ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከሌሎች ቀናት በተለየ ተውቧል፣ መዳረሻ መንገዱ ለስጦታ የሚሆኑ አበባዎችን፣ የመልካም ምኞት መግለጫ የሰፈረባቸው ጽሑፎችን …ለመሸጥ በሚሯሯጡ ወጣቶች ደምቋል፤ ከግቢው ጀምሮ ደግሞ ከመንገዱ የጀመረው በነጫጭ አልባሳት እና በሱፍ የተዋቡት የአስመራቂዎች መገፋፋት ውስጥ ዘልቆ ገዋን ከለበሱ ተመራቂ ተመሪዎች ጋር ተቀላቅሎ ልዩ ሕብር ፈጥሯል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በእንኳን ደህና መጣችሁ! ጽሑፎች እና በሌሎችም አሸብርቋል – ሰኔ 20 ቀን 2018 ዓ ም፡፡
እለቱ በዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት አይነቶች ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እና ከዘጠኝ የውጭ ሀገራት ተቀብሎ ሲያስተምራቸው የነበሩ ተማሪዎች የዓመታት ልፋታቸው ተጠናቆ ለስኬት የደረሱበት የምረቃ ቀን ነው – የሁሉም የጋራ የደስታ ቀን፡፡
ከእለቱ ተመራቂዎች መካከልም ኒያሙዎት ፑኦት አንዷ ናት፤ “ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕልሜን እውን አድርጎልኛል!” በማለት ዩኒቨርሲቲው ለውጭ ተማሪዎች የሚሰጠውን ድጋፍና አቀባበል የእለቱ ተመራቂ ደቡብ ሱዳናዊቷ ኒያሙዎት ፑኦት አድናቆቷን በደስታ ገልጻለች፡፡በምረቃው እሷን ጨምሮ ከዘጠኝ ሀገራት የመጡ የውጭ ተማሪዎችም ተመርቀዋል።
ኒያሙዎት የባህልና የቋንቋ ልዩነቶችን በመሻገር የተገኘው ስኬት ትልቅ ትምህርት እንደሆነም ገልጻለች። ይህም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከሚያስመርቃቸው ተማሪዎች በላይ ለሀገር የሚፈጥረው ዘላቂ እሴት ምን ያህል እንደሆነ በግልጽ አሳይቷል።
የደስታ ስሜት ከተላበሱ ተመራቂዎች መካከልም የአካል ጉዳት ለስኬት እንቅፋት እንደማይሆን ያስመሰከረው የማነብርሐን ወርቅዬ ሌላው ነው፡፡ በግዕዝ ቋንቋ 3 ነጥብ 32 ውጤት በማምጣት የሜዳሊያ ተሸላሚው የማነብርሐን ዐይነ ስውር ቢሆንም በተሰማራበት የትምህርት ዘርፍ የላቀ ውጤት በማስመዝገብ አካል ጉዳት ከማንኛውም ቦታ ወደ ኋላ እንደማያስቀር አረጋግጧል።
በብዙ ውጣ ውረድ ለውጤት መብቃቱን የሚናገረው ተመራቂው የማነብርሐን “ በክፍል የሚሰጥ ትምህርትን በጽሞና እከታተላለሁ፤ ያልገባኝንም መምህራንን እጠይቃለሁ፣ ከጓደኞቼ ጋርም ባልገባኝ ጉዳይ እወያያለሁ፣ በፕሮግራም አጠናለሁ፡፡
ይህን በማድረጌ አካል ጉዳተኝነት ከምንም እንደማያግድ አሳይቻለሁ! በተለይ ብዙ የሀገራችን ታሪካዊ ቋንቋ በሆነው ግዕዝ በከፍተኛ ነጥብ መመረቄ ደስተኛ አድርጎኛል። ’አካል ጉዳተኞችን ማስተማር ሀገርን ማስተማር ነው’ እንደ ሚባለው አካል ጉዳተኞችን አስተምሮ ከችግር እንዲወጡ ማስቻል እና አዕምሯቸውን መጠቀም ይገባል”በማለት ጠይቋል፡፡
ተመራቂው እንደ ሚለው ግዕዝ ቋንቋ የሀገር ታሪክና ቅርስ በመሆኑ ይበልጥ ሊስፋፋና ሊጠናከር ይገባል፤ አሁን ያለው ጅማሮ መልካም ነው፡፡ በቀጣይ ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማሩን ሥራ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ጠቁሟል። በቀጣይ የሥራ ዘመኑ የግዕዝ ቋንቋ መምህር መሆን እንደሚፈልግ የጠቆመው ተመራቂው፤ የግዕዝ ቋንቋ እንዲያድግም የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ጥረት እንደሚያደርግ ተናግሯል።
ሌላዋ በሴቶች 3 ነጥብ 98 ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው የማኔጅመንት ተመራቂ ማህሌት ማተቤ ናት፡፡ ማህሌት የስኬት ምስጢሯ ጊዜዋን በፕሮግራም ከፋፍላ መጠቀሟ፣ ራስን መምራትና ከራስ ጋር መወዳደር መሆኑን ገልጻለች። የዩኒቨርሲቲ ሕይወት ከመማር ባሻገር የመቻቻል፣ የመግባባትና የአመራር ብቃትን የሚያዳብር መሆኑንም አስታውቃለች።
በሌላ በኩል በአካውንቲንግና ፋይናንስ 43 A+ እና 9A በማምጣት 4 ነጥብ ውጤት ያስመዘገበው እዝራ አንዱዓለም የዓመቱ አጠቃላይ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል። አዝራ እንደሚለው ምረቃ የትምህርት ጉዞ መጨረሻ ሳይሆን የተሻለ ስኬት መጀመሪያ ነው፡፡ በመሆኑም ተመራቂዎች በቀጣይም መማራቸውን እንዲቀጥሉ መክሯል።
በአጠቃላይ የ2018 የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምረቃ የዕውቀት፣ የብቃት፣ የጽናትና የተስፋ በዓል ነበር። የተመራቂዎች የሕይወት ታሪኮች ስኬት በምቾት ሳይሆን በትጋት፣ በጽናትና በዓላማ እንደሚገኝ ያሳያሉ። ዩኒቨርሲቲዎች ዲግሪ የሚሰጡ ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ ችግር ፈቺ ምሁራንን፣ አዳዲስ ሀሳቦችን እና የሀገር ለውጥ መሪዎችን የሚያፈሩ ማዕከላት እንደሆኑ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሲያስተምራቸው የነበሩ ተማሪዎቹን ባስመረቀበት ወቅት አሳውቋል፡፡
በ2018 ዓ.ም ያካሄደው የምረቃ ሥነ-ሥርዓትም ከዲግሪ አሰጣጥ በላይ የዕውቀት፣ የጽናት፣ የብቃትና የሀገር ተስፋ መገለጫ ሆኖ ተስተውሏል።
በእለቱ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ስድስት ሺህ 492 ተማሪዎች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ እንዲሁም በከፍተኛ ዲፕሎማ፣ በድህረ-ምረቃ ዲፕሎማ፣ በስፔሻሊቲና በሰብ-ስፔሻሊቲ ፕሮግራሞች ተመርቀዋል። ከእነዚህም 152 ተማሪዎች በዶክትሬት ዲግሪ መመረቃቸው በዩኒቨርሲቲው ታሪክ ከፍተኛው ቁጥር መሆኑ በእለቱ ተገልጿል። ይህም ተቋሙ በምርምርና በከፍተኛ የአካዳሚክ ስልጠና ያለውን አቅም የሚያሳይ አስፈላጊ ምዕራፍ ነው።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ስትራቴጅ ኮሙኒኬሽን ም/ፕሬዝዳንት ዘውዱ እምሩ (ዶ/ር) ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ! መልእክት ካስተላለፉ በኋላ እለቱ ለእነሱ የረጅም ጊዜ ጥረትና ትጋት ውጤት ዕውን የሆነበት እንደሆነ አብስረዋል። ምረቃ የመጨረሻ ሳይሆን ወደ ሥራና ሕይወት አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ጅማሮ መሆኑንም አስታውሰዋል።
ዶ/ር ዘውዱ አክለውም ዩኒቨርሲቲው ከ60 ዓመታት በላይ ጥራት ያለው ትምህርት፣ ምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት በማበርከት በሀገሪቱ ቀዳሚ የምርምር ተቋማት መካከል ተጠቃሽ ሆኗል። ሀገራችን እውቀት ያላቸውን፣ ችግር ፈቺ እና ተጠያቂ ዜጎችን እንደምትፈልግ በማስታወስ ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በተግባር በመተርጎም ለእድገቷ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል። ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም ራሳቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን፣ ህብረተሰቡን እና ሀገራቸውን የሚገነቡ ብቁ ዜጎችን ለማፍራት በቁርጠኝነት እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት መንገሻ አየነ (ዶ/ር) በበኩላቸው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ18 አካዳሚክ ክፍሎች 452 የትምህርት መርሃ ግብሮችን እያስኬደ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ የድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞች ናቸው። ይህም ተቋሙ ወደ ምርምር ተኮር ዩኒቨርሲቲነት በፍጥነት እየተሸጋገረ መሆኑን ያሳያል።
“የዩኒቨርሲቲ ስኬት የሚለካው በሚያስመርቃቸው ተማሪዎች ብዛት ሳይሆን በሚፈታቸው የማኅበረሰብ ችግሮች ነው” በማለት ዩኒቨርሲቲው ዕውቀትን ወደ ተግባራዊ መፍትሔ ለመቀየር እየሠራ መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
በዕለቱ ዋና እንግዳ የነበሩት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር በላይ ካሳ ባደረጉት ንግግር ከፍተኛ ትምህርት የሀገር ልማትና የድህነት ቅነሳ ወሳኝ መሣሪያ መሆኑን ጠቅሰው፣ ባለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ሥርዓት ከፍተኛ መስፋፋት አሳይቷል፤ በዚህም ሁለት ብቻ የነበሩ ዩንቨርሲቲዎች በአሁኑ ወቅት ከ50 በላይ ደርሰዋል፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ በከፍተኛ ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥርም ወደ 800 ሺህ መጠጋቱን ነው የገለጹት፡፡ ሆኖም ከ18 እስከ 23 ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶች የከፍተኛ ትምህርት የተሳትፎ መጠን ሰባት ነጥብ ሰባት በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህ ከአፍሪካ አማካይ 10 በመቶ እና ከዓለም አማካይ ከ40 በመቶ በታች መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
እንደ ፕሬዚዳንቱ መግለጫ በሀገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተደራሽነትን እና ጥራትን የበለጠ ለማሻሻል ተጨማሪ ጥረት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡የአሁን ተመራቂዎችም የሙያ እውቀታቸውን ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለሀገር እድገትና ለማኅበረሰብ ጥቅም እንዲያውሉም አሳስበዋል። የሀገር አለኝታ የሚሆኑ ባለሙያዎች እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።
ግዕዝ በአማርኛ
ኀብስት —— ዳቦ
ብእሲ ——- ወንድ
ብእሲት —– ሴት
ነግህ —— ጠዋት
ምሴት —– ማታ
ልሳን —— ቋንቋ
ደጅ —– በር
(ሰናይት በየነ)
በኲር የሰኔ 29 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


