ባለክንፍ መንገደኞች

0
227

የአየር ሁኔታው እየቀዘቀዘ ሲሄድ እና የዛፎች ቅጠል መርገፍ ሲጀምሩ ወደ ሰማይ ቀና ብላችሁ አይታችሁ ታውቃላችሁ? በመቶዎች የሚቆጠሩ ወፎች ተሰብስበው በአንድ ላይ ወደ አንድ አቅጣጫ ሲበሩ ማየት የተለመደ ነው። እነዚህ ወፎች “ስደተኛ ወፎች” ይባላሉ።

ስደተኛ ወፎች ማለት የአየር ሁኔታ ሲቀየር እና የሚበሉት ምግብ ሲጠፋ ረጅም ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው ወደ ሌላ ሞቃት ሀገር የሚበሩ ወፎች ናቸው። በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወፎች ውቅያኖሶችን፣ በረሃዎችን እና ረዣዥም ተራራዎችን አቋርጠው ይህንን አስደናቂ ጉዞ ያደርጋሉ።

ታዲያ ወፎቹ ይህንን ረጅም መንገድ ለምን ይጓዛሉ? ዋናው ምክንያት ምግብ እና ሙቀት ፍለጋ ነው። በትውልድ ቦታቸው ክረምት ሲመጣ እና ቅዝቃዜው ሲበዛ፣ የሚበሏቸው ትላትሎች፣ ፍራፍሬዎች እና ዘሮች በረዶ ውስጥ ይቀበራሉ ወይም ይጠፋሉ። ስለዚህ ወፎቹ የሚበሉት ምግብ በብዛት እና ሞቅ ያለ አየር ወዳለበት አዲስ ሀገር ይበራሉ። እዚያም ለአምስት ወይም ለስድስት ወራት ከቆዩ እና ክረምቱ አልፎ በጋ ሲሆን እንደገና ወደ መጡበት ቦታ ይመለሳሉ። ለምሳሌ በርካታ ወፎች ከአውሮፓ ተነስተው ረጅም መንገድ በመብረር ወደ እኛ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ።

ትልቁ ጥያቄ ወፎቹ መንገዱን እንዴት ያውቁታል? የሚገርመው ነገር ወፎቹ እንደ እኛ ስልክ ወይም  የአቅጣጫ አመላካች (ጂፒኤስ) የላቸውም። ነገር ግን ተፈጥሮ የሰጣቸው ድንቅ ኮምፓስ አላቸው። በቀን ውስጥ የፀሐይን አቅጣጫ፣ ማታ ደግሞ የከዋክብትን አቀማመጥ በመመልከት መንገዳቸውን ያውቃሉ። ከዚህም በላይ በምድር ላይ ያሉትን ትላልቅ ወንዞች፣ ተራራዎች እና ባህሮችን እንደ ምልክት ይጠቀማሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ በአየር ላይ የሚበሩት የ”V” (ቪ) ቅርጽ በመሥራት ነው፤ ይህም የፊት ለፊቱ ወፍ አየር እየቀደደ የኋላኞቹ በቀላሉ እንዲበሩ እና እንዳይደክማቸው ይረዳቸዋል።

የስደተኛ ወፎች ጉዞ እጅግ አድካሚ እና አደገኛ ቢሆንም በየዓመቱ ሳይሰለቹ የሚያደርጉት ተፈጥሯዊ ግዴታቸው ነው። እነዚህ ወፎች በዓለም ዙሪያ ያሉ ሀገራትን እና ሰዎችን የሚያገናኙ የተፈጥሮ ውብ ስጦታዎች ናቸው ይላል ናሽናል ጂኦግራፊክ ኪድስ ላይ ያገኘነው መረጃ።

 

ተረት

ደጉ ገበሬ

ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ መንደር ውስጥ አለሙ የሚባል በጣም ደግ ገበሬ ይኖር ነበር። አለሙ በየቀኑ ማልዶ በመነሳት በእርሻ መሳው ላይ ደክሞ ያርሳል፤ ያመረተውንም እህል ለተቸገሩ ጎረቤቶቹ በደስታ ያካፍላል። አንድ ቀን ምሽት ላይ ከሥራ ወደ ቤቱ እየተመለሰ ሳለ በመንገድ ዳር በረሃብ የደከሙ አንድ አረጋዊ ሽማግሌ አገኘ። ወዲያውኑ ውኃ አጠጣቸው እና በጀርባው አዝሎ ወደ ቤቱ በመውሰድ ሞቅ ያለ ምግብ መገባቸው።

በማግስቱ ሽማግሌው ከመሄዳቸው በፊት ለአለሙ አንዲት ትንሽ የዛፍ ዘር ሰጡት እና “ይህች የደግነትህ ምላሽ ናት፤ በጓሮህ ትከላት” አሉት። አለሙ ዘሯን ሲተክላት በአንድ ሌሊት አድጋ የወርቅ ፍሬ የምታፈራ ድንቅ ዛፍ ሆነች። አለሙ በዛፉ ምክንያት ትልቅ ሀብት ቢያገኝም ደግነቱን አልተወም፤ ይልቁኑ ካገኘው ወርቅ እየቀነሰ በመንደሩ ውስጥ የተቸገሩትን መርዳቱን ቀጠለ። ተረቱ የሚያስተምረን ደግነት መቼም ቢሆን ከንቱ እንደማይቀር እና መልካምነት በበረከት ተመልሶ ወደ እኛ እንደሚመጣ ነው።

ሞክሩ

 

  1. ነጭ ላም ጥቁር ጥጃ ወለደች ምንድን ነው?
  2. አንገት አለው ራስ የለውም፣ ሆድ አለው ጀርባ የለውም?

 

  1. የሰውነት ክፍላችን እንዲያድግና ጥርሳችን እንዲጠነክር የሚረዳው ነጭ መጠጥ ምንድን ነው?

መልስ

 

  1. ጥጥ እና ፍሬው
  2. ማሰሮ
  3. ወተት

ነገር በምሳሌ

-ካለፈው ስህተት የዛሬው ጥንቃቄ፡- ከሠራነው ስህተት ተምረን ራሳችንን ማስተካከል እንዳለብን ያሳያል።

-የቆረጠ ወንዝ ያቋርጣል፦ አንድን ሥራ ለመሥራት በቁርጠኝነት ከተነሳን ማሳካት እንደምንችል ያሳያል።

-ካልዘሩት አይበቅልም፦ ጥሩ ውጤት ለማግኘት መጀመሪያ ጠንክሮ መሥራት እና ማጥናት እንዳለብን ያስተምራል።

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የሐምሌ 13  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here