ሊጉ እንዴት ተጠናቀቀ?

0
174

የ2018 ዓ.ም የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ  በአራት የተለያ ከተሞች ተደርጎ ተጠናቋል፤ አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ሀዋሳ እና ድሬዳዋ ጨዋታዎች የተደረጉባቸው ከተሞች ሲሆኑ 20 ክለቦች በአጠቃላይ 380 ጨዋታዎችን አድርገዋል፡፡ በእነዚህ  ጨዋታዎች ውስጥ 675 ግቦች ተቆጥረዋል፤ ይህም በአንድ ጨዋታ በአማካይ ከአንድ ግብ በላይ ተቆጥሯል ማለት ነው፡፡ የዘንድሮው የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስደናቂ፣ ያልተገመቱ ክስተቶች የበዙበት እና እስከ መጨረሻው  ፉክክር የታየበት ዓመት ሆኖ ተጠናቋል፡፡

ሲዳማ ቡና 68 ነጥቦች በመሰብሰብ የ2018 ዓ.ም የሊጉ ሻምፒዮን በመሆን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የዘውድ አክሊል ደፍቷል፡፡ በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ መሪነት በውድድር ዓመቱ ያሳየው ወጥ የሆነ አቋም በዋንጫ ታጅቦ እንዲጨርስ አድርጎታል፡፡ በተለይ በሁለተኛው ዙር ከተፎካካሪዎቻቸው የሰበሰቧቸው ነጥቦች ሁለት ቀሪ ጨዋታ እየቀራቸው ዋንጫ ማንሳታቸውን እንዲያረጋግጡ አስችሏቸዋል።

እስከ መጨረሻዎቹ ሳምንታት ድረስ ሲዳማ ቡናን እግር በእግር እየተከተለ ከፍተኛ ፉክክር ሲያደርግ የነበረው አዲስ አዳጊው ነገሌ አርሲ በዚህ ዓመት የሊጉ ክስተት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ነገሌ አርሲ በመጀመሪያው ዓመት የሊጉ ቆይታው ያሳየው ፍርሃት አልባ እና ፈጣን የማጥቃት እግር ኳስ የፕሪሚየር ሊጉን ታላላቅ ክለቦች የፈተነ ነበር፡፡ ክለቡ በመጨረሻም በ60 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል፡፡

መቻልም በጠናቀቀው የውድድር ዓመት ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች ከታዳጊዎች ጋር በማጣመር ጥሩ የሚባል የውድድር ጊዜ አሳልፏል፤ ክለቡ በ57 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ መጨረስ ችሏል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ወጥ አቋም ማሳየት የተሳነው አንጋፋው የፕሪሚየር ሊጉ ክለብ  ቅዱስ ጊዮርጊስ በትልልቅ ጨዋታዎች ላይ ያለውን  ልምድ ተጠቅሞ በቅርብ ርቀት የዋንጫ ተፎካካሪ ሆኖ አጠናቋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የሊጉ ድምቀት እና ጠንካራ ተፎካካሪ የነበሩት ሁለቱ የአማራ ክልል ክለቦች ፋሲል ከነማ እና ባሕር ዳር ከተማ የዘንድሮው አቋማቸው ለብዙ የእግር ኳስ ተንታኞች ዋነኛ የመነጋገሪያ ርእስ ነበረ፡፡ በ55 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት አፄዎቹ በአማካይ ክፍላቸው የነበራቸው የኳስ ቁጥጥር እና የጨዋታን ፍጥነት የመወሰን ብቃት  ድንቅ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከኳስ ውጭ የነበራቸው የተደራጀ መዋቅር እና ወደ ማጥቃት የሚሸጋገሩበት ፍጥነትም በበጎ የሚነሳ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የተፈጠሩ ዕድሎችን ወደ ግብ የመቀየር ብቃት የቡድኑ ዋነኛ ክፍተቶች እንደነበሩ በተደጋጋሚ ተመልክተናል፡፡ የኋላ ክፍሉም በቀላሉ የሚሸበር እና በቀላሉ ግብ የሚቆጠርበት ነበር፤ በዚህ ምክንያት ብዙ ጨዋታዎችን እየመሩ ውጤታቸውን አስጠብቀው መውጣት ተስኗቸው በተደጋጋሚ ነጥብ ሲጥሉ ዐይተናል፡፡

የጣናው ሞገድ ዘንድሮ በ48 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ይዞ ነው ያጠናቀቀው፡፡ 20 ጨዋታዎችን ነጥብ ተጋርቶ ከሜዳ ወጥቷል፤ ይህም በዚህ ዓመት የአቻ ውጤት አባዜ የተጠናወተው ቀዳሚ የሊጉ ክለብ ነው፡፡ የተከላካይ ክፍላቸው ግን በታክቲክ ዲሲፕሊን የታነጸ በመሆኑ በሊጉ ጥቂት ግቦች ከተቆጠሩባቸው ክለቦች ተርታ አሰልፏቸዋል፡፡

አራት ክለቦች ወደ ታችኛው ሊግ በወርዱበት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ለማንሳት ብቻ ሳይሆን ላለመውረድ የነበረው ትንቅንቅም ትንፋሽን የሚያስውጥ እና ልብን የሚያሞቅ እንደነበር ተመልክተናል፡፡ አርባምንጭ ከተማ፣ መቀሌ 70 እንደርታ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ምድረ ገነት ሽረ በቀጣይ ዓመት በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የማንመለከታቸው ወደ ታችኛው የሊግ እርከን የወረዱ ክለቦች ናቸው፡፡ የመከላከል ክፍተቶች፣ የፋይናንስ እጥረቶች እና አሰልጣኞችን ማሰናበት የነዚህ ክለቦች ዋና መለያዎች እንደነበሩ የሚታወስ ነው፡፡

የተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ለአርባምንጭ ከተማ  እጅግ ፈታኝ ነበር፡፡ አዞዎቹ በሜዳቸው ነጥብ የመጣል አባዜ ተጠናውቷቸው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ከሜዳቸው ውጭ ባደረጉት ጨዋታም የአቋም መዋዥቅ ታይቶባቸዋል፡፡ በውድድር ዓመቱ መገባደጃ  ከአስከፊው የውጤት ቀውስ ለማገገም ያደረጉት  ሙከራ ባለመሳካቱ ወደ ታችኛው የሊግ እርከን ሊወርዱ ችለዋል ። የአምናውን ችግር ሳይቀርፍ ዘንድሮ ውድድሩን የጀመረው መቀሌ 70 እንደርታም አስቸጋሪ ዓመት አሳልፏል፡፡ የተጫዋቾች ስብስብ ጥራት ማነስ እና ከሜዳ ውጭ በነበሩ ጨዋታዎች ላይ የነበረው ደካማ ስነ ልቦና ቡድኑን ለውድቀት ዳርጎታል።

ድሬዳዋ ከተማም በውድድር ዓመቱ የተረጋጋ የጨዋታ ፍሰት ማሳየት አልቻለም፡፡ በተለይም በሁለተኛው ዙር የገጠመው ተከታታይ ሽንፈት  ወደ ከፍተኛ ሊግ እንዲወርድ አድርጎታል። ሌላው በደጋፊዎቹ ዘንድ ትልቅ መነቃቃት ፈጥሮ የነበረው  ምድረ ገነት ሽረ የታክቲካዊ ብስለት ችግር ከነበረባቸው ክለቦች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህ ችግራቸውም በመጨረሻ መራራውን ጽዋ እንዲጎነጩ አስገድዷቸዋል፡፡

የ2018 ዓ.ም የውድድር ዓመት ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ለመጨረስ የታየው ፉክክር የሊጉን ውበት ወደ ላቀ ደረጃ አሳድጎታል፡፡ ሁለት ተጫዋቾችም እኩል 15 ግቦችን በማስቆጠር ኮከብ ግብ አግቢ ሆነው ጨርሰዋል፡፡  የፋሲል ከነማው አጥቂ ታምራት እያሱ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጥቂው ናትናኤል ዳንኤል በጋራ የኮከብ ግብ አግቢነት ክብር ተጋርተዋል፡፡ የሲዳማ ቡናው ግብ ጠባቂ ደግሞ በውድድር ዓመቱ ከግማሽ በላይ በሚሆኑ ጨዋታዎች ላይ መረቡን ሳያስደፍር በመውጣት የሊጉ ምርጥ ግብ ጠባቂነቱን አስመስክሯል፡፡

በ2018 ዓ.ም በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በርካታ ወጣት ተጨዋቾች ደምቀው ታይተዋል፤ ለክለቦቻቸውም ትልቅ አስተጽኦ በማበርከት እገዛ አድርገዋል፡፡ በሊጉ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የነገሌ አርሲው አማካይ በረከት ወልዴ፣ የፋሲል ከነማው አጥቂ ታምራት እያሱ፣ የምድረ ገነት ሽረ ሁለገቡ አጥቂ ዳንኤል ዳርጌ፣ የሸገር ከተማው አማካይ ቢኒያም አብርሃ እና ሌላኛው የሸገር ከተማው አጥቂ ዳዊት ካሰው ዘንድሮ ድንቅ የውድድር ጊዜ ካሳለፉ ወጣቶች መካከል ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ወጣት ተጫዋቾች በእድሜአቸው ወጣት ቢሆኑም እይታቸው፣ እርጋታቸው እና ጨዋታን የማንበብ ብቃታችው በእግር ኳስ ቤተሰቡ ዘንድ አድናቆት ተችሯቸዋል፡፡

የ2018 ዓም የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስኬታማ የውድድር ዓመት ነበር ማለት ይቻላል፤ አዳዲስ ወጣት ተጫዋቾች ብብዛት የታዩበት፣ አዲስ ያደጉት ነገሌ አርሲ እና ሸገር ከተማ አስደናቂ ፉክክር ያሳዩበት፣ የተሳታፊ ክለቦች ቁጥር ወደ 20 ያደገበት እና አዲስ ክለብ ሻምፒዮን የሆነበት  ዓመት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በሊጉ ጥራት እና ደረጃ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ክፍተቶች እንደነበሩ ደግሞ አይካድም፡፡

በውድድር ዓመቱ ከነበሩ ችግሮች መከከል የሜዳ ችግር አንደኛው ነው፡፡ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበት ታድሶ የነበረው አንጋፋው የአዲስ አበባ ስቴዲየም በጣለው ኃይለኛ ዝናብ ምክንያት የሜዳው ሳር ሙሉ በሙሉ በጎርፍ በመጠልቀለቁ በጨዋታዎች ላይ ትልቅ እክል ገጥሞ እንደነበር በቀጥታ ስርጭት ተመልክተናል፡፡ በዚህም የተነሳ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ ቡና ተጠባቂ የነበረው የሊጉ ጨዋታ ሜዳው ዝግጁ ባለመሆኑ በጊዜያዊነት እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ ይህ  ክስተት የመገናኛ ብዙኃንን ትልቅ ትኩረት የሳበ ዜና ሆኖ መሰንበቱ አይዘነጋም።

በተጨማሪም የመብራት መቆራረጥ ሌላው የሊጉ ፈተና የነበረ ሲሆን በተለይም በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስቴዲየም በተደረገው ጨዋታ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት መብራት በድንገት በመጥፋቱ ጨዋታው ተቋርጦ በማግስቱ ጠዋት እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ ሜዳ ላይ የስነ ምግባር ችግር በታየባቸው ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች እና የቡድን መሪዎች የሚተላለፉ የዲሲፕሊን ኮሚቴ የቅጣት ውሳኔዎች መዘግየታቸው በሊጉ ላይ የራሱን ጥላ ጥሎ አልፏል፡፡ የዳኝነት ስህተቶች መበራከት እና በውድድር ዓመቱ በአጠቃላይ አነስተኛ ግቦች መቆጠር በሊጉ ዘንድሮ የታዩ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው፡፡

በቀጣዩ የ2019 ዓ.ም ሊጉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የስቴዲየሞች መሰረተ ልማት ማሻሻል እና ማደስ የመጀመሪያው እርምጃ ነው፡፡ በምሽት ጨዋታዎች የኤሌክትሪክ መቆራረጥ እንዳይከሰት አስተማማኝ እና ዘመናዊ የሀይል ማመንጫ አማራጮችን በየስታዲየሞቹ መገንባት ይኖርበታል፡፡  የዳኞችን አቅም ማሳደግ እና አወዛጋቢ ውሳኔዎችን የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት እና በተደራጀ መልኩ ሥራ ላይ ማዋል የሊጉን ጥራት ለማሳደግ ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

ውድድሮች ከመጀመራቸው በፊት ጨዋታዎች የሚካሄዱባቸው የስቴዲየሞች የሳር ጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ መሆናቸው መፈተሽ ይኖርበታል። የዲሲፕሊን ኮሚቴው የሚያስተላልፋቸው ቅጣቶችን እና ውሳኔዎችን ያለምንም መዘግየት፣ በግልጽነት እና በገለልተኝነት ወዲያውኑ ተግባራዊ መደረግ አለባቸው- የብዙ የእግር ኳስ ቤተሰቡ ሀሳብ ነው። እነዚህን እና ሌሎችንም ስር ነቀል ማሻሻያ ማድረግ ከተቻለ ሊጉ በምሥራቅ አፍሪካ  ተወዳዳሪ እና ተመራጭ መሆን እንደሚችል አያጠራጥርም።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሰኔ 29   ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here