ኢትዮጵያ ከኬፕ ቨርዲ ምን ትማር?

0
90

በዘመናዊው እግር ኳስ መድረክ የሚታዩት ሁነቶች የስፖርቱን ባህላዊ እሳቤ ሙሉ በሙሉ እየቀየሩት ይገኛሉ፡፡ እግር ኳስን በሕዝብ ብዛት ወይም በታሪክ ብቻ ለመለካት መሞከር ጊዜ ያለፈበት አካሄድ መሆኑን የሚያሳዩ ተጨባጭ መረጃዎች በየቀኑ ታይተዋል፤ እየታዩም ነው፡፡ ለዚህም ትልቁ ማረጋገጫ የሕዝብ ቁጥሯ ከ560 ሺህ የማይበልጠው ኬፕ ቨርዲ በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ መድረኮች እያሳየችው ያለችው ጥንካሬ ነው፡፡ ደሴቷ ሀገር ኬፕ ቨርዲ በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ያሳየችው አቋም የረጅም ጊዜ ዝግጅት ፍሬ መሆኑን የቢቢሲ ስፖርት መረጃ አመልክቷል፡፡

በምድብ ድልድል ውስጥ ከታላላቅ ብሄራዊ ቡድኖች ጋር ተደልድላ የወቅቱ የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊዋን ስፔንን እና የደቡብ አሜሪካዋን  ኡራጓይን የፈተነችበት መንገድ የዕቅድ ውጤት መሆኑን የዘ ጋርዲያን መረጃ አስነብቧል፡፡ መላው ዓለም ይበልጥ ቆሞ ያጨበጨበላት ግን ከኳታሩ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ አርጀንቲና ጋር ባደረገችው ጨዋታ ነው፡፡ እናም በሊዮኔል ሜሲ የሚመራውን የአርጀንቲና ስብስብ በታክቲክ ብስለት እና በአካል ብቃት የፈተነችበት መንገድ የሕዝብ ብዛት ለእግር ኳስ ውጤት ወሳኝ እንዳልሆነ ያሳያል ወይም ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡

ኬፕ ቨርዲ በኮከቦች የተሞላውን የአርጀንቲና በሄራዊ ቡድን የገጠመችበት መንገድ ለብዙ ሀገራት ትልቅ የስነ ልቦና ትምህርት ሰጥቷል፡፡

ያ ጨዋታ ኬፕ ቨርዲን ወደ ጥሎ ማለፍ ከማሸጋገሩም በላይ ትንሿ ደሴት በዓለም እግር ኳስ ካርታ ላይ በክብር እንድትሰፍር አድርጓታል፡፡ ይህ ታሪካዊ ክስተት እግር ኳስ በሳይንሳዊ ስሌቶች እና በተቋማዊ ጥራት የሚመራ ኢንዱስትሪ መሆኑን ያሳያል ይላል መረጃው፡፡  ተጫዋቾቿ ሜዳው ላይ የነበራቸው የታክቲክ ጥንካሬ፣ ፈጣን መልሶ ማጥቃት እና የተጋጣሚን የኋላ ክፍል የማሸበር ክህሎታቸው  ከአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች የቀሰሙት ልምድ እንደሆነ ቢቢሲ ስፖርት  ጠቁሟል፡፡

የኬፕ ቨርዲ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለፉት 15 ዓመታት የተከተለው የረጅም ጊዜ ዕቅድ እና ተቋማዊ ግንባታ ለዛሬው ውጤት መሠረት እንደጣለ ይነገራል፡፡ ፌዴሬሽኑ ለአጭር ጊዜ ዝግጅቶች በጀቱን ከማባከን ይልቅ በዘመናዊ መሠረተ ልማት እና በዲያስፖራ ተጫዋቾች ፍለጋ ላይ ፈሰስ በማድረግ ውጤታማ ሆኗል፡፡ የሀገሪቱ ትልቁ የእግር ኳስ ተቋም ለተጫዋቾቹ የሚሰጠው ክብር ከአውሮፓ ክለቦቻቸው ጋር ተመጣጣኝ እንዲሆን ማድረጉ ለውጤቱ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ከሰሜን አትላንቲክ ውቅያኖስ ትንሿ ደሴት ሀገር የዘር ሀረጋቸው የሚመዘዝ እና በአውሮፓ የሚኖሩ  ፕሮፌሽናል ተጫዋቾችን በብሔራዊ ቡድኑ በማካተት የስብስብ ጥራቷን አሳድጋለች፡፡

ይሁን እንጂ የዲያስፖራው ጥንካሬ ብቻውን ኬፕ ቨርዲን ስኬታማ አላደረጋትም፡፡ ሀገሪቱ በውስጧ የዘረጋችው የስፖርት ሳይንስ እና የአካዳሚ ሥርዓት ለተጫዋቾች ማሳደጊያ ትልቅ ሞተር እንደሆነ ይነገራል፡፡ የፊፋ ፎርዋርድ ፕሮግራምን በመጠቀም ዘመናዊ ሜዳዎችን በመገንባት በሀገር ውስጥ የሚገኙ ታዳጊዎች ዘመናዊ ስልጠና እንዲያገኙ አስችሏል፡፡

አርጀንቲናን የመሰለ ግዙፍ ቡድን ለ90 ደቂቃ መቋቋም የቻሉትም በዚህ መንገድ ጭምር እንደሆነ የዘ ጋርዲያን መረጃ ያስረዳል፡፡ የኬፕ ቨርዲ ተጫዋቾች አንዳች ፍርሀት ሳያድርባቸው የአርጀንቲናን ኮከቦች የገጠሙት በውስጣቸው ከፍተኛ በራስ መተማመን ስለተገነባ ጭምርም ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከኬፕ ቨርዲ ጋር ስትነጻጸር በህዝብ ብዛት፣ በተሰጥኦ እና ለእግር ኳስ ባለው ፍቅር እጅግ የላቀች ብትሆንም በአስተዳደር፣ በመሠረተ ልማት፣ በፋይናንስ አጠቃቀም እና በውጤት ረገድ ግን በከፍተኛ ደረጃ ወደ ኋላ ቀርታለች፡፡ በ2026 ሰኔ ወር በወጣው የፊፋ ወርሃዊ የደረጃ ሰንጠረዥ  ኬፕ ቨርዲ በዓለም 63ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፤ ኢትዮጵያ ግን 147ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ይህ የደረጃ ልዩነት የመጣው ኢትዮጵያ ስፖርቱን በሳይንሳዊ እና መዋቅራዊ መንገድ መምራት ባለመቻሏ እንደሆን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ የሚታዩት በርካታ ስር የሰደዱ ችግሮች እንዳሉ በተደጋጋሚ ባለሙያዎች ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው፤ ከችግሮች መካከልም የአመራር ብቃት ማነስ፣ የሊግ ጥራት መውረድ፣ የወጣቶች ልማት እቅድ አለመኖር እና የክለቦች አስተዳደር ድክመት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች አሁንም በመንግሥታት በጀት ላይ ጥገኞች በመሆናቸው ፕሮፌሽናል ተቋም መገንባት አልቻሉም፤ ከዚህም በተጨማሪ በዘመናዊ እግር ኳስ ውስጥ ወሳኝ የሆኑት የቴክኒክ እቅድ፣ የመረጃ ትንተና እና የስፖርት ሳይንስ አጠቃቀም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ፈጽሞ የማይታወቁ ወይም ችላ የተባሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ከሁሉም በላይ ግን የካፍ ዓለም አቀፍ መመዘኛን የሚያሟላ አንድም ስታዲየም በሀገሪቱ ባለመኖሩ ብሔራዊ ቡድኑ በሜዳው ማድረግ የነበረበትን ጨዋታዎች በስደት ለማድረግ መገደዱ የውድቀቱ ማረጋገጫ ነው፡፡ በ2026 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያም ዋሊያዎቹ ገና በጊዜ ከማጣሪያው ውድድር መሰናበታቸው አይዘነጋም፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ያለው ችግር የተሰጥኦ ማጣት ሳይሆን የአሰራር ስርዓት ችግር ነው፡፡ በየገጠሩ የሚታዩት ታዳጊዎች ሳይንሳዊ ስልጠና የሚያገኙበት አካዳሚ የለም፡፡ ኢትዮጵያ ከውጤት ድርቅ ወጥታ ተወዳዳሪ ለመሆን የኬፕ ቨርዲን ልምዶች መተግበር አለባት፡፡ ከረጅም ጊዜ ዕቅድ ውጪ የሚመጡ ጊዜያዊ ስኬቶች ዘላቂ እንዳልሆኑ መገንዘብም ቀዳሚ የፌዴሬሽኑ ተግባር ነው፡፡

የፌዴሬሽኑን አመራር ከፖለቲካዊ ተጽዕኖ ነፃ ማድረግ እና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ አካዳሚዎችን በየክልሉ መገንባት ያስፈልጋል፡፡ የሀገር ውስጥ ሊጉን ጥራት ማሻሻል እና የዲያስፖራ ተጫዋቾችን የሚከታተል የስካውቲንግ ክፍል ማቋቋም ሌላኛው የማይናቅ ጉዳይ ነው፡፡

የኬፕ ቨርዲ የስኬት ጉዞ እግር ኳስ በዘፈቀደ የሚመራ ጨዋታ አለመሆኑን ያስተምራል፡፡

ዘመናዊው እግር ኳስ በሳይንስ እና በተቋማዊ ጥራት ላይ የተመሰረተ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የሰው ኃይል ተጠቅማ ወደ ቀድሞ ክብሯ ለመመለስ የኬፕ ቨርዲን የአሰራር ጥራት እንደ ማስተማሪያ መውሰድ ይኖርባታል፡፡

አርጀንቲናን የፈተነችው ኬፕ ቨርዲ በውስጧ የነበረው ራዕይ ከደሴቱ ስፋት የላቀ እንደነበር የሚታወስ ነው፤ ኢትዮጵያ ከቆየ የእግር ኳስ ትርክት ወጥታ ወደ ተግባራዊ ሳይንስ መሸጋገር ይኖርባታል፡፡

የኬፕ ቨርዲ ተጫዋቾች በሀገር ውስጥ ሊግ ብቻ ሳይወሰኑ ገና በወጣትነታቸው ወደ አውሮፓ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲቪዚዮን ሊጎች በመሄድ ሙያዊ ብቃታቸውን ያሳድጋሉ፡፡ ይህ ሂደት ተጫዋቾቹ ከአውሮፓ እግር ኳስ የሚያገኙትን ታክቲካዊ ስነ ስርዓት እና አካላዊ ጥንካሬ በቀጥታ ወደ ብሄራዊ ቡድኑ እንዲያመጡና ጠንካራ የልምድ ልውውጥ እንዲኖር ያስችላል፡፡

ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በሀገር ውስጥ ብቻ መጫወታቸው በዝቅተኛ የፉክክር መንፈስ ውስጥ እንዲቆዩ ያደርጋቸዋል፤ ይህ ደግሞ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ትልቅ ክፍተት ይፈጥራል፡፡ ኬፕ ቨርዲ አርጀንቲናን የፈተነችበት የአካል ብቃት የመጣው ተጫዋቾቿ በአውሮፓ ሊጎች መጫወታቸው ነው፡፡ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገትም የሀገሪቱ ተጫዋቾች በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ካለው የተደላደለ ክፍያ ወጥተው ፈታኝ ወደሆኑት የውጭ ሀገር ሊጎች በተለይም በሰሜን ወይም ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በአውሮፓ ሄደው እንዲጫወቱ ማበረታታት እና ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

ኬፕ ቨርዲ የረጅም ጊዜ ፕሮጀክት በመቅረጽ ለአሰልጣኞቿ ለምሳሌ እንደ አሰልጣኝ ቡቢስታ ላሉ ባለሙያዎች ቡድኑን በሂደት እንዲገነቡ ሙሉ ስልጣን እና ጊዜ ትሰጣለች፡፡ በአንድ ጨዋታ መሸነፍ ወይም ማሸነፍ ላይ ብቻ ተመስርታ አሰልጣኞችን በየጊዜው አትቀያይርም፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከዚህ በመማር በተደጋጋሚ አሰልጣኞችን የመቀየር ልማዱን ማቆም አለበት፡፡ ይልቁንም የረጅም ጊዜ እቅድ እና ራዕይ ላለው አሰልጣኝ የተረጋጋ የሥራ አካባቢ በመፍጠር በቂ ድጋፍ መስጠትን መልመድ ይኖርበታል፡፡

ኢትዮጵያ ልክ እንደ ኬፕ ቨርዲ ስኬታማ ለመሆን የተጫዋቾች የዝውውር ፖሊሲ መቅረጽ እና የፌዴሬሽኑን የፋይናንስ ምንጭ ለልማት ብቻ መዋል ይኖርበታል፡፡ ኬፕ ቨርዲ እያንዳንዱን ሳንቲም ለሜዳ ግንባታ ስታውል ኢትዮጵያ ግን ለአጭር ጊዜ ዝግጅቶች በጀት ስታባክን ትታያለች፡፡ ይህ ልዩነት አንዷን በዓለም ዋንጫ ታዋቂ ሲያደርግ ሌላኛዋን ከማጣሪያ እንድትሰናበት አድርጓታል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ አሁን ከገባበት ችግር ወጥቶ በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ ለማድረግ ነባሩን እና ውጤት አልባውን አሠራር በአዲስ መዋቅራዊ ለውጥ መተካት የግድ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደ ኬፕ ቨርዲ ያሉ ሀገራት የተከተሉትን የእግር ኳስ ሞዴል  እና አሰራር መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ ይህ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ በመጀመሪያ ደረጃ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ከረጅም ጊዜ ዕቅድ ውጪ የሚመጡ ጊዜያዊ ስኬቶች ዘላቂ እንዳልሆኑ መገንዘብ እና ለአጭር ጊዜ ውድድሮች የሚባክነውን ከፍተኛ ገንዘብ በማስቀረት ለዘላቂ ልማት ማዋል ነው፡፡

የእግር ኳስ አመራር ጥበብ በራሱ ሙያዊ እውቀትን የሚጠይቅ በመሆኑ የፌዴሬሽኑም ሆነ የክለቦች አስተዳደር ከፖለቲካዊ ተጽዕኖ ነፃ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ታዲያ ዘርፉ በስፖርት ማኔጅመንት እና በእግር ኳስ እውቀት ባላቸው ባለሙያዎች እንዲመራ ማድረግ፣ ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን  ለማስፈን ያግዛል፡፡

በየክልሉ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ እና በስፖርት ሳይንስ የተደገፉ የእግር ኳስ አካዳሚዎችን መክፈት የነገ ተጫዋቾችን ለማፍራት ዋስትና ነው፡፡ የስታዲየም ግንባታዎችን  በግልጽ የጊዜ ሰሌዳ በጥራት አጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃት ለነገ የማይተው የቤት ሥራ መሆን አለበት፡፡

የሀገር ውስጥ ሊግን ጥራት ለማሻሻል ደግሞ ክለቦች ከመንግሥት በጀት ወጥተው በራሳቸው ገቢ እንዲተዳደሩ የሚያስችል የፋይናንስ ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት ይኖርበታል፡፡ ይህም ክለቦች እንደ ተቋም እንዲጠናከሩ እና ለተጫዋቾች ዕድገት ትኩረት እንዲሰጡ ያደርጋቸዋል፡፡ የአሰልጣኞች ማሰልጠኛ ተቋማትን በማዘመን የዘመናዊ ታክቲክ እና የስፖርት ሳይንስ እውቀት ያላቸውን የሀገር ውስጥ አሰልጣኞች በብዛት ማፍራት እንዲሁም በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የተጫዋቾችን የአካል ብቃት እና የተጋጣሚን የአጨዋወት ስልት የሚተነትን የመረጃ ትንተና ክፍል መተግበር ያስፈልጋል ይላል መረጃው፡፡

የኬፕ ቨርዲ ብሄራዊ ቡድን ውድድሮችን የሚያሸንፈው በግል ችሎታ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓ እግር ኳስ ዘመናዊ የታክቲክ ስነ ስርዓት፣ በጥናት በታቀደ የመልሶ ማጥቃት ስልት እና በአካላዊ ጥንካሬ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ያላቸውን ማራኪ አጭር እና ፈጣን የኳስ ቅብብል ዘይቤ ከዚህ ዘመናዊ የታክቲክ ጥንካሬ እና ከአካላዊ ብቃት ጋር ማዋሃድ ይኖርባቸዋል፡፡ እነዚህን የኬፕ ቨርዲን ጠንካራ ጎኖች ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም የሀገሪቱን እግር ኳስ ወደ ላቀ ዓለም አቀፍ ደረጃ ማሸጋገር ይቻላል፡፡

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሐምሌ 6 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here