ክብር ወይስ ክህደት?

0
119

የዓለም ዋንጫ ለአንድ ተጫዋች የመጨረሻው የክብር ማማ ነው፤ የሀገርን መለያ በኩራት ለብሶ ደረትን ነፍቶ ብሔራዊ መዝሙርን እየዘመሩ ወደ ሜዳ መግባት ከምንም ነገር ጋር የማይወዳደር የሕይወት ዘመን ስኬት እንደሆነ የፊፋ ዶት ኮም መረጃ ያስነብበናል፡፡ ለዚህም ነው ይህንን ታላቅ ክብር ለመጎናጸፍ የፖለቲካ ማዕበልን፣ ስደትን እና የዘመኑን የሕግ ክፍተት ተጠቅመው ለሁለት (አንዳንዴም ለሦስት) የተለያዩ ሀገራት የተጫወቱ ተጫዋቾችን የምናገኘው፡፡ በተለይ እ.አ.አ ከ1930ዎቹ እስከ 1960ዎቹ  ተጫዋቾች የአንድ ሀገር ዜግነት ወይም ፓስፖርት ካገኙ ለሌላ ሀገር መጫወትን የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ (ፊፋ) ይፈቅድላቸው ነበር፡፡

በ1964 እ.አ.አ ግን ተጫዋቾች እንደፈለጉ ብሄራዊ ቡድን እንዳይቀይሩ ለማድረግ “አንድ ተጫዋች ለአንድ ሀገር በይፋዊ የፉክክር ጨዋታ ላይ ከተጫወተ በኋላ ሀገር መቀየር አይችልም” የሚለውን ጥብቅ ሕግ አጸደቀ፡፡

በአሁኑ ወቅት ግን ሕጉ ይበልጥ ተለዋዋጭ እና ቀላል በመሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጫዋቾች በየዓመቱ ብሔራዊ ቡድናቸውን በይፋ ሲቀይሩ እንመለከታለን፡፡ በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ላይ ከተሳተፉት አንድ ሺህ 248 ተጫዋቾች መካከል  25 በመቶ የሚሆኑት  የተወለዱበትን ሀገር ሳይሆን ሌላ ሀገር ወክለው እየተጫወቱ እንደሚገኙ የቢቢሲ ስፖርት መረጃ አስነብቧል፡፡ ለአብነት ሴባስቲያን ሃለር፣ ሀኪም ዚያች፣ አይሜሪክ ላፖርት፣ ዲክላን ራይስ እና ፎላሪን ባሎጉ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በዓለም ዋንጫ ታሪክ ልዩ ክብረ ወሰን ያስመዘገበው አርጀንቲናዊው አማካይ ሉዊስ ሞንቲ ነው፡፡ የሞንቲ ታሪክ በፖለቲካ እና በሞት ዛቻ የታጀበ እንደነበር ያሆ ስፖርት ያስነብባል፡፡ እ.አ.አ በ1930ው የዓለም ዋንጫ አርጀንቲናን እየመራ ለፍጻሜ ማድረሱን የስፖርት የታሪክ ድርሳናት ያስነብባሉ፡፡ አርጀንቲና ዋንጫውን ስትነጠቅ ሞንቲ የሽንፈቱ ተጠያቂ ተደርጎ በደጋፊዎች ተወገዘ፤ በአርጀንቲና መሸነፍ ክፉኛ የተበሳጩ ደጋፊዎች ሞንቲን ለሞት የሚደርስ ዛቻ እና ማስፈራሪያ አደረሱበት፡፡ በዚህ ምክንያትም ሞንቲ አውሮፓን ተሸግሮ ጣሊያን ምድር ገብቷል፡፡

በወቅቱ የጣሊያኑ አምባገነን መሪ ቤኒቶ ሙሶሊኒ እግር ኳስን ለፕሮፓጋንዳ ይጠቀምበት ስለነበር “ኦሪዩንዲ” በሚለው አሰራራቸው ሊዊስ ሞንቲ የጣሊያን ብሄራዊ ቡድንን እንዲቀላቀል ፈቅደዋል፡፡ ሞንቲ ብቻ ሳይሆን የቡድን አጋሩ አቲሊዮ ዴማሪያም የጣሊያን ዜግነት ተሰጥቷቸው ብሄራዊ ቡድኑን እንዲያገለግሉ ተደርገዋል፡፡ እ.አ.አ በ1934ቱ የዓለም ዋንጫም ሞንቲ የጣሊያን ብሔራዊ ቡድን ዋና አንቀሳቃሽ ሞተር መሆን እንደቻለ መረጃዎች ይነግሩናል፡፡

ፋሺስቱ ቤንቶ ሙሶሊኒ በሀገሩ የተዘጋጀውን የዓለም ዋንጫ ለማስቀረት ለብሄራዊ ቡድኑ  “ማሸነፍ ወይም ሞት” የሚል ቀጭን ትዕዛዝ አስተላልፎ እንደነበር ይነገራል፤ ብሄራዊ ቡድኑም ተሳክቶለት ዋንጫውን በማንሳት ከሞት ተርፏል፡፡ ሞንቲ እና ዴማሪያ በዓለም ዋንጫ ለሁለት የተለያዩ ሀገራት የተጫወቱ የመጀመሪያዎቹ ተጫዋቾች በመሆን ስማቸውን በእግር ኳስ የክብር መዝገብ አስፍረዋል፡፡ በተለይም ሞንቲ ለሁለት ሀገራት የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ የተጫወተ ብቸኛው ተጫዋች ሆኖ ስሙ ይነሳል፡፡

ከሁለት ዐስርት ዓመታት በኋላ ደግሞ እ.አ.አ በ1950ዎቹ ዝነኛው ፈረንክ ፑሽካሽ በተመሳሳይ ለሁለት ሀገራት መጫወቱን የያሆ ስፖርት መረጃ አመልክቷል፡፡ እ.አ.አ በ1954ቱ ስዊዘርላንድ በተደረገው የዓለም ዋንጫ ከሀንጋሪ ብሔራዊ ቡድን ጋር ለፍጻሜ ደርሷል፡፡ እ.አ.አ በ1956 በሀንጋሪ ምድር አብዮት ሲቀሰቀስ ፑሽካሽ ወደ ስፔን በማቅናት ሪያል ማድሪድን ተቀላቀለ፡፡ የስፔን ብሄራዊ ቡድንም የዓለም አቀፍ ዝናውን ተጠቅሞ በብሄራዊ ቡድኑ እንዲካተት አድርጎታል፡፡

ፈረንክ ፑሽካሽ እ.አ.አ በ1962ቱ የዓለም ዋንጫ የስፔንን ቀይ መለያ ለብሶ ወደ ሜዳ እንደገባ ያሆ ስፖርት አስነብቧል፡፡ ከፑሽካሽ ጋር በተመሳሳይ የስፔንን መለያ የለበሰው ሌላኛው ኮከብ ሆሴ ኤሚሊዮ ሳንታማሪያ ነው፡፡ ሳንታማሪያ በ1954ቱ የዓለም ዋንጫ የትውልድ ሀገሩን ኡራጓይን ወክሎ እስከ ግማሽ ፍጻሜ ደርሶ የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ዜግነት ቀይሮ ከፑሽካሽ ጋር በመሆን ለስፔን ብሄራዊ ቡድን ተጫውቶ አሳልፏል፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ተጫዋቾች ከስፔን ብሄራዊ ቡድን ጋር የጠበቁትን ስኬት እንዳለገኙ የፎር ፎር ቱ መረጃ አመልክቷል፡፡

በብራዚል እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ “ማዞላ” በሚል ቅጽል ስም የሚታወቀው ሆሴ አልታፊኒ በ1958ቱ የዓለም ዋንጫ የብራዚል ቁልፍ አጥቂ እንደነበር ፎር ፎር ቱ ጋዜጣ አስነብቧል፡፡ አልታፊኒ ከወጣቱ ፔሌ እና ጋርሪንቻ ጋር በመሆን አስደናቂ ጥምረት በመፍጠር ብራዚልን ለዓለም ዋንጫ ክብር አብቅተዋታል፡፡ ከዚህ ስኬት በኋላ ግን የጣሊያኑ ክለብ ኤሲ ሚላን አልታፊኒን በከፍተኛ ገንዘብ እንዳስፈረመው የግል የታሪክ ማህደሩ ይነግረናል፡፡ የአልታፊኒ ወላጆች የጣሊያን የዘር ሀረግ ስለነበራቸው በ1962ቱ የዓለም ዋንጫ የጣሊያንን መለያ ለብሶ ተጫውቷል፡፡ በወቅቱ በብራዚላውያን ደጋፊዎች ዘንድ እንደ ከሀዲ ተቆጥሮ ከፍተኛ ቁጣን አስነስቶ ነበር ይላል መረጃው፡፡

የባልካን ፖለቲካም በእግር ኳሱ ላይ የራሱን አሻራ ጥሎ ማለፉን ያሆ ስፖርት ያስነብባል፡፡ የቀድሞዋ ዮጎዝላቪያ ሳትበታተን እ.አ.አ በ1990 ድጋሚ በጣሊያን ምድር በተካሄደው የዓለም ዋንጫ መሳተፏን የስፖርት የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡ በ1990ው የጣሊያን የዓለም ዋንጫ ላይ ያሳየችው ብቃት በሀገሪቱ ታሪክ እጅግ ድንቅ ነበር ይባላል፡፡ ሀገሪቱ ውጥረት ውስጥ በነበረችበት በዚያ ወቅት ብሔራዊ ቡድኑ እስከ ሩብ ፍጻሜ በመጓዝ የዓለምን ትኩረት እንደሳበ ይነገራል፡፡ የቀድሞው የመሀል ሜዳ ሞተር ሮበርት ፕሮሲኔስኪ በዚህ መድረክ በመሳተፍ የውድድሩ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል፡፡

በወቅቱ 21 ዓመት የነበረው ወጣት ፕሮሲኔስኪ በቴክኒክ ብቃቱ፣ በኳስ ቁጥጥሩ እና በአስደናቂ እይታው የዓለምን ትኩረት መሳብ ችሏል፡፡ ዮጎዝላቪያ በጦርነት ስትከፋፈል ፕሮሲኔስኪ አዲሷን ሀገሩን ክሮኤሺያን ወክሎ በ1998 እና 2002 እ.አ.አ ተጫወተ፡፡ በዓለም ዋንጫ ታሪክ ለሁለት የተለያዩ ሀገራት ግብ ያስቆጠረ ብቸኛው ተጫዋች በመሆንም አዲስ ታሪክ አስመዘገበ፡፡

ዴያን ስታንኮቪች በዓለም እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ሦስት የተለያዩ ሀገራትን ወክሎ በዓለም ዋንጫ ላይ የተጫወተ ብቸኛው ተጫዋች ነው፡፡ ሰርቢያዊ የቀድሞው የመሀል ሜዳ ተጫዋች በዚህ መልኩ የተጫወተው ዜግነቱን በመቀየሩ ሳይሆን በባልካን ሀገራት በነበረው የፖለቲካ ችግር ምክንያት የሀገሩ ስም እና ባንዲራ በየጊዜው በመለዋወጡ ነው፡፡ የሀገሩ ስያሜ እና ድንበር መቀየሩ ስታንኮቪችን በግዙፉ የእግር ኳስ ድግስ ለሦስት የተለያዩ ሀገራት እንዲጫወት ምክንያት ሆኖታል፤ ይህም በዓለም ዋንጫ ታሪክ እስካሁን አዲስ ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ እ.አ.አ በ1998 ለዩጎዝላቪያ፣ በ2006 ለሰርቢያ እና ሞንቴኔግሮ  እንዲሁም በ2010 ለሰርቢያ ተጫውቷል፡፡ ዲያጎ ኮስታ እ.አ.አ በ2013 ለብራዚል ብሔራዊ ቡድን ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ካደረገ ከአንድ ዓመት በኋላ የስፔን ብሔራዊ ቡድንን መቀላቀሉ ይታወሳል፡፡

በወቅቱ የነበረው የፊፋ ሕግ አንድ ተጫዋች በይፋዊ የፉክክር ጨዋታ ላይ ካልተሰለፈ በስተቀር በወዳጅነት ጨዋታዎች ብቻ ሀገር መቀየር እንዲችል ይፈቅድ እንደነበር የፊፋ ዶት ኮም መረጃ አመልክቷል፡፡

በቀደሙት ጊዜያት አንድ ተጫዋች የሌላ ሀገር ዜግነት ማግኘት ከቻለ ብቻ ቀደም ሲል ሌላ ሀገርን ቢወክልም በቀላሉ መለያ መቀየር ይችል ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ታላላቅ ሀገራት የታዳጊ ሀገራትን ኮከቦች በጥቅማጥቅም እንዲያስኮበልሉ በር ከፍቶ ቆይቷል፡፡ አሁን ላይ ግን አንድ ተጫዋች ለዋናው ብሔራዊ ቡድን በይፋዊ የፉክክር ጨዋታ ላይ አንዴ ከተሰለፈ ሀገር መቀየር እንደማይችል ሕጉ ያትታል፡፡

እ.አ.አ በ2020 በተደረገው ማሻሻያ ደግሞ አንድ ተጫዋች ብሄራዊ ቡድን መቀየር የሚችለው ለመጀመሪያው ቡድን ሲጫወት ዕድሜው ከ21 ዓመት በታች ከሆነ፤ የተጫወታቸው ጨዋታዎች ብዛት (ወዳጅነትንም ጨምሮ) ከሦስት ጨዋታዎች የማይበልጡ ከኾኑ፤ በመጨረሻ ጨዋታው እና ለአዲሱ ቡድን ለመጫወት ቢያንስ የሦስት ዓመታት ልዩነት ካለ እና በዓለም ዋንጫ ወይም በአህጉራዊ ትልልቅ ውድድሮች ላይ ተሰልፎ ካልተጫወተ ብቻ መሆኑን የፊፋ ዶት ኮም መረጃ ያስነብባል፡፡

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here