ለአንዳንዶቹ ዝናን ለማግኘት ዓመታት የፈጀ ልምምድ አይጠይቅም። አንዳንዴ የሚያስፈልገው ባንክ ውስጥ መከራከር፣ በአውሮፕላን ማረፊያ መጠበቅ፣ ወይም በድንገት የፊልም ቀረጻ ቦታ ላይ መታየት ብቻ ነው።
በጥንታዊ ፈላስፎች (በተለይም እንደ ማኪያቬሊ ባሉ) አስተሳሰብ ዝና የሁለቱ ተቃራኒ ኃይሎች ውጤት ነው፤ የአጋጣሚ እና የጥረት።
ፎርቹን (አጋጣሚ) ልክ እንደ ወንዝ ሞገድ ነው፤ መቼ እንደሚጎርፍ እና መቼ እንደሚያቆም አይታወቅም። ማሪሊን ሞንሮ በፋብሪካ ውስጥ በነበረችበት ወቅት ፎቶግራፍ አንሺው መምጣቱ፣ ወይም ፓሜላ አንደርሰን በስታዲየም ስክሪን ላይ መታየቷ ሙሉ ለሙሉ ከቁጥጥራቸው ውጪ የሆነ የ’አጋጣሚ’ ድርሻ ነው።
ዝና የሰው ልጅ ጥረት ብቻ ሳይሆን አጽናፈ ሰማይ (ዩኒቨርስ) በተወሰነ ሰዓት እና ቦታ ላይ እንዲገናኙ የሚያደርገው አጋጣሚ ነው።
ሆኖም አጋጣሚ (ፎርቹን) ብቻውን በቂ አይደለም። ቨርቹ (ጥረት) ያስፈልጋል። ይህም ችሎታ፣ ብርታት፣ ዝግጁነት እና ድፍረትን የሚይዝ ነው።
ዛሬ አጋጣሚ በሩን የከፈተላቸውን የዓለም ከዋክብት እንመለከታለን። አጋጣሚው ሲመጣ ያንን ዕድል ተጠቅሞ ወደ ስኬት የሚቀይር የውስጥ ብርታት (ቨርቹ) ካልኖረ ዝናው ዘለቄታ እንዳላገኘ ልብ እንበል። ዝና የጥረት እና የአጋጣሚዎች ውጤት ነው።
ብራይት ሳይድ ድረ-ገጽ “በአጋጣሚ ዝነኛ የሆኑ 15 ታዋቂ ሰዎች” በሚል ርዕስ የከዋክብትን ታሪክ አስነቧል።
ጄኒፈር አኒስተን
ዓለም አቀፍ ዝነኛ ተዋናይት ከመሆኗ በፊት ጄኒፈር አኒስተን ብዙ ስኬታማ ያልሆኑ ሥራዎችን ሞክራለች። አንድ ቀን ሆሊውድ ውስጥ በምትገኝ የነዳጅ ማደያ የቀድሞውን የኤን ቢ ሲ ኢንተርቴይንመንት ፕሬዝዳንት ዋረን ሊትልፊልድን አገኘችው። መኪናውን ነዳጅ ሞልቶ ሲጨርስ አኒስተን “ለኔ እድሉ ይፈጠርልኝ ይሆን?” ብላ ጠየቀችው።
ሊትልፊልድ ለትንሽ ጊዜ ካሰበ በኋላ “እንዲፈጠርልሽ ፈልጌ ነበር” አላት። ብዙም ሳይቆይ በ”ፍሬንድስ” ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ የራሄል ግሪንን ታዋቂ ሚና እንድትጫወት ተጋበዘች። የዝና ታሪኳ በዚያች አጋጣሚ ጀመረ።
ክሎይ ሴቪኒ
የ17 ዓመቷ ክሎይ ሴቪኒ ከጓደኞቿ ጋር በኒውዮርክ ስኬትቦርድ ስትጫወት በነበረበት ወቅት ከሙዚቃ እና ፋሽን መጽሔት (አይ ዲ) የመጣ ፎቶግራፍ አንሺ ተመለከታት። እሱም የፎቶ ቀረጻ እንድታደርግ ጋበዛት። ክሎይ እድሉን አልተወችም። በአሁኑ ጊዜ ይህች ዝነኛ ሞዴል እና ተዋናይት ያ የፎቶ ቀረጻ በሙያዋ ውስጥ ምርጡ እንደሆነ ትናገራለች።
ዴቪድ ቦሬናዝ
ዴቪድ ቦሬናዝ ለዓመታት ብዙ ልምምዶችን (ኦዲሽኖችን) በማድረግ በፊልም ስክሪን ላይ ለመታየት ሲሞክር ቆይቷል። ነገር ግን ህልሙ እውን የሆነው በአጋጣሚ በተፈጠረ መገናኘት ነው።
እ.ኤ.አ በ1996 የ”ባፊ ዘ ቫምፓየር ስሌየር” ተከታታይ ፊልም ዳይሬክተር ማርሺያ ሹልማን የአንጀልን ሚና የሚጫወት ቆንጆ ወንድ ትፈልግ ነበር። ነገር ግን ጥረቷ ሁሉ አልተሳካም። ያኔ ነው ውሻዋን አስራ ስትራመድ ቦሬናዝን ያስተዋለችው። ተዋናዩ ለሚናው ተመረጠ እና ለሚቀጥሉት 25 ዓመታት የቲቪ ተከታታይ ፊልሙ ኮከብ ሆኖ ቆየ።
ብራድ ፒት
ብራድ ፒት በተማሪነት ዘመኑ ጋዜጠኝነትን ያጠና የነበረ ቢሆንም ከምረቃው ሁለት ሳምንት ቀደም ብሎ ትምህርቱን አቋርጧል። ዝና በአንድ ጊዜ አልመጣለትም። የባንክ ሒሳቦቹን ለመክፈል ማንኛውንም ሥራ ለመሥራት ተገደደ።
በካፌ ውስጥ የዶሮ ልብስ ለብሶ የካፌው መለያ ሆኖ ሠርቷል። እንደ ተዋናዩ አባባል እነዚህ ስራዎች ትክክለኛ ሰዎችን እንዲያገኝ አድርገውት ወደ ትወና አስተማሪው ሮይ ለንደን አደረሱት፤ እሱም ችሎታውን እንዲያወጣ እና የመጀመሪያ የፊልም ሚናዎቹን እንዲያገኝ ረድቶታል።
ላና ተርነር
ላና ተርነር ለሙያዋ የምትጠይቀው ለሆሊውድ የፊልም ኢንደስትሪ መሪ መጽሔት “ዘ ሆሊውድ ሪፖርተር” መስራች ለነበረው ለዊሊያም አር ዊልከርሰን ነው። ነጋዴው የ16 ዓመቷን ላናን ከጓደኞቿ ጋር ሶዳ መጠጥ እየጠጣች ባገኘ ጊዜ፣ ወደፊት ትልቅ ኮከብ እንደምትሆን ወዲያውኑ ተረዳ።
ዊልከርሰን ላናን ለችሎታ ወኪሉ ለዜፖ ማርክስ አስተዋወቃት። እሱም በ”ዴይ ዎንት ፎርጌት” ፊልም ላይ ትንሽ ሚና እንድታገኝ ረድቷታል። ብዙም ሳይቆይ በፊልም ስክሪን ላይ ታላቅ ስራዋ ተጀመረ።
ጆን ዋይን
የላቀ ኮከብ ከመሆኑ በፊት ጆን ዋይን “ማሪዮን ሞሪሰን” በመባል ይታወቅ ነበር። ለደቡብ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ እግር ኳስ ይጫወት ነበር። ነገር ግን ከባድ ጉዳት ከደረሰበት በኋላ የስፖርት ስኮላርሺፑን አጥቶ ሌላ ስራ ለመፈለግ ተገደደ። ዋይን በፊልም ስክሪን ላይ እግር ኳስ ተጫዋቾችን በመጫወት ስራውን ጀመረ። ከዚያም ቀስ በቀስ ወደ ትልልቅ ሚናዎች ተቀይሮ በ1970 ኦስካር አሸንፏል።
ጀስቲን ቢበር
ጀስቲን ቢበር ከልጅነቱ ጀምሮ ሙዚቃ ይወድ ነበር። በ12 ዓመቱ ካናዳ ውስጥ በተደረገ የዘፈን ውድድር ሁለተኛ ወጣ። እናቱ የልጁን ቪዲዮ በዩቲዩብ የለጠፈችው በውድድሩ ላይ መገኘት ያልቻሉ ቤተሰቦች እና ጓደኞች እንዲያዩት ነበር።
ከዚያም ጀስቲን ተወዳጅ ዘፈኖችን ሲዘፍን የሚያሳይ ተጨማሪ ቪዲዮዎችን ለጠፈች። ተመልካቾቹ ቀስ በቀስ እየጨመሩ ቪዲዮዎቹ ከ60 ሺህ በላይ እይታዎችን ማግኘት ጀመሩ። ዘፈኖቹን ከሰሙት መካከል የሙዚቃ አዘጋጁ ስኮት ብራውን አንዱ ነበር። የ13 ዓመቱን ዘፋኝ በአትላንታ ስቱዲዮ የመጀመሪያውን ዘፈን እንዲቀርጽ ጋበዘው።
ኬት ሞስ
ኬት ሞስ በለጋነት ዕድሜዋ በ1990ዎቹ እና 2000ዎቹ ከነበሩት ታዋቂ ሱፐር ሞዴሎች አንዷ እንደምትሆን አስባ አታውቅም። በአቀራረቧ እንደምትሸማቀቅ ትናገራለች። ሁሉም ነገር የተለወጠው የሞዴሊንግ አሰልጣኝ የነበረችው ሳራ ዶካስ በእሷ ስታምን ነው።
ሞስ የዶካስን ወንድም በኒውዮርክ አየር ማረፊያ አገኘችው። የ14 ዓመቷ ልጅ አውሮፕላን እስክትሳፈር ድረስ እየተዘዋወረች በነበረበት ወቅት እሱ ወደ እሷ መጥቶ “ስለ ሞዴልነት አስበሽ ታውቂያለሽ?” ብሎ ጠየቃት። ከሁለት ዓመት በኋላም በ16 ዓመቷ “ዘ ፌስ” በተሰኘ መጽሔት ሽፋን ላይ የመጀመሪያዋን የፎቶ ቀረጻ አደረገች።
ኦፕራ ዊንፍሬይ
ኦፕራ ዊንፍሬይ የ17 ዓመት ልጅ ሳለች የናሽቪል አካባቢ የሬዲዮ ጣቢያ በውበት ውድድር ላይ እንድትሳተፍ ጋበዛት። አሸናፊዋ “ሚስ ፋየር ፕሪቬንሽን” የሚል ማዕረግ እንደሚሰጣት ተነግሮ ነበር። ኦፕራ ይህን ማዕረግ እንደምታገኝ አላሰበችም ነበር።
ነገር ግን “አንድ ሚሊዮን ዶላር ብታገኚ እንዴት ታጠፊዋለሽ?” የሚል ጥያቄ ሲጠየቅ ሌሎች ተወዳዳሪዎች በልግስናቸው ሲፎካከሩ ዊንፍሬይ በቅንነት “አንድ ሚሊዮን ዶላር ቢኖረኝ ገንዘብ አባካኝ እሆን ነበር። ምን ላይ እንደማውለው እርግጠኛ አይደለሁም። ግን አወጣዋለሁ” ብላ መለሰች። ቅንነቷ እና ቀልዷ ዳኞችን ማረከ እና ዘውዱን አሸነፈች። ከዚህም በላይ በዚያው የሬዲዮ ጣቢያ ሥራ አገኘች እና በሚዲያ ዓለም የተሳካ ጉዞዋን ጀመረች።
ቢል ኮስቢ
ቢል ኮስቢ በተማሪነት ዘመኑ በኒውዮርክ ካፌ ውስጥ ባርማን ሆኖ ሠርቷል። እንዲሁም ታዳሚውን የሚያዝናና ሥራ ይሠራ ነበር። ጎብኚዎች ቀልዱን ስለወደዱት ቢል በአሜሪካ ዙሪያ ቀልዶችን ማቅረብ ጀመረ።
ኮሜዲያኑ በቴሌቪዥን ታይቶ እ.አ.አ በ1965 “ዘ ቱናይት ሾው” ላይ ቀረበ። ብዙም ሳይቆይ በዋርነር ብራዘርስ ጋር በመገናኘት በርካታ ስኬታማ የኮሜዲ ፕሮጀክቶችን ፈጠሩ።
ፓሜላ አንደርሰን
ፓሜላ አንደርሰን የአካል ብቃት አስተማሪ ሆና ትሠራ ነበር፤ በኋላም በካናዳ በእግር ኳስ ጨዋታ ላይ ሳለች ተገኘች። ወደ ጨዋታው የመጣችው በላዩ ላይ አርማ ያለበት ጥብቅ ቲሸርት ለብሳ ነበር፤ በስታዲየሙ ግዙፍ ስክሪን ላይም ታየች። ያልታሰበው ማስታወቂያ የኩባንያውን ሰዎች ስላስደሰተ አንደርሰን የውል ስምምነት ቀረበላት። ብዙም ሳይቆይ ለመጽሔቶች የፎቶ ቀረጻ አደረገች፣ ከዚያም በ”ቤይዋች” ፊልም ላይ ያላትን ታዋቂ ሚና አገኘች።
በሀገራችንም እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። ምናልባት ያች አንድ አጋጣሚ ባታገኛቸው ኖሮ ስማቸውን የምንጠራቸው ዝነኞች የማይታወቁ ሰዎች ሊሆኑ ይችሉ ነበር።
(አቢብ በዓለሜ)
በኲር የሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


