በማሳየቷ የተዘረፈችው

0
5

በማህበራዊ መገናኛዎች ሀብት፣ ንብረቷን ከሁሉም በላይ ጌጣጌጦችዋን በማሳየት የምትታወቀው ህንዳዊት ተፅእኖ ፈጣሪ በሰኔ ወር አጋማሽ ሌሊት ቤቷ ተሰብሮ መዘረፏን ኦዲቲ ሴጋትራል ድረ ገጽ ከሰሞኑ ለንባብ አብቅቶታል፡፡

ራችና ጉርጃር የተሰኘችው ጌጣጌጦችዋን እና ሌሎች ሀብቶችዋን “ዩቲዩብ”ን በመሰሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች በማሳየት ታዋቂ እና ተፅእኖ ፈጣሪ የሆነችው ህንዳዊት በማድያ ኘራዴሽ ሺቭፑሪ አውራጃ ቤተሰቡ በሙሉ ሌት በተኛበት መዘረፏን ተናግራለች፡፡

የዝርፊያው ሰለባ እንደተናገረችው ቤተሰቧ በሙሉ እንደተኙ የሽቦ አጥሩን ቆራርጠው ወደ ግቢው በመግባት የተኙበትን ቤት በላያቸው ላይ ቆልፈው ሀብት ንብረቷ  መውሰድ ችለዋል፡፡

ራችና ጉርጃር መዘረፏን ያወቀችው ጠዋት ከእንቅልፏ ነቅታ ለመውጣት ስትሞክር የቤቱ በር ከውጩ በመቆለፉ ነበር፡፡ በስልክ ከውጪ ጐረቤት ጠርታ ሲከፍቱላትም ውድ ጌጣጌጦቹ እና ሌሎች ሀብቶችዋ ተወስደዋል- የተረፉትም በየቦታው ተበታትነዋል፡፡

ከ800 – 1000 ”ዶላር” የሚያወጣ ጌጣጌጥ እና ገንዘብ መዘረፏን የተናገረችው ራችና ጉርጃር ዘራፊዎቹ በግቢ መቆጣጠሪያ የምስል መቅረጫ ካሜራ ማንነታቸው ተቀርፆ እንዳይለይ አቅጣጫውን መቀያየራቸውን አስረድታለች- ለፖሊስ፡፡

ምርመራውን የያዘው የፓሊስ ቡድንም ራችና ጉርጃር በቅርቡ በቤት ውሰጥ ጌጣጌጧ እና ገንዘቧ ተቀርፆ ለተከታዮቿ በማህበራዊ ድረ ገፆች መለቀቁ የዝርፊያ ኢላማ ሳያደርጋት እንዳልቀረ በቅድመ ግምት የክትትል መነሻ ማድረጉን  ድረ ገጹ  በማጠቃለያነት አስነብቧል፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር  የሐምሌ 6 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here