ዛሬ ሀገራችን በበርካታ ውስብስብ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች ውስጥ በምትገኝበት ወቅት፣ “ሀገራዊ ምክክር” የሚለው ጽንሰ-ሀሳብ በተደጋጋሚ ይደመጣል። ነገር ግን ምክክር ማለት ዝም ብሎ መሰብሰብና መነጋገር ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም የጋራ መጻኢ እጣ ፈንታችንን የምንቀርጽበት፣ የቆሰሉ ትውስታዎችን የምናክምበት እና አዲስ ማህበራዊ ውል የምንመሠርትበት ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ነው።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በግልጽ እንደሚያስቀምጠው፣ ይህ ሂደት የሀገርን ህልውና ከማስጠበቅ ጀምሮ ዘላቂ ሰላምን እስከማስፈን የዘለቀ ታላቅ ብሄራዊ ዓላማ አለው።
ምክክር መሠረታዊ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ጥበብ ነው፡ሀገራዊ ምክክር በዋናነት የሚነሳው በዜጎች፣ በብሔረሰቦችና በፖለቲካ ኃይሎች መካከል ያሉትን መሰረታዊ ልዩነቶች በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ነው። በሀገራችን የታሪክ ሂደት ውስጥ የተጠራቀሙና ለሀገር ህልውና ስጋት የሆኑ ልዩነቶችን ለመፍታት ከምክክር ውጭ ሌላ የተሻለ አማራጭ የለም።
ይህ እውን እንዲሆንም በአንድ ሀገር የተከሰቱ ከባድ የፖለቲካ ችግሮችንና በማሕበረሰቡ ውስጥ ያሉ መሠረታዊ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት የህልውናችን መሠረት ነው። ከዚህ ባሻገር ዘላቂ መግባባትን በመፍጠር ጊዜያዊ ማስታገሻዎችን ከመፈለግ ይልቅ፣ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን ከስር መሰረታቸው በመፍታት ዘላቂ ሀገራዊ መግባባትን መፍጠር ይገባል።
ይህ ምክክርም በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መተማመንን መገንባት የሚያስችል ትልቅ አቅም አለው፡፡ ታሪካችን እንደሚያሳየን በህዝብና በመንግስት መካከል ያለው የመተማመን ክፍተት ለብዙ ግጭቶች መንስኤ ሆኖ ቆይቷል። ሀገራዊ ምክክሩ ይህንን ክፍተት ለማጥበብ ታላቅ ዕድል ይዞ መጥቷል።
ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው ልዩነቶችን በኃይል ሳይሆን በውይይትና በምክክር የመፍታት ባህል ማዳበር ሲቻል ብቻ ነው። ይህም በመንግሥትና በሕዝብ መካከል የጠፋውን እምነት ለመመለስና መተማመንን ለማስፈን ዓይነተኛ መፍትሔ ነው።
ምክክሩ ትላንት የነበሩ ስህተቶችን ብቻ የምናርምበት ሳይሆን፣ ነገ የምንኖርባትን አዲስ (ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ) ያደገና የተለወጠ ሥርዓት የምንገነባበት መሠረት እና ወደ አዲስና የተሻሻለ ሥርዓት የምንሻገርበት ምዕራፍ ነው፡፡
ዜጎች እርስ በርስ የሚደማመጡበት፣ የሚከባበሩበትና በአዲሱ ሥርዓት ውስጥ ባለቤትነታቸው የሚረጋገጥበት ምቹ ሁኔታ መፈጠር አለበት። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ግጭቶችን በዘላቂነት መፍታትና በዜጎች መካከል የተሻሻለ ማህበራዊ ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ የሚቻለው።
በአጠቃላይ፣ ሀገራዊ ምክክር የአንድ ወገን ፍላጎት መጫኛ ሳይሆን የሁላችንም የጋራ ይዞታና የወደፊት ተስፋችን ነው። የዚህ ታሪካዊ ሂደት ስኬት የሚወሰነው በሁላችንም በሰላማዊ መንገድ ለመወያየት፣ ለመደማመጥ እና ለመቻቻል ባለን ቁርጠኝነት ላይ ነው። አሁን ላይ ከእኛ የሚጠበቀው በቅንነትና በሀቀኝነት ወደ ምክክር መድረኩ በመቅረብ የነገዋን የተሻለችና የተረጋጋች ሀገር በጋራ መገንባት ብቻ ነው።
በኲር የሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


