እግር ኳስን በታሪክ

0
70

በጥንታዊቷ ቻይና ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው እና በሦስተኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ የሀን ሥርወ መንግሥት ወታደሮች የአካል ብቃታቸውን ለማሳደግ “ሱጁ” የተባለ ጨዋታ ይጫወቱ ነበር። ይህ ጨዋታ ከቆዳ የተሠራ እና በላባ የተሞላ ኳስን በእግር እየመቱ መሬት ላይ በተተከሉ ሁለት የቀርከሃ ምሰሶዎች መካከል ወደተዘረጋ መረብ ማስገባትን ይጠይቅ ነበረ፤ ይህ በታሪክ የመጀመሪያው የእግር ኳስ ዓይነት ተደርጎ በፊፋ ዕውቅና ተሰጥቶታል። በተመሳሳይ መልኩ በጥንታዊቷ ግሪክ “ኤጲስኪሮስ” የተባለ እንዲሁም በሮማውያን ዘንድ “ሀርፓስተም” የሚባሉ የኳስ ጨዋታዎች ይዘወተሩ የነበረ ቢሆንም እነዚህ ጨዋታዎች እጅግ ኃይል የበዛባቸው፣ ሕግ የሌላቸው እና እጅን ጭምር ለመጠቀም የሚፈቅዱ ነበሩ።

ይህ የመዝናኛ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመካከለኛው ዘመን ወደ አውሮፓ በተለይም ወደ ብሪታንያ ደሴቶች ሲሻገር ይበልጥ ሕዝባዊ እና ሁከት የበዛበት መልክ ያዘ። በወቅቱ በጎረቤት መንደሮች እና ከተሞች መካከል የሚደረጉ ጨዋታዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያሳታፉ ነበሩ። ጨዋታው የተወሰነ የሜዳ ክልል፣ የሰው ቁጥር ገደብ ወይም ግልጽ ሕግ ስላልነበረው ከፍተኛ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት ያስከትል ነበር። በዚህም ምክንያት ንጉሥ ኤድዋርድ ሦስተኛን ጨምሮ በርካታ የእንግሊዝ ነገሥታት ጨዋታው ሰላምን ያደፈርሳል በሚል ፍርሃት ሙሉ በሙሉ አግደውት ነበር። ሆኖም ግን ሕዝቡ ለጨዋታው የነበረው ፍቅር እና ስሜት ጠንካራ በመሆኑ ጨዋታው በምስጢር እና በየገጠሩ መካሄዱን አላቋረጠም ነበር።

የዘመናዊው እግር ኳስ እውነተኛ መሠረት የተጣለው በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ በእንግሊዝ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ነበር። እንደ ኬምብሪጅ እና ኢተን ያሉ ታዋቂ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸውን በስነ-ስርዓት እና በቡድን ሥራ ለማነጽ ጨዋታውን በስፋት መጠቀም ጀመሩ። ሆኖም እያንዳንዱ ትምህርት ቤት የራሱ የተለየ ሕግ የነበረው መሆኑ (አንዳንዶቹ ኳስን በእጅ ይዞ መሮጥን ሲፈቅዱ፤ ሌሎቹ ደግሞ በእግር መምታትን ብቻ ይመርጡ ነበር) ትምህርት ቤቶቹ እርስ በርስ እንዳይወዳደሩ ትልቅ ማነቆ ሆነ። ይህንን ውዝግብ ለመፍታት እና ወጥ የሆነ የጋራ ሕግ ለማውጣት በ1863 እ.አ.አ የለንደን የእግር ኳስ ማኅበር (The FA) ተመሠረተ። በማኅበሩ አማካኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ በጽሑፍ የሰፈሩ ይፋዊ ሕጎች የወጡ ሲሆን ኳስን በእጅ ይዞ መሮጥ እና ተጫዋችን መጥለፍ ሙሉ በሙሉ ተከለከለ። ይህ የሕግ መለያየት በእግር ኳስ እና በራግቢ (ኃይል የተቀላቀለበት እግር ኳስ መሰል ጨዋታ) ስፖርት መካከል ግልጽ የድንበር መስመር ያሰመረ ነበር፤ ዛሬ ለምናውቀው ውብ እና ስልታዊ ጨዋታ መወለድ ዋነኛውን በር ከፈተ።

የሕጎቹ መውጣት እና ጨዋታው መደበኛ መልክ መያዝ ስፖርቱ በእንግሊዝ የኢንዱስትሪ ከተሞች ውስጥ በሠራተኛው መደብ ዘንድ በከፍተኛ ፍጥነት እንዲስፋፋ አደረገው። በ1872 እ.አ.አ በእንግሊዝ እና በስኮትላንድ መካከል የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ጨዋታ ተካሄደ።  በዚሁ ዘመን የዓለማችን ጥንታዊው የዋንጫ ውድድር የሆነው የኤፍኤ ካፕ (FA Cup) ተጀመረ። የእንግሊዝ መርከበኞች፣ ነጋዴዎች እና መሐንዲሶች ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሲጓዙ ጨዋታውን ይዘውት መሄድ ጀመሩ። በዚህም ምክንያት ስፖርቱ በአውሮፓ፣ በደቡብ አሜሪካ እና በአፍሪካ አህጉራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተወዳጅነትን አተረፈ። የጨዋታው ዓለም አቀፋዊ ዕድገት እጅግ ፈጣን ከመሆኑ የተነሳ ሁሉንም ሀገራት የሚያስተባብር አንድ የበላይ አካል መኖሩ ግድ ሆነ።

በ1904 እ.አ.አ ሰባት የአውሮፓ ሀገራትን በማስተባበር ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) በፓሪስ ከተማ ተመሠረተ። ፊፋ ከተመሠረተ በኋላ ስፖርቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትልልቅ ሥራዎችን የሠራ ሲሆን በፈረንሳዊው ዡልስ ሪሜ መሪነት በ1930 እ.አ.አ የመጀመሪያውን የዓለም ዋንጫ ውድድር በኡራጓይ አስተናጋጅነት በድምቀት አካሄደ። የዓለም ዋንጫው መጀመር ሀገራት የራሳቸውን ብሔራዊ ማንነት እና ክብር በስፖርቱ መድረክ ላይ የሚያሳዩበት ታላቅ አጋጣሚን ፈጠረ። በተለይም የደቡብ አሜሪካ ሀገራት እንደ ብራዚል እና አርጀንቲና ያሉ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታውን ወደ ጥበብ እና ውበት በመቀየር የዓለምን ትኩረት መሳብ ቻሉ።

በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ እና ማጠናቀቂያ ላይ እግር ኳስ በከፍተኛ የቴክኖሎጂ እና የኮሙኒኬሽን ዕድገት ውስጥ አልፏል። የቴሌቪዥን ስርጭት መጀመር ጨዋታዎችን በቀጥታ ወደ ቢሊዮኖች መኖሪያ ቤት ያደረሰ ሲሆን ይህም ለክለቦች እና ለተጫዋቾች ከፍተኛ የገቢ ምንጭ እና ታዋቂነትን አመጣ። እንደ ፔሌ፣ ዲዬጎ ማራዶና እና በቅርብ ጊዜ ደግሞ እንደ ሊዮኔል ሜሲ እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ ያሉ ተጫዋቾች ከስፖርተኝነት ባለፈ የዓለም አቀፍ ባህል ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ለመሆን በቅተዋል። ጨዋታው ከወንዶች ባሻገር በሴቶች ዘንድም በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ  መጥቷል። የሴቶች የዓለም ዋንጫም የራሱን ትልቅ ታዳሚ ማፍራት ችሏል።

የዓለም ዋንጫ ታሪክ በስፖርታዊ ድራማዎች፣ ባልተጠበቁ ድሎች፣ በፖለቲካዊ ተጽዕኖዎች እና በዓለም አቀፍ ቀውሶች የተሞላ እጅግ ማራኪ ጉዞ  ያለው ነው። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መፈንዳት ምክንያት የ1942 እና የ1946 እ.አ.አ የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ሙሉ በሙሉ ተሰርዘው ነበር። በእነዚህ የጦርነት ዓመታት ውስጥ በርካታ የስፖርት መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፤ የፊፋ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ኦቶሪኖ ባራሲ የወርቅ ዋንጫውን ናዚዎች እንዳይሰርቁት በጫማ ሳጥን ውስጥ ደብቀው ከአልጋቸው ሥር በማስቀመጥ እስከ ጦርነቱ ማክተሚያ ድረስ በሰላም ጠብቀውታል። ከጦርነቱ በኋላ ውድድሩ በ1950 እ.አ.አ በብራዚል አስተናጋጅነት በድጋሚ ሲጀምር በርካታ ሀገራት በጦርነቱ በደረሰባቸው ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ ምክንያት ሳይሳተፉ ቀርተዋል።

በውድድሩ ታሪክ ውስጥ የተመዘገቡ ሌሎች አስደናቂ እውነታዎች እና ታሪካዊ አጋጣሚዎችም ጨዋታውን ይበልጥ ማራኪ ያደርጉታል። ለምሳሌ ብራዚል እስካሁን የተካሄዱትን ሁሉንም የዓለም ዋንጫ ውድድሮች በመሳተፍ እና አምስት ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ብቸኛዋ ሀገር በመሆን ትመራለች። በግል ተጫዋቾች ታሪክ ውስጥ ደግሞ አርጀንቲናዊው አጥቂ ሊዬኔል ሜሲ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ላይ 21 ግቦችን በማስቆጠር የዘመናት ከፍተኛ ግብ አግቢነት ክብርን ይዟል። በሌላ በኩል በአንድ ጨዋታ ላይ ከፍተኛ ግብ በማስቆጠር የሚታወቀው ሩሲያዊው ኦሌግ ሳሌንኮ ሲሆን እሱም በ1994 እ.አ.አ በካሜሩን ላይ በአንድ ጨዋታ ብቻ አምስት ግቦችን አስቆጥሮ ታሪክ ሰርቷል። እንዲሁም በዓለም ዋንጫ ታሪክ ፈጣኑ ግብ የተመዘገበው በ2002 እ.አ.አ በቱርኩ አጥቂ ሀካን ሹኩር ሲሆን እሱም ጨዋታው በጀመረ በ11ኛው ሰከንድ ላይ በደቡብ ኮሪያ መረብ ላይ ግብ አሳርፏል።

በቅርብ ጊዜ ከተመዘገቡት ታሪካዊ ክስተቶች መካከል ደግሞ በ2022 እ.አ.አ በኳታር የተካሄደው ውድድር ይጠቀሳል። ይህ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በመካከለኛው ምስራቅ እና በክረምት ወራት የተካሄደ ሲሆን ሞሮኮ እስከ ግማሽ ፍጻሜ በመጓዝ የመጀመሪያዋ የአፍሪካ እና የአረብ ሀገር በመሆን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ጽፋለች። እንዲሁም ሊዮኔል ሜሲ አርጀንቲናን መርቶ ዋንጫውን በማንሳት የእግር ኳስ ታሪኩን ፍጹም ያደረገበት እና በውድድሩ ታሪክ ብዙ ጨዋታዎችን (26 ጨዋታዎችን) የተጫወተ ቀዳሚ ተጫዋች የሆነበት አጋጣሚ ነበር።

በእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ከአንድ በላይ ለሆኑ ብሔራዊ ቡድኖች የተጫወቱ በርካታ ታዋቂ ተጫዋቾች አሉ። በጥንቱ ዘመን የፊፋ ሕግ ጥብቅ ስላልነበረ ተጫዋቾች ሃገር ቀይረው መጫወት የሚችሉ ሲሆን፣ በአሁኑ ዘመን ግን ሕጉ የተቀየረው በወዳጅነት ጨዋታዎች ላይ ብቻ ለተሳተፉ ወይም የተወሰነ መስፈርት ላሟሉ ተጫዋቾች ብቻ ነው። ለአብነት አልፍሬዶ ዲ ስቴፋኖ (አርጀንቲና እና ስፔን)፣ ዲዬጎ ኮስታ (ብራዚል እና ስፔን)፣ ዊልፍሬድ ዛሃ (እንግሊዝ እና አይቮሪ ኮስት) እና ዴክላን ራይስ (አየርላንድ እና እንግሊዝ) ለሁለት ሃገራት በተለያየ ጊዜ የተጫወቱ ናቸው፡፡

ዛሬ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እግር ኳስ ከቀላል ስፖርታዊ እንቅስቃሴነት ተሻግሮ የቪዲዮ ረዳት ዳኝነትን (VAR) ጨምሮ በዘመናዊ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የታገዘ፣ እጅግ ግዙፍ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ያለው ዓለም አቀፋዊ ክስተት ሆኗል። ጨዋታው የተለያየ ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት እና የፖለቲካ አመለካከት ያላቸውን ሕዝቦች በአንድ ስታዲየም ውስጥ በአንድ ስሜት እና ፍቅር ማሰባሰብ የሚችል ብቸኛው የምድራችን ታላቅ ስፖርት በመሆን የታሪክ ምዕራፉን እየቀጠለ ይገኛል።

ምንጭ፡- የፊፋ ይፋዊ ድረ ገጽ፣ ብሪታኒካ እና ኦፒቲኤ ስፖርትስ።

ሳምንቱ በታሪክ

የመጀመሪያው ሕገ መንግሥት

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘመናዊ የተጻፈ ሕገ መንግሥት በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ አማካኝነት ሐምሌ 9 ቀን 1923 ዓ.ም ጸደቀ። ይህ ሰነድ ሀገሪቱ ለዘመናት ትመራበት የነበረውን የፍትሐ ነገሥት ሕግ ተክቷል።

ሕገ መንግሥቱን ያረቀቁት በሩሲያ የተማሩት በጅሮንድ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም ሲሆኑ ለዝግጅቱም የእንግሊዝ እና የጃፓን ሕገ መንግሥቶች በምሳሌነት አገልግለዋል። ይህ ሕግ በሰባት ምዕራፎችና 55 አንቀጾች የተዋቀረ ነው፡፡ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሕግ መወሰኛ እና የሕግ መምሪያ ምክር ቤቶችን አቋቁሟል።

ሆኖም ሕጉ ለዘውዳዊው ሥርዓት ያደላ እና ለንጉሠ ነገሥቱ ፍጹም የበላይ ሥልጣን የሰጠ ነበር። የንጉሡም የሥልጣን መስመር ከንጉሥ ሰሎሞን እና ከንግሥተ ሳባ እንደሚመዘዝ ደንግጓል።

ዋና ዓላማው የመሳፍንትን ኃይል በመቀነስ ማዕከላዊ መንግሥትን ማጠናከር እና ኢትዮጵያ በሕግ የምትመራ ሥልጡን ሀገር መሆኗን ለዓለም ማሳየት ነበር።

የዲሞክራሲ መብቶችን ሙሉ በሙሉ ባያከብርም ሀገሪቱ ወደ ዘመናዊ የመንግሥት መዋቅር እንድትሸጋገር መሠረት ጥሏል። በኋላም በ1948 ዓ.ም በተሻሻለው ሕገ መንግሥት ተተክቷል።

ምንጭ፡- “የሕይወቴ ታሪክ”፡- ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የሐምሌ 6 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here