የመድኃኒት አጠቃቀማችን ምን መሆን አለበት?

0
273

ከሰሞኑ በእለተ እሁድ ከጎረቤቶቼ ጋር የተለመደውን ቡና ሰብሰብ ብለን  እየጠጣን ነበር፤ አንዱን ሐሳብ እያነሳን አንዱን  እየጣልን ወጉን ተያይዘነዋል፡፡ በጨዋታችን መሐልም የአንደኛዋ ቡና ታዳሚ የአራት ዓመት  ልጅ  ተዳጋጋሚ ከፍተኛ ሳል ትኩረታችንን በመሳቡ “ለምን አታሳክሚያትም?” የሚል ጥያቄ መሰል አስተያየት ወረወር አደረግን፤ እሷ ግን ፈርጠም ብላ “አይ መጀመሪያ የሳል መድኃኒት በራሴ ገዝቼ  እሰጣት እና ካልተሻላት ግን ወደ ሐኪም እወስዳታለሁ፤ ብዙ ጊዜ ልጆቼ በተለያዩ በሽታዎች ሲታመሙ መጀመሪያ የማደርገው  መድኃኒት ቤት በመሄድ ለፋርማሲስቱ የሕመማቸውን ምልክት እነግረውና መድኃኒቱን ይወስዳሉ፡፡ የሰጠኋቸው መድኃኒት ካሻላቸው እሰየው፤ ካላሻላቸው ግን  በሀኪም አስመርምሬ በሽታቸው  ታውቆ ሀኪሙ ያዘዘላቸውን መድኃኒት እንዲወስዱ አደርጋለሁ” በማለት ለአስተያየታችን ምላሽ ሰጠች፡፡

ሌላኛዋም “አዎ የምን ብርን ማክሰር ነው፤  እድሜውን ያርዝመውና ብላ የመድኃኒት ቤቱን ባለቤት በመጥራት እሱ ነው የቤተሰቤ ሀኪም፤ እኔ ከእሱ ዘንድ እግሬ ሳይረግጥ ሀኪም ደጂ አልደርስም፤ እንዲያውም የሱ መድኃኒቶች ዋጋቸው ይቀንሳሉ፤ ሌላ ቦታ ግን ተመሳሳዩ መድኃኒት ዋጋው ይጨምራል” አለች፡፡

አንደኛዋ ጎረቤቴ ደግሞ ተግባራቸው ስህተት መሆኑን ነገረቻቸው፤ ፊቷን ወደኔ በማዞርም እናንተ የሚዲያ ሰዎች ይህንን የተሳሳተ ግንዛቤ ማስተካከል አለባችሁ! በማለት የቤት ሥራ ሠጠችኝ፤ እኔም ቡናየን አክትሜ ስለያቸው በዚህ ጉዳይ ላይ በጤና አምድ መሥራት እንዳለብኝ በማቀድ ነበር፡፡

ከባሕርዳር ጤና መምሪያ የጤና እና ጤና ነክ ግብዓት ቁጥጥር የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሄኖክ በየነ ጋርም ስለመድኃኒት አጠቃቀም እና መወሰድ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች ቆይታ አድርገናል፡፡ ማንኛውም ሰው ፋርማሲ መክፈት ይችላል? የሚለውን ጥያቄ አስቀደምሁ፡፡ በኢትዮጵያ መድኃኒት መደብር(Drug Shop) ለመክፈት ቢያንስ ሦስት ዓመት ልምድ ያለው “ድራጊስት” ወይም የአንድ ዓመት ልምድ ያለው “ፋርማሲስት” እንደ ሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

መድኃኒት መደብር (Drug Shop) እና ፋርማሲ (Pharmacy) የተለያዩ መሆናቸውን የጠቆሙት አስተባባሪው፤ መድኃኒት ቤት (Pharmacy) ባለሙያው ድግሪና ከዛ በላይ በመድሃኒት ዘርፍ ያጠና ሲሆን፤ በጣም የተለያዩ የመድኃኒቶችን ያቀርባል፤  ፋርማሲስቱ ጥልቅ ምክር መለገስ ይችላል፤ የመድኃኒትን የጎንዮሽ ጉዳት ክትትል ያደርጋል፤ መድኃኒት መደብር (Drug Store)ደግሞ አነስተኛ የመድኃኒት መሸጫ ተቋም ነው፡፡ ድራጊስቱ በመድሃኒት ዘርፍ ዲፕሎማ ያለው ነው፡፡ የተወሰኑ መድሃኒቶችን ብቻም ይሸጣል፡፡

የኢትዮጵያ የምግብ እና የመድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣንም በነዚህ መድኃኒት ቤቶች እና መድኃኒት መደብሮች የመድኃኒቶችን ጥራት ለማረጋገጥ በመድኃኒቱ መያዣ ሳጥን/ቦትል ላይ የተጻፈውን የመጠቀሚያ ጊዜ(Expiry Date) ይመለከታል፤ እንዲሁም በባለስልጣኑ የጥራት ቁጥጥር ላቦራቶሪ – መድኃኒቶች በየጊዜው ጥራታቸው ይረጋገጣል፡፡  ገበያ ላይ ከዋለ በኋላም (Post-Marketing Surveillance መድኃኒቶች ደኅንነታቸው)እና ጥራታቸው እንደተጠበቀ መቆየታቸውን እንደሚያረጋገጥ ነው የገለጹን፡፡

በአካባቢያችን በርካታ ሰዎች የሕመም ምልክቶች ሲያጋጥሟቸው ወደ ሕክምና ተቋም ከመሄድ ይልቅ በራሳቸው ተነሳስተው መድሃኒት ገዝተው መውሰድን ይመርጣሉ፡፡ ለመሆኑ መድኃኒቶችን ያለ ሀኪም ትዛዝ መሸጥ ይቻላል? በማለት  ለአስተባባሪው ላቀረብሁት ጥያቄም አንዳንድ መድኃኒቶች ያለ ሀኪም ትዛዝ ሊሸጡ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ እነሱም የህመም ማስታገሻዎች ማለትም እንደ ፓራሲታሞል፣ አስፒሪን እና የተለያዩ ቫይታሚኖች ሲሆኑ በሀኪም ትዛዝ ብቻ የሚሸጡት ደግሞ አንቲባዮቲክስ፣ የልብ ፣ከባድ ሕመምን እና የአዕምሮን ጤና ለማከም የሚውሉ መድሃኒቶች በሀኪም ትእዛዝ ብቻ ሚሰጡ መድኃኒቶች ናቸው፡፡

መድኃኒት ሲወስዱ ማድረግ ያለበዎት ጥንቃቄ!

አቶ ሄኖክ እንዳስረዱት የመድኃኒት አጠቃቀም ከሰው ጤና ጋር በቀጥታ የተያያዘ ስለሆነ በጥንቃቄ መግዛትና መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ሰዎች መድኃኒትን መግዛት ያለባቸውም ሕጋዊ ፈቃድ ካላቸው መድኃኒት ቤቶች (Pharmacy) ወይም መድኃኒት መደብሮች (Drug Store) ብቻ ነው፡፡ ከመንገድ ዳር፣ ከገበያ ወይም ከማይታወቁ ግለሰቦች  መግዛት አደገኛ ነው፡፡ ከመድኃኒት ቤት ውጭ የሚገዙ መድኃኒቶች  የሐሰት፣ ጥራታቸው የተጓደለ ወይም ጊዜያቸው ያለፈ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ያለ ሐኪም ወይም ፋርማሲስት ምክር መድኃኒት አለመውሰድ፣ መመሪያዎችን በጥንቃቄ ማንበብ፣ የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበትን (expired) አለመጠቀም፣  የሕመሙ ስሜት ወይም ምልክቶች ከባድ ከሆኑ በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም መሄድ ይመከራል፡፡

ያለ ሀኪም ፈቃድ መድኃኒት መውሰድ ለጊዜው ቀላል መፍትሔ ቢመስልም ለተሳሳተ ሕክምና ይዳርጋል፤ ከባድ የጎንዮሽ ጉዳትም ይፈጥራል፡፡  የመድኃኒት አለርጂ ወይም አለፍ ሲልም ጉበትንና ኩላሊትን ሊጎዳ እንዲሁም የአንቲባዮቲክ መቋቋም(ባክቴሪያዎች መድሃኒቱን በመላመድ የሚፈለገው ውጤት እንዳይመጣ ያደርጋሉ) እና በጊዜ ሥር ሳይሰዱ መታወቅ ያለባቸውን በሽታዎች እንዲደበቁ በማድረግ ዘላቂ የጤና እክል ሊያስከትል ይችላል፡፡

ተመሳሳይ መድኃኒቶች ሆነው ለምን ዋጋቸው ተለያዬ? በማለት  ላነሳንላቸው ጥያቄም

ተመሳሳይ መድኃኒቶች የተለያየ ዋጋ የሚኖራቸው በብራንድ፣ በምርምር ወጪ፣ በማምረቻ ጥራት፣ በማሸጊያ፣ በመጓጓዣ፣ በማስታወቂያ እና በገበያ ሁኔታ ምክንያት ነው፡፡ የብራንድ (Brand) እና ጀነሪክ (Generic) ልዩነት ብራንድ መድኃኒት በመጀመሪያ የተፈጠረ ሲሆን በምርምርና በልማት (Research and Development) ብዙ ገንዘብ ወጥቶበታል፡፡ ጀነሪክ መድኃኒት ደግሞ የፈጠራ የባለቤትነት መብት(ፓተንት) ጊዜ ካለፈ በኋላ በሌሎች ኩባንያዎች የሚመረት ሲሆን ብዙ ጊዜ ዋጋው ዝቅ ያለ ይሆናል፡፡

አንዳንድ ኩባንያዎች ከፍተኛ የጥራት ደረጃን ይጠብቃሉ፤ ይህም የማምረቻ ወጪን ያሳድጋል፡፡   የማሸጊያ ጥራት፣ የእርጥበትና የብርሐን መከላከያ ያላቸው መድኃኒቶች በተለምዶ ዋጋቸው ከፍ ይላል፡፡ ከውጭ የሚገቡ መድኃኒቶች የጉምሩክ፣ የመጓጓዣና የመድን ወጪ ስለሚጨመርባቸው  ዋጋቸው ሀገር ውስጥ ከሚመረተው ከፍ ሊል ይችላል፡፡  በኢትዮጵያ የመድኃኒት ዋጋ ቁጥጥር የለም – ስለዚህ ገበያው ዋጋውን ይወስናል፡፡ ሆኖም ከታመነ ምንጭ የተገኘና በሕጋዊ ቁጥጥር የተፈቀደ  ጀነሪክ (ተመሳሳይ) መድኃኒት በአብዛኛው እንደ ብራንድ መድኃኒት ተመሳሳይ የሕክምና ውጤት ይሰጣል፡፡ ልብ ሊባል የሚገባው የመድኃኒት ዋጋ ብቻ የጥራት መለኪያ አለመሆኑን ነው፤ትክክለኛው መለኪያ የጥራት ቁጥጥርን አልፎ ደኅንነቱና ውጤታማነቱ የተረጋገጠ መሆኑ ነው፡፡

አቶ ሄኖክ የቁጥጥር ሂደቱንም ሲያብራሩ በመጀመሪያ በኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን  አማካኝነት የመድኃኒት ምዝገባ (Drug Registration)መድኃኒቶች ገበያ ላይ ከመውጣታቸው በፊት ይመዘገባሉ፡፡ እንዲሁም ቦታው ድረስ በመሄድ መድኃኒት ቤቶች፣ መድኃኒት መደብሮች እና ማከፋፈያዎች ይቃኛሉ፡፡ በተጨማሪም በጥራት ቁጥጥር ላቦራቶሪ (Quality Control Lab) መድኃኒቶች ይመረመራሉ፣ ከገበያው በኋላም የመድኃኒቱን አደገኛ የጎንዮሽ ጉዳቶች መኖር አለመኖራቸው ክትትል ይደረግባቸዋል፡፡ ችግሮች ሲገኙ ከገበያ እንዲሰበሰቡ ይደረጋል፡፡

አንዳንድ ጊዜ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያበቃ እና የተከለከሉ መድኃኒቶችን ባለመድኃኒት ቤቶች እና መድኃኒት መደብሮች በሕግ አፈጻጸም ችግር እና በተቆጣጣሪ አካል እጥረት ሊሸጡ እንደሚችሉ አስተባባሪው ገልፀዋል፡፡ ችግሩን  ለመቅረፍም ሰዎች ሕጋዊ የመድኃኒት ቤት ፈቃድ ካላቸው እና በኢትዮጵያ መድኃኒት ቁጥጠር ባለስልጣን የተመዘገቡትን ብቻ እንዲገዙ መክረዋል፡፡  ሕብረተሰቡም ዋጋቸው ሊቀንስ ይችላል በሚል መድኃኒቶችን ከሕገ ወጥ ቦታዎች መግዛት እንዲቆጠብ እና የመጠቀሚያ ጊዜያቸውን አስተውሎ እንዲገዛ አሳስበዋል፡፡

አስተባባሪው የተከለከሉ እና ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶችን ሲሸጡ የተገኙ  በአዋጅ ቁጥር 176/1999 መሰረት ከ10 ዓመት እስከ 20 ዓመት በሚደርስ እስራት ይቀጣሉ፡፡ በተጨማሪም ከ20ሺህ እስከ 50ሺህ ብር ያስቀጣል፡፡ የተከለከሉ መድኃኒቶችን መሸጥ ደግሞ ከሁለት ዓመት እስከ አምስት ዓመት እስራት እና ከአምስት ሺህ እስከ 20ሺህ ብር ቅጣት ያስቀጣል፡፡  በድብቅ መድኃኒት መሸጥ ከአንድ ዓመት እስከ ሦስት ዓመት እስራት እና ከአምስት ሺህ እስከ 20ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ ጠቁመዋል፡፡  በተጨማሪም የቁጥጥር ባለሙያን መረጃ በመከልከል ለሥራ እንቅፋት መሆን እስከ ስድስት ወር እስራት ወይም እስከ 10ሺህ ብር ሊያስቀጣ ይችላል፡፡

መረጃ

*መድኃኒቶች   ያለ ሐኪም ማዘዣ አይግዙ፡፡

*መድኃኒቱን ከመግዛትዎ በፊት የመድኃኒቱ ስም፣ የማለቂያ ቀን (Expiry Date)፣የምርት ቁጥር (Batch Number)፣የማሸጊያው ደኅንነት (ያልተከፈተ) መሆኑን ያረጋግጡ፤ ከፋርማሲስት ምክር ይጠይቁ፤ እንዴት እንደሚወሰድ ማለትም ከምግብ ጋር ወይም ያለ ምግብ መውሰድ እንዳለበት ይጠይቁ፡፡

*የሚወስዱት መድኃኒት ከሌሎች መድኃኒቶች ጋር የሚኖረውን መስተጋብር በመጠየቅ ተረድተው መግዛት አለበዎት፡፡

*በጓደኛ ወይም በዘመድ ምክር ብቻ መድኃኒትን መውሰድ፣ ቀደም ሲል የታዘዘለዎትን መድኃኒት ለራስዎ ደግመው መግዛት አይመከርም፡፡

*የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈ መድኃኒት መጠቀምን፤ መድኃኒትን ከሌላ ሰው ጋር መጋራት፣ የታዘዘውን መጠን ወይም ቀን በራስ መቀየር የለበዎትም!

*መድኃኒት ሕይወትን የሚያድን ቢሆንም በተሳሳተ መንገድ ከተጠቀሙበት  ከባድ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡

*የመድኃኒት የጎንዮሽ ጉዳቶች ሲያጋጥሙም ለኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ያሳውቁ፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here