ግብ አዳኙ ከነአን ማርክነህ

0
221

ወቅቱ የኦማን ፕሮፌሽናል ሊግ የሚጠናቀቅበት የመጨረሻ ሳምንት ነው፤ አል-ሻባብ ክለብ ከአል-ናህዳ ጋር እየተጫወተ ነው፡፡ ውጥረቱ ዐይን ያፈዛል፤ ጆሮ ውስጥም ይገባል፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ግን ስታዲየሙ በደስታ እብደት ተናወጠ፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ አጥቂ ኳስ እና መረብን አገናኘ፡፡ አንድ ግብ አይደለም፤ ሁለትም አይደለም፤ ሦስት ጊዜ! ሦስታት! (ሄት-ትሪክ!)

እነዚያን ግቦች ያስቆጠረው የእግር ኳስ ኮከብ የገዘፈ ተክለ ሰውነቱ እና ቁመናው ሜዳ ላይ የተጋጣሚ ቡድንን ያስፈራል፤ በተጋጣሚ ቡድን ተከላካዮች ሽብር የሚፈጥር እና ግብ ጠባቂዎችን እረፍት የሚነሳ ባለ ተሰጥኦ አጥቂ ነው፡፡ በአጨዋወት ስልቱ እግር ኳስን በጥልቀት  የተረዳ፣ ታታሪ፣ ትሁት እና ሥራው ብቻ የሚናገርለት አጥቂ ነው- ከነአን ማርክነህ፡፡

 

ከነአን ማርክነህ ከመስከረም 2017 ዓ.ም ጀምሮ በኦማን ሊግ ለአልሸባብ ክለብ እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ክለቡ በሊጉ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ በጨረሰበት በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ኢትዮጵያዊዉ አጥቂ በ21 ጨዋታዎች 21 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ የውድድር ዘመኑን ጨርሷል፡፡ ይህ አስደናቂ ቁጥር የኦማን ሊግ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ክብርን እንዲጎናጸፍ አድርጎታል፡፡

 

ኢትዮጵያዊ ተጫዋች በባዕድ ምድር ነግሦ ስንመለከት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ አዲስ ብስራት ነው፡፡ ግብ አነፍናፊው ከነአን ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ “ከዚህ ስኬት በስተጀርባ እጅግ ከፍተኛ ጥረት እና መስዋዕትነት አለ” በማለት ድንቅ የውድድር ዘመን ማሳለፉን ተናግሯል፡፡

የከነአን የእግር ኳስ ህይወት ከዚህ ይጀምራል፤ የተወለደው በናዝሬት ከተማ ነው፡፡ እግር ኳስን የጀመረውም በተወለደበት እና በአደገበት የሰፈር ሜዳ ነው። እነዚያ አቧራማዎቹ ሜዳዎች የእግር ኳስን ታክቲክ እና ቴክኒክ ሀሁ የተማረባቸው ትምህርት ቤቶቹ ናቸው፡፡

 

ከነአን የፕሮፌሽናል እግር ኳስን በ2008 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ክለብን በመቀላቀል ነው የጀመረው፡፡ በአዲስ አበባ ክለብ ለአንድ ዓመት ያህል የተሳካ ቆይታ ካደረገ በኋላ በ2009 ዓ.ም ወደ ትውልድ ከተማው ክለብ አዳማ ከተማ አቀና፡፡ በአዳማ ከተማ በነበረው ቆይታም በሊጉ አስደናቂ ብቃቱን በማሳየት የኢትዮጵያ ታላላቅ ክለቦችን ትኩረት ሳበ፡፡

 

ይሁን እንጂ የግዙፉ አጥቂ የእግር ኳስ ህይወት ጉዞ  አልጋ በአልጋ እንዳልነበር የትራንስፈር ማርኬት መረጃ ያስነብባል። ብዙ ጊዜ አጭር እና ፈጣን ተጫዋቾች በሚፈለጉበት በኢትዮጵያ እግር ኳስ  የእርሱ ረጅም ቁመት እንደ ቁም ነገር አይቆጠርም ነበር፡፡ ተስፋ መቁረጥን የማያውቀው ከነአን ግን ጠንክሮ በመስራት ይሄንን ኋላቀር አስተሳሰብ መስበር በኢትዮጵያ ታላላቅ ክለቦች ራዳር ውስጥ መግባት ቻለ፡፡

በ2012 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊጉን አንጋፋውን ክለብ ቅዱስ ጊዮጊስን በመቀላቀል በእግር ኳስ ህይወቱ ማርሽ ቀያሪውን ዝውውር አደረገ፡፡ በፈረሰኞቹ ቤት የነበረው ቆይታ እጅግ ፍሬያማ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በ2014 የውድድር ዓመት ከፈረሰኞቹ ጋር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን በማንሳት የእግር ኳስ ህይወቱን አደመቀ፡፡

 

ዋንጫ ባነሳበት በዚሁ ዓመት ወደ ሌላኛው የፕሪሚየር ሊግ ክለብ መቻል መዘዋወሩን የግል የታሪክ ማህደሩ ያስነብባል፡፡ በ2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መቻል ሁለተኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ ቁልፍ ሚና ከተጫወቱት ተጫዋቾች መካከል አንዱ ከነአን ማርክነህ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

 

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ለዓመታት የለመድነው የአጭር ቅብብል (Tiki-taka) አጨዋወት ፍልስፍና ነው፡፡ ከነአን ማርክነህ ግን ይህንን ልማድ በመስበር ክለቦች እና አሰልጣኞች ሜዳ ላይ አዲስ ታክቲክ እንዲያማትሩ አስገድዷቸዋል፡፡ በአንድ ጨዋታ ሦስት ጊዜ ቦታውን በመቀያየር ለአሰልጣኞች እፎይታ ይሰጣል፡፡ በርካታ የእግር ኳስ ባለሙያዎችም የታክቲክ ተለዋዋጭ ተጫዋች እንደሆነ ይመሰክሩለታል፡፡ የግዙፉ አጥቂ ተፈጥሯዊ ቦታው ከአጥቂዎች ጀርባ ቢሆንም እንደ አስፈላጊነቱ ወደፊት በመጠጋት የፊት መስመሩን የመምራት ልዩ ብቃት እንዳለው በተጫወተባቸው ክለቦች ተመልክተናል፡፡

 

አንድ ሜትር ከ90 ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው ከነአን በአየር ኳሶች ላይ ፍፁም የበላይነት በመያዝ፣ ጨዋታን በማረጋጋት፣ ከግብ ግብ በመሮጥ እና የተጋጣሚ ቡድን ተከላካዮችን በማሸበር ድንቅ ክህሎት እንዳለው ይነገራል፡፡ ከኳስ ውጪ የሚያደርገው እንቅስቃሴ የተጋጣሚን የኋላ ክፍል እረፍት እንደሚነሳ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በአየር ላይ ኳስ ያለው የበላይነት ተጫዋቹን ልዩ ያደርገዋል፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በኦማን ሊግ ያሳየው አስደናቂ ብቃትም የዚህ ታክቲካዊ ብስለቱ ውጤት እንደሆነ የትራንስፈር ማርኬት መረጃ ያስነብባል፡፡

 

ከነአን የሀገር ውስጥ ሊግን ጥሎ በ2017 ዓ.ም መጀመሪያ ወደ ሰሜን አፍሪካ ሊቢያ በመጓዝ  ለአል-መዲና እና ለሻባብ አል-ጋር ክለቦች ለአጭር ጊዜ ተጫውቷል፡፡ በ2018 ዓ.ም መስከረም ወር ወደ ኦማኑ አል ሻባብ በይፋ መዛወሩ ይፋ ሆነ፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመንም በአል ሻባብ ቤት  21 ግቦችን በማስቆጠር የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል። ይህም በውጪ ሀገር ሊግ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ የጨረሰ የመጀመሪያው ተጫዋች በመሆን አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል፡፡

 

ከነአን ማርክነህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ዋነኛ የማጥቂያ መሳሪያ ነው፡፡ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ለዋሊያዎቹ በቋሚነት እየተጫወተ ይገኛል፤ አሰልጣኞች ብሄራዊ ቡድኑን ለመገንባት ቅድሚ ከሚሰጧቸው ተጫዋቾች ውስጥም አንዱ ሆኗል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ የመልሶ ማጥቃት ጨዋታዎችን በሚጫወትበት ጊዜ ከነአን የአማካይ ክፍሉን ከአጥቂ ክፍሉ ጋር የሚያገናኝ ድልድይ በመሆን ያገለግላል፡፡ እስካሁን በተሰለፈባቸው 35 ጨዋታዎችም አምስት ግቦችን ከመረብ አገናኝቷል፡፡

ከነአን ማርክነህ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ሊጎች ባገኘው ሰፊ ልምድ ብሄራዊ ቡድኑ ውስጥ ወጣት ተጫዋቾችን የመምራት ትልቅ ሀላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here