ከምርጫ ማግስት

0
195

ምርጫ ለሀገር ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ሀገርን በመንግሥትነት ለመምራት የሚያስችል በሕገመንግሥት የተሰጠ ሥልጣን ነው። ይህን መነሻ በማድረግ ሀገራችን ጠቅላላ ወይም ሀገር አቀፍ ምርጫ ማድረግ ከጀመረች ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ሆኗታል። ይህም በየአምስት ዓመቱ የሚደረግ ሲሆን ዘመኑም የፓርላማ እድሜ  ነው።

ለሰባተኛ ጊዜ በተደረገው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እሁድ ሰኔ 14/2018ዓ.ም. የተረጋገጡ እና የፀደቁ የምርጫ ውጤቶችን ለሕዝቡ ይፋ አድጓል። በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተቃዋሚ ፓርቲዎች 41፣ የግል ዕጩዎች ደግሞ 8 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ማሸነፋቸውን በተጨማሪ ይፋ ሆኗል።

ብልጽግና ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ 20 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን፣ በአማራ ክልል 117፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 8፣ በጋምቤላ ክልል 3፣ በኦሮሚያ ክልል 167 መቀመጫዎች ማሸነፍ ችሏል። በሲዳማ ክልል እንዲሁ 13፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ 17፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ደግሞ 35 መቀመጫዎችን በማግኘት አሸንፏል። በተመሳሳይ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲ 28 መቀመጫዎች፣ በሶማሌ ክልል ደግሞ 19 መቀመጫዎች በማግኘት አሸንፏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በምርጫ ወቅት ቅሬታ በቀረበባቸው የምርጫ ክልሎች ላይ   አብዛኛዎቹ ተጣርተው እልባት ማግኘታቸውን  ቅሬታዎችንም በአግባቡ ለማጣራት ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የሕግ ባለሙያዎች በትኩረት መሥራታቸውን  ገልጸዋል።

ብልጽግና ፓርቲ በሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ በዋናነት ሰላም ማስፈን፣ የሀገርን ሉዓላዊነት መጠበቅ፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረግ እና የኑሮ ውድነትን መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ ለመሥራት ቃል ገብቷል። ፓርቲው ከተመረጠበት ጊዜ ጀምሮ ሀገራዊ ምክክርን በማካሄድ እና “ከምርጫ ማግስት ጠንካራ መንግሥት” በሚል መሪ ቃል ቃሎቹን ለመፈጸም እየሠራ መሆኑን ይገልጻል።

በምርጫው የተገቡ ዋና ዋና ቃሎች

  • ሰላምና ሀገር አንድነት የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ፣
  • ግጭቶችን በውይይት መፍታት እና በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ።
  • የኑሮ ውድነት ቅነሳና ኢኮኖሚ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር፣
  • የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እና የሕዝቡን የኑሮ ጫና ማቃለል።
  • በልማትና መሠረተ ልማት በኩል የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን ማስፋፋት።
  • ሀገራዊ ምክክር የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራዎችን በማገዝ በሀገሪቱ የፖለቲካ እና ህገ-መንግስታዊ ጉዳዮች ላይ በስምምነት መጓዝ ናቸው።

ፓርቲውም  የአሸናፊ ውጤት ይፋ ከሆነ  በኋላ የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ በማስፋት እና በማጽናት የሕዝብን ሁለንተናዊ ደህንነት ማረጋገጥ የፓርቲው ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን ገልጾ፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ የውስጠ ፓርቲ ጤንነታችንን መጠበቅ፣ ከሌብነትና ከተደራጀ ስርቆት አንጻራዊ ነጻነቱን የጠበቀ የአመራር ስምሪት ማረጋገጥ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ የአገልጋይ አመራር ስብዕናን የተላበሰ ጠንካራ የፓርቲ መስተጋብር ለመፍጠር መወሰኑን ነው የገለፀው፡፡  ያለጠንካራ ሥራ እና አቅም ግንባታ እቅዶችን ማሳካትም ሆነ የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ስለማይቻል ለዚህ ዘርፍ የተለየ ትኩረት  እንደሚሰጥ አረጋግጧል፡፡

በምርጫ 2018 ውጤት ብልጽግና ፓርቲ ከ500 በላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ውስጥ 438ቱን በማሸነፍ በድጋሚ መንግሥት መስርቷል። ፓርቲው የገባውን ቃል ለመፈፀም እና ከሕዝብ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ታሳቢ ያደረገ መድረኮችን በማዘጋጀት ላይ ይገኛል።

ፓርቲው አሻናፊነቱን አስመልክቶ በሠጠው ሀገራዊ መግለጫ በታሪካዊው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ፣ ሕዝቡ  ለብልፅግና ፓርቲ ዳግም ታላቅ ኃላፊነትና አደራ ሰጥቷል።

በምርጫው ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መሳተፋቸው የሕዝቡን 42 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከ10 ሺህ በላይ ዕጩ ተወዳዳሪዎች መካከል ብልጽግና ፓርቲ አብላጫ ድምጽ በማምጣት መመረጡን ቦርዱ አሳውቋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ የአፍሪካ ህብረት እና ኢጋድ “ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ” የሚለውን

መርህ ተከትሎ በቀጣይ ዘላቂ ሰላምና ፀጥታን ለማስፈንና የሕግ የበላይነትን በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባት፣ የኑሮ ውድነትን ለማቃለልና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ዘላቂ የሥራ ዕድሎችን በስፋት ለመፍጠርና የዜጎቻችንን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ሀገራዊ አስተዋጽኦ ለማሳደግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ መግለጫው አመላክቷል፡፡

የተጀመረውን የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን በሀገር አቀፍ ደረጃ በስፋት በማስፋፋት፣ የቢሮክራሲ ማነቆዎችን በመበጣጠስና የአገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ በማዘመን፣ ሌብነትንና ብልሹ አሠራርን በቆራጥነት ለመከላከልና የተገልጋዩን ሕዝብ እርካታ በከፍተኛ ደረጃ ለማረጋገጥም በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ከምርጫ ማግስት ቃል ገብቷል።

በተጨማሪም በመገባደድ ላይ የሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ሂደት የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ በሚገባ በመደገፍ፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን ይበልጥ ነፃ፣ ገለልተኛና ጠንካራ እንዲሆኑ በማጠናከር፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ብሔራዊ ጥቅማችንን ማዕከል ባደረገ መልኩ በትብብር በመስራት ገንቢ ሃሳቦቻቸውንና አቅማቸውን ለማካተት የጀመርናቸውን ጥረቶች አጠናክሮ እንደ ሚቀጥል አሳውቋል፡፡

በአጠቃላይ ብልፅግና ፓርቲ የገባውን ቃል ሳይሸራረፍ በመተግበር፣ ምርጫ የሥልጣን መቆናጠጫ ሳይሆን ሕዝብን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገያ ታላቅ አደራ መሆኑን በተጨባጭ በመግለጫው አረጋግጧል፡፡

ለዚህም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና በተግባር የማረጋገጥ ታሪካዊ ጉዞ ከምንጊዜውም በላይ በበለጠ ትጋት፣ አንድነትና ቁርጠኝነት አጠናክሮ  ለመቀጠል  ለሕዝቡ አሳውቋል፡፡

የሕግ አንቀፅ

የኢትዮጵያ ሀገር አቀፋዊ የምርጫ አይነቶች

በአዋጅ ቁጥር 1162/11 አንቀጽ 6 መሠረት አምስት የምርጫ አይነቶች አሉ፡፡

1-ጠቅላላ ምርጫ

ይህ በየአምስት ዓመቱ የሚደረግ የፖለቲካ ፓርቲዎች መንግሥት ለመሆን ወይም በፓርላማ የሕዝብ ተወካይ ለመሆን የሚወዳደሩበት ሲሆን የግል ተወዳዳሪዎችም ይሳተፉበታል።

2-የአካባቢ ምርጫ

ይህ በዞኖች፣ ወረዳዎች፣በቀበሌዎች ምርጫ በምክር ቤት የሕዝብ ውክልና እንዲያገኙ የሚመረጡበት ነው።

3-ማሟያ ምርጫ-

ይህ ምርጫ ተመራጭ አባላት ከምክር ቤቶች በየደረጃቸው በተለያየ ምክንያት ሲጓደሉ የሚሟላበት የምርጫ አይነት ነው።

4 ድጋሚ ምርጫ

ድጋሚ ምርጫ ከሚከተሉት ምክንያቶች በአንዱ ሊካሄድ ይችላል፤ በአዋጅ ቁጥር 1133/2011 እና በዚህ አዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሠረት ቦርዱ የምርጫ ውጤት እንዲሰረዝና ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ ሲወስን ወይም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቀረበለት አቤቱታ ላይ ተመስርቶ የምርጫ መደገም ውጤትን የሚያስከትል ውሳኔ ሲወስን፤   በአዋጅ ቁጥር 1162/11 አንቀጽ 61(3) መሠረት እጩ ተወዳዳሪዎች እኩል ድምፅ በማግኘታቸው ምክንያት አሸናፊውን መለየት ያልተቻለ እንደሆነ የሚካኄድነው።

5- ሕዝበ ውሳኔ –

ምርጫ ቦርዱ በሕገ መንግሥቱ ወይም በሌሎች ሕጎች መሠረት አግባብ ባለው አካል ሲወሰን የሕዝብን ፍላጎት ለመለካት ወይም ለመወሰን ድምጽ እንዲሰጥ ህዝበ ውሳኔ የሚሰጥበትን ምርጫ  የሚያዘጋጅበት ነው።

6-የምርጫ መርሆች

የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 38 ላይ የተቀመጠ ሲሆን እነዚህም ሚስጥራዊነት ፣ ነጻ እና ሀሉን አቀፍ እና ገለልተኛ ናቸው።

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሰኔ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here