የአፍሪካ እግር ኳስ ትናንት እና ዛሬ የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት አላቸው። የቀደመው የአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክ በተሰጥኦ የበለፀገ ቢሆንም በታክቲክ ድህነት እና በልምድ ማነስ የታጠረ ነበር። ብሄራዊ ቡድኖችም በአውሮፓ እና በደቡብ አሜሪካ ታላላቅ ሀገራት በቀላሉ የሚንበረከኩ ነበር። በዓለም ዋንጫ መድረክ ቀድመን ተሸናፊ መሆናቸውን አምነን፣ ሜዳ ላይ ተመልካችን እንዲያዝናና ብቻ ነበር የምንፈልገው። ዛሬ ግን ያ ታሪክ እየተቀየረ ነው።
አፍሪካ አሁን ሜዳ ላይ የምትገባው ሰርግ እና ምላሽ ለማድመቅ አይደለም፤ ዋንጫውን ለማሸነፍ እንጂ። በአህጉሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዐስር ብሄራዊ ቡድኖች ተሳትፈዋል፤ እነዚህ ተሳታፊ ሀገራትም አውሮፓውያንን በአካላዊ ጥንካሬ እና በታክቲክ የበላይነት አስጨንቀው አዲስ ምዕራፍ ከፍተው አሳይተውናል።
በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የአፍሪካውያን ብሄራዊ ቡድኖች የአቋም መሻሻል መላውን ዓለም አስደምሟል። ቀደም ሲል አንድ ወይም ሁለት የአፍሪካ ቡድኖች ብቻ ከምድባቸው ሲያልፉ ማየት የተለመደ ነበር። ዘንድሮ ግን በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ዘጠኝ የአፍሪካ ሀገራት ወደ 32ቱ (90 በመቶ) የጥሎ ማለፉን ዙር ተቀላቅለዋል፡፡ ይህም የአህጉሪቱ የእግር ኳስ እድገት ማረጋገጫ ሆኗል ይላል የቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ዘገባ።
“የአፍሪካ እግር ኳስ ደረጃ አሁን ላይ ተቀይሯል። ማንኛውንም የዓለም ታላቅ ቡድን ማሸነፍ የምንችልበት ታክቲካዊ ብስለት ላይ ደርሰናል!” ሲሉ የቀድሞው የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዋሊድ ረግራጊ ተናግረዋል፡፡ የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔም የአፍሪካ እግር ኳስ ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነቱን ማንም ሊክደው የማይችለው እውነታ ሆኗል ብለዋል።
የዘንድሮው የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች ካልተደራጀ እግር ኳስ ተላቀው በታክቲክ ዲሲፕሊን የታነጸ ዘመናዊ እቅድ ይዘው ቀርበዋል። በመከላከል ስልት፣ በፈጣን ሽግግር እና አደገኛ በሆነ የመልሶ ማጥቃት ስልቶች ትልቅ ለውጥ አሳይተዋል፡፡ ሞሮኮ ከብራዚል ጋር አንድ አቻ ስትለያይ የታየው የታክቲክ ብስለት በግለሰብ ክህሎት ብቻ ሳይሆን በቡድን አደረጃጀት እና ጨዋታን በብልሀት በመምራት የመጣ መሆኑን ያረጋግጣል።
ግብፅም በተመሳሳይ ከቤልጂየም ጋር አንድ አቻ ስትለያይ አውስትራሊያን በማሸነፍ ጥሎ ማለፉን ዙር መቀላቀሏ የሚታወስ ነው። በጥሎ ማለፉም ምንም እንኳ በአርጀንቲና ባለቀ ሰዓት ብትሸነፍም ያሳየችው ተጋድሎ በሚገባ መሻሻሏን በርካቶች መስክረውላታል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ጎን የተደራጀ የኋላ ክፍላቸው እንደሆነ መረጃዎች አመልክተዋል፤ ሞሮኮ እና ግብፅ የተጠቀሙባቸው የ 4-1-4-1 እና የ 4-4-2 አሰላለፎች የአውሮፓ እና የደቡብ አሜሪካ ታላላቅ አጥቂዎችን መፈናፈኛ አሳጥተዋቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ከሞሮኮ እና ከግብፅ ስኬት በተቃራኒ አልጄሪያ እና ቱኒዚያ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የተለየ ጉዞ ነበራቸው። አልጄሪያ በገጠማት የመከላከል ክፍተት ወደ ጥሎ ማለፉ የመሸጋገር ህልሟ አልተሳካም። ቱኒዚያም በተመሳሳይ በወሳኝ ጨዋታዎች የታየባት የትኩረት ማጣት እና የግብ እድሎችን በአግባቡ አለመጠቀም ለሽንፈት ዳርጓታል።
በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የምዕራብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች ድንቅ የአካል ብቃት እንደነበራቸው አይካድም። ሴኔጋል ኢራቅን አምስት ለባዶ በረታችበት ጨዋታ ያሳየችው የመልሶ ማጥቃት ስልት አስደናቂ እንደነበር የቢቢሲ ስፖርት መረጃ ያረጋግጣል። ኮትዲቫርም በምድብ ጨዋታ ኢኳዶርን አንድ ለባዶ ማሸነፏ የሚታወስ ነው፤ በጥሎ ማለፉ ጨዋታ ግን በገጠማት የትኩረት ማጣት ችግር ምክንያት ለመሰናበት ተገዳለች። ጋናም ጥሎ ማለፉን የተቀላቀለች ሌላኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ብትሆንም ለማጣሪያ ከኮሎምቢያ ጋር በነበራት ጨዋታ ያገኘችውን የግብ ዕድሎች በአግባቡ ባለመጠቀሟ ከውድድሩ ተሸኝታለች። እነዚህ ብሄራዊ ቡድኖች በአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ በርካታ ከዋክብት ቢኖሯቸውም ዘጠናውን ደቂቃ በጥበብ እና በብልሀት የመጨረስ ችግር ግን በስፋት ታይቶባቸዋል።
በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የስፖርት መገናኛ ብዙኃንን ቀልብ የሳበችው ኬፕ ቨርዴ ናት። በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ የተሳተፈችው ትንሿ ደሴት ከስፔን እና ከኡራጓይ ጋር ነጥብ መጋራቷ ዓለምን አስገርሟል። ከአርጀንቲና ጋርም እልህ አስጨራሽ ፉክክር ማድረጓ በታላላቅ እና በታናናሽ ብሄራዊ ቡድኖች መካከል ያለው ልዩነት እየጠበበ መምጣቱን ያረጋግጣል። ከረጅም ዓመታት በኋላ ወደ መድረኩ የተመለሰችው ደቡብ አፍሪካም በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከምድብ ያለፈችበት ነው የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ። ይህም ለደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ አዲስ ተስፋ ፈንጥቋል።
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሜዳዋ ያሳየችው እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ የሚደነቅ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በጥሎ ማለፉ ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃ ግብ ተቆጥሮባት ብትሰናበትም በምድብ ጨዋታዎች ያሳየችው ጥንካሬ ለተጋጣሚዎቿ አስፈሪ ነበር፤ ተጫዋቾቿ ሜዳ ላይ የነበራቸው አካላዊ ጥንካሬ አፍሪካ በመካከለኛው እና ደቡባዊ ክፍሏ ያለውን እምቅ አቅም ዳግም ያሳየችበት ሆኗል።
ኬፕ ቨርዴ በምድብ ድልድል ውስጥ ከታላላቅ ብሄራዊ ቡድኖች ጋር ተደላድላ የወቅቱ የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊዋን ስፔንን ፣ የደቡብ አሜሪካ ታላላቅ ቡድኖችን ኡራጓይን እና አርጀንቲናን የፈተነችበት መንገድ አስገራሚ እንደነበር የዘ ጋርዲያን መረጃ አስነብቧል፡፡ በተለይ ደግሞ በኮከቦች የተሞላውን የአርጀንቲና በሄራዊ ቡድን የገጠመችበት መንገድ ለብዙ ሀገራት ትልቅ የስነ ልቦና ትምህርት ሰጥቷል፡፡ ያ ጨዋታ ትንሿን ሀገር በዓለም እግር ኳስ ካርታ ላይ በክብር እንድትሰፍር አድርጓታል፡፡
የአፍሪካ ቡድኖች በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ምርጥ የሆኑበት የመጀመሪያው እና ዋናው ሚስጥር የታክቲክ ዲሲፕሊን (Tactical Discipline) ነው። ከዚህ ቀደም የአፍሪካ ቡድኖች በከህሎት የተሻሉ ቢሆኑም ጨዋታዎችን በታክቲክ የመምራት እና የተደራጀ መከላከል ስልት ላይ ድክመት ይታይባቸው እንደነበር የካፍ ኦንላይን መረጃ ያስታውሰናል።
ዘንድሮ ግን እንደ ሞሮኮ እና ኬፕ ቨርዴ ያሉ ቡድኖች የነበራቸው የተደራጀ የመከላከል ስልት በተጋጣሚዎቻቸው በቀላሉ የማይሰበር ምሽግ እንደነበረ አያጠያይቅም። በሀገር በቀል እና በውጭ አሰልጣኞች የሚመሩት እነዚህ ብሄራዊ ቡድኖች የጨዋታውን ፍጥነት እንዴት መቆጣጠር እንዳለባቸው፣ መቼ መከላከል እና መቼ በጥልቀት ማጥቃት እንዳለባቸው ከፍተኛ የታክቲክ ብስለት አሳይተዋል። ተጫዋቾችም ሜዳ ላይ ያላቸው የስራ ድርሻ የመወጣት ፍላጎት እና የዲሲፕሊን ደረጃ ጥሩ እንደነበር ሁሉም ይመሰክራል።
ሌላው አብዛኞቹ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የተሳተፉ በሄራዊ ቡድኖች ተጫዋቾቻችው በአምስቱ ታላላቅ የአውሮፓ ሊጎች መጫወታቸው(Premier League, La Liga, Serie A) ትልቅ ልምድ እና የበሰለ እውቀት አግኝተዋል። እንደ ብራሒም ዲያዝ (ሞሮኮ) እና አንቶኒዮ ሴሜንዮ (ጋና) ያሉ ኮከቦች በየሳምንቱ ከአውሮፓ ምርጥ ተከላካዮች እና አጥቂዎች ጋር የሚፋለሙ በመሆናቸው በዓለም ዋንጫው መድረክ ምንም አይነት የፍርሃት ስሜት እንዳይታይባቸው ማድረጉን ኤን ዲ ቲቪ ስፖርት ዘግቧል፡፡
በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የአካል ብቃት የበላይነት እና ፍጥነት የአፍሪካውያን መለያ እንደነበር የሚታወስ ነው። እንደ ጋና፣ ሴኔጋል እና ኮትዲቫር ያሉ ብሄራዊ ቡድኖች ሜዳ ላይ የነበራቸው ከፍተኛ የአካል ብቃት የአውሮፓ ተጫዋቾችን በእጅጉ ሲፈትን ተመልክተናል። ይህ የአውሮፓ ታክቲካዊ እውቀት እና የአፍሪካውያን የተፈጥሮ አካላዊ ጥንካሬ ውህደት የአፍሪካን ብሄራዊ ቡድኖች ሜዳ ላይ አስፈሪ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
አፍሪካውያን ዘንድሮ ድንቅ ተጋድሎ ቢያደርጉም ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ እንዳይሸጋገሩ ያደረጓቸው መሠረታዊ ደካማ ጎኖች እንደነበሩም የቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ መረጃ ያስረዳል። ማንኛውም ወርቃማ ታሪክ ያለ ስህተት አይጠናቀቅም። ታዲያ ይህን ስህተት “የ86ኛው ደቂቃ እርግማን” (The 86th-Minute Curse) ብለውታል።
በአፍሪካ ብሄራዊ በድኖች ላይ በጥሎ ማለፉ ከታዩት ድክመቶች መካከል ጨዋታን በብልሀት መጨረስ አለመቻል (የደቂቃዎች ትኩረት ማጣት) ፣ የግብ እድሎችን በአግባቡ አለመጠቀም ፣በትልልቅ ጨዋታዎች ላይ የሚታይ የስነ-ልቦና መረበሽ ይጠቀሳሉ፡፡
በጥሎ ማለፉ ጨዋታዎች ኮትዲቫር፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ሴኔጋል ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት በገጠማቸው የትኩረት ማጣት ችግር ምክንያት ግብ ተቆጥሮባቸው በጠባብ ውጤት ለመሰናበት ተገደዋል፡፡ ከሞሮኮ እና ግብፅ ስኬት በተቃራኒ አልጄሪያ እና ቱኒዚያ የተለየ ጉዞ ነበራቸው። አልጄሪያ በገጠማት የመከላከል ክፍተት ምክንያት ወደ ጥሎ ማለፉ የመሸጋገር ህልሟ አልተሳካም። ቱኒዚያም በተመሳሳይ በወሳኝ ጨዋታዎች የታየባት የትኩረት ማነስ እና የግብ እድሎችን በአግባቡ አለመጠቀሟ ለሽንፈት ዳርጓታል። ጨዋታዎችን በጥበብ እና በብልሀት መጨረስ ላይ ገና ሰፊ ሥራ እንደሚጠይቃትም መረጃው ያመለክታል።
ይሁን እንጂ የ2026 እ.አ.አ የዓለም ዋንጫ ለአፍሪካ ትልቅ የእግር ኳስ ታሪክ እመርታ እንደሆነ የካፍ ኦንላይን መረጃ አስነብቧል። የአፍሪካ እግር ኳስ ከቀደመው የተሸናፊነት ስነ ልቦና ወጥቶ ዛሬ በታክቲክ እና በስኬት ማማ ላይ ለመቀመጥ መሰረት ጥሏል። ታዳጊዎችን በማሰልጠን እና የስነ ልቦና ጥንካሬን በማሳደግ በቀጣይ የዓለም ዋንጫ አፍሪካ ከነክብሯ እንደምትመለስ ይታመናል፡፡
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የሐምሌ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


