የመላቅ ፍላጎት

0
105

ክሮሺያዊው ቡዲሚር ሶባት በፈረንጆች 2021 ለ24 ደቂቃ ከ37 ሰከንድ ያለምንም ትንፋሽ ውሃ ውስጥ ቆይቷል፡፡

የጃማይካው አትሌት ዩሴይን ቦልት አ.አ.አ በ2009 በበርሊን በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 100 ሜትርን በ9.58 ሰከንድ በመጨረስ የዓለም ክብረ ወሰን አስመዝግቧል፡፡

አሜሪካዊው ዲን ካርናዜስ በ2005 በሦስት ቀናት ውስጥ (75 ሰዓታት) ያለ እረፍት እና ያለ እንቅልፍ 560 ኪሎ ሜትር ሮጧል፡፡ አይስላንዳዊው ሃፍቶር ጆርንሰን በ2020 እ.አ.አ 501 ኪሎ ግራም ክብደት አንስቷል፡፡

የጊነስ የዓለም ክብረ ወሰኖች መዝገብ የሰው ልጅን የማወቅ ጉጉት፣ የመፈታተን አቅም እና ከሚጠበቀው በላይ የመሄድ ፍላጎት የሚያሳይ ልዩ ሰነድ ነው፡፡ ከጥንታዊ ስልጣኔዎች እስከ ዘመናዊው የቴክኖሎጂ ዘመን ድረስ የሰው ልጅ ሁሌም የበለጠ፣ የፈጠነ፣ ረጅሙ ወይም አስገራሚው ማን እንደሆነ ለማወቅ ይጓጓል፡፡

ነገር ግን እነዚህ የዓለም ክብረ ወሰኖች ከደረጃዎች፣ ከሜዳሊያዎች እና ከቁጥሮች ባሻገር ስለ ሰው ልጅ አእምሮ፣ የነርቭ ሳይንስ እና የስነ-ልቦና አቅም ምን ይነግሩናል?

ሰዎች ክብረ ወሰን ለመስበር ያላቸውን ከፍተኛ ፍላጎት የስነ-ልቦና ባለሙያዎች በተለያዩ ሳይንሳዊ መንገዶች ያብራሩታል፡፡

የስነ-ልቦና ባለሙያው ዴቪድ ማክሌላንድ እንደገለጹት የሰው ልጅ በራሱ ውስጥ የስኬት ፍላጎት አለው፡፡ አንድ ሰው “በዓለም ላይ ምርጥ” ለመሆን ሲሞክር በአእምሮው ውስጥ ያለው የሽልማት ስርዓት ከፍተኛ የሆነ የደስታ ስሜት ይፈጥራል፡፡ ይህ ደስታ ከባድ ተግዳሮቶችን የመጋፈጥ ጉልበት ይሰጣል፡፡

በዝግመተ ለውጥ ሳይንስ መሰረት በቡድን ውስጥ “ልዩ” ወይም “የላቀ” መሆን ማህበራዊ ደረጃን ከፍ ያደርጋል፡፡ ይህ የዘመናዊው ክብረ ወሰን ፍለጋ ጥንታዊው ሰው በተሻለ አዳኝነት ወይም ጥንካሬ በቡድኑ ውስጥ ተቀባይነት ለማግኘት ከነበረው ጥረት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

አብርሃም ማስሎው እንደገለጸው የሰው ልጅ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የመድረስ ፍላጎት አለው፡፡ ክብረ ወሰን መስበር ለብዙዎች የራሳቸውን ውስጣዊ አቅም ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ የሚደረግ ጉዞ ነው፡፡

በየዓመቱ የሚሰበሩ ክብረ ወሰኖች የሰው ልጅን የፈጠራ እና የፅናት አቅም ያሳያሉ፡፡

በጣም ረጅም ርቀት በባዶ እግር መሮጥ ወይም ለሰዓታት ያለማቋረጥ በአንድ አቋቋም በመቆየት የሚገኙ ክብረ ወሰኖች የሰው ልጅን የአእምሮ ጽናት ያሳያሉ፡፡ የነርቭ ሳይንስ እንደሚያሳየው ከፍተኛ ህመም በሚኖርበት ጊዜ አንጎል የሚፈጥረው ኢንዶርፊን የተባለው ተፈጥሯዊ የህመም ማስታገሻ ግለሰቡ ህመምን እንዲቋቋም እና ግቡን እንዲመታ ይረዳል፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ ብዙ መረጃዎችን ማስታወስ ወይም በጭንቅላት ብቻ አስቸጋሪ የሒሳብ ስሌቶችን መሥራት የሰው ልጅን  የመሻሻል አቅም (የኒውሮፕላስቲሲቲ) አቅም ያሳያሉ፡፡ አንጎል አዳዲስ ስልጠናዎችን ሲያገኝ የነርቭ ግንኙነቶቹን እንደገና በመገንባት የአእምሮ ፍጥነትን እና የማስታወስ ችሎታን ይጨምራል፡፡

ለምን ሰዎች የዓለም ረጅሙን የፒዛ ሰንሰለት ወይም እጅግ ብዙ ሰዎች በአንድ ላይ ሆነው የሚሰሩትን አስቂኝ ድርጊት ይወዳሉ?

መዝናኛ ሰዎችን የሚያቀራርብ ማህበራዊ ሙጫ ነው፡፡ አንድ ሰው በዓለም ረጅሙን የሰው ሰንሰለት ሲፈጥር በዚያ ውስጥ ያለው ስሜት የአንድነት እና የጋራ ስኬት ነው፡፡ ይህ በአእሯችን ውስጥ ኦክሲቶሲን የተባለውን የመተሳሰር ሆርሞን እንዲለቀቅ ያደርጋል፡፡

ሰው ተፈጥሮው አዲስ እና ያልተለመደ ነገር ሲያይ ይደሰታል፡፡ የጊነስ መዝገብ መዝናኛን ወደ ሳይንሳዊ ደረጃ ያሸጋግራል፤ ለምሳሌ “በዓለም እጅግ ፈጣኑ የቪዲዮ ጨዋታ ተጫዋች” ወይም “በጣም ረጅም ጊዜ የፈጀ የቲያትር ትርኢት” ሲል መዝናኛን ለዕውቅና እና ለብቃት መለኪያነት ይጠቀማሉ፡፡

በመዝናኛ ዘርፍ የተመዘገቡ አስገራሚ ክብረ ወሰኖች የሰው ልጅን የፈጠራ አድማስ ያሳያሉ፡፡

ለምሳሌ “በዓለም ረጅሙ ተከታታይ ፊልም” ወይም “በጣም ብዙ አሻንጉሊቶችን በአንድ ፊልም ውስጥ የተጠቀመ ፕሮዳክሽን” ሲባል መዝገቦች የጥበብን ዘላቂነት እና የቴክኒክ አቅምን ያሳያሉ፡፡

በዘንድሮው ዓመት በጨዋታዎች ላይ የተሰበሩ ክብረ ወሰኖች በጣም ብዙ ናቸው፡፡ አንድ ተጫዋች ለ72 ሰዓታት ያለምንም እረፍት የቪዲዮ ጨዋታ ሲጫወት ይህ ለአእምሮው ትልቅ ፈተና ነው፡፡ በነርቭ ሳይንስ ይህ ከፍተኛ የትኩረት ማሰባሰብ ሲሆን አእምሯችን ለረጅም ጊዜ በስክሪን ላይ ባለ መረጃ ላይ ሲያተኩር የሚፈጠረው የዶፓሚን መረጋጋት ለተጫዋቹ እርካታን ይሰጣል፡፡

ነገሮች ሁለት ገጽ አላቸው፡፡ ክብረ ወሰን መከተል በሳይንሳዊ እይታ ጥቅምና ጉዳት አለው፡፡ ክብረ ወሰን ለመስበር የሚደረግ ዝግጅት አእምሮን አዳዲስ ችሎታዎችን እንዲያዳብር ያስገድዳል፡፡ ይህ ሂደት አእምሮ አዳዲስ የነርቭ ግንኙነቶችን በመፍጠር አቅሙን እንዲጨምር ያደርጋል፡፡

መዝናኛ የጭንቀት ሆርሞን የሆነውን ኮርቲሶልን ይቀንሳል፡፡ አስቂኝ ክብረ ወሰኖችን ማየት ወይም መሳተፍ አንጎላችንን “ከባድ ከሚባሉ ጉዳዮች” ነፃ በማውጣት ለመዝናናት እድል ይሰጣል፡፡

ለጊነስ መዝገብ ለመድረስ አዳዲስ የመዝናኛ ስልቶችን መፍጠር የፈጠራ ችሎታን ያሳድጋል፡፡

ይሁን እንጂ ጉዳቶችም አሉት፡፡ አንዳንድ ክብረ ወሰኖች ሰውነትን ከሚችለው በላይ በመጫን ወደ ከባድ ጉዳት ይወስዳሉ፡፡ ለምሳሌ ከመጠን በላይ ክብደት ማንሳት በጡንቻ እና በአጥንት ስርዓት ላይ ዘላቂ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡

ስኬታማ ለመሆን በሚደረግ ከፍተኛ ፉክክር፣ ግለሰቦች ለጭንቀት እና ለራስ መተማመን መታወክ ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ ስኬቱ ሲሳካ የሚገኘው ደስታ የአጭር ጊዜ ሲሆን ብዙ ጊዜ “ከዚያ ቀጥሎስ ምን አለ?” የሚለው ጥያቄ ወደ ባዶነት ስሜት ሊመራ ይችላል፡፡

የመዝናኛ ክብረ ወሰኖች የሚሰጡት የደስታ ስሜት አጭር ነው፡፡ ተሳታፊው ሁልጊዜ “ከዚህ የበለጠ ማዝናናት አለብኝ” በሚል ስሜት ለሱስ ሊጋለጥ ይችላል፡፡

በዚህ ዘመን በብዛት የተሰበሩ ክብረ ወሰኖች ከቴክኖሎጂ ጋር በከፍተኛ ሁኔታ የተሳሰሩ ናቸው፡፡

አትሌቶች አሁን የራሳቸውን የአካል እና የአእምሮ መረጃ (ባዮሜትሪክስ) በመጠቀም አቅማቸውን በተሻለ መንገድ ማሳደግ ችለዋል፡፡ ለምሳሌ የእንቅልፍ ጥራት፣ የልብ ምት እና የአመጋገብ ስርዓት በዲጂታል መንገድ በመለካት አፈፃፀምን ማሻሻል ይቻላል፡፡

ሳይንሳዊ የአመጋገብ እና የፊዚዮሎጂ ጥናቶች በመጠቀም የሰው ልጅ ከዚህ በፊት የማይቻል መስሎ የታየውን ክብረ ወሰን ለመስበር እየቻለ ነው፡፡

ከቁጥሮች ባሻገር ሌላ እውነት አለ፡፡ የጊነስ የዓለም ክብረ ወሰኖች የሚያስተምሩን ዋናው ነገር ህይወት ከባድ ብቻ መሆን የለባትም የሚለውን ነው፡፡ መዝናኛ እና ጨዋታ የሰው ልጅ ባህል ዋና አካል ናቸው፡፡

የዓለም ክብረ ወሰኖች የሰው ልጅ የህልውና ጉዞ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በየዓመቱ የምንሰማቸው እነዚህ አስገራሚ ታሪኮች በሰውነታችን ውስጥ ያለውን የባዮሎጂካል አቅም እና በአእምሮአችን ውስጥ ያለውን የስነ-ልቦና ጥንካሬ የሚያንጸባርቁ ናቸው፡፡

ጥንካሬያችንን ለበጎ ነገር እና ለሰፊው የሰው ልጅ ጥቅም ስንጠቀምበት እያንዳንዱ የክብረ ወሰን መዝገብ ታሪክ ለዓለም አዲስ ተስፋን እና መነሳሳትን ይሰጣል፡፡

እያንዳንዱ ትልቅ ስኬት የሚጀምረው የራስን ድንበር ለመሻገር በሚደረግ የመጀመሪያ እርምጃ ነው፡፡ ነገር ግን ያ እርምጃ በሳይንሳዊ ግንዛቤ፣ በራስ መተማመን እና ለአእምሮ ጤና በሚሰጥ እንክብካቤ የተደገፈ መሆን አለበት፡፡ የዓለም ምርጥ ከመሆን በላይ የራስ ምርጥ መሆን ይበልጥ አስፈላጊ ነው፡፡

ፈረንጆች “ዘ ስካይ ኢዝ ዘ ሊሚት” እንደሚሉት የሰው ልጅ የማድረግ አቅም ወሰን አልባ ነው፡፡ በጥረቱ ልክ ነው፡፡።

  

ማረፊያ

አዳምና ጥበቡ

በመጀመሪያ አዳም ሳተ

ከገነትም ተጎተተ

አዳም ከገነት ሲባረር

እነሆ እርቃኑን ነበር

ብርዱ፣ ውርጩ አንዘፈዘፈው

ዶፉ፣ ጠሉ ወረደበት

ያንዠረገገውን አይተው

አእዋፍ አራዊት ሳቁበት

ይሄኔ አዳም ተማረረ

ተማረረና ተመራመረ

ተመራምሮም አልቀረ

ጋቢ መስራት ጀመረ

ጅማሬውን ወደደ

ተጀምሮ እስኪፈጠም

የእድሜውን ግማሽ ወሰደ

ያሳዝናል

ጋቢውን ጨርሶ ሲቋጭ

ገላው ብርዱን ለመደ::

ከበውቀቱ ስዩም

(አቢብ በዓለሜ)

በኲር የሐምሌ 6 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here