ሀገራት ለስደተኞች በራቸውን  ለምን ዘጉ?

0
179

ስደት  ከቀደምት የሰው ልጅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ክስተት ቢሆንም ስደተኞችን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጠብቅ ሕጋዊ ሥርዓት የተገነባው ግን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ነው፡፡

ጦርነቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት እና ከመኖሪያ ቀያቸው አፈናቅሏል፡፡ ይህም ዓለም አቀፍ ማሕበረሰቡ ስደተኞችን ለመጠበቅ የተደራጀ ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲያዘጋጅ አነሳስቶታል፡፡ እ.አ.አ በ1945 የተቋቋመው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.አ.አ በ1950 የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽንን (UNHCR) በመመስረት ስደተኞችን የመጠበቅ ዓለም አቀፍ ተቋም ፈጠረ፡፡ በመቀጠልም በዓመቱ (በ1951) የስደተኞች ስምምነት ጸደቀ፤ በ1967(እ.አ.አ) ደግሞ ፕሮቶኮል በመጨመር በመላው ዓለም ተፈጻሚነቱ ተስፋፋ፡፡

እ.አ.አ በ1951ዱ የስደተኞች ስምምነት መሠረትም ስደተኞች የሕይወትና የደኅንነት ጥበቃ፣ ከመድልዎ ነፃ የሆነ የመኖር መብት፣ የሃይማኖት ነፃነት፣ ትምህርት የማግኘት መብት፣ የመሥራት መብት፣ የፍርድ ቤት ተደራሽነት፣ የማንነት እና የጉዞ ሰነዶችን የማግኘት መብት እንዳላቸው የደነገገ ሲሆን ከእነዚህ መብቶች ጋር በተያያዘ ስደተኞችም የሚኖሩበትን ሀገር ሕግና ደንብ የማክበር ግዴታ አለባቸው፡፡

ሰዎች በምን ምክንያት ሊሰደዱ ይችላሉ?

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት(IOM) እንዳስታወቀው ሰዎች በበርካታ ምክንያቶች ሊሰደዱ ይችላሉ፡፡ ከምክንያቶቹ መካከልም፡-

ጦርነትና የትጥቅ ግጭት፡- ዜጎች ሀገራቸውን ጥለው ለመሰደድ ዋነኛው ምክንያት ጦርነት እና ግጭት ነው፡፡ ጦርነት ሲከሰት ሰዎች ሕይወታቸውን ለማዳን ይሸሻሉ፡፡ ቤቶች ይፈርሳሉ፤ ትምህርት ይቋረጣል፤ ሆስፒታሎች ይዘጋሉ፤ የምግብና ውኃ እጥረት ይፈጠራል፡፡ በዚህም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በግጭት ምክንያት ከመኖሪያቸው ይፈናቀላሉ፡፡

የፖለቲካ  ግፍና ሰብአዊ መብት ጥሰት፡-

አንዳንድ ሰዎች በፖለቲካ አመለካከታቸው፣ በሃይማኖታቸው፣ በዘራቸው ወይም በማንነታቸው ምክንያት በሚደርስባቸው በደል  (እስር፣ ማሰቃየት፣ ማስፈራራት ወይም ለሕይወት የሚያሰጋ ሁኔታ ሲፈጠር) ወደ ሌላ ሀገር መሸሽን/መሰደድን ይመርጣሉ፡፡

ድህነትና የሥራ እጥረት፡-  በታዳጊ እና ደሃ ሀገራት የሚኖሩ ወጣቶች ትምህርት ቢማሩም በቀላሉ ሥራ ማግኘት አይችሉም፡፡ ዝቅተኛ ገቢ፣ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት እና የወደፊት ተስፋ ማጣት ሰዎችን ወደ ሌሎች ሀገራት እንዲሄዱ ያደርጋል፡፡ ይህን አይነት ፍልሰት በአብዛኛው “የኢኮኖሚ ፍልሰት” ተብሎ ይጠራል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ፡- ድርቅ፣ ጎርፍ፣ በረሃማነት እና ከባድ የአየር ክስተቶች ሰዎች መኖሪያ ቀያቸውን እንዲለቁ ያደርጋሉ፡፡ በተለይ በግብርና ላይ የገቢ ምንጫቸውን  ያደረጉ  ከፍተኛ ተጽዕኖ ይደርስባቸዋል፡፡

ትምህርትና ሙያ፡- አንዳንድ ሰዎች ለከፍተኛ ትምህርት፣ ለሙያ ስልጠና ወይም ለምርምር ወደ ሌላ ሀገር ይሄዳሉ፡፡ ከዚያም ሥራ አግኝተው በዚያው ሀገር ሊቆዩ ይችላሉ፡፡

የቤተሰብ መቀላቀል፡- ብዙዎች በውጭ ሀገር ከሚኖሩ የትዳር አጋሮቻቸው፣ ወላጆቻቸው ወይም ልጆቻቸው ጋር ለመኖር ይሰደዳሉ፡፡

የተሻለ የኑሮ ፍለጋ፡- ደረጃውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት፣ የተሻለ ትምህርት፣ የተሻለ የሕግ ሥርዓት እና የተሻለ የሥራ ዕድል ለማግኘት ፤እንዲሁም ገቢን በማሳደግ የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል እና የተማሩ ዜጎች በሙያቸው ተገቢውን ክፍያ ወይም የሥራ እርካታ ባለማግኘታቸው ስደትን ይመርጣሉ፡፡

ሀገራት ስደተኞችን ለምን ጠሉ?

የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን በበኩሉ እንዳስታወቀው በርካታ  ሀገራት ስደተኞችን  ይቀበላሉ፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ የስደተኛ ተቀባይ ሀገራት አንዳንድ ዜጎች እና መንግሥታት ለስደተኞች  አሉታዊ አመለካከት እያዳበሩ ናቸው፡፡ ይህን አመለካከት ሊያዳብሩት  የቻሉት  በተለያዩ ምክንያቶች ነው፡፡ ከምክንያቶች መካከልም የኢኮኖሚ ጫና አንዱ ነው፡፡

ስደተኞች በሥራ ዕድል፣ በመኖሪያ ቤት፣ በትምህርት እና ጤና አገልግሎት ላይ ጫና ያሳድራሉ ብለው የሚያምኑ ሰዎች አሉ፡፡ ሌላው የደኅንነት ስጋት ነው፤ ሁሉም ስደተኞች ወንጀል ይፈጽማሉ  የሚል ማስረጃ ባይኖርም        አንዳንዶች ስደተኞችን መቀበል ወንጀል ወይም ሽብርተኝነት ይጨምራል ብለው ይፈራሉ (አንዳንድ ሀገራት ላይ በስደተኞች የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችን ተከትሎ)፡፡

አንዳንድ ሰዎች ብዙ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው መምጣታቸው የሀገራቸውን ባህል፣ ቋንቋ ወይም ማንነት ይቀይራል ብለው ያስባሉ፡፡ በተጨማሪም አንዳንድ ፖለቲከኞች የስደተኞችን ጉዳይ በምርጫ ወቅት ለድምፅ ማሰባሰብ ይጠቀሙበታል፤ ይህም አሉታዊ አመለካከትን በስደተኞች ላይ አምጥቷል፡፡

በሌላ በኩል ብዙ ሀገራት ስደተኞችን የሚቀበሉበት ምክንያትም አለ፡፡ ስደተኞች በተሰደዱበት ሀገር የራሳቸውን ኢኮኖሚ ይፈጥራሉ፤ በዚህም ግብር ይከፍላሉ፣ አዳዲስ ንግዶችን ይመሰርታሉ በዚህም የከተሙበትን ሀገር ኢኮኖሚን ያጠናክራሉ፡፡

በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ሕግ በተለይም የተባበሩት መንግሥታት እ.አ.አ  በ1951  የስደተኞችን ስምምነት አስመልክቶ  የወጣው ሕግ  እንደሚለው ከጦርነት  ወይም ከከባድ ግፍ የሸሹ ሰዎችን መጠበቅ የሀገራት ኃላፊነት መሆኑን ደንግጓል፡፡

የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት(IOM) ባወጣው የቅርብ ጊዜ አሃዝ መሠረት  አሜሪካ ትልቋ የስደተኞች መዳረሻ ናት፡፡ ወደ 51 ሚሊዮን የሚጠጉ ዓለም አቀፍ ስደተኞች መኖሪያ ናት፡፡ ቀጥሎ ጀርመን እና ሳዑዲ አረቢያ በ13 ሚሊዮን፣ የሩሲያ ፌዴሬሽን በ12 ሚሊዮን እና እንግሊዝ በዘጠኝ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ይከተላሉ፡፡ ሁለት ሦስተኛ የሚጠጉ ዓለም አቀፍ ስደተኞች ከፍተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ውስጥ ይኖራሉ፡፡

አሁናዊው የሀገራት የስደተኞች ፖሊሲ

በ2025/2026 ብዙ ሀገራት የስደተኞችንና የጥገኝነት ጠያቂዎችን ፖሊሲ አጥብቀዋል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ሕጋዊ ሰነድ (የመኖሪያ ፈቃድ) የላቸውም ብለው የሚቆጥሯቸውን ሰዎች ወደ መጡበት ሀገር እየመለሱ ነው፡፡

ሆኖም የተመዘገበ ስደተኛን (refugee) ለሕይወቱ አደጋ ወደ ሚፈጥርበት ሀገር መመለስ    በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከለ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ሰዎችን እያስወጡ ወይም በስፋት ወደ መጡበት እየመለሱ ካሉ ሀገራት መካከልም አሜሪካ፣ ጀርመን፣ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ በኢኮኖሚ የበለጸጉ ሀገራት ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን እና የጥገኝነት ጥያቄያቸው አጥጋቢ ባለመሆኑ ውድቅ የሆነ ሰዎችን   ወደ መጡበት ሀገር ለመመለስ እርምጃዎችን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡

ፓኪስታን በበኩሏ በ2023 የጀመረችውን በተለይም በአፍጋኒስታን ዜጎች ላይ ያተኮረ ስደተኞችን የማስወጣት ዘመቻ አሁን ድረስ ቀጥላለች፡፡ ኢራንም ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸውን የአፍጋን ዜጎችን በብዛት እየመለሰች ነው፡፡

ተርኪዬ በበኩሏ በተለይ አንዳንድ የሶሪያ እና ሌሎች ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸውን ሰዎች እየመለሰች ነው፡፡

ሀገራቱ ስደተኞችን ወደ መጡበት ሀገር እየመለሱ የሚገኙት በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የሚያቋርጡ ሰዎች እና የመንግሥት ወጪ መጨመር፣ በመኖሪያ ቤትና በማኅበራዊ አገልግሎት ላይ ጫና መፈጠሩ፣ የደኅንነት ስጋቶች መኖራቸው እንዲሁም በውስጥ ፖለቲካና በምርጫ ግፊት  እንደሆነ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ ሀገራትም የጥገኝነት ጥያቄ ያቀረቡ ሰዎችን ወደ መጡበት ሀገር ሳይሆን ወደ ሦስተኛ ሀገር ለመላክ ወይም የጥገኝነት ሂደታቸውን እዚያ እንዲከናወን ውል ገብተዋል፡፡ ይሁንና ይህ ውሳኔ በሕግ  እና በሰብዓዊ መብት ዙሪያ ብዙ ክርክር ያስነሳ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ለአብነትም በእንግሊዝ የሚገኙ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ እቅድ ተይዞ ነበር፡፡ ነገር ግን በሀገሪቱ (በእንግሊዝ)የፖለቲካ ለውጥ ምክንያት እቅዱ ተሰርዟል፡፡ ጣሊያንም ከአልባኒያ ጋር ስምምነት በማድረግ በባሕር የደረሱ አንዳንድ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ጉዳያቸው በአልባኒያ እንዲታይ እያደረገች ነው፡፡  ይሁንና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እንዲህ ያሉ እቅዶች አ.አ.አ የ1951 የስደተኞች ስምምነትን መንፈስ ሊጥሱ ይችላሉ በማለት ተቃውመዋል፡፡

ደቡብ አፍሪካም ከአውሮፓዊያን 2026 መግቢያ ጀምሮ ከፍተኛ የፀረ-ስደተኛ እንቅስቃሴዎችን እያስተናገደች ትገኛለች፡፡ የእንግሊዝ፣ የኔዘርላንድስ እና የሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ግፊት እንዳለበት  በሚነገርለት የደቡብ አፍሪካዊያን የውጭ ሀገር ዜጋ ጠል እንቅስቃሴ ነጮች ከፍተኛውን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ተቆጣጥረው እያለ በትናንሽ የንግድ ዘርፍ  ላይ የተሰማሩ አፍሪካዊያን ላይ ትኩረት በማድረግ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ማስገደዳቸው ትዝብት ላይ ጥሏቸዋል፡፡

መንግሥት “ከኔ ወገን አይደሉም”  ያላቸው ፀረ-ስደተኛ ቡድኖች “ሕገ-ወጥ ስደተኞች እስከ ሰኔ 30/2026 እ.አ.አ ሀገሩን ይልቀቁ” የሚል ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡ ቀነ ገደቡ  ከተጠናቀቀ በኋላም  የዚህ ዘመቻ አስተባበሪዎች ለአራት ወራት የሚቀጥል ዘውትር ሐሙስ  ሀገሪቱን ለቃችሁ ውጡ የሚል ታላቅ ሰልፍ እንደሚካሄድ አሳውቀዋል፡፡ ይህ ሁኔታም ስጋ ላይ እንደጣላቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

ቢቢሲ በበኩሉ እንደዘገበው በደቡብ አፍሪካ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው የውጭ ሀገር ዜጎች አሉ፡፡

ሌላዋ ከሰሞኑ ስደተኞች ጥብቅ ርምጃ የወሰደችው ሊቢያ ናት፡፡ በምሥራቅ ሊቢያ ያለው አስተዳደር የሱዳን፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ዜጎች በየብስ፣ በአየር እና በባሕር ወደ ሊቢያ እንዳይገቡ መከልከሉን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ አምነስቲ አስታውቋል፡፡

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ሪፖርት እንደሚያሳየው በ2025 መጨረሻ 117 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በጦርነት፣ በግፍ እና በሰብአዊ መብት ጥሰት ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ነበር፡፡ ይህ ማለት በዓለም ላይ ከ70 ሰዎች አንድ ሰው በግዳጅ ተፈናቅሏል ማለት ነው፡፡ ከእነዚህ 117 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ውስጥ 41 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ያህሉ በሌላ ሀገር የሚገኙ ስደተኞች ናቸው፡፡ 67 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ያህሉ ደግሞ በራሳቸው ሀገር ውስጥ ተፈናቅለው የሚኖሩ ዜጎች ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ስደትን  ማስቀረት አይችልም፤ የስደት ችግር በድንበር መዝጋትና በማባረር ብቻ አይፈታም፡፡ ዋናዎቹ መፍትሔዎች ጦርነትን ማስቆም፣ የፖለቲካ መፍትሔ ማምጣት፣ ኢኮኖሚያዊ እድሎችን መፍጠር፣ የሰብዓዊ መብቶችን ማክበር እና ዓለም አቀፍ ትብብርን ማጠናከር ናቸው፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሰኔ 29  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here