ለእግር ኳስ  የተከፈለ ህይወት

0
201

በእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ተሰጥኦ እና ስነ ምግባርን አጣምረው የያዙ ተጫዋቾች ጥቂት ናቸው፡፡ ከእነዚህ ጥቂት ኮከቦች መካከል ኮሎምቢያዊው ተከላካይ አንድሬስ ኤስኮባር ሳልዳሪያጋ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡ በሜዳ ላይ ባለው የተረጋጋ አጫዋወት፣ ድንቅ የተከላካይነት ብቃት እና ለተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች በሚያሳየው አክብሮት  በሀገሩ ሕዝብ ዘንድ “El Caballero del Fútbol” ወይም “የእግር ኳሱ ጨዋ ሰው” የሚል የክብር ቅፅል ስም ተሰጥቶት ነበር፡፡

ኤስኮባር ለእግር ኳስ የነበረው አመለካከት ከስፖርታዊ ፉክክር የዘለለ ነበር፤ ለእሱ እግር ኳስ የሰላም፣ የአንድነት እና የወጣቶች ተስፋ ማደሻ መሳሪያ ነበር፡፡ በተወለደበት የሜዴሊን ከተማ በአስከፊ የአደንዥ እፅ ወንጀል ሳይበከል ለታዳጊዎች አርአያ በመሆን ህይወቱን ለስፖርቱ የገበረ እውነተኛ ኳሰኛ ነበር፡፡ ይህ ሰው ግን ሜዳ ላይ በሰራው አንድ  ስህተት ህይወቱን በአሰቃቂ ሁኔታ እንደሚያጣ ማንም የገመተ አልነበረም፡፡

የአንድሬስ ኤስኮባር የእግር ኳስ ጉዞ የጀመረው በትውልድ ከተማው ባለው ግዙፍ ክለብ አትሌቲኮ ናሲዮናል ነው፡፡ ከክለቡ ጋርም ስኬታማ ጊዜ ማሳለፉን የቢቢሲ መረጃ አመልክቷል፡፡ አንድሬስ ኤስኮባር ከአትሌቲኮ ናሲዮናል ጋር ሦስት የፕሪሜራ ኤ፣ አንድ የኮፓ ሊበርታዶረስ እና አንድ የኮፓ አሜሪካን ዋንጫ አሳክቷል፡፡ ለኮሎምቢያ ብሄራዊ ቡድንም ኤስኮባር ቁልፍ ተከላካይ እና መሪ እንደነበር የጎል ዶት ኮም መረጃ ያስነብባል፡፡ ከነ ካርሎስ ቫልደራማ፣ ፋውስቲኖ አስፕሪላ እና ፍሬዲ ሪንኮን ጋር በመሆን የኮሎምቢያን ብሄራዊ ቡድን በዓለም መድረክ ላይ አስፈሪ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

በወቅቱ የኮሎምቢያ ብሄራዊ ቡድን እጅግ ማራኪ እና ፈጣን የማጥቃት እግር ኳስ ይጫወት የነበረ ሲሆን በአርጀንቲና ምድር ባደረገው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አርጀንቲናን አምስት ለባዶ በሆነ  ውጤት ማሸነፉን የጎል ዶት ኮም መረጃ ያስታውሰናል፡፡ ኤስኮባር ከዚህ ስኬት በኋላ የአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች ዐይን ውስጥ የገባ ሲሆን በተለይም የጣሊያኑ ኤሲ ሚላን እርሱን ለማስፈረም ስምምነት ላይ ደርሶ ነበር፡፡ እ.አ.አ በ1994 በአሜሪካ ምድር የተካሄደው የዓለም ዋንጫ ግን ነገሮቹን እስከ ወዲያኛው ቀይሯቸዋል፡፡

የኮሎምቢያ ብሄራዊ ቡድን ወደ 1994ቱ የአሜሪካ የዓለም ዋንጫ ሲያቀና የእግር ኳስ ንጉሡ ፔሌን ጨምሮ በርካታ የስፖርት ተንታኞች ቡድኑን ለዋንጫው ቅድመ ግምት ሰጥተውት ነበር፡፡ በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታ ቡድኑ በሮማኒያ ሦስት ለአንድ ተሸነፈ፡፡ እ.አ.አ ሰኔ 22 ቀን 1994  ኮሎምቢያ ከውድድሩ አስተናጋጅ  አሜሪካ ጋር ወሳኝ ጨዋታ አደረገች፡፡ በ35ኛው ደቂቃ ላይ አሜሪካዊው አማካይ ጆን ሃርክስ ወደ ኮሎምቢያ የግብ ክልል ያሻማውን ኳስ ለመከላከል አንድሬስ ኤስኮባር ተንሸራቶ ለመመለስ ሞከረ፡፡ ነገር ግን ኳሷ አቅጣጫዋን ቀይራ የኮሎምቢያ መረብ ላይ አረፈች፡፡ ኤስኮባር በራሱ መረብ ላይ ያስቆጠራት ግብ ኮሎምቢያ ሁለት ለአንድ ተሸንፋ ከዓለም ዋንጫው በጊዜ እንድትሰናበት አድርጓታል፡፡

ይህም በኤስኮባር ላይ ትልቅ የስነ ልቦና ስብራት እና ፀፀት እንዳደረሰበት የግል የታሪክ ማህደሩ ያስረዳል፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ የነበረው ከፍተኛ ውጥረት እና ከአደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪዎች (ካርቴሎች) የሚላኩ ዛቻዎች በቡድኑ አባላት ላይ ከባድ የስነ ልቦና ጫና ፈጥረው ነበር፡፡ በርካታ ተጫዋቾችም ደህንነታቸው አደጋ ላይ በመውደቁ አሜሪካ ለመቆየት መረጡ፡፡ አንድሬስ ኤስኮባር ግን “የበደልኩትን ሕዝቤን ይቅርታ መጠየቅ  አለብኝ” በማለት ወደ ትውልድ ከተማው ሜዴሊን ተመለሰ፡፡

የአንድሬስ ኤስኮባር በራስ መረብ ላይ የተቆጠረች ግብ በቁማር በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ያጡትን የአደንዥ እፅ ጌቶችን አስቆጥቶ ነበር፡፡ ወደ ሀገሩ ከተመለሰ ከጥቂት ቀናት በኋላ እ.አ.አ ሐምሌ ሁለት ቀን  1994  እኩለ ሌሊት ላይ ኤስኮባር በሜዴሊን ከተማ ከሚገኝ አንድ የምሽት ክለብ በመኪና ማቆሚያ ስፍራ ላይ በግልጽ ከማይታወቁ ሦስት ሰዎች ጋር አላስፈላጊ ቃላት መለዋወጥ ጀመሩ፡፡

ውዝግቡ እየከረረ ሲሄድ ከገዳይ ቡድኑ አንደኛው ሽጉጡን አውጥቶ ስድስት ጊዜ ተኮሰበት፡፡ ገዳዩ በእያንዳንዱ ጥይት ወቅት የዓለም ዋንጫው ኮሜንታተሮች ግብ ሲቆጠር የሚጮኹበትን “ጎል!” የሚለውን ቃል ይጮኽ እንደነበር የዐይን እማኞችን ጠቅሶ ቢቢሲ ስፖርት ዘግቧል፡፡ አንድሬስ ኤስኮባር ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም ህይወቱ ሊተርፍ አልቻለም፡፡ በአስከሬን ሽኝት ስነ ስርዓቱ ላይ ከ120 ሺህ በላይ ሕዝብ እንደተገኘም መረጃው ይነግረናል፡፡ የኤስኮባር ገዳይ ኡምቤርቶ ካስትሮ ሙኞዝ ለታዋቂዎቹ የእፅ አዘዋዋሪዎች እና ቁማርተኞች (የጋሎን ወንድማማቾች) የግል ጠባቂ የነበረ ሲሆን ይህም ግድያው ከቁማር ጋር በቀጥታ የተያያዘ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

እግር ኳስ፣ ፖለቲካ እና አደንዛዥ እፅ የአንድሬስ ኤስኮባር ግድያ ውሳኔ ሳይሆን የኮሎምቢያ የወቅቱ አስከፊ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ውድቀት ነጸብራቅ ነው፡፡ ምንም እንኳ አሁንም ብዙ የተለየ ነገር ባይኖርም በ1980ዎቹ እና 90ዎቹ መጀመሪያ ላይ ኮሎምቢያ በዓለም ላይ እጅግ አደገኛ የወንበዴዎች እና የአደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪዎች ሀገር እንደነበረች የቢቢሲ ስፖርት መረጃ የሳያል፡፡ ሀገሪቱ በሜዴሊን እና ካሊ የእፅ ካርቴሎች (Drug Cartels) ቁጥጥር ስር ወድቃ እንደነበር ይነገራል፡፡

የአንድሬስ ኤስኮባር አሰቃቂ ሞት በዓለም እግር ኳስ ላይ ከባድ ድንጋጤን ፈጥሮ ነበር፤ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ ከተጫዋቾች ደህንነት እና ስነ ልቦና ጋር በተያያዘ ጥብቅ መመሪያዎችን እንዲያወጣ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህ አሳዛኝ ክስተት በኮሎምቢያ ምድርም ቢሆን ሕዝቡ የሀገሪቱን ውድቀት እና የወንጀል ስርጭት ቆም ብሎ እንዲመረምር ያደረገ ትልቅ የለውጥ መነሻ ምዕራፍ ነበር፡፡

ታዋቂው የአደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪ ፓብሎ ኤስኮባር በታህሳስ 1993 እ.አ.አ በፖሊስ መገደሉን ተከትሎ በሜዴሊን ከተማ ውስጥ የነበረው የወንጀል ቁጥጥር ሙሉ በሙሉ መስመር ስቶ ነበር፡፡ የአደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪዎች (ካርቴሎች) ገንዘባቸውን ሕጋዊ ለማድረግ እግርኳሱን ይደግፉት እንደነበር ተነግሯል፡፡ ይህ ተዝቆ የማያልቅ የአደንዛዥ እፅ ገንዘብ ግን የኮሎምቢያን እግር ኳስ ቢያሻሽልም ስፖርቱ ከሕገ ወጥ ቁማር እና ከወንጀል ጋር በቀጥታ እንዲቆራኝ አድርጎታል፡፡

ዛሬም ድረስ በአትሌቲኮ ናሲዮናል ደጋፊዎች ልብ ውስጥ አንድሬስ ኤስኮባር አልሞተም፡፡ ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም ሲመጡ የእርሱን መለያ እና ምስል የያዙ ባነሮችን ይዘው ይገባሉ፡፡ ልክ ከ32 ዓመታት በኋላ ድጋሚ በአሜሪካ ምድር ኮሎምቢያ በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ እየተፎካከረች ትገኛለች፡፡ በአሁኑ ወቅትም የኮሎምቢያ ብሄራዊ ቡድን እንደነ ሉዊስ ዲያዝ እና ሀሜስ ሮድሪጌስ ፊታውራሪነት እየተመራች ነው፡፡

የአንድሬስ ኤስኮባር አሳዛኝ ታሪክ ጥላ ግን አሁንም ከብሄራዊ ቡድኑ ጀርባ ያንዣብባል፡፡ የአሁኑ የኮሎምቢያ ስብስብ ምንም እንኳን አሁን ላይ የተሻለ የጸጥታ እና ከባቢ ቢኖረውም አሁንም ድረስ በደጋፊዎች እና በእግር ኳስ ተንታኞች ዘንድ አንድ ጥያቄ ይነሳል፡፡

“ዛሬ ላይ ይህ ቡድን ከውድድር ውጪ ቢሆን ወይም ተጫዋቾቹ በራሳቸው መረብ ላይ ግብ (Own Goal) ቢያስቆጥሩ የአንድሬስ ኤስኮባር አሰቃቂ እጣ ፈንታ እንደማይደርሳቸው ምን ማረጋገጫ አላቸው?” ይህ ስጋት ዝም ብሎ የመነጨ አይደለም፡፡ የስፖርት ቁማር በዲጂታል መድረኮች ላይ በቢሊዮን ዶላሮች መዘወሩ እና ደጋፊዎች ከእግር ኳስ ውጤት ጀርባ የሚያሳዩት የለየለት አክራሪነት እና ዛሬም ድረስ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተጫዋቾች ስህተት ሲሰሩ የሚሰነዘሩባቸው የሞት ዛቻዎች  የስፖርተኞችን ህይወት አሁንም አደጋ ላይ መውደቁን ያሳያል፡፡ ኮሎምቢያ የአደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪዎች (ካርቴሎች) ከሚያደርሱት ቀውስ ወጥታ ወደ ተሻለ መረጋጋት ብትሻገርም የኤስኮባር ታሪክ ለዘመኑ ተጫዋቾች ዘላቂ ማስጠንቀቂያ ሆኖ ዘሬም ቀጥሏል፡፡

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሰኔ 29   ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here