ተመራማሪዎች በአንጐል ውስጥ የመርዛማ ፕሮቲን መከማቸት ህዋሳትን በመግደል ለመርሳት በሽታ (አልዛይመር) እና ለአእምሮ መናጋት (ዳመንቲያ) የሚዳርግበትን ሂደት ለይተው መገንዘባቸውን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል፡፡
በለንደን ኪንግስ ኮሌጅ በተካሄደው ምርምር የተገኘው አዲስ ግኝት ለበሽታው ሁነኛ መድኃኒት ለመሻት በር ከፋች ነው ተብሎለታል፡፡
ተመራማሪዎቹ በአንጐል ውስጥ የመርዛማ ፕሮቲን ክምችት በሚፈጥረው የኬሚካል ውህደት የሚከሰተውን የግንኙነት መቋረጥ ወይም (ክሪፕቶሲስ) መሠረት አድርገው ባካሄዱት ምርምርና ባገኙት ግኝት ተመሥርተው ከአሁን በፊት ያልተሞከሩ ጥረቶችን በማድረግ የተሻለ ውጤት ለማግኘት ተስፋ መሰነቃቸውን ነው ያረጋገጡት፡፡
የኪንግስ ኮሌጅ እና የዩኬ ከአእምሮ መናጋት /ዳመንሽያ/ የምርምር ተቋም ጋር ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት የህዋሳትን ሞት የሚያፋጥነውን ችግር መለየት ችለዋል፡፡
ለጥናት እና ምርምሩ የአእምሮ መናጋት ካጋጠማቸው 28 ሰዎች ሶስት ሺህ የአንጐል ህዋሳት ተሰብስበው በግብአትነት አገልግለዋል፡፡ በስልተ ቀመር (አልጐሪዝም) በተሰራ ንፅፅርም በአንጐል ክፍል ውስጥ በተለያየ ደረጃ የህዋሳት ሞት መከሰቱን መገንዘብ ችለዋል፤ ተመራማሪዎቹ፡፡ በውጤቱም 35 በመቶ የአልዛይመር በሽታ ካለባቸው ሰዎች ፊት ለፊት ከሚገኘው የአንጐል ክፍል 35 በመቶ የ “ካሪፕቶሲስ” የህዋሳት ሞት እና የግንኙነት መቋረጥ ምልክት መገኘቱ ነው የተረጋገጠው፡፡
በመጨረሻም የህዋሳት ሞትን መከላከል እና ሂደቱን ማቋረጥ የአንጐል ህዋሳት መጥፋትን ለሚቀንሱ ህክምናዎች በር በመክፈት በጤና ችግሩ ዋነኛ መሰረት ላይ አነጣጥሮ መድኃኒት ማግኘት እንደሚቻል ነው ያረጋገጡት፤ ተመራማሪዎቹ፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


