ባለ ሁለት መልክ ተፅዕኖ

0
52

የዓለም የሚቲዎሮሎጂ  ድርጅት (WMO) እንዳስታወቀው በዓለም የሙቀት መጠን በየዓመቱ እየተባባሰ በመምጣቱ የመንግሥታት የጤና በጀት እና የአደጋ ምላሽ ወጪ እየጨመረ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የምዕራብ አማራ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል በዘንድሮው የክረምት ወቅት ሊከሰት የሚችለውን የኢሊኖ የአየር ንብረት መዛባት ተጽዕኖ አስቀድሞ ለመቀነስ የሚያስችል ሰሞኑን በባሕር ዳር ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

የማዕከሉ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሲሳይ ቀለሙ በሰጡት ማብራሪያ የዘንድሮው ክረምት በኢሊኖ ተጽዕኖ ስር እንደሚሆን ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ (የኢጋድ) እና ሀገራዊ የትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ። ኢሊኖ በምሥራቅ እና መካከለኛው የፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ የሚከሰት የሙቀት መጠን መጨመር ሲሆን ይህ ክስተት በሀገራችን የክረምት ዝናብን ከመቀነሱም ባሻገር እጅግ ተለዋዋጭ የሆኑ የአየር ጠባይ መዛባቶችን ያስከትላል ብለዋል። በዚህም ምክንያት በአንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ ድርቅ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ነው ያብራሩት። ይህንን የተፈጥሮ አደጋ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባይቻልም በሕይወት እና በንብረት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት በቅድመ ማስጠንቀቂያና ዝግጅት መቀነስ እንደሚቻል አቶ ሲሳይ አስታውቀዋል።

ማዕከሉ ባደረገው እንቅስቃሴ  በምዕራብ አማራ ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ተለይተዋል። በዚህም በሰሜን ጎንደር በየዳ፣ ጃናሞራ እና ጠለምት  እንዲሁም በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደጀን እና አዋበልን ጨምሮ በአጠቃላይ የዓባይ ሸለቆ ተፋሰስ አካባቢዎች የዝናብ እጥረት (ድርቅ) ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ጥናቱን ዋቢ አድርገው አቶ ሲሳይ  አስገንዝበዋል። በሌላ በኩል እንደ ባሕር ዳር ዙሪያ፣ ፎገራ፣ አዲስ ዘመን እንዲሁም የጣና እና የዓባይ ተፋሰስ አካባቢዎች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ መሆናቸው ተለይቷል ነው ያሉት።

በተያዘው የምርት ወቅት(2018/19) የተደቀነውን ስጋት ለመቋቋም በግብርናው ዘርፍ ላይ ልዩ ትኩረት መደረግ እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡ የዝናብ እጥረት በሚኖርባቸው አካባቢዎችም አርሶ አደሮች የዝናብ ውኃን ማሰባሰብ፣ በአጭር ጊዜ ሊደርሱ የሚችሉ የሰብል ዝርያዎችን መጠቀም እንዲሁም የሳር ግጦሽ እጥረት ስለሚያጋጥም አስቀድሞ የእንስሳት መኖን ማዘጋጀት እንደሚገባቸው ጥሪ ቀርቧል። ሌላው  ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ደግሞ የውኃ መውረጃ ቦዮችን (ዲቾችን) በማጽዳት እና በማስተካከል አደጋን መከላከል እንደሚቻል ተመላክቷል።

ተቋሙ የትንበያ መረጃዎችን በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ፣ በድረ-ገጽ እና በቴሌግራም በየጊዜው እያሰራጨ ቢሆንም በሕብረተሰቡ ዘንድ ያለው መረጃን የመጠቀም ባህል ገና በበቂ ሁኔታ ስላላደገ በአካል በመውረድ ከማሕበረሰቡ ጋር እየሠራ ይገኛል። ለአብነትም በሰሜን ጎንደር ዞን ከሚገኙ አሥተዳደሮች ጋር በመቀናጀት ልዩ ግብረ-ኀይል ተዋቅሮ ወደ ሥራ መገባቱ ተገልጿል።

ሕብረተሰቡ የየዕለቱን፣ በየሦስት እና የአስር ቀናት፣ የወሩን እና የወቅቱን የአየር ጠባይ ትንበያ መረጃዎችን በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ድረ-ገጽ ወይም የምዕራብ አማራ ማዕከልን የቴሌግራም ገጽ በመከታተል እንዲሁም በስልክ በመደወል መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት እንደሚችል አቶ ሲሳይ  አመላክተዋል።

በዘንድሮው የምርት ዘመን ሊከሰት ይችላል ተብሎ የተተነበየውን የአየር ፀባይ መዛባት ተፅዕኖ እና የዝናብ እጥረት ለመቋቋም በሰሜን ጎንደር ዞን ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

የመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ጥላሁን ዓለምነህ በተለይም ከሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የተሰጠውን መረጃ ጠቅሰው ለበኩር  እንደገለጹት በዘንድሮው ዓመት  የኢሊኖ ክስተት ሊኖር እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ አርሶ አደሩን ከጉዳት ለመታደግ የሚያስችሉ ሥራዎች በመሠራት ላይ ይገኛሉ። ችግሩ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ አስቀድሞ ለመከላከል በደባርቅ ከተማ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር መካሄዱን የገለጹት አቶ ጥላሁን፤ ግብርና መምሪያውን ጨምሮ  አይ በግሬ (Resilience) ከተሰኘው የስሜን ጎንደር ፕሮጀክት እና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት ልዩ ግብረ ኀይል ተዋቅሮ ወደ ተግባር መገባቱን አብራርተዋል።

ባለሙያው አክለውም እስካሁን ባለው ምልከታ በዞኑ ውስጥ ከሚገኙ 202 ቀበሌዎች መካከል በ93ቱ  ምንም ዓይነት ዝናብ እንዳልዘነበ ገልጸዋል። ቀሪዎቹ ቀበሌዎችም ቢሆን ከሁለት ቀን በላይ ዝናብ ያላገኙ በመሆናቸው አጠቃላይ ሁኔታው የዝናብ እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችል ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል። የተጋረጠውን የድርቅ ስጋት ለመቀልበስ ግብረ ኀይሉ ማሳው ድረስ በመሄድ ከአርሶ አደሩ ጋር እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

“ድርቁ ይበልጥ ቢከሰት እና የተዘራው ሰብል ቢበላሽ የምትተኩበት የግብዓት ዝግጅት ምን ይመስላል?” ተብሎ ለአቶ ጥላሁን ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “ዕቅዱ ሙሉ በሙሉ ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል። ጉዳት ቢደርስ እንኳን አርሶ አደሩ በድጋሚ መዝራት የሚችልባቸውን የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘርን የመሳሰሉ ግብዓቶችን ለማቅረብ ጥያቄው ተደራጅቶ ወደ ክልሉ ግብርና ቢሮ ተልኳል፤” ብለዋል። በቀጣይም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ የግብርና ተቋማትን እና አርሶ አደሩን በማስተባበር ሊመጣ የሚችለውን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለማለፍ ሌት ተቀን ጥረት እየተደረገ መሆኑን የሰብል ልማት ባለሙያው አረጋግጠዋል። በተመሳሳይ በዘንድሮው የክረምት ወቅት ሊከሰት የሚችለውን  የጎርፍም ሆነ የዝናብ እጥረት (ድርቅ) አደጋ ለመቀነስ የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ገልጿል።

የመምሪያው የሰብል ልማት ጥበቃ ባለሙያ አቶ ሙሌ ክንዴ ለበኩር ዝግጅት ክፍል እንደገለጹት በዞኑ የሚገኙ  የተወሰኑ  ወረዳዎች በጎርፍ ሌሎች ደግሞ በዝናብ እጥረት ተደጋጋሚ ተጽዕኖ ይደርስባቸዋል። ይህንን ታሳቢ በማድረግም መምሪያው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ ይገኛል ብለዋል። በዞኑ በጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ከሚባሉት አካባቢዎች መካከል የፎገራ እና የሊቦ ከምከም ወረዳዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ።

አቶ ሙሌ እንዳብራሩት “እነዚህን የጎርፍ አደጋ ስጋቶች ለመቀነስ ከቅድመ ማስጠንቀቂያ አካላት ጋር በጋራ እየሠራን እንገኛለን። እስካሁንም ስጋት ላለባቸው ወረዳዎች መረጃዎችን በማድረስ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እንዲሠሩ እየተደረገ ነው” ብለዋል። በተግባርም ማሕበረሰቡን የማንቃት እና የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን የማሰራጨት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በደቡብ ጎንደር ዞን የአንዳንድ አካባቢዎች አቀማመጥ እና የአየር ንብረት ጠባይ ለዝናብ እጥረት ተጋላጭ ያደርጋቸዋል። እንደ እብናት፣ መቀጠዋ እና ላይ ጋይንት (በተለይም ወደ በረሃማው አካባቢ ያሉ) ወረዳዎች ላይ እስካሁን ባለው መረጃ ዝናብ በሚገባ አለመጀመሩን ባለሙያው ገልጸዋል። “በእነዚህ የዝናብ እጥረት ሊያጋጥማቸው በሚችሉ ወረዳዎች ላይም ከቅድመ ማስጠንቀቂያ ክፍል ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን ክትትል እያደረግን ነው” ያሉት አቶ ሙሌ፤ አርሶ አደሩም ሆነ የሚመለከተው አካል ሁኔታውን ተገንዝቦ አማራጭ እርምጃዎችን እንዲወስድ መረጃ የመለዋወጥ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ዘንድሮ በሚኖረው (የኢሊኖ) የአየር ጠባይ መዛባት ምክንያት በአማራ ክልል ድርቅ ሊከሰትባቸው በሚችሉ አካባቢዎች የቅድመ ጥንቃቄ እና የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገልጿል። በኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ባለሙያ  አቶ መልካሙ ጫኔ ለበኩር እንደገለጹት ምንም እንኳን በክረምቱ ወቅት የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ሊከሰቱ ቢችሉም የዘንድሮው ዋነኛ ስጋት ከኢሊኖ ጋር ተያይዞ ሊመጣ የሚችለው የድርቅ አደጋ ነው። ከብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ከተሰጠው ትንበያ ጋር በማስተሳሰር በተደረገ ልየታም በክልሉ 51 ወረዳዎች ላይ የድርቅ ስጋት እንዳለ ታውቋል። ይህንን ተከትሎም የድርቅ መከላከያ እና መጠባበቂያ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ታችኛው መዋቅር እንዲወርድ መደረጉን ባለሙያው ተናግረዋል።

“ማሕበረሰቡ ድርቁ ከመከሰቱ በፊት  ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተሠሩ ነው” ያሉት አቶ መልካሙ፤ ችግሩ በግብርናው ዘርፍ ላይ ብቻ ሳይሆን በጤና፣ በትምህርት፣ በውኃ እና በእንስሳት ሀብት ላይ ጭምር ዘርፈ ብዙ ጫና ሊያሳድር ስለሚችል ተቋማት  የየራሳቸውን የቅድመ ዝግጅት ዕቅድ አውጥተው በጋራ እየሠሩ መሆኑንም አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ ክትትል የሚያደርግበትን ሳምንታዊ እና ወርሃዊ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሪፖርት ዋቢ በማድረግ አቶ መልካሙ እንደገለጹት፤ የተተነበየው የድርቅ ስጋት እውን እየሆነ መምጣቱን የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ። “በሰኔ ወር ሦስተኛ ሳምንት ሪፖርት መሰረት ክትትል ከተደረገባቸው በ151ዱ ወረዳዎች ውስጥ በ101ዱ  ዝናብ አላገኙም። ይህም ድርቁ በተጨባጭ ሊከሰት እንደሚችል አመላካች ነው” ብለዋል።

በዚህም ምክንያት ሊያጋጥም የሚችለውን የምርት መቀነስ ስጋት ለመቋቋም በግብርናው ዘርፍ በኩል ትልቅ ሥራ እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል። በተለይም ዝናብ አቋርጦ አርሶ አደሩ ዘሩን መልሶ መዝራት (ገልብጦ ማረስ) ቢያስፈልገው ቶሎ ሊደርሱ የሚችሉ እና ድርቅን የሚቋቋሙ የምርጥ ዘር ዝርያዎችን እንዲሁም የማዳበሪያ አቅርቦትን የማሟላት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም አቶ መልካሙ አብራርተዋል፡፡

ዜና

ጥራታቸዉ ያልተረጋገጠ የግብርና ግብዓቶች ወደ አርሶ አደሩ እንዳይገቡ  ቁጥጥር እየተደረገ ነው

ከደረጃ በታች የሆኑ እና  ሕገ-ወጥ የግብርና ግብዓቶች ወደ አርሶ አደሩ እንዳይገቡ ጥብቅ ቁጥጥር መደረጉ ተገለጸ

የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ወሳኝ ሚና ያላቸውን የግብርና ግብዓቶች ጥራት ለማስጠበቅ ሰፊ ሥራዎች መሠራታቸውን የግብርና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታውቋል።  በዚህም 10 ሺህ 814 ሄክታር የዘር ብዜት ማሳ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ተደርጓል።

የዘር እና ችግኝ ጥራት ቁጥጥርን በተመለከተ ከዚህ ቀደም የነበሩ የአሰራር ክፍተቶችን በማረም በዚህ ዓመት ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን ነዉ የአማራ ክልል የግብርና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ኃላፊ አቶ ፈንታሁን ስጦታዉ ለበኩር የተናገሩት። ጥራቱ ያልተረጋገጠ ምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያ ለአረሶ አደሩ እንዳይሰራጭ ጥብቅ ቁጥጥር መደረጉን ነው ያብራሩት፡፡

በተለይም የዘር ጥራት ተቆጣጣሪዎች ወደ አርሶ አደሩ ማሳ በመውረድ በጂፒኤስ (GPS) እና በዳታ ቤዝ የታገዘ የጥራት ቁጥጥር ማድረጋቸው እንደ ትልቅ ስኬት ተነስቷል። በአጠቃላይ በማሳ እና በላቦራቶሪ የዘር ጥራትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ፍተሻ መደረጉን ተናግረዋል።   በተጨማሪም በፍራፍሬ ችግኝ ልማት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ የተሠራ  መሆኑን የገለጹት አቶ ፈንታሁን 866 ሚሊዮን የሚሆኑ ችግኞች የጥራት ቁጥጥር ተደርጎባቸዉ ለተከላ መዘጋጀታቸዉን አስታዉቀዋል።

ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትዉዉቅ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል፡፡

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የሐምሌ 6 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here