ዘመናዊ የትምህርት ቤት ግንባታ – ለትምህርት ጥራት

0
341

ትምህርት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን በመፍታት የሀገርን እድገት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና አለው፡፡ ይህም ትውልድን በመቅረጽ፣ አቅም የፈጠረ ብቁ የሰው ኀይል በማፍራትና በሰላም ግንባታ ላይ የማይተካ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ የተማረ፣ ብቃት ያለውና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት ደግሞ ከትምህርት ሥርዓቱ ጥራት ባሻገር ምቹ የመማሪያ  አካባቢ መፍጠር ወሳኝ ጉዳይ ነው።

በተለይ በቅድመ አንደኛ ደረጃ የሚገኙ ሕፃናት ለመማር በሚያደርጉት የመጀመሪያ ጉዞ የሚቀረጹት በሚገኙበት አካባቢ ነው። ለዚህም ከግቢው ውጭ ጀምሮ እስከ መማሪያ ክፍል የዘለቀ  ንጹህ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ለመጫዎትና ለመማር ምቹ የሆነ ትምህርት ቤት መገንባት የሕፃናትን የወደፊት ስኬት መሠረት መጣል ነው።

በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘው የመስከረም 16 ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደግሞ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህርት ወ/ሮ አየሁ ባለው ለበኵር ጋዜጣ እንደተናገሩት ከዚህ በፊት ሕፃናት ይማሩበት የነበረው ሕንጻ ንጽህናው ያልተጠበቀ፣ በቂ የመቀመጫ ወንበርና ጠረጴዛ የሌለው፣ ለሕፃናት ደህንነት የማይመች እና ለመማር ማስተማር ተስማሚ ያልሆነ ነበር። በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ የሚማሩ ሕፃናት ደግሞ የትምህርት ፍላጎታቸው እንዲቀንስ እና በጤናቸውም ላይ ተጽዕኖ እንዲያድር  የማድረግ ተጽእኖው ከፍያለ ነው፡፡

ሆኖም ትምህርት ቤቱ  በ2018 የትምህርት ዓመት በመንግሥት፣ በግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና በተለያዩ አጋር ተቋማት ትብብር 14 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ሦስት ሕንጻዎች  ተገንብተው ወደ ሥራ መግባቱን ርእሰ መምህርቷ ገልጸዋል። በትምህርት ዘመኑም ትምህርት ቤቱ 757 የሚደርሱ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ቆይቷል፡፡ በተገነቡት ክፍሎች ለሕፃናቱ ተስማሚ  ወንበሮችና ጠረጴዛዎች ተሟልተውላቸዋል፡፡ የመጫወቻ አሻንጉሊቶች፣ የፈጠራ ክህሎትን የሚያዳብሩ የግንባታ ቁሳቁሶች እና ራስን በራስ ለመማር የሚያበረታቱ የትምህርት መሳሪያዎችም  ለሕጻናቱ ቀርበዋል።

እንደ ርዕሰ መምህርቷ ገለጻ ቁሳቁሶች ሕፃናት በጨዋታ ቁምነገር እንዲጨብጡ፣ በፈጠራ እያሰቡ እና በራሳቸው ችሎታ እንዲያድጉ የሚያግዙ ናቸው። ተማሪዎች ምሳቸውንና የትምህርት ቁሳቁሶቻቸውን በሥርዓት የሚያስቀምጡባቸው መደርደሪያዎችም መዘጋጀታቸው  ከትምህርት ጎን ለጎን  ሥነ ሥርዓትን ከልጅነት ጀምሮ ለማዳበር ያግዛል።

ትምህርት ቤቱ የሁሉንም ሕፃናት የመማር መብት ለማረጋገጥ ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች የተለየ ክፍል ማዘጋጀቱም በጎ ተሞክሮ መሆኑን ሆኖ ተጠቅሷል። በዚህ ክፍል ኮምፒውተሮችን ጨምሮ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ሕፃናት ሊያግዙ የሚችሉ የተለያዩ ቁሳቁሶች መሟላታቸውን እኛም በቆይታችን አረጋግጠናል። ይህ አካሄድ ማንኛውም ሕፃን ከትምህርት ውጭ እንዳይቀር የሚደረገውን ጥረት ያሳያል።

በትምህርት ቤቱ  ንጹህ የመጠጥ ውኃ እና ደረጃውን የጠበቀ መጸዳጃ ቤት መገንባቱ ለተማሪዎች ጤና እና ደህንነት የተሰጠውን ትኩረት ያረጋግጣል። ንጹህ እና ማራኪ የትምህርት  አካባቢ መፍጠርም የተማሪዎች የትምህርት ተሳትፎአቸው እና የመማር ፍላጎታቸው ከፍ ይላል፤  ይህ ሲሆን ደግሞ የትምህርት ጥራት እንደሚሻሻል  ርእሰ መምህሯ ጠቁመዋል፡፡

መምህርት አየሁ ባለው እንደሚናገሩት ትምህርት ቤት በመንግሥት ብቻ የሚገነባ አይደለም፤ የማህበረሰብ፣ የልማት አጋሮች እና የተለያዩ ተቋማት ተሳትፎን የሚጠይቅ ሥራ ነው። በዚህም  የአካባቢውን ነዋሪዎች አቅም በማገናዘብ ለአንድ ተማሪ 350 ብር ወርሃዊ ክፍያ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡ አቅም የሌላቸው ቤተሰቦች ልጆቻቸው በነጻ የሚማሩበት ሁኔታ መመቻቸቱንም ገልጸዋል።

በቀጣይም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ለሕፃናት የውጭ መጫወቻ ሥፍራዎችን ለማዘጋጀት  በሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በትምህርት ቤቱ ዙሪያም ተማሪዎችን ሊያውኩ የሚችሉ የንግድ ወይም ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ከትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ በማራቅ የተሻለ የመማሪያ አካባቢ ለመፍጠር ተጨማሪ ሥራዎች እንዳሉ አስረድተዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ትበይን ባንትይሁን እንደገለጹት በከተማው ውስጥ የመስከረም 16 ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ጨምሮ በሌሎችም  አዳዲስ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ሕንጻዎች፣ አጥር እና መጸዳጃ ቤቶች ተገንብተዋል። በአጠቃላይ 43 የመማሪያ ክፍሎችን ያካተቱ 12 ሕንጻዎች  ለመገንባት 71 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ መደረጉንም ገልጸዋል።

ወ/ሮ ትበይን እንደሚሉት ግንባታዎች በአብዛኛው ለቅድመ አንደኛ ደረጃ  ተማሪዎች የተዘጋጁ ሲሆን፣ ሕፃናት ከትምህርት ጉዟቸው መጀመሪያ ጀምሮ በንጹህ፣ በውብ እና ለትምህርት በሚያነሳሳ አካባቢ እንዲማሩ ታሳቢ ተደርገው የተገነቡ ናቸው። እንደ እርሳቸው ገለጻ ጤናማ እና የተሻለ ራዕይ ያለው ትውልድ ለመፍጠር ከሕፃናት የመጀመሪያ የመማሪያ አካባቢ መጀመር ይገባል።

የትምህርት ቤት ግንባታ በትምህርት ጥራት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ በዓለም ላይ በተለያዩ ሀገራት ተረጋግጧል። ፊንላንድ፣ ሲንጋፖር እና ደቡብ ኮሪያን የመሳሰሉ ሀገራት ከመምህራን ብቃት ጋር ተያይዞ ለትምህርት መሠረተ ልማት ትኩረት በመስጠታቸው ውጤታማ የትምህርት ሥርዓት መገንባት ችለዋል። ለሕፃናት ተስማሚ የሆኑ ክፍሎች፣ የመጫወቻ ሥፍራዎች፣ ቤተ መጻሕፍት እና የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች የትምህርት ውጤትን በእጅጉ እንደሚያሻሽሉም ተረጋግጧል።

በባሕር ዳር ከተማ የተገነቡት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሕንጻ ግንባታ ብቻም የሚገለጹ አይደሉም፤ ለነገው ትውልድ የሚደረግ ረጅም ጊዜ የሚያስቆጥር ኢንቨስትመንት ናቸው። ዛሬ በንጹህና በምቹ ክፍሎች ውስጥ የሚማሩ ሕፃናት ነገ ሀገራቸውን የሚመሩ፣ ችግሮችን የሚፈቱ እና ለእድገት መሠረት የሚሆኑ ዜጎች ይሆናሉ። በዚህ ሂደት የመንግሥት፣ የማህበረሰብ፣ የልማት አጋሮች እና የግል ተቋማት ተሳትፎ እየጠነከረ መሄድ ደግሞ የተሻለ የትምህርት ሥርዓትን ለመገንባት ቁልፍ መሆኑን ምክትል መምሪያ ኃላፊዋ አብራርተዋል።

ሆኖም የመማር ማስተማሩን ሂደት የተሻለ እና ውጤታማ ለማድረግ ሕንጻ ከመገንባት ባለፈም ትምህርትን ሊጎዱ እና ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው ሊያደናቅፉ  ከሚችሉ ተግባራት ማራቅ ይገባል፡፡ በመሆኑም በትምህርት ቤቶች አካባቢ ተማሪዎችን ከትምህርታቸው ሊያደናቅፉ እና ሊረብሹ  ከሚችሉ የንግድ ሥራዎች  ለማራቅ የሚያስችል ሥራ መጀመሩን  ነው የተናገሩሩ፡፡

እንደ ወ/ሮ ትበይን ማብራሪያ ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ ሁኔታ ቢኖርም ሙሉ በሙሉ ጸድቷል  ማለት አያስችልም፤ በቀጣይ ቅሬታቸውን ይዘው የሚመጡ አካላትን እየተከታተልን በማጣራት ከክፍለ ከተማው ጋር በመነጋገር መፍትሔ ለመስጠት ጥረት እየተረገ ነው፡፡

 

መረጃ

በትምህርት ቤቶች አካባቢ የተማሪዎችን ደህንነት፣ ሥነ-ምግባር፣ ጤና እና የመማር አካባቢ ለመጠበቅ ሲባል የሚከተሉት ዓይነት የንግድ ተቋማት በትምህርት ቤቶች አጠገብ መኖራቸው ተገቢ አይደለም፦

የአልኮል መሸጫ ቤቶች (ባሮች፣ መጠጥ ቤቶች)

የሺሻ እና የትንባሆ ሽያጭ ቦታዎች

የቁማር እና ውርርድ ቤቶች

የሌሊት መዝናኛ ቤቶች (ናይት ክለቦች)

የቪዲዮ ጌም ማዕከላት እና የመዝናኛ ሱቆች

በትምህርት ሰዓት ተማሪዎችን ከትምህርት ሊያስቀሩ የሚችሉ

የእጽ እና ሕገ-ወጥ መድኃኒት ሽያጭ ቦታዎች እና ሌሎችም

ለተማሪዎች ጤና አደገኛ የሆኑ ምግቦችን ወይም የማይጠበቁ ምግቦችን የሚሸጡ ሱቆች ናቸው።

እነዚህ ተቋማት ከትምህርት ቤቶች ርቀው እንዲገኙ ማድረግ የተማሪዎችን ትምህርት ትኩረት፣ ጤና እና ደህንነት ለማረጋገጥ ይረዳል።

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የሰኔ 22  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here