ብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ተሰማ – ‘‘የምፅዋዉ ዳግማዊ ቴዎድሮስ’’

0
420

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ወታደራዊ ታሪክ ውስጥ በጀግንነት፣ በቆራጥነት እና በኃላፊነት ስሜት ወታደራዊ ግዳጅን በመፈጸም የሚጠቀሱ ብዙ ወታደራዊ መኮንኖች አሉ። ከነዚህ መካከል በ1982 ዓ.ም ምፅዋ ላይ በተካሄደው ጦርነት ከተሳተፉት መካከል ብርጋዴር ጄነራል ተሾመ ተሰማ ጎልተው ይጠቀሳሉ። በወቅቱ የመከላከያ ሠራዊት ስድስተኛ ነበልባል ክፍለጦር አዛዥ በመሆን በምፅዋ ወደብ የተከፈተውን ጦርነት መርተዋል።

የብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ተሰማን አይረሴ የጦር ሜዳ ጀግንነት “አይ ምፅዋ” በተሰኘው የታደሰ ቴሌ ሳልሳኖ መፅሐፍ፣ በፕሮፌሰር መሳይ ከበደ “The Massawa Epic Battle” የመፅሃፍ ግምገማ ላይ እና በሌሎችም የታሪክ ድርሳናት በጉልህ ተፅፏል። ለዚህ ፅሑፍም ዋና የመረጃ ምንጭ ሆነዋል።

የጦር ሜዳ አዋጊ ጀኔራል ሥራ ትዕዛዝ መስጠት ብቻ አይደለም። ስትራቴጂ መንደፍ፣ ሠራዊትን ማነሳሳት፣ ሃብትን ማስተዳደር እና የጦር ህጎችንም ያስከብራል።

የጀኔራል ሥልጣን ትልቅ ቢሆንም ተጠያቂነቱም እንዲሁ ከባድ ነው። የሚሰጣቸው ውሳኔዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች እና ሲቪሎች ህይወት ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ስለዚህ ሃላፊነትን በጥበብ፣ በጥንቃቄ እና በሥነምግባር መወጣት ይጠበቅበታል። ኢትዮጵያዊው የጦር ሜዳ ጠቢብ ብርጋዲየር ጄኔራል ተሾመ ተሰማ ደግሞ ይህን ጠንቅቀው ያውቁ ነበር።

የካቲት 1982 ዓ.ም.። የቀይ ባሕር ዕንቁ የምትባለው ታሪካዊቷ የምጽዋ ወደብ፣ ከተፈጥሯዊው የሞቃት አየር ፀባይዋ ይልቅ በባሩድ ጭስ እንዲሁም በከባድና ቀላል መሣሪያ የተኩስ ድምጽ  ግላለች። የባሕሩ ማዕበል ከዳርቻው ጋር የሚጋጨው በተለመደው የሰላም ዜማ ሳይሆን፣ በሁለቱም ወገን የሚተኮሱ መድፎች በሚፈጥሩት አስገራሚ የድንጋጤ ንዝረት ነበር። “ኦፕሬሽን ፈንቅል” የተሰኘውና በሻዕቢያ ታጣቂዎች የተሰነዘረው መጠነ-ሰፊ ጥቃት፣ ከተማዋንና በውስጧ የነበረውን የመከላከያ ሠራዊት ሙሉ በሙሉ ከበባ ውስጥ ጥሎታል። ስትራቴጂካዊቷ ወደብ እና በውስጧ የነበረው የሰራዊት እጣ ፈንታ በደቂቃዎች ውሳኔ ላይ የተንጠለጠለበት ያ እጅግ አስፈሪና ታሪካዊ ምዕራፍ፣ ለብዙዎች የፍጻሜ ዋዜማ ይመስል ነበር።

ነገር ግን፣ በዚያ በጭስና በባሩድ በታፈነ፣ ተስፋ መቁረጥ በነገሰበት የጦር ግንባር እምብርት ውስጥ፣ የሚንቀሳቀስ አንድ የማይበገረ ስብዕና ነበር። እርሳቸው—ብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ተሰማ ናቸው።

ጄኔራሉ በወቅቱ የነበረውን አስከፊና አስጨናቂ እውነታ የተጋፈጡት በወታደራዊ ማዕረጋቸው ብቻ ሳይሆን፣ ካላቸው ጥልቅ የሀገር ፍቅር ስሜትና ፍጹም ከሆነ ቁርጠኝነት መነሻነት ጭምር ነበር። ዙሪያውን በከበባቸው ከባድ ጦርነት መሃል ሆነው፣ የሰራዊታቸውን ሞራል ለመጠበቅ እና እያንዳንዱን ስልታዊ እርምጃ በብልሃት ለመምራት ያሳዩት ፅናት፣ የምጽዋን ውጊያ በኢትዮጵያ ወታደራዊ ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ እንዲኖረው አድርጎታል። የጦርነቱ ድምፅ በጆሯቸው ላይ እየጮኸ፣ ሞት በቅርብ ርቀት ላይ እያዣበበ፣ እርሳቸው ግን የነደደውን እሳት ሰንጥቀው ለመሻገር የሚያስችል ወታደራዊ ጥበብን ይነድፉ ነበር።

በቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ የተከሰተው ያ! ከባድ  የውጊያ ድባብ ብቻ ሳይሆን፣ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እውነተኛ መሪዎች እንዴት እንደሚወለዱ የሚያሳይ ትልቅ ማሳያ ነው። ብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ተሰማ፣ በዚያ ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ የነበራቸው ሚና፣ ዛሬም ድረስ በወታደራዊ ሳይንስ፣ በታሪክ ድርሳናት እና በሌሎችም አጫጭር መጣጥፎች ውስጥ በጉልህ የሚወሳ ታላቅ የጀግንነት ታሪክ ነው።

ብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ተሰማ በኢትዮጵያ ወታደራዊ ታሪክ ውስጥ እጅግ ከተከበሩና እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ ለሀገር ሉዓላዊነት በፅናት ከተዋጉ እውነተኛ የጦር መሪዎች መካከል ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛሉ። የጄኔራሉ ወታደራዊ ስብዕና እና የሕይወት ታሪክ፣ ሀገራዊ ፍቅርና ወታደራዊ ዲሲፕሊን የተዋሃዱበት፣ ለሙያ የታመነ መሪነት ምን እንደሚመስል ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ ማሳያ ሆኖ የተመዘገበ ነው።

በዘመነ ደርግ ወታደራዊ መዋቅር ውስጥ በብቃትና በዕውቀታቸው ደረጃ በደረጃ እያደጉ የመጡት ጄኔራል ተሾመ፣ በተለይም እጅግ አስቸጋሪና ስልታዊ በሆኑ የጦር ግንባሮች ላይ በመመደብ ሰራዊቱን የመምራት ሰፊ ልምድ ነበራቸው። በታሪክ ማህደሮች እንደሚብራራው፣ እርሳቸው በጦር ሜዳ ላይ ያላቸውን የውጊያ ጥበብ እና መሪነት ያስመሰከሩት በንድፈ-ሀሳብ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ተራ ተዋጊ ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ይዘው ከሰራዊቱ ጋር አብረው በመፋለም ጭምር ነበር። ይህ ተግባራቸው በበታች መኮንኖቻቸው እና በተራው ሰራዊት ዘንድ ፍጹም ተሰሚነትንና ታላቅ ክብርን እንዲያገኙ አድርጓቸዋል።

ብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ተሰማ የምጽዋን ወደብ እና የቀይ ባሕር አካባቢን የመከላከል ኃላፊነት የነበረው የታዋቂው የ6ኛ ነበልባል ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ነበሩ። የ6ኛ ነበልባል ክፍለ ጦር በወቅቱ እጅግ በሰለጠነ የሰው ኃይል እና የውጊያ ስምሪት የሚታወቅ ወሳኝ ዕዝ ነበር። ጄኔራሉ ይህንን እልኽኛ እና ስልታዊ ክፍለ ጦር እየመሩ በቀይ ባሕር ጠረፍ ላይ የሀገሪቱን ታሪካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ደህንነት ለመጠበቅ በርካታ ውጊያዎችን በበላይነት መርተዋል።

በወታደራዊ ሳይንስ ዕውቀታቸው፣ ሰራዊቱን በማስተናበር እና ስልታዊ እቅዶችን በማውጣት ረገድ የነበራቸው ብቃት የሚደነቅ እንደነበር የታሪክ ፀሐፊው ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ “አይ ምጽዋ” በተሰኘው የታሪክ መጽሐፋቸው ላይ በሰፊው አስፍረውታል። ጄኔራል ተሾመ ከፖለቲካዊ ውሳኔዎች ይልቅ ለወታደራዊ ሙያዊ ግዴታቸው እና ለሀገር አንድነት ቅድሚያ የሚሰጡ መኮንን ነበሩ። ይህም በወቅቱ በነበሩት የፖለቲካ ካድሬዎችና በሰራዊቱ መካከል ፍጹም የሆነ ስምምነትና አንድነት እንዲፈጠር፣ ሰራዊቱም እስከ መጨረሻው የሞት ሽረት ሰዓት ድረስ በአንድነት እንዲቆም ለማድረግ አስችሏል።

ከወታደራዊ መሪነታቸው ባሻገር፣ ጄኔራሉ ለታሪክ እና ለቀጣዩ ትውልድ የነበራቸው አርቆ አሳቢነት ልዩ ያደርጋቸዋል። “የትኛውም ሀገር ያለ በር እና መስኮት አይሠራም” የሚለው የጄኔራሉ ጥልቅ ወታደራዊ እና ስልታዊ እይታ፣ የቀይ ባሕር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና እና የታሪክ ጉዳይ መሆኑን ቀድመው የተረዱ መሪ እንደነበሩ ያሳያል። ይህ በዕውቀት እና በደምና በአጥንት የተገነባው የወታደራዊ ሕይወት ጉዟቸው፣ በየካቲት 1982 ዓ.ም. በምጽዋ ግንባር ላይ ለተከሰተው እጅግ ታሪካዊና መራር ለሆነው የመጨረሻው ምዕራፍ መሰረት የጣለ ነበር።

የካቲት 1982 ዓ.ም. የተካሄደው የምጽዋ ውጊያ በሻዕቢያ ስያሜው “ኦፕሬሽን ፈንቅል” በኢትዮጵያ ወታደራዊ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስከፊ፣ መራር እና ወሳኝ የየብስና የባሕር ውጊያ የተካሄደበት ምዕራፍ ነበር። የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ) ታጣቂዎች ከየብስ ጥቃት ከመሰንዘራቸውም በላይ፣ የስዊድን ስሪት የሆኑ ፈጣን የውጊያ ጀልባዎችን በባሕር ላይ በማሰማራት ምጽዋን ከሌላው የሀገሪቱ ክፍል ሙሉ በሙሉ ለመቁረጥ ስልታዊ እቅድ ነደፉ። የታሪክ ጸሐፊው ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ _“አይ ምጽዋ”_ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት፣ በጥቃቱ መጀመሪያ ላይ የነበረው የኃይል ሚዛን እጅግ የተራራቀ እና መከላከያ ሰራዊቱ ባልተዘጋጀበት ሰዓት የተሰነዘረ ድንገተኛ ጥቃት ነበር።

በዚህ አስፈሪ ከበባ ውስጥ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ተሰማ፣ የ6ኛ ነበልባል ክፍለ ጦርን እየመሩ በከተማዋ ምሽግ ውስጥ ሆነው የሞት ሽረት መከላከል ጀመሩ። የምጽዋ ወደብ፣ የሲቪል ህዝቡ እና በሺዎች የሚቆጠሩ የሰራዊቱ አባላት እጣ ፈንታ በእርሳቸው ጠንካራ አመራር ላይ ወደቀ። በወቅቱ ሰራዊቱ ከባድ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የጥይት እጥረት ገጥሞት እንደነበርና ከአስመራ ይደረግለት የነበረው የአየር ላይ ድጋፍ በጠላት ጸረ-አውሮፕላን ምክነያት መድረስ እንዳልቻለ ጄኔራል ተሾመ ተሰማ ራሳቸው “የምጽዋው እሳት” በተሰኘው የግል ማስታወሻ መጽሐፋቸው ላይ በዝርዝር አስፍረውታል።

በዚህ እጅግ እልህ አስጨራሽ እና በተለያዩ ሴራዎች ምክንያት ምፅዋ በጠላት እጅ ወደቀች።

ጀግናው ብርጋዴር ጀኔራል ተሾመ ተሰማ “እኔ የሚፈለግብኝን አደራ ተወጥቻለሁ። ከጥር 30 ቀን 1982 እስከ ዛሬ የካቲት 9 ቀን 1982 ዓ.ም ድረስ የሞት ሽረት ትግል አድርጌያለሁ። የሻቢያን የጥፋት አላማ  ለመግታት ያላደረግሁት ጥረት የለም። ከዚህ በኋላ ግን የራስን ህይወት በክብር ከማጥፋትና ለኢትዮጵያ ጀግኖች እና ታሪክ ጸሐፊዎች ታላቅ ተምሳሌት ከመሆን ሌላ አማራጭ የለኝም። ጀግንነት ማለት በሁሉም መልክ ለጠላት ምቹ ሆኖ አለመገኘት ነው” በማለት ጀግናው ብርጋዴየር ጀኔራል ተሾመ ተሰማ በጠላት እጅ መውደቅን አልተመኙም። ከዚህ ይልቅ አፄ ቴወድሮስ መቅደላ የፈፀሙትነ ጀግንነት አሳቸውም ደገሙት።  በታጠቁ መሳሪያ ምፅዋ ወደብ ዳርቻ የካቲት 9 ቀን 1982 ዓ.ም መስዋትነትን ለኢትዮጵያ ከፈሉ።

ጀግናው ብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ተሰማ በምፅዋ ውጊያ ከተሰው በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት መጋቢት 1983 ዓ.ም የላቀ የጦር ሜዳይ ሸልሟቸዋል።

ሳምንቱ በታሪክ

የንጉሡ አቤቱታ

ፋሽስታዊው የኢጣሊያ ጦር በግፍ ሃገራችን ላይ ወረራ ፈፀመ። በቅኝ መገዛትን ያልመረጡ ጀግኖች በየአካባቢው ወራሪውን መዋጋት ቀጠሉ። ንጉሡ አፄ ኃይለ ሥላሴም ተሰደዱ።

ንጉሡ በስደት ላይም ሆነው ኢትዮጵያ ከወራሪው ነፃ እንድትወጣ የተለያዩ ጥረቶችን አድርገዋል። ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዠኔቭ በሚገኘው የዓለም መንግሥታት ማህበር ላይ በመገኘትም የኢጣሊያን ግፈኝት እና የኢትዮጵያን አቤቱታ ሰኔ 23 ቀን 1928 ዓ.ም አቀረቡ።

ቀዳሚው የቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት

“Our World” በዓለም የመጀመሪያው በሳተላይት የተገናኘ ዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ቀጥታ ስርጭት ነው። ስርጭቱ የተደረገው ደግሞ ሰኔ 25 ቀን 1967 ዓ.ም ነበር። በቴሌቪዥን ታሪክ ላይም አዲስ ምዕራፍ ሆኖ ተመዝግቧል።

በዚህ የመጀመሪያ ቀጥታ ስርጭት ፕሮግራም አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይን ጨምሮ 14 ሀገራት ተሳትፈዋል።

በቀጥታ ስርጭት ፕሮግራሙ የብሪታኒያው የሙዚቃ ቡድን The Beatles አዲሱን ዘፈን All You Need Is Love በቀጥታ አቅርቧል።

ምንጭ፦ Wikipedia

 

(ጥላሁን ወንዴ)

በኲር የሰኔ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here