“ዲጂታል ዲቶክስ”

0
56

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አእምሮአችን እንደ አሁኑ ዘመን ከፍተኛ የሆነ የመረጃ ጫና ደርሶበት አያውቅም፡፡ ስማርት ስልኮች፣ የማህበራዊ ሚዲያ አልጎሪዝሞች እና የማያቋርጥ የዲጂታል ግንኙነት የአኗኗር ዘይቤያችንን  ቀይረውታል፡፡

ይህን ተከትሎ ደግሞ ለአእምሮ ጤንነታችን አስጊ የሆኑ የጎንዮሽ ጉዳቶች መጥተዋል፡፡ “ዲጂታል ዲቶክስ” ወይም ከዲጂታል መሳሪያዎች እረፍት መውሰድ እንደ አስፈላጊ የህይወት ክህሎት እና የአእምሮ ንፅህና መጠበቂያ ስልት እየታየ ነው።

የዲጂታል መድረኮች አሠራር በአጋጣሚ የተፈጠረ አይደለም፡፡ እነዚህ መድረኮች የተገነቡት የስነ-ልቦናዊ መሳቢያዎችን በመጠቀም ነው፡፡

ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የምንለጥፈው ነገር የሚሰበስበው “ላይክ”፣ “ኮሜንት” ወይም “ሼር” በአእምሮአችን ኒውክሊየስ አኩምበንስ በተባለ የሽልማት ማዕከል ውስጥ ዶፓሚን እንዲለቀቅ ያደርጋል፡፡

ይህ የኬሚካል ፍሰት የአጭር ጊዜ ደስታን ቢሰጥም አእምሮአችን ለተመሳሳይ የደስታ መጠን ደጋግመን ተመሳሳይ ድርጊት እንድንፈጽም ይገፋፋናል፡፡

ካል ኒውፖርት በ“ዲጂታል ሚኒማሊዝም” መጽሐፋቸው ላይ እንደሚሉት እነዚህ መድረኮች የተነደፉት ተጠቃሚዎችን በሱስ መልክ እንዲቆዩ በማድረግ ትኩረታችንን እንደ ሸቀጥ በመሸጥ ነው፡፡

በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ እና በሌሎች የምርምር ማዕከላት እንደተረጋገጠው የማያቋርጥ የዲጂታል መሳሪያዎች አጠቃቀም የአንጎልን የፊተኛው ክፍል ሥራ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡ ይህ የአእምሮ ክፍል ለውሳኔ አሰጣጥ፣ ለስሜት ቁጥጥር እና ለትኩረት ኀላፊነት አለበት፡፡

ያለማቋረጥ ተደራራቢ ሥራዎችን መሥራት ወይም ስልክን እያዩ ሌላ ነገር ማድረግ ይህንን የአእምሮ ክፍል ያደክመዋል፤ ውጤቱም የማስታወስ ችሎታ መቀነስ እና በቀላሉ የመረበሽ ስሜት ነው፡፡

አእምሯችን መረጃን በሚያጣራበት ወቅት የሚፈጠረው የትኩረት መከፋፈል በጥልቅ የማሰብ ችሎታችን ላይ ክፍተት ይፈጥራል፡፡

ማይክሮሶፍት ኩባንያ ባደረገው ጥናት መሠረት የዲጂታል መሳሪያዎች መብዛት የሰው ልጅ የትኩረት ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ አድርጓል፡፡

ያለማቋረጥ የኢሜይል፣ የቲክቶክ፣ የፌስቡክ ማሳዎቂያዎች ሲመጡ አእምሮአችን ለአደጋ የተዘጋጀ (መግጠም ወይም መሸሽ) አይነት ሁኔታ ውስጥ ይቆያል፡፡

ይህም በሰውነት ውስጥ ኮርቲሶል የተባለው የጭንቀት ሆርሞን እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ ይህ ሆርሞን ለረጅም ጊዜ ከፍ ባለ ቁጥር ሥር የሰደደ የጭንቀት ስሜት ይፈጥራል፡፡

በሊዮን ፌስቲንገር የተዘጋጀው የማህበራዊ ንጽጽር ስነ-ልቦና ጽንሰ-ሀሳብ እንደሚያስረዳው ሰዎች ራሳቸውን ከሌሎች ጋር የማነፃፀር ተፈጥሯዊ ዝንባሌ አላቸው፡፡ የማህበራዊ ሚዲያ ደግሞ የሌሎችን ህይወት “የተመረጡ እና የተዋቡ” ጊዜያትን ብቻ ስለሚያሳይ ተመልካቾች የራሳቸውን ህይወት ዝቅ አድርገው እንዲመለከቱ እና ለድብርት እንዲጋለጡ ያደርጋል፡፡

በተለይም በወጣቶች ላይ የሚታየው የራስን ምስል የመጥላት ስሜት ከማህበራዊ ሚዲያ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡

በስክሪኖች የሚለቀቀው አጭር የሞገድ ርዝመት ያለው ሰማያዊ ብርሃን በሰውነታችን ውስጥ የሚገኘውን የሜላቶኒን ሆርሞን በማፈን የእንቅልፍ ዑደታችንን ያዛባል፡፡ የእንቅልፍ መዛባት የስነልቦና ተጽዕኖዎች አሉት፤ ይህም ብስጭትን፣ የትኩረት ማጣት እና የስሜት መለዋወጥን ያስከትላል፡፡

ዲጂታል ዲቶክስ ማለት ስልክን ማጥፋት ብቻ አይደለም፤ ከአእምሮ ጋር ዳግም መገናኘት ነው፡፡

ወደ ጥልቅ አስተሳሰብ መመለስ ነው፡፡ ካል ኒውፖርት እንደሚገልጹት ከዲጂታል ትኩረት መከፋፈል ሲንወጣ አእምሮ ረጅም እና ውስብስብ የሆኑ ስራዎችን የመሥራት ችሎታውን መልሶ ያገኛል፡፡ ይህ ለአእምሮ እድገት እና ለሙያዊ ልህቀት ወሳኝ ነው፡፡

የሥሜት ብልህነት ማደግ ይጀምራል፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የምንሰጣቸው ምላሾች የሰከኑ አይደሉም፡፡ ከዲጂታል ዓለም መራቅ ግን ስሜታችንን በስርዐት የመረዳት እና በእውነተኛ ግንኙነቶች ውስጥ የሰውን ፊት፣ ድምፅ እና ስሜት የማንበብ ችሎታችንን ያሳድጋል፡፡ የፊት ለፊት ግንኙነት የሰው ልጅን ስሜታዊ የመተሳሰብ ችሎታ ያዳብራል፡፡

የፈጠራ ሥራ መነቃቃት ይጀምራል፡፡ አእምሮአችን በቂ እረፍት ሲያገኝ ነባሪ ሁኔታ (ዲፎልት ሞድ ኔትወርክ) የሚባል ክፍል ይነቃል፡፡ ይህ ክፍል ለህልም አላሚነት፣ ለፈጠራ ሀሳቦች እና ለራስ ግምገማ ዋና ምንጭ ነው፡፡

ስልካችን ላይ በተጠመድን ቁጥር ይህ የፈጠራ ማእከል እንዲተኛ እናደርገዋለን፡፡ ከቴክኖሎጂ እረፍት መውሰድ አእምሮአችን አዳዲስ መፍትሄዎችን እና ሀሳቦችን እንዲፈልግ እድል ይሰጠዋል፡፡

አሁን ይህን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምንችል እንመልከት፡፡

  1. የጠዋት እና የሌሊት ዲቶክስ ወሳኝ ነው፡፡

ከመተኛትዎ አንድ ሰዓት በፊት እና ከእንቅልፍዎ ከተነሱ በኋላ ባለው የመጀመሪያ ሰዓት ስልክ አይንኩ፡፡ ይህ አእምሮዎ ቀኑን በሰላም እንዲጀምር እና እንዲጨርስ ይረዳል፡፡ ስልክዎን ወደ መኝታ ቤት አለመውሰድ የጠዋት ምርታማነትን በ20 በመቶ እንደሚያሳድግ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

  1. የአካባቢ ቁጥጥር ቀጥሎ የሚመጣው መፍትሔ ነው፡፡

ስልኩን በእንቅልፍ ጊዜ ከመኝታ ክፍል ውጪ ያድርጉት፡፡ ሳይንሱ እንደሚነግረን ስልክ በአቅራቢያችን መኖሩ ብቻ እንኳን ትኩረታችንን በእጅጉ ይከፋፍለዋል፡፡ የዲጂታል መሳሪያዎች በአይን እይታ ውስጥ መኖራቸው ጠቃሚ ነገር ያመለጠን ያህል እንዲሰማን ያደርጋል፡፡ ያም ወደ ስልካችን እንድንሄድ ያደርገናል፡፡

  1. የአልጎሪዝም ማጽዳት አስፈላጊ ነው፡፡

የማይጠቅሙ፣ የሚያስጨንቁ ወይም የማያነሳሱ ገጾችን አይከተሉ፡፡ ዲጂታል አካባቢዎን ለርስዎ ጥቅም ብቻ እንዲቆም ያድርጉ፡፡ ያስታውሱ የሚከተሉት ሰዎች ወይም ገጾች የአእምሮ ንፅህናዎን የሚወስኑት ናቸው፡፡

  1. ጥንቃቄ የተሞላበት አጠቃቀም ያድርጉ፡፡

ስልክ ሲከፍቱ “ለምን ይህን አያለሁ?” ብለው ራስዎን ይጠይቁ፡፡ ዓላማ የሌለው  ስልክ ማንሸራተት (ስክሮሊንግ) የአእምሮን ኃይል እንደሚያባክን ያስታውሱ፡፡ አፕሊኬሽኖችን በሚጠቀሙበት ጊዜ ሰዓት መወሰን  ትልቅ የዲሲፕሊን ለውጥ ያመጣል፡፡

  1. የሳምንት መጨረሻ “ዲጂታል በዓል” ያክብሩ፡፡

በሳምንቱ መጨረሻ ቢያንስ ለግማሽ ቀን ስልኮችን እና ኮምፒውተሮችን ሙሉ በሙሉ ይዝጉ፡፡ ይህ ለነርቭ ስርዓትዎ እውነተኛ እረፍት ነው፡፡

  1. የዕይታ ታሪክዎን ያጽዱ።

ማህበራዊ ሚዲያ በተደጋጋሚ የምንከታተላቸውን ይዘቶችን ይመዘግባል። ከዚያም ተመሳሳይነት ያላቸውን ይዘቶችን ያቀርብልናል። ይህም ራሱ ስልተ ቀመሩ (አልጎሪዝሙ) የመረጠልንን የምናይ ያደርገናል። በየጊዜው የዕይታ ታሪክን (ሂስትሪ) ማጽዳት ከእስራት ነጻ ያወጣናል።

በዲጂታል ዓለም ውስጥ መኖር የዘመናችን እውነታ ነው፡፡ ሆኖም እውነታው ለቴክኖሎጂው ባሪያ መሆን አይደለም፡፡ ዲጂታል ዲቶክስ የነጻነት ጉዞ ነው፡፡ አእምሮአችን እንደ አንድ ህያው አካል እረፍት፣ መረጋጋት እና ከቴክኖሎጂ ውጪ የሆነ እውነተኛ ልምምድ ያስፈልገዋል፡፡

የስነ-ልቦና ባለሙያዎች እንደሚመክሩት ዲጂታል ዲቶክስ ማድረግ አእምሮአችንን ከጫጫታ ነፃ በማውጣት ወደ ቀደመው የአስተሳሰብ ጥልቀት እና የስሜት መረጋጋት እንድንመለስ ይረዳናል፡፡

ከስክሪን ለጥቂት ጊዜ መራቅ ወደ እርስዎ የፈጠራ፣ የሰላም እና የጥልቅ አስተሳሰብ ዓለም ለመመለስ የሚወስዱት ትልቁ እርምጃ ነው፡፡

ዛሬውኑ ይጀምሩ፡፡ የዲጂታል የዓለሙን ጫጫታ ቀነስ ያድርጉ፤ የአእምሮዎን ድምፅ በግልፅ መስማት ይጀምራሉ፡፡ የዲጂታል ዲቶክስ ጥቅሙ ለአንድ ቀን ብቻ ሳይሆን ለወደፊት ህይወትዎ የአእምሮ ጤና እንደ ኢንቨስትመንት የሚቆጠር ነው፡፡ ያስታውሱ ቴክኖሎጂ ለሰው ልጅ አገልግሎት የተፈጠረ ነው እንጂ የሰው ልጅ ለቴክኖሎጂ ሊገዛ አይገባም!።

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሐምሌ 6 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here