና ቤተሰብ በመምራታቸው የገጠሟቸውን ተደራራቢ ፈተናዎች ያነሱት ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፤ “ ሴትነትና እናትነት ብቻውን ፕሮፌሰርነት ነው “ በማለት ጥንካሬንና ትዕግስትን የሚጠይቁትን እነዚህን ድርብ ማህበራዊ ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ራሱ ትልቅ ማዕረግ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዩኒቨርሲቲውም ሆነ ለህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጁ የመጀመሪያዋ ሴት ሙሉ ፕሮፌሰር መሆናቸውን የጠቀሱት ምሁሯ፤ ፕሮፌሰር በግላቸው ካስመዘገቡት ስኬት ባሻገር፣ ሌሎች ሴቶች በምርምርና በአካዳሚክ ዘርፍ እንዲበረቱና እርስ በርስ እንዲደጋገፉ የጀመሩትን አበረታች ሥራ አጋርተዋል።

ሌሎች ሴቶችን ለማገዝ በነበራቸው ቁርጠኝነት መሰረት ቀደም ሲል ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በ10 ሴቶች ብቻ የጀመሩት “የኢትዮጵያ ሴት ተመራማሪዎች ማህበር” በአሁኑ ወቅት በአስደናቂ ሁኔታ አድጎ የአባላት ቁጥሩ ከ600 በላይ መድረሱን ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ በህብረተሰብ ጤና፣ በክሊኒካዊ ምግብ እና በአካዳሚክ መሪነት ላይ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የላቀ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ አገልግሎት ያበረከቱ እውቅ ባለሙያ ናቸው።  በተለይ በእናቶችና ሕጻናት ጤና፣ በስነ-ምግብ፣ በካንሰር ኤፒዲሚዮሎጂ እና የጤና ስርዓትን በማጠናከር ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጠቀሱ ተመራማሪ ናቸው ፡፡

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ በአቻ በሚገመገሙ ዓለም አቀፍ መጽሔቶች ላይ ከ50 በላይ ጥናታዊ ጽሑፎችን አሳትመዋል፡፡

ማናት

 

በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ጥቂት የሙሉ ፕሮፌሰር ማዕረግ ካላቸው ሴቶች መካከል ቀዳሚዎቹ የሚከተሉት ናቸው።

  • ፕሮፌሰር ዓለምፀሀይ መኰንን- በሴል እና በሰውነት ፊዚዮሎጂ (Cell and Human Physiology) የካቲት 2001 ዓ.ም የሙሉ ፕሮፌሰር ማዕረግ በማግኘት በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሮፌሰር ሆነው ተመዝግበዋል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እውቅ የባዮ-ሜዲካል ሳይንቲስት ሲሆኑ በርካታ ዓለም አቀፍ የምርምር ሥራዎችን አከናውነዋል፡፡
  • ፕሮፌሰር ፊቲን ዓባይ  በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የግብርና እና ገጠር ሀብት አስተዳደር ፣ በእጽዋት ሳይንስ ምርምር እና በዘር ጥናት ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡
  • ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም- በቋንቋ ጥናትና ሥነ-ልሳን ከፍተኛ እውቅና ያላቸው ምሁር ሲሆኑ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር እንዲሁም በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነቶች አገልግለዋል።

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር በኲር የሰኔ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here