በደቡብ አሜሪካ ሰማይ ስር፣ አንደስ በሚባለው የተራራ ሰንሰለት እምብርት ውስጥ ተፈጥሮ እና የሰው ልጅ እጅ ለእጅ ተያይዘው የፈጠሯት አስደናቂ ከተማ ትገኛለች። ይህች ከተማ የቦሊቪያ ዋና ከተማ ላፓዝ ናት። ከተማዋ ልክ እንደ አንድ ግዙፍ እና ጥልቅ ጎድጓዳ ሳህን ውስጥ እንደተሞላች፣ በገደል አፋፎች እና በተራራ ዳገቶች ላይ እንደ ሸረሪት ድር ተጣብቃ ትታያለች። ከባህር ወለል በላይ ከ3ሺህ640 እስከ 4ሺህ150 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው ላፓዝ በዓለማችን ላይ ካሉ ዋና ከተሞች ሁሉ ከፍተኛው ቦታ ላይ የምትገኝ ከተማ ናት። ላፓዝ ከህንፃዎች ክምችት በተጨማሪ ከጥንታዊ አመሰራረት ታሪኳ ጀምሮ እስከ አስደማሚ የተፈጥሮ ሀብቶቿ፣ ከሌላው ዓለም ከተለየው ሚስጥራዊ ሀይቋ እስከ ህያው ባህሏ ድረስ ህያው ቤተ መዘክር ናት።
የላፓዝ ከተማ አመሰራረት ታሪክ እጅግ ማራኪ እና ከስፔን ቅኝ ግዛት እንዲሁም ከጥንታዊው የአይማራ ስልጣኔ ጋር በጥልቀት የተቆራኘ ነው። ስፔናውያን መጥተው ከተማዋን ከመቆርቆራቸው በፊት፣ ይህ ጥልቅ ሸለቆ በአይማራ ተወላጆች «ቹኪያጎ ማርካ» በመባል ይታወቅ ነበር። «ቹኪያጎ» ማለት በአይማራ ቋንቋ “የወርቅ እርሻ” ማለት ሲሆን፣ ይህ ስያሜ የተሰጠው ሸለቆውን ሰንጥቆ በሚያልፈው የቾኬያፑ ወንዝ ውስጥ ይገኝ የነበረውን የተፈጥሮ የወርቅ ማዕድን በማሰብ ነበር።
በ1540ዎቹ የስፔን ወራሪዎች የኢንካን ግዛት ካሸነፉ በኋላ በመካከላቸው በስልጣን እና በሀብት ክፍፍል ምክንያት ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነት ተነስቶ ነበር። ይህ ጦርነት ጋብ ሲል ጥቅምት 20 ቀን 1548 ዓ.ም ካፒቴን አሎንሶ ዴ ሜንዶዛ አዲስ ከተማ እንዲመሰርት ታዘዘ። በመጀመሪያ ከተማዋ የተመሰረተችው ላሃ በተባለ ስፍራ ቢሆንም፣ ከቀናት በኋላ ከ«አልቲፕላኖ» (ከፍተኛው አምባ) ከሚነፍሰው ከባድ እና ቀዝቃዛ ንፋስ ለመከለል እንዲሁም በቾኬያፑ ወንዝ ውስጥ ያለውን ወርቅ ለመበዝበዝ ሲባል ከተማዋ ወደ አሁኑ ጥልቅ ሸለቆ ተዛወረች። የከተማዋም ስም የስፔናውያኑን የእርስ በእርስ ጦርነት ማብቃት እና የሰላም መምጣት ለማሰብ «ኑዌስትራ ሴኞራ ዴ ላፓዝ» (የሰላሟ እመቤታችን) ተብሎ ተሰየመ። በጊዜ ሂደት ያ የወርቅ ማዕድን ቢሟጠጥም ከተማዋ ግን ራሷን ወደማይገኝ የባህል እና የፖለቲካ ማዕከልነት ቀይራለች።
የላፓዝን መልክዓ ምድር ከሌሎች የዓለማችን ከተሞች ፍፁም የተለየ የሚያደርገው እንግዳ የሆነ የተፈጥሮ አቀማመጥ ነው። ከተማዋን በበላይነት የሚቆጣጠረው እና የላፓዝ ዘላለማዊ ጠባቂ ተደርጎ የሚቆጠረው ኢሊማኒ ተራራ ነው። ከባህር ወለል በላይ 6ሺህ438 ሜትር ርዝመት ያለው ይህ ባለ አራት ጫፍ ተራራ አናት ላይ ዘላለማዊ በረዶ ተከናንቦ ከማንኛውም የከተማዋ አቅጣጫ ይታያል። ኢሊማኒ ለላፓዝ ነዋሪዎች ተራራ ብቻ ሳይሆን፣ የተቀደሰ የተፈጥሮ ሀብት እና የከተማዋ መለያ አርማ ነው።
ከከተማዋ ማዕከል ትንሽ ራቅ ብሎ በደቡባዊ አቅጣጫ ደግሞ ሌላ አስገራሚ የተፈጥሮ ስጦታ ይገኛል። «የጨረቃ ሸለቆ» በመባል የሚጠራው ይህ ስፍራ፣ በውሃ እና በንፋስ መሸርሸር ምክንያት የተፈጠሩ፣ ልክ እንደ ሸክላ እና የአሸዋ ድንጋይ ሹል ሆነው የቆሙ ቅርፆች ስብስብ ነው። በዚህ ስፍራ መራመድ ምድርን ትቶ ጨረቃ ላይ እንደመጓዝ ይቆጠራል። ከተማዋ በተጨማሪም «የሞት መንገድ» ወደሚገኝበት እና አየሩ ሞቃት ወደሚሆንበት የ«ዩንጋስ» ክልል የሚያስገባው በር ናት።
ከላፓዝ ከተማ ወጣ ብሎ የቦሊቪያ እና የፔሩን ድንበር የሚያዋስነው የቲቲካካ ሀይቅ ይገኛል፡፡ ቲቲካካ ሀይቅ ከባህር ወለል በላይ 3,812 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል፡፡ በአንዲስ ተራሮች አናት ላይ የተዘረጋው ይህ ግዙፍ ሀይቅ ጠለቅ ያለ ሰማያዊ ቀለም ያለው ሲሆን በ8ሺህ372 ካሬ ኪ.ሜ ላይ ተንጣሎ የሚገኝ ውቅያኖስ መሰል ሀይቅ ነው።
ቲቲካካ ሀይቅ በአካባቢው ሕዝብ ዘንድ እጅግ ቅዱስ እና ሚስጥራዊ ስፍራ ነው። በጥንታዊው የ«ኢንካ» ስልጣኔ አፈ-ታሪክ መሰረት፣ የዓለም ፍጥረት የተጀመረው ከዚሁ ሀይቅ ነው። የፀሀይ አምላክ የመጀመሪያዎቹን የኢንካ ነገስታት (ማንኮ ካፓክ እና ማማ ኦክሎን) የፈጠረው በዚህ ሀይቅ ውስጥ በምትገኘው «ኢስላ ዴል ሶል» የፀሐይ ደሴት) ላይ ነው ተብሎ ይታመናል። ዛሬም ድረስ በሀይቁ ላይ የሚኖሩ ማህበረሰቦች ከ«ቶቶራ» ከተባለ ልዩ የቄጠማ ዝርያ የሚሰሯቸው ባህላዊ ጀልባዎች በሀይቁ ላይ ሲንሳፈፉ ማየት፣ ዘመንን ወደ ኋላ የሚመልስ የውበት እና የታሪክ መገለጫ ነው። ይህ ሀይቅ የላፓዝን ዙሪያ ገባ ተፈጥሯዊ ሀብት ወደር የለሽ እና መንፈሳዊ ያደርገዋል።
በዚህ አስደናቂ የተፈጥሮ ስፍራ የሚኖሩት የላፓዝ ዜጎች (በአካባቢው አጠራር “ፓሴኞስ”) ማህበረሰባዊ መስተጋብር እጅግ ጥልቅ ነው። አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ የ«አይማራ»፣ የ«ኬቹዋ» እና የስፔናውያን ቅልቅል የሆኑት የ«ሜስቲዞ» አባላት ናቸው። በዚህ ከፍተኛ ስፍራ ላይ፣ ስስ በሆነው ኦክስጅን መኖር ይችል ዘንድ የህዝቡ የሰውነት ተፈጥሮ ራሱ አካላዊ ለውጥ አድርጓል፤ ሳንባዎቻቸው ሰፋ ያሉ እና በደማቸው ውስጥ ያለው የቀይ የደም ሴል መጠን ከፍተኛ ነው። የላፓዝ ማህበረሰብ «አይኒ» በሚባል የቆየ የአንዲያን የጋራ መረዳዳት ፍልስፍና ይተዳደራል። ይህ መርህ “ዛሬ ላንተ፣ ነገ ለእኔ” የሚል ትርጉም ሲኖረው፣ ህዝቡ በማህበራዊ ስራዎች እና በችግር ጊዜ እንዴት በህብረት እንደሚቆም ያሳያል።
የላፓዝ ህዝብን ማንነት በግልፅ ከሚያሳዩት መገለጫዎች መካከል «ቾሊታስ» በመባል የሚታወቁት አይማራ ሴቶች ቀዳሚዎቹ ናቸው። የነዚህ ሴቶች አለባበስ እና አቋም የከተማዋ ህያው ቀለም ነው። ቾሊታዎች በራሳቸው ላይ «ቦውለር» የተሰኘ አነስተኛ ባርኔጣ፣ ትከሻቸው ላይ ደማቅ ቀለም ያለው «ማንታ» የተሰኘ በርካታ ንብርብር ያለው «ፖዬራ» የተባለ ሰፊ ቀሚስ ይለብሳሉ። ፀጉራቸውን በሁለት ጎን በመገመድ ጫፉን በጥቁር ሱፍ ያስራሉ።
ከታሪክ አኳያ እነዚህ ሴቶች በህብረተሰቡ ዘንድ እንደ ኋላቀር ተቆጥረው ከፍተኛ መገለል ይደርስባቸው ነበር። ነገር ግን በቅርብ አስርት ዓመታት ውስጥ፣ ቾሊታዎች ታሪካቸውን ቀይረው የቦሊቪያ የኢኮኖሚ ሞተር እና የጥንካሬ ተምሳሌት ሆነዋል። ዛሬ ላይ በቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት፣ በጠበቃነት፣ በፖለቲካው መድረክ፣ አልፎ ተርፎም «ቾሊታስ ሉቻዶራስ» በመባል በሚታወቀው የነፃ ትግል ስፖርት ውስጥ ሰፊ ቀሚሳቸውን እያውለበለቡ በመታገል ዓለም አቀፍ ትኩረትን ስበዋል።
ላፓዝ ሚስጥራዊ እና መንፈሳዊ ከተማም ጭምር ናት። የላፓዝ ህዝብ እምነት የካቶሊክ ክርስትና እና የጥንታዊ አንዲያን መንፈሳዊነት (የእናተ ምድር – ፓቻማማ አምልኮ) ጥልቅ ውህድ ነው። የዚህ ማሳያ በከተማዋ መሃል የሚገኘው ታዋቂው «የጠንቋዮች ገበያ» ነው።
በዚህ ገበያ ውስጥ፣ በባህላዊ ህክምና ባለሙያዎች የሚሸጡ የተለያዩ የደረቁ የላማ ፅንሶች በስፋት ይገኛሉ። በአካባቢው እምነት መሰረት፣ አንድ ሰው አዲስ ቤት ሲገነባ የላማውን ፅንስ በመሬት ውስጥ ከቀበረ፣ ለፓቻማማ እንደ መስዋዕት ተቆጥሮ ቤቱን ከክፉ ነገር ይጠብቃል። ከዚህም ጋር በተያያዘ «የኮካ ቅጠል» ለነዋሪው የተቀደሰ እና የዕለት ተዕለት ህይወት አካል ነው። ቅጠሉን ማኘክ የከፍታ ህመምን (ሶሮቼን) ለማስታገስ፣ ጉልበት ለማግኘት እና ለመንፈሳዊ ስነ-ስርዓቶች በስፋት ያገለግላል።
ላፓዝ ታሪኳን እና ባህሏን ሳትለቅ ዘመናዊነትን በሚያስደንቅ ሁኔታ የተቀበለች ከተማ ናት። የላፓዝ መልክዓ ምድር እጅግ ዳገታማ በመሆኑ፣ ከተማዋ በዓለማችን እጅግ አስደናቂ የሆነውን የኬብል መጓጓዣ ስርዓት «ሚ ቴሌፌሪኮ» ገንብታለች። በሰማይ ላይ የተዘረጉት የኬብል መኪኖች ከተማዋን በአየር ላይ ያገናኛሉ። በዚህ መጓጓዣ ውስጥ ቾሊታዎች፣ የቢሮ ሰራተኞች እና ቱሪስቶች አብረው ተቀምጠው የከተማዋን እና የኢሊማኒ ተራራን ግርማ ከላይ ሆነው ይመለከታሉ።
የከተማዋን የነፃነት ስሜት እና ፀረ-ቅኝ ግዛት አቋም ከሚያሳዩት ነገሮች አንዱ በ«ፕላዛ ሙሪዮ» በሚገኘው የብሄራዊ ምክር ቤት ህንፃ ላይ ያለው ሰዓት ነው። የዚህ ሰዓት ቁጥሮች የተፃፉት በተቃራኒው (ከቀኝ ወደ ግራ) ሲሆን፣ ጠቋሚዎቹም ወደ ኋላ ነው የሚሽከረከሩት። ይህ «የደቡብ ሰዓት» የላፓዝ ህዝብ በውጭ ሀይሎች የጊዜ ፍልስፍና እንደማይገዛ የሚያሳይ ነው። በየዓመቱ የሚከበረው ታላቁ «የግራን ፖደር ፌስቲቫል» ዳንሰኞች በወርቅ የተጠለፉ ልብሶችን ለብሰው ጎዳናዎችን የሚያደምቁበት፣ በማለዳ የሚሸተው የ«ሳልቴኛ» (ጣፋጭ የስጋ ቂጣ) ጠረን ደግሞ የከተማዋ የዕለት ተዕለት የምግብ ትርታ ነው።
ምንጭ፦ የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሰነዶች፤ ሎንሊ ፕላኔት፣National Geographic፣ ግርሃም ሀንኩክ፣ ዘ ፊንገርፕሪንትስ ኦፍ ጋድስ፣ የቦሊቪያ የባህል ሚኒስቴር መረጃዎች፣ Lonely Planet እና የBBC Travel ዘገባዎች፣ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ
አጫጭር መሰረታዊ መረጃዎች ስለ ቦሊቪያ፡-
- ቦሊቪያ በደቡብ አሜሪካ ትገኛለች፤ ብራዚልን፣ አርጀንቲናን፣ ፔሩን፣ ቺሊን እና ፓራጓይን ታዋስናለ፤ቦሊቪያ በደቡብ አሜሪካ ከሚገኙ ሁለት “ወደብ አልባ” (የባህር በር የሌላቸው) ሀገራት አንዷ ናት።
-ቦሊቪያ ሁለት ዋና ከተሞች አሏት፤ እነሱም ሱክሬ እና ላፓዝ ናቸው፡፡
-የህዝብ ብዛቷ 12 ሚሊዮን ይገመታል።
- ቦሊቪያ በዓለም ላይ ብዙ ይፋዊ ቋንቋዎች ካላቸው ሀገራት አንዷ ናት። ከስፓኒሽ (Spanish) በተጨማሪ 36 የሚሆኑ ሀገር በቀል አሏት።
- ቦሊቪያ ከስፔን ቅኝ ግዛት ነፃነቷን በ1825 እ.አ.አ አውጃለች።
- ሳላር ዴ ኡዩኒ የተባለው በዓለማችን ላይ ትልቁ የጨው ሜዳ በዝናብ ወቅት ወደ ግዙፍ የተፈጥሮ መስተዋትነት ይቀየርና ሰማዩን ከምድር ጋር ያመሳስለዋል።
-ቦሊቪያ በዓለማችን ላይ ካሉ እጅግ ግዙፍ የሊቲየም ማዕድን ክምችት ባለቤቶች አንዷ ናት፤ በተጨማሪም የተፈጥሮ ጋዝ፣ ብር እና ዚንክ በሰፊው ይመረታል።
(መሰረት ቸኮል)
በኲር የሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


