ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ? ክረምቱስ እንዴት ነው? ልጆች በክረምት ብዙ ጊዜ ስለሚከሰተው ቀስተ ደመና ሳይንሳዊ እውነት እንገራችሁ፡፡ ቀስተ ደመና ዝናብ ዘንቦ ልክ እንደጨረሰ ፀሐይ ስትወጣ በሰማይ ላይ የሚፈጠር እጅግ በጣም አስደናቂ፣ ማራኪ እና ባለብዙ ቀለም (የታጠፈ መስመር) ነው። ይህ ክስተት ተፈጥሮ በሰማይ ላይ በነፃ የምታሳየን ግዙፍ የስዕል ሥራ ሲሆን ለልጆች ሁልጊዜም ልዩ ደስታን፣ መደነቅን እና የማወቅ ጉጉትን ይፈጥራል።
የፀሐይ ብርሃን ለዓይናችን ዝም ብሎ ነጭ ወይም ቢጫ ቢመስልም በውስጡ ግን ሰባት የተለያዩ ቀለማትን አጣምሮ የያዘ ሚስጥራዊ ብርሃን ነው። ዝናብ ጥሎ በሚያባራበት ጊዜ ወይም ገና እያካፋ በሚገኝበት ወቅት በአየር ላይ የሚቀሩት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ትናንሽ የዝናብ ጠብታዎች ልክ እንደ አስማታዊ መስተዋት ያገለግላሉ። የፀሐይ ብርሃን በእነዚህ የዝናብ ጠብታዎች ውስጥ ገብቶ፤ አልፎ ሲወጣ ብርሃኑ ይጣመማል፤ ከዚያም ይበተንና በውስጡ የደበቃቸውን ውብ ቀለማት በግልጽ ለይቶ ሰፊ መስመር በመስራት ያሳየናል።
በዚህ አስደናቂ የተፈጥሮ ሳይንሳዊ ሂደት ምክንያት ቀስተ ደመና ሁልጊዜም ሳይቀያየሩ በአንድ ዓይነት የክብር ቅደም ተከተል የሚቀመጡ ሰባት ደማቅ ቀለማትን በውስጡ ይይዛል። እነዚህም ቀለማት ከላይ ወደ ታች በቅደም ተከተል ቀይ፣ ብርቱካናማ፣ ቢጫ፣ አረንጓዴ፣ ሰማያዊ፣ ኢንዲጎ ወይም ደማቅ ሰማያዊ እና ሐምራዊ በመሆን በሰማይ ላይ ተስማምተው ይሳላሉ። ቀስተ ደመና በውስጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቀለማት ያሉት ትልቅ እና አስማታዊ የቀለም ሳጥን ነው። ነገር ግን ከደማቅ ብርሃን የተሠራ ስለሆነ የእኛ ዓይን በቀላሉ መለየት የሚችለው ሰባቱን ዋና ዋና ደማቅ ቀለማት ብቻ ነው።
እኛም ይህንን ድንቅ የተፈጥሮ ትዕይንት ለማየት ሁልጊዜም ጀርባችንን ለፀሐይ ሰጥተን ፊታችንን ወደ ዝናቡ ማዞር ይኖርብናል። ቀስተ ደመና ምንም እንኳን ሰማዩን የነካ ግዙፍ ድልድይ ቢመስልም በዓይናችን የምናየው የብርሃን ነጸብራቅ እንጂ በእጃችን ልንነካው ወይም ሄደን ልንደርስበት የምንችል እውነተኛ አካል አይደለም። ልጆች ይህንን ውብ የቀለማት ሰንሰለት ሲመለከቱ ስለ ተፈጥሮ አስደናቂነትና ስለ ብርሃን ሳይንሳዊ ሚስጥር ይበልጥ እንዲረዱ፣ እንዲመራመሩ እና አእምሯቸው በፈጠራ እንዲሰፋ ያደርጋቸዋል ይላል የናሽናል ጂኦግራፊክ ሶሳይቲ መረጃ።
ተረት
የብርሃን ልዩ ጥንካሬ
በአንድ ወቅት፣ ጥቅጥቅ ባለ ጫካ ውስጥ የሚኖር ብርሃን የሚባል አንድ ትንሽ ወፍ ነበር። ብርሃን እንደ ሌሎቹ ወፎች መብረር አይችልም ነበር፤ ምክንያቱም አንደኛው ክንፉ በጣም አጭር ነበር።
ሌሎቹ ወፎች በሰማይ ላይ ሲምዘገዘጉ፤ እሱ ግን መሬት ላይ እየዘለለ ፍራፍሬዎችን ይለቅም ነበር። በዚህም ምክንያት ሁልጊዜ ያዝን ነበር።
አንድ ቀን፣ በጫካው ውስጥ ከባድ የንፋስና የዝናብ ማዕበል ተነሳ። ማዕበሉ በጣም የበረታ ከመሆኑ የተነሳ ትላልቅ ዛፎችን ሳይቀር ነቀላቸው። በሰማይ ላይ የነበሩት ወፎች በሙሉ ክንፋቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው መሬት ላይ ወደቁ። ሁሉም ተሸበሩ።
በዚህ ጊዜ፣ ብርሃን መሬት ላይ የመኖርና የመሮጥ ልምድ ስላለው ሳይፈራ ተነሳ። በዛፎች ስርና በድንጋዮች መካከል ያሉትን ትናንሽ ዋሻዎች ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። ወዲያውኑ እየሮጠ በመሄድ፤ የተጎዱትንና የፈሩትን ጓደኞቹን አንድ በአንድ እየመራ ወደ አስተማማኝ ዋሻዎች አስገባቸው።
ማዕበሉ ሲያበቃ፣ ጫካው እንደገና ጸጥ አለ። ወፎቹ በሙሉ ከከባድ አደጋ ስለተረፉ ብርሃንን ከበው አመሰገኑት። ከዚያ ቀን ጀምሮ፣ ብርሃን መብረር ባለመቻሉ ማዘኑን አቆመ። ምክንያቱም እያንዳንዱ ፍጡር የተፈጠረበት የራሱ የሆነ ልዩ ጥንካሬና ጥቅም እንዳለው ተረዳ።
ምንጭ፡- የቤንጋል ተረቶች
ሞክሩ
- ቀንና ሌሊት የሚሮጥ ግን ፈጽሞ የማይደክም ምንድነው?
- የዓለማችን ትልቁ ውቅያኖስ ማን ይባላል?
- ቡና ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በየትኛው የኢትዮጵያ አካባቢ ነው?
መልስ
- ሰዓት
- ፓሲፊክ (ሰላማዊ) ውቅያኖስ
- ከፋ (በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ)
ነገር በምሳሌ
አንድ ልጅን ለማሳደግ ሙሉ መንደር ያስፈልጋል- ማህበራዊ ኃላፊነትን እና የአብሮነትን ጥቅም ያሳያል (የናይጄሪያዊያን አባባል)።
-በዝግታ የሚጓዝ ሰው ሩቅ ይደርሳል፦ ትዕግስት እና ዘላቂ ጥረት ስኬትን እንደሚያመጡ ይገልጻል (የኬኒያዊያን አባባል)።
– ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም፦ ታላላቅ እና ውብ ነገሮችን ለመስራት ረጅም ጊዜ እና ትዕግስት ይጠይቃል (የጣሊያናዊያን አባባል)።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የሐምሌ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


