ክልሉ ለአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች ትኩረት ሰጥቷል

0
325

ደቡብ ኮሪያ በዓለም ላይ በደን ልማትና በአረንጓዴ ሽፋን ማስፋፋት የተሳካ ተሞክሮ ካላቸው ሀገራት አንዷ ናት። ከ1950–1953 በተካሄደው Korean War በኋላ የሀገሪቱ ደኖች በእጅጉ ተጎድተው ነበር። ድህነት፣ የእንጨት እጥረት እና ከፍተኛ የአፈር መሸርሸር ችግር በሃገሪቱ ተከስቶ ነበር። ነገር ግን ከ1960ዎቹ ጀምሮ የሃገሪቱ መንግሥት፣ ማህበረሰብ እና ተቋማት በተቀናጀ ሁኔታ የሀገር አቀፍ የደን ልማት መርሃ ግብርን አስጀመሩ። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችም ተተከሉ፣ የተራቆቱ ተራሮች እንደገና አረንጓዴ ሆኑ፣ ህዝቡም በዘመቻው ውስጥ በንቃት ተሳተፈ። ኮሪያውያን በዚህ ተግባራቸው የአፈር መሸርሸርና የጎርፍ አደጋ በእጅጉ ቀነሰ፣ የውሃ ምንጮችም ተጠብቀው የውሃ አቅርቦቷ ተሻሽሎ የአካባቢው የአየር ንብረት ስርዓትን መመለስ ችለዋል፤ ከደን ውጤቶችና ከኢኮ ቱሪዝም የሚገኝ ገቢዋም ጨምሯል። ይህ ተግባ[ም በዓለም ላይ የተራቆተን መሬት ወደ አረንጓዴ ደን በመመለስ ምሳሌ ሀገር እንድትሆንም አስችሏታል።

 

በኢትዮጵያም የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ከተጀመረበት 2011ዓ.ም ጀምሮ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። ይህም በሀገሪቱ ለበርካታ ዓመታት የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ እና የሀገሪቱ የደን ሽፋን ከ17 በመቶ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ገደማ እንዲያድግ ማድረጉን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት መረጃ ያሳያል።

 

የተተከሉት ዛፎችም የአፈር መሸርሸርን በመከላከል የከርሰ ምድር ውኃ እንዲጠናከር፣ የውኃ ምንጮች እና ወንዞች እንደገና ወደነበሩበት እንዲመለሱ ረድተዋል። የካርቦን ልቀትን በመቀነስ ረገድም ሀገራዊ እና ዓለምአቀፋዊ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

 

ከዚህ በተጨማሪም ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እና ለምግብ ዋስትናም አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው፡፡ ከተራ ዛፎች በተጨማሪ ለምግብነት የሚውሉ እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ እና ቡና ያሉ ዘላቂ ጠቀሜታ ያላቸው ተክሎች በስፋት መተከላቸው አርሶአደሮች ከምግብ ፍጆታ ባሻገር ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ አግዟቸዋል።

 

ይህ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ኢትዮጵያ አቦካዶ ምርትን ለውጭ ገበያ በመላክ በአፍሪካ  ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ እንድትልም አድርጓል። የቡና ልማት መስፋፋት እና የውጭ ምንዛሬ ግኝትም ማደግ ችሏል። በችግኝ ማፍላት፣ በመንከባከብ እና የጥበቃ ሥራዎች ላይ ተሳትፎ ላደረጉ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድሎችንም ፈጥሯል።

 

ይህ መርሃ ግብር ኢትዮጵያውያን ሃይማኖት፣ ብሔር፣ ዕድሜ እና መሠል ጉዳይ ሳይገድባቸው ለአንድ ዓላማ በጋራ እንዲሰለፍ በማድረግ ረገድ ትልቅ ማኅበራዊ ትስስር ፈጥሯል። ችግኝ መትከል ብቻ ሳይኾን የመንከባከብ እና የማሳደግ “የአረንጓዴነት” ባሕል እና ንቃተ ህሊና እንዲዳብርም አድርጓል።

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የምታደርገውን ጥረት ለዓለም በማሳየት ረገድም የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ኾኗል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ አርዓያ መኾን እንድትችልም አድርጓታል።

 

በአማራ ክልልም መርሃ ግብሩ ከተጀመረበት 2011 ዓ.ም ጀምሮ የተከላ መጠኑ በየዓመቱ እየጨመረ መጥቷል። በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ትኩረቱ በደን ዛፎች ላይ የነበረ ሲሆን፣ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ግን ፍራፍሬዎችን፣ የእንስሳት መኖ የሚሆኑ ዝርያዎችን እና ለአርሶ አደሩ ቀጥተኛ ጥቅም የሚያስገኙ ተክሎችን በማካተት እየተስፋፋ መጥቷል፡፡

 

 

በዋግ þምራ ብሔረሰብ አሥተዳደርም ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጀመሩን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኀላፊ አዲሱ ወልዴ ገልጸዋል።

 

ዋግ þምራን ከበረሃማነት ለማላቀቅ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዋነኛ መፍትሄ መኾኑን ለአሚኮ የገለጹት የመምሪያ ኀላፊው ለዚህም በ41 የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች እስከ አሁን ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

በ360 ተፋሰሶች በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልኾኑ ተቋማት እንዲሁም በሃይማኖት ተቋማት ላይ የችግኝ መትከያ ጉድጓድ እየተዘጋጀ መኾኑንም አብራርተዋል። ለዚህም ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የችግኝ መትከያ ጉድጓድ ተዘጋጅቷል ነው ያሉት።

 

የተዘጋጁ የችግኝ ዓይነቶችም ለዝናብ አጠር አካባቢዎች ተስማሚ የኾኑ ሀገር በቀል ችግኞች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች እና የደን ችግኞች መኾናቸውንም አክለው ተናግረዋል። በ47 የችግኝ ጣቢያዎች ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ ቀሪ ችግኞችን ለማፍላት እየተሠራ እንደኾነም ጠቁመዋል።

ዋግ þምራን ከበረሃማነት እና ከድርቅ ለመታደግ ሁሉም ማኅበረሰብ የራሱን አሻራ ለማስቀመጥ ሊዘጋጅ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በሰቆጣ ከተማ 02 ቀበሌ የሚገኘው የበለስ ችግኝ ጣቢያ ሠራተኛ አቶ መንግሥቱ ኃይሌ እና አቶ ተገኘ አበራ ባለፉት ዓመታት ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሀገር በቀል ችግኞችን እንዳቀረቡ ገልጸው በተያዘው ዓመትም በችግኝ ጣቢያው የደን፣ የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞችን እንዳዘጋጁ ጠቅሰዋል።

 

በዋግ þምራ ባለፈው ዓመት የነበረው የችግኝ የጽድቀት መጠኑ 66 በመቶ የነበረ ሲኾን በተያዘው ዓመት የጽድቀት መጠኑን ከ80 በመቶ በላይ ለማድረስ እንደ ብሔረሰብ አሥተዳደር እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ እስካለፈው ዓመት ድረስ በክልሉ ከ10ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ከ1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይ መተከላቸው ትልቅ ውጤት ነው ያሉት የአማራ ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት ናቸው ።

 

ዳይሬክተሩ ለአሚኮ እንደተናገሩት በመርሃ ግብሩ መጀመሪያ ዓመታት 70 በመቶ ገደማ የነበረው የችግኞች ጽድቀት ዛሬ 80 በመቶ ደርሷል። ይህ የተገኘው ውጤት የሚያሳየው የአረንጓዴ ዐሻራ ስኬት በተተከሉ ችግኞች ብዛት ብቻ የሚለካ ሳይሆን የድህረ ተከላ እንክብካቤን በጥብቅ መከታተል በመቻሉ ነው ብለዋል።

 

የተተከሉት ችግኞች በተግባር የደን ሽፋን ለውጥ ማምጣታቸውም ተጠቃሽ ነው። በክልሉ የደን ሽፋን ከ13ነጥብ 9 በመቶ ወደ 18 ነጥብ 9 በመቶ ከፍ ማለቱ የመርሃ ግብሩን ተጨባጭ ውጤት ያሳያል ብለዋል። ይህም በአፈር መሸርሸር መቀነስ፣ በውሃ ሀብት ጥበቃ፣ በብዝሃ ሕይወት መጠበቅ እና በአካባቢ ሙቀት ላይ የሚኖረውን አዎንታዊ ተጽዕኖ በማጠናከር ረገድ ውጤት አምጥቷል፡፡

ደይሬክተሩ አክለውም በመርሃ ግብሩ ውስጥ የተወሰደው ሌላ ጠቃሚ አቀራረብ የ“ጥምር ደን እርሻ” ሥርዓት ነው። ይህ አቀራረብ ዛፎችን ከሰብል እርሻ ጋር በማዋሃድ የአፈር ለምነትን ለማሳደግ፣ የእርሻ ምርትን ለማሻሻል እና ለአርሶ አደሮች ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለመፍጠር ያገለግላል። በጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ የተሰጠው ትኩረትም የቤተሰብ ምግብ ደህንነትን ከማጠናከር ባለፈ የገቢ ምንጭ እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

 

የመርሃ ግብሩ ስኬት ከቅድመ ዝግጅት ስራ ጋር በቅርብ የተገናኘ መሆኑንም አቶ እስመለአለም ያስረዳሉ። ተከላ ከመጀመሩ በፊት የአካባቢውን አግሮ-ኢኮሎጂ በመለየት፣ ደጋ፣ ወይናደጋ እና ቆላ አካባቢዎችን በተለየ መልኩ በመመደብ፣ ለእያንዳንዱ አካባቢ የሚስማሙ የዛፍ ዝርያዎችን መምረጥ ይከናወናል። የጉድጓድ አቆፋፈር፣ የእርጥበት ሁኔታ ጥናት እና የተከላ ቦታ ዝግጅት በሳይንሳዊ መንገድ መፈጸማቸው የጽድቀት መጠኑን ለማሳደግ ያገለገሉ ዋና ምክንያቶች ናቸው።

 

ከአካባቢ ጥበቃ በተጨማሪ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በሥራ ዕድል ፈጠራ ረገድም አስፈላጊ ሚና ተጫውቷል። ችግኝ በማፍላትና በመሸጥ፣ የደን ዘር በመሰብሰብ፣ የተፈጥሮ ሀብት ቦታዎችን በማልማት፣ ንብ በማነብ እና የእንስሳት መኖ በማምረት በየዓመቱ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች የሥራ ዕድል እያገኙ መሆኑ መርሃ ግብሩ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም እንዳለው ያሳያል።

የማህበረሰቡ አመለካከት መቀየሩም ከቁጥር በላይ የሚታይ ስኬት ነው። “አንድም ችግኝ ያለባለቤት መተከል የለበትም” የሚለው አቀራረብ ማህበረሰቡን በቀጥታ ባለቤት በማድረግ የችግኞችን ጽድቀት እና የድህረ ተከላ እንክብካቤ አጠናክሯል።

 

በ2018 የበጀት ዓመትም 1 ነጥብ 76 ቢሊዮን የሚጠጉ ችግኞች መዘጋጀታቸውና ከ261 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለተከላ መዘጋጀቱ መርሃ ግብሩ በቀጣይ ዓመታትም በተመሳሳይ መንፈስ እንደሚቀጥል ያመለክታል። ከእነዚህ ውስጥ 25 ሚሊዮን የሚሆኑት የፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸው ደግሞ የአረንጓዴ ዐሻራው ወደ ምግብ ዋስትና እና ወደ ገቢ ማሻሻያ እያመራ መሆኑን ያሳያል ነው ያሉት።

በአጠቃላይ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ዛፍ የመትከል ዘመቻ ብቻ ሳይሆን የአፈር ጥበቃን፣ የምግብ ዋስትናን፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን፣ የገጠር ኢኮኖሚ ማነቃቂያን እና የአካባቢ ዘላቂነትን በአንድ ላይ ያቀፈ ልማታዊ እንቅስቃሴ ሆኗል። በቀጣይ ዓመታት የተከላው ጥራትና የድህረ ተከላ እንክብካቤ ተጠናክሮ ከቀጠለ፣ መርሃ ግብሩ በአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን በአገር ደረጃም የአካባቢና የኢኮኖሚ ለውጥ አስፈላጊ ምሰሶ ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል።

 

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የሰኔ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here