የማንኛውም ዜጋ መብት

0
103

በአንድ ሀገር ዜጎች ላይ የሚከሰቱ የልደት፣ የጋብቻ፣ የፍቺ እና የሞት ክስተቶችን በተቋም ደረጃ የመመዝገብ ተግባር ነው የሲቪል እና ቤተሰብ  ምዝገባ፡፡   በዋነኛነት  የዜጎች ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ  ልማትን  ለማቀድ እንዲሁም የተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ  አገልግሎቶችን ለመስጠት፣ በፍትሕ አስተዳደር ቀልጣፋና ውጤታማ  አሠራር እንዲኖር ለማስቻል   ምዝገባው ቁልፍ  ሚና አላቸው፡፡

የወሳኝ ኩነት ምዝገባና ብሔራዊ መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 760/2004 የሲቪል እና ቤተሰብ  ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 1370/2017 (እንደተሻሻለው) የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የማያስችል በመሆኑ አዋጁን እንደገና ማውጣት አስፈሊጊ ሆኖ ስለታመነ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ  ሪፐበሊክ  ሕገ መንግሥት አንቀጽ 55 ንዐስ አንቀፅ (1) እና (6) መሠረት እንደ አዲስ ታውጇል፡፡

አዋጁ ሊወጣ የቻለው ዜጎች ወሳኝ ኩነቶችን በአግባቡና በወቅቱ  እንዲያስመዘግቡ የሚያስችል እንዲሁም  ተደራሽ፣ ሁሉን አቀፍ  እና አስገዳጅ የሆነ የሲቪል   እና የቤተሰብ  ምዝገባ ሥርዓት መዘርጋት አስፈሊጊ ሆኖ  በመገኘቱ ፣ ብሔራዊ ጥቅምንና ደኅንነትን ለማስጠበቅ እና  በመንግሥትና በግል ዘርፍ ለዜጎች የሚሰጡ  አገልግሎቶችን ቀልጣፋ ለማድረግ የሲቪል  እና የቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት መስጠት  አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡

አገልግሎቱ ሥሙን በሚያመለክተው መንገድ የቤተሰብ ምዝገባን የሚያካትት እንደሆነ የገለፁልን የአማራ ክልል የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት ኃላፊ ወ/ሪት መአዛ በዛብህ ናቸው፡፡ ወደ ፊት ደግሞ ይህ አገልግሎት ቤተሰብን በመመዝገብ የቤት ቆጠራን የሚያስቀር እንደሚሆን ይታመናል ነው ያሉት፡፡

ስለአብክመ ሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት  አሠራር  ኃላፊዋ በሰጡት መግለጫ የተለያዩ የግንዛቤ መፍጠሪያ መንገዶችን በመጠቀም ሕብረተሰቡ ስለአገልግሎቱ እንዲያውቅ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡   ከምዝገባው እቅድ አኳያም አፈጻፀሙ ወቅታዊ እና የዘገየ የምዝገባ አፈጻጸም ሲታይ ልደት 144 ከመቶ፣ ሞት 74 ከመቶ ፣ ጉዲፈቻ መቶ ከመቶ፣ ጋብቻ 54 ከመቶ እና ፍች 47 ከመቶ ነው፡፡ በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ለመመዝገብ የታቀደው  982 ሺህ 801 የጋብቻ፣ የልደት…ኩነቶች ሲሆን  ክንውኑ  ከአንድ ሚሊዮን በላይ በመቶኛ ደግሞ ( 107) ከመቶ ነው አፈጻጸሙ፡፡

ከግንቦት 2017 እስከ መጋቢት 2018 በወቅታዊና በዘገየ ለተመዘገቡ ኩነቶች የተሰጠ ምስክር ወረቀት አፈፃፀም ሲታይ በሁሉም ኩነቶች  ሙሉ በሙሉ መሆኑን ያሳያል፡፡ በአጠቃላይ  ለተመዘገቡትም  የምስክር ወረቀት መስጠት ተችሏል፡፡

 

ኩነቶች (ልደት፣ጋብቻ፣ፍችእና ሞት)

ልደት፣ ጋብቻ፣ ፍች… ሲፀም ከተቋሙ የሚሰጡ ማስረጃዎችን (ሰርተፍኬቶች) መያዝ መብት በመሆኑ ማንኛውም ዜጋ በአቅራቢያው ካለ ማዕከል አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ወ/ሪት ማዕዛ ጠቁመዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ማብራሪያ ልደት በ90 ቀን፣ ሞት በ50 ቀን እና ሌሎች ኩነቶች ደግሞ በ30 ቀናት ውስጥ ሲመዘገቡ ምንም አይነት ክፍያ አይኖረውም፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ የማመሳከር የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን እና ለማሻሻል እንዲሁም  ደንበኞችን ከሰው ንክኪ ለማዳን የሚያስችሉ በሦስት መስኮቶች አገልግሎቱ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡  የአገልግሎቱን ሥራ ለማሳለጥም በተቋሙ ሁለት ተጨማሪ እንዲሁም  በመሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት ሌሎች ሁለት ባለሙያዎች መመደባቸውን ኃላፊዋ ጠቁመዋል፡፡

 

የአንድ ማዕከል ምዝገባ አገልግሎት

የአንድ ማዕከል የልደትና የሞት ምዝገባ አገልግሎት በመስጠት በኩል በጤና ተቋማት  84 ሆስፒታሎች እና  450 ጤና ጣቢያዎች  ሥራ  መጀመራቸውን ወ/ሪት መአዛ  ተናግረዋል፡፡

ይህም ወቅታዊ የምዝገባ ሽፋን እንዲጨምር ማስቻሉን ነው ያነሱት፡፡ የምስክር ወረቀት ማመሳከር በቡድኑ ከሚሰጡ አገልግሎቶች አንዱ በመሆኑ ባለፉት 11 ወራት  በአጠቃላይ ልደት 5 ሺህ 762፣ ጉዲፈቻ 7፣ ጋብቻ 998፣ ፍች 56 እንዲሁም ሞት 137 ተገልጋዮች ወደ ማእከሉ መጥተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ መሟላት ያለበትን ቅድመ ሁኔታና ደጋፊ ማስረጃ አሟልተው አገልግሎቱን ያገኙ 6ሺህ 764 ተገልጋዮች ናቸው፡፡

ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ምዝገባውን ለማስፋት በኢትዮ ቴሌኮም በኩል በ15 ዞኖች፣ በ72 ወረዳዎች/ክፍለ ከተሞች እና በ329 ቀበሌዎች   ዝርጋታ ተካሂዷል፡፡ በተጨማሪም በእነዚህ መዋቅሮች (የደ/ማርቆስ እና  የደ/ታቦር ከተማ አስተዳደሮች፣ የምሥራቅ ጎጃም፣ የደቡብና የሰሜን ወሎ፣  የዋግ፣ የአዊ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደሮች፣ የማዕእከላዊ ፣ የምዕራብ፣ የደቡብ እና  የሰሜን ጎንደር፣ የምዕራብ እና የሰሜን ጎጃም እና የሰሜን ሸዋ ቀበሌዎች ለስልጠናው የሚያስፈልጉ ግብዓቶች መላካቸውን ኃላፊዋ ጠቁመዋል፡፡

የጋብቻ፣ የልደት…ምዝገባ ከወረቀት ወጥቶ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም   ወደ ዲጂታል ምዝገባ ተሸጋግሯል፡፡ በ11 ወራት ውስጥ በቀጥታ ምዝገባ ከተመዘገበው ውስጥ 1 ሺህ 135 የአካል ጉዳተኞች እንደሆኑ መረጃው ያሳያል፡፡  በኩነት ዓይነት ሲታይ ደግሞ ልደት 603፣ ሞት 180 ፣ ጋብቻ 336 እና ፍች 16 የአካል ጉዳት ያለባቸው ተመዝጋቢዎች እንደሆኑ ያሳያል፡፡

በ2018 በጀት ዓመት የቀጥታ ምዝገባ ስርዓት ተግባራዊ በመደረጉ ለክብር መዝገብ ሕትመት ፣ለቅፅ ቅብብሎሽ እና መጓጓዣ (ትራንስፖርት) ይውል የነበረ   32 ሚሊዮን 806ሺህ 672 ብር የሚገመት ወጭ ማስቀረት ተችሏል፡፡

ምዝገባው የሚፈጸመው በዲጂታል መሆኑ ደግሞ  የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት ሀሰተኛ ማስረጃን በቀላሉ መከላከል ማስቻሉን  ኃላፊዋ ጠቁመዋል፡፡   የተዘረጋው አሠራር (ሲስተሙ) ካለመቆራረጥ ለ24 ሰዓታት አገልግሎት መስጠቱ  መረጃን ለዜጎች በጥራት፣ በወቅቱ ፣ በፍጥነት መስጠት አስችሏል፡፡ እንደ ኃላፊዋ ማብራሪያ በተለያዩ ምክንያት በሰነድ ላይ  ይደርስ የነበረውን ጉዳት በማስቀረት መረጃውን ማደራጀት እና መያዝም ተችሏል፡፡

ለአብነት በቅርቡ  ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ሕብረት ሥራ ማሕበር በሀሰተኛ መረጃ  ቦታ ለማግኘት የተደራጁ  አንድ ሺህ 322 ግለሰቦች ከተቋሙ የመረጃ ቋት ላይ  ባስመዘገቡት የልደት እና ጋብቻ መረጃ መሠረት ሕገ ወጥ መሆናቸውን ተረጋግጧል፡፡ በዚህም ለከተማ አስተዳደሩ ከ አራት  ቢሊዮን ብር በላይ ያወጣ የነበረ መሬት ማዳን ተችሏል፡፡

ተቋማትም የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ የምስክር ወረቀት እንደ ቅድመ ሁኔታ መጠቀም መጀመራቸው በተጠቃሚው በኩል ከፍተኛ ፍላጎት  አድጓል፡፡ በዚህም በ534 ጤና ተቋማት የአንድ ማዕከል የልደትና ሞት ምዝገባ መመዝገብ ተጀምሯል፡፡

ወ/ሪት መአዛ  እንዳሉት ከሐምሌ 1/2018 ዓ.ም  ጀምሮ ከበጎ ፍቃድ አገልግሎት ጋር ተጣምሮ  የልደት ሠርተፍኬትን የመሥጠት ሥራ በንቅናቄ ይሠራል፡፡ በ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምን በመገምገም ቀጣይ ትኩረት የሚሰጣቸው ተግባራት ደግሞ የተሻለ ለፈጸሙ እውቅና መስጠት እና የ2019 በቴክኖሎጂ የተደገፉ መዝገባ ማስፋት፣ ጊዜ ገደቡ ያለፈ የልደት የንቅናቄ ምዝገባ ማጠናከር እና  ግንባር ቀደም (ሞዴል) ከተሞችን ማስፋት ላይ በትኩረት ይሰራል፡፡

የሕግ አንቀጽ

 

አምስት ዋና ዋና የሕይወት ኩነቶች ይመዘገባሉ

 

  • ልደት (የተወለዱ ሕፃናት መረጃ)
  • ሞት (የሟቾች መረጃ) በተለይ በጤና ተቋም
  • ጋብቻ (የተጋቡ ጥንዶች መረጃ)
  • ፍች (የፍች ውሳኔ የተሰጣቸው)
  • ጉዲፈቻ (በሕጋዊ መንገድ የተደረጉ ጉዲፈቻዎች)

ከክፍያ ነፃ የሚመዘገቡበት ጊዜ ገደብ

  • ልደት፦ ከተወለደበት ቀን ጀምሮ በ 90 ቀናት ውስጥ ከተመዘገቡ
  • ሞት፦ ከሞተበት ቀን ጀምሮ በ 50 ቀናት ውስጥ
  • ጋብቻ፣ ፍች እና ጉዲፈቻ፦ ኩነቱ ከተፈፀመበት ቀን ጀምሮ በ 30 ቀናት ውስጥ መመዝገብ አለባቸው፡፡ ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውጪ ለሚከናወኑ ምዝገባዎች ግን (በአብዛኛው 300 ብር) ብቻ ነው የሚጠየቀው፡፡

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሰኔ 29  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here