በኢትዮጵያ ለምግብ ዋስትና እና ለሀገር አቀፍ ምርት ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው በክረምት (ከሰኔ እስከ ጥቅምት) ዝናብ ከመኸር እርሻ የሚገኘው ምርት ነው፡፡ በተለይም የብርዕ እና አገዳ ሰብሎች በክረምቱ መግቢያ ላይ ይዘራሉ፡፡
ከሀምሌ አምስት ጀምሮ ደግሞ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ገብስና የመሳሰሉት ይቀጥላሉ፡፡
የክረምቱን መግባት ተከትሎም አርሶ አደሩም፤
ሰኔ ደግሞ መጣ ክረምት አስከትሎ
ገበሬው ተነሳ ማረሻውን ስሎ፡፡
ሀምሌ ተከተለ ገባ ዝናብ ጭኖ
ቀንና ለሊቱን በዝናብ ጨፍኖ፡፡
ነሀሴ ተተካ ኀይለኛው ክረምት
ያወርደው ጀመረ የዝናብ መዓት፡፡በማለት ወራቱን እያነሱ እንዲህ በሥነ ቃል ያንጎራጉራሉ
እኛም የ2018/19 የመኸር ወቅት መግቢያ ላይ በተለይ ግንቦት እና ሰኔ ወር ዝናቡ ዘንቦ በቆሎ የሚዘራበት ወሳኝ ወቅት በመሆኑ በባሕር ዳር ዙሪያ የጎንባት ቀበሌ ነዋሪ የሆኑትን አቶ ፋንታሁን ከበደ የእርሻ ሥራው እንዴት ነው? ስንል በስልክ ጠየቅናቸው፡፡አርሶ አደሩ እንደሚሉት ዘንድሮ በዝናቡ መዘግየት መሬቱን አርሶ እና አለስልሶ ከሰማይ የሚወርድ ዝናብ ለመጠበቅ ተገዷል፡፡አለፍ አለፍ እያለ ዝናብ መጣል ሲጀምር “ያው ወቅቱ ስለሆነ መዝነቡ አይቀርም የሚል ተስፋ ሰማዩ ላይ ጥለን ዘር በመጣል ላይ ነን” በማለትም የዝናቡ መዘግየት ስጋት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡ይህም ሆኖ አልፎ አልፎ በሚጥለው ዝናብ በአንድ ሄክታር ተኩል ማሳቸው ላይ በቆሎ እና ዳጉሳ ዘርተዋል፡፡ባለፈው ዓመት በዚሁ ማሳቸው ላይ በቆሎ 20 ኩንታል ዳጉሳ ደግሞ 10 ኩንታል ምርት ማግኘት መቻላቸውን አስታውሰዋል፡፡
አቶ ፋንታሁን በ2018/19 የምርት ዘመን የማዳበሪያ እጥረት እንዳይገጥማቸው በማሰብ ቀድመው የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፓስት) በሥፋት አዘጋጅተው በቆሎ ሲዘሩ (ሲጥሉ) አብረው እየበተኑ እንደዘሩ ነው የገለጹት፡፡
የዘንድሮ እርሻ ሥራ ላይ ከባለፈው ዓመት በተለየ መንገድ እንዲሠሩ በግብርና ባለሙያዎች ምክር አግኝተዋል፡፡ በመስመር ዘር ሲጣል ከቀድሞው በተለየ አንድ አንድ እያደረጉ ስለሚጥሉ የማዳበሪያ አጠቃቀሙ ከባለፈው ዓመት መጠን በላይ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡ እንደ አርሶ አደሩ ገለጻ ቀድሞ ለአንደ ሄክታር ይበቃ የነበረ ማዳበሪያ ዘንድሮ ለግማሽ ሄክታር ብቻ ይውላል፡፡
የማዳበሪያ ዋጋም ዘንድሮ ከፍተኛ በመሆኑ እንኳን አቅሙ ለሌለው ላለውም ለመግዛት ከባድ መሆኑን አርሶአደሩ ጠቁመዋል፡፡ከዚህ ባለፈም ገንዘቡ ቢኖር እንኳ የቀረበው የማዳበሪያ መጠን አነስተኛ በመሆኑ አቅርቦቱ በመቆራረጡ ችግር እንደ ሆነባቸው አንስተዋል፡፡
ሌላው የወንዳጣ ቀበሌ ነዋሪው ቄስ አሌ አለቃ በበኩላቸው እርሳቸውን ጨምሮ በብዛት ከብት ያላቸው አርሶ አደሮች ለ2018/19 የምርት ዘመን የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፓስት) በሥፋት ማዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡የአርሶ አደሩ ዝግጅት እና የባለሙያው ድጋፍ በተሟላ ሁኔታ ቢጠናቀቅም የማዳበሪያ ፍላጎት በግማሽ መቅረብ እና የኩንታሉ ዋጋ ከ11 እስከ 12 ሺህ ብር መሆኑን እንደ ችግር አንስተዋል፡፡በምርጥ ዘር አቅርቦት በኩል ግን የፈለጉት አይነት ዘር በሥፋት እየቀረበ መሆኑን ነው ለበኵር የተናገሩት፡፡
የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ሰብል ልማት እና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ጌጡ ዓለሙ እንደነገሩን በዘንድሮ በወረዳው የመኸር እርሻ በዘር ለመሸፈን የታቀደው 49 ሺህ 413 ሔክታር መሬት ነው፡፡ከዚህ ውስጥ የታረሰው መሬት ግን 50 ሺህ 998 ሔክታር ነው፡፡ይህም አፈጻጸሙ ከታቀደው በላይ ነው፡፡አርሶ አደሮች በአሁኑ ወቅት ማሳቸውን በዘር የመሸፈን ሥራ ጀምረዋል፡፡ለአርሶአደሩ አማራጭ ዘሮች ሁሉ መቅረብ መቻላቸውንም ነው ያረጋገጡት፡፡
እንደ ቡድን መሪው ማብራሪያ የዝናብ እጥረት ቢኖርም መዝነቡ አይቀርም በሚል ተስፋ አርሶ አደሩ በደረቁ ዘር እየዘራ ነው፤ የማዳበሪያ አቅርቦቱ ግን የሚፈለገውን ያህል መጠን ባይሆንም የተመደበውን በወቅቱ ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡የቀረበውን ማዳበሪያም ቢሆን ዋጋው ውድ ነው በሚል አርሶ አደሩ እየወሰደው አለመሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በተፈጥሮ ማዳበሪያ ልማት በኩል በኮምፓሰት እና በርሚ ኮምፓስት ሥራ ወደ አንድ ሚሊየን አንድ መቶ አስራ አንድ ሺህ ኩንታል ተመርቶ ለመስኖ እና ለመኸር ሰብል ልማት ተዘጋጅቷል፡፡ ይህም በዘር ወቅት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ በ2018/19 የምርት ዘመንም በወረዳው ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊየን ኩንታል ምርት ይመረታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው የገለፁት፡፡ለእቅዱ መሳካት ግን የዝናብ ስርጭቱ ዋናው መሆኑን ነው አቶ ጌጡ ያነሱት፡፡
በዘንድሮው የመኸር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ከሚለማው መሬት ከ205 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለፁት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ/ር) ናቸው። የሚገኘው ምርት ከባለፈው ዓመት በ18 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡ በሰብል ለመሸፈን ከታቀደው መሬት ውስጥ እስካሁን አራት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት አንደኛ ዙር እርሻ ታርሷል።
ዳይሬክተሩ እንደገለጹት የግብርና ሥርዓቱን ማዘመን እና ከልማዳዊ አሠራር ማውጣት ይጠበቃል። ለዚህም አርሶ አደሩን ከበሬ ጫንቃ ለማላቀቅ፣ ጊዜ እና ጉልበቱን ለመቆጠብ እና ምርታማነትን ለማሳደግ የእርሻ ሜካናይዜሽን አሠራር በትኩረት እየተተገበረ ነው። ለእቅዱ ስኬታማነትም በክልሉ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሔክታር መሬት በትራክተር ለማረስ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።
በምርት ዘመኑ ምርታማነትን ለማሳደግ እና የታለመውን ዕቅድ ለማሳካት የኩታ ገጠም እርሻ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ነው ዳይሬክተሩ ያብራሩት። ለአማራ ክልል በ2018/19 የምርት ዘመን ከስምንት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ (ዳኘ እና ዩሪያ) እንደሚያስፈልገው ታቅዶ እየተሠራ ሲሆን ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት (እስከ ሰኔ አጋማሽ) ከ46 በመቶ በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ እንደገባ ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በ2017/18 የምርት ዘመን በዞኑ 321 ሺህ 531 ሔክታር መሬት ለምቶ 16 ሚሊዮን 571 ሺህ 108 ኩንታል ምርት መገኘቱም መረጃው አመላክቷል፡፡ የዘንድሮው እቅድ መሬትን ከ10 ሺህ ሔክታር በላይ ምርትን ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ለማሳደግ ያለመ መሆኑም ጠቁሟል።
መረጃ
እንደ ሀገር በመኸር እርሻ ዙሪያ ያሉ ቁልፍ እውነታዎች
ዋና ዋና ሰብሎች – በዋናነት ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ሩዝ፣ አኩሪ አተር እና ሠሊጥ በስፋት ይመረታሉ።
የኩታ ገጠም ልማት- ከጠቅላላው የመኸር እርሻ መሬት ከፍተኛው (ከግማሽ በላይ ወይም 70%) የሚሆነው በአጎራባች አርሶ አደሮች የጋራ አሠራር በሆነው በኩታ ገጠም (ክላስተር) ዘዴ ይመረታል። ይህ አሠራር የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን እና ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ ለመጠቀም ያስችላል።
የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም- ምርትን ለማሳደግና ለዘመናት ያልታረሱ አዳዲስ መሬቶችን ጭምር ለማልማት ትኩረት ተሰጥቷል።
የምርት ተስፋ- በዘመናዊ አሠራርና ምርጥ ዘር አጠቃቀም አርሶ አደሮች ከሚለሙት ማሳ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ያገኛሉ።
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የሰኔ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


