“የዛሬ ተማሪዎች እና ታዳጊዎች ዛሬ ላይ የተመቻቸ እና የሚያስደስት ሕይወት ላይኖረን ይችላል፣ ነገር ግን ዛሬ የምንማረው የተሻለ ነገን ለማግኘት ነውና ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳትሉ በብርታት እና በተስፋ ጉዟችሁን ከቀጠላችሁ የልፋታችሁን ዋጋ ከነ ሽልማቱ ታገኛላችሁ” በማለት አስተያየቱን የሰጠን ከዘንድሮ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች መካከል በቢዝነስ ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ በአካውንቲንግ እና ፋይናንስ የትምህርት መስክ የተመረቀው እዝራ አንዱዓለም ነው፡፡ ተመራቂው ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ዋንጫ ተሸልሟል፡፡ እዝራ በዩኒቨርሲቲው ከወሰዳቸው አጠቃላይ የትምህርት መስኮች መካከል 43ቱን A+ እና ዘጠኙን A በማምጣት ሙሉ 4 ነጥብ በማስመዝገብ በከፍተኛ ውጤት መመረቅ ችሏል።
ትውልዱ እና ዕድገቱ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ነው፡፡ እዝራ እናት እና አባቱ በልጅነቱ ስለተለያዩ ከአያቱ(ከእናቱ እናት) ጋር ገጠር ለማደግ ተገደደ፡፡ በልጅነቱ አያቱ ጋር ገጠር ሲያድግ ቤተሰቦቹን በግብርና ሥራ ያግዝ ነበር፡፡ እዝራ ሰባተኛ ክፍል ሲደርስ ግን የእናቱ ትልቅ ወንድም ትምህርቱ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲማር ወደ ዳንግላ ከተማ ወሰደው፡፡
ከልጅነቱ ጀምሮ የትምህር ፍቅር እንደ ነበረው የሚያነሳው እዝራ፤ በተለይም መምህራን በክፍል ውስጥ ሲያስተምሩ በደንብ ተከታትሎ እና ካልገባው እዛው ጠይቆ የመረዳት ልምድ ማዳበሩ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ የላቀ ውጤት እንዲያመጣ ረድቶታል፡፡ በትምህርት ቆይታውም ጥሩ የመረዳት ልምድን እንደፈጠረለት ያነሳል፡፡
“አንደኛ ደረጃ ተማሪ ሆነን ጀምሮ መምህራን ወደ ፊት መሆን የምንፈልገውን የሥራ መስኮች ሲያስረዱን ሐኪም እሆናለሁ የሚል ሕልም ኖረኝ፣ እስከ 12ተኛ ክፍል በተፈጥሮ ሳይንስ ተምሬ ነበር፤ እንደምሆንም እርግጠኛ ነበርሁ፡፡”
የሚለው እዝራ 12ኛ ክፍልን አጠናቆ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገባ ቶሎ ተምሮ እንዲጨርስ የሚያስገድደው ሃሳብ ተፈጠረ፡፡ የትምህርት ዘርፉንም ወደ ሶሻል ሳይንስ በመቀየር ወደ አካውንቲንግ እና ፋይናንስ የትምህርት መስክ በመግባት መከታተል እንደጀመረ ያስታውሳል፡፡
እዝራ ዩኒቨርሲቲ ከገባ በኋላ በየእለቱ የሚሰጠውን ትምህርት ቀድሞ በማንበቡ ቶሎ ይገነዘባል፡፡ ሊብራራለት የሚፈልገው እና ያልገባውን ቀድሞ በመያዝም ወደ ክፍል በመግባት መምህራኑን ይጠይቃል፤ በመምህራን ከተረዳ በኋላ መምህሩ ያስረዳውን ትምህርት ቀድሞ ስላነበበ በመከለስ ፈተና ሲደርስ ለፈተና ብሎ የተለየ የሚጨነቅበት ሁኔታ እንደሌለ እና ፈተናን ፈተና ሳያስመስል ዘና ብሎ በነፃነት ስለሚሠራ ጥሩ ውጤት እንደሚያመጣ ያስታውሳል፡፡ ዋናው ትኩረት ክፍል ውስጥ መረዳት እንደሆነም ያነሳል፡፡
እስከ ሦስተኛ ዓመት ድረስ የዋንጫ ተሸላሚ ለመሆን ሳይሆን የላቀ ውጤት ለማምጣት ብቻ በማሰብ ሲሠራ እንደቆየ እዝራ ጠቁሟል፡፡ ከእሱ የበለጠ ጓደኞቹ ለዚህ ውጤት እንደሚበቃ ያላቸውን ተስፋ ስለሚነግሩት ይህም ብርታት እንደሆነው ነው የሚገልፀው፡፡
ከምረቃ በኋላም “ለመኖር መሥራት ያስፈልጋል” የሚል እምነት ያለው እዝራ፤ ጥሩ የሒሳብ ባለሙያ ሆኖ ተቀጥሮ መሥራት እንዲሁም ብዙ ሳይቆይ ትምህርቱን የመቀጠል ፍላጎት እንዳለው ነው የገለፀልን፡፡ በሕይወት ውስጥ እቅድ ሊኖር እንደ ሚገባም ያምናል፡፡
ካለእቅድ ከሰማይ የሚመጣ ነገር የለም፤ ልፋትም ይጠይቃል ይላል፡፡ ተማሪዎች በትምህርት ወቅት የአቅማቸውን ያህል መትጋት ይገባቸዋል የሚለው እዝራ፤ በትጋት በመሥራት የከፈልነው ዋጋ ጊዜውን ጠብቆ ስለሚከፈለው የአቅምን ሁሉ በመሥራት ያምናል፡፡
“ከወጣትነት ጋር ተያይዞ የአቻ ግፊት መኖር ብቻ ሳይሆን የወጣትነት የውሥጥ ፈተና ከውስጥ የሚኖር ’አድርግ፣ አታድርግ’ ብሎ ሊገፋፋ ይችላል” ይህንን ፈታና የወደፊቱን ቀና ነገር አስቦ መቋቋም እንደሚገባም ነው የሚመክረው፡፡
ወጣቶች መለወጥ እና መበርታት የሚገባቸው ለራሳቸው ነገ እና የነሱን መቀየር ለሚጠብቁ ወላጆች እንደሆነ ይገልፃል፡፡ በየአካባቢው ካለው የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ወጣቱ የትምህርት መቋረጥን ’ትምህርት ምን ያደርጋል’ ወደ ሚል ሃሳብ መሄዱ አሳሳቢ ነው” የሚለው እዝራ ተቀጥሮም ሆነ በራሥ ፈጥሮ ሥራ ለመሥራት መጀመሪያ መሠረታዊ የትምህር ዕውቀት ወሳኝ በመሆኑ ወጣቱ ተስፋ ሊቆርጥ እንደማይገባ ጠቁሟል፡፡ “ጊዜ ይለወጣል፤ ዛሬ ያልተፈለገ ነገር ነገ መፈለጉ ስለማይቀር በመማር እና በማወቅ ማንም ተስፋ ሊቆርጥ አይገባም” በማለትም የትምህርትን ጠቀሜታ ጠቁሟል፡፡
የክፍል ጓደኛው ኤርሚያስ ገበዜ እዝራ የፈለገውን ነገር ሳያስመልስ ወደ ኋላ የማይል፣ ያሰበውን የሚፈፅም አንዲሁም ተግባቢ እንደሆነ ነው የገለፀው፡፡ ሁሉንም ለማገዝ ፈቃደኛ እንደሆነ የሚገልፀው ኤርሚያስ ሲያጠና የጨበጠውን ፍሬ ነገር ለሌሎች ለማጋራት ቅን ጓደኛው እንደሆነም ነው የገለፀልን፡፡
አጎቱ አቶ ሙሉቀን በላይ በበኩላቸው ከታች ክፍል ጀምሮ ጎበዝ ተማሪ ስለነበር ጥሩ ውጤት ይኖረዋል ብለው ቢገምቱም ብዙዎች በቤተሰብ በጣም ስሚታገዙ ዋንጫ ይወስዳል ብለው አላሰቡም ነበር፡፡ “በልጅነቱ መምህራንን አክብር፣ የምትፈልገውን እና ያልገባህን ለመጠየቅ ግን አትፍራ” በማለት ይመክሩት እንደ ነበርም አጎቱ ያስታውሳሉ፡፡ ምክሩን ተቀብሎም ትምህርቱን ሲማር በደንብ ጠይቆ እና ተረድቶ ስለሚመጣ ብዙ እንደማይለፋ ተናግረዋል፡፡
ገጠር እያለ በግብርና ሥራው እንደሚያግዝ ሁሉ ቤት ውስጥም አስፈላጊውን ሥራ ያግዛል፤ ጊዜውንም በአግባቡ ስለሚጠቀም ለዚህ እንደበቃ ነው የገለፁት፡፡
የአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ዲፓርትመንት መምህሩ ሆነልኝ እሸቴ(ዶ/ር) በበኩላቸው “ተማሪ እዝራ ከፍሬሽማን ኮርስ ወደ ዲፓርት መንቱ ሲገባ ሙሉ አራት ነጥብ በማምጣት ነው፤ ለሚማረው ትምህርት ትኩረት ያደርጋል፣በተግባር ልምምድ በደንብ ተዘጋጅቶ ገብቶ ይሠራል፣ በባህሪውም ትሁት ነው፡፡ ብዙ ተማሪዎች ጎበዝ ሲሆን ላይበራሪ ይደበቃሉ፣ ማህበራዊ ሕይወት የላቸውም፡፡ እሱ ግን የክፍሉ ተወካይ በመሆን የየተማሪውን ፍላጎት በመጠየቅ ለማግባባት እና ለማስተባበር ይተጋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲው ውጭ የሚሠጡ አጫጭር ኮርሶችንም ለመሰልጠን እድል እንዲያገኙ የሚያደርግ ጎበዝ ልጅ ነው!”በማለት አድናቆታቸውን ችረውታል፡፡
ዶ/ር ሆነልኝ የአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል በዩኒቨርሲቲው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አራት ነጥብ ሙሉ በማምጣት እና ዋንጫ እንዲያገኝ ማድረግ ማስቻሉ ደግሞ ደስተኛ እንዳደረጋቸው ነው የገለፁት፡፡
ለዛ
- “ሕይወት ሰዎች ከምንም በላይ ለመጠበቅ የሚጥሩት እና ከሁሉም ትንሽ የሚንከባከቡት ነው። ” ጄ ላ ብሩየር
- “በኋላ በእርጅና ጊዜ ሕይወትዎን በከንቱ ለኖሩት ዓመታት አሳፋሪ እንዳይሆን በሚያስችል መንገድ መኖር ተገቢ ነው።” ማክሲም ጎርኪ
- “መኖር ነገሮችን መሥራት እንጂ ማግኘት አይደለም።” አርስቶትል
- “ሕይወት አስደናቂ ጀብዱ ናት፣ ለስኬት ሲል ውድቀቶችን ለመቋቋም ብቁ ነው።” ሪቻርድ አልዲንግተን፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የሰኔ 29 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


