የብድር ተጽዕኖ በአፍሪካ ሀገራት ያሳደረው ጫና

0
207

የአፍሪካ ሀገራት በአሁኑ ወቅት የተሸከሙት ከፍተኛ የውጭ ብድር በኢኮኖሚያቸው፣ በማኅበራዊ ዕድገታቸው እና በፖለቲካዊ ነፃነታቸው ላይ ከባድ እና ዘርፈ-ብዙ ተጽዕኖ እያሳደረባቸው ይገኛል፡፡ በተለይም እንደ ቻይና ያሉ አዳዲስ አበዳሪዎች እና የአውሮፓ ሀገራት (ፓሪስ ክለብ፡- በዓለም ላይ ያሉ ባለሀብት እና በብዛት ምዕራባውያን የሆኑ አበዳሪ ሀገራት የተሰባሰቡበት መደበኛ ያልሆን ቡድን ነው) ዋና ዋና የገንዘብ ምንጮች ሲሆኑ ይህንን የብድር ፍላጎት ተገን በማድረግ የየራሳቸውን ስትራቴጂካዊ ፍላጎቶች እያስፈጸሙበት ይገኛሉ።

የውጭ ብድር በአፍሪካ ሀገራት ላይ እያሳደረ ያለው ተፅዕኖ

ሀገራቱ የሚያገኙትን አብዛኛውን ገቢ ለጤና፣ ለትምህርት እና ለንጹሕ መጠጥ ውኃ አገልግሎት ከማዋል ይልቅ የብድር ወለድ ለመክፈል እንዲያውሉ መገደዳቸው የማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲዳከሙ እያደረገ ነው። ሀገራት የወሰዱትን ብድር በዶላር ወይም በሌሎች የውጭ ገንዘብ ስለሚከፍሉ የውጭ ምንዛሬ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሲሉ የሀገር ውስጥ ገንዘባቸውን ዋጋ እንዲቀንሱ ያደርጋል፤ ይህም ከፍተኛ የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበትን ያስከትላል።

ሀገራቱ አዲስ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እና መሠረተ-ልማቶችን ለመገንባት ያላቸውን አቅም ስለሚያዳክም አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገታቸው እንዲቀዘቅዝ እያደረገው ነው።

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለማድረግ እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ከሁለት ዓመታት በላይ ከውጭ አበዳሪዎች እና ከዩሮቦንድ ባለቤቶች ጋር ረጅም እና አድካሚ የብድር ሽግሽግ ድርድር ለማድረግ ተገድደዋል።

ቻይና ብድሩን ተገን በማድረግ ምን እየሠራች ነው?

ቻይና ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ለአንጎላ፣ ለኮንጎ… የምትሰጠው ብድር በተፈጥሮ ሀብት የሚከፈል በመሆኑ የአፍሪካን የነዳጅ፣ የኮባልት እና የክሮሚየም ማዕድናት በቀጥታ የማግኘት መብት አግኝታለች። ቻይና የምትሰጠው  ብድርም አብዛኛውን ጊዜ  ከኩባንያዎቿ ጋር የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ይህን ተከትሎም በአፍሪካ የሚገነቡ እንደ ባቡር መስመር፣ የኀይል ማመንጫ እና የቴሌኮም መሠረተ-ልማቶችን የቻይና ኩባንያዎች እንዲረከቡት በማድረግ የራሷን የሀገር ውስጥ ምርት እና የሥራ ዕድል ታነቃቃለች።

ቻይና በአፍሪካ ያላትን የኢኮኖሚ የበላይነት በመጠቀም በዓለም አቀፍ መድረኮች (ለምሳሌ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት) የአፍሪካ ሀገራት ለቻይና የፖለቲካ አቋሞች (እንደ አንድ ቻይና ፖሊሲ) ድጋፍ እንዲሰጡ ታደርጋለች።

የአውሮፓ ሀገራት እና ምዕራባውያን ብድሩን ተገን በማድረግ ምን እየሠሩ ነው?

የአውሮፓውያን እና የምዕራባውያን ተቋማት (IMF እና የዓለም ባንክ) ብድር ወይም የብድር ማሻሻያ ለመፍቀድ እንደ ቅድመ-ሁኔታ የሀገር ውስጥ ገበያን ለውጭ ውድድር ክፍት ማድረግ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን መሸጥ እና የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን ማድረግን የመሳሰሉ ከባድ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ያስገድዳሉ። የአውሮፓ ሀገራት ብድራቸውን ተገን በማድረግ በአፍሪካ ያሉ ነባር የጥሬ ዕቃ አቅራቢዎቻቸውን ለማስጠበቅ እና የራሳቸውን ምርቶች ወደ አፍሪካ ገበያ የሚያስገቡበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ።

ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በአፍሪካ እና በኢትዮጵያ የውጭ ብድር ቀውስ ዙሪያ የሚያወጧቸው ዘገባዎች የአበዳሪዎችን ስትራቴጂካዊ ፍላጎት እና የአፍሪካን የወደፊት እጣ ፈንታ በተመለከተ በሦስት ዋና ዋና ጎራዎች ከፍለው ይተነትኑታል።

የሮይተርስ  የቅርብ ጊዜ የመረጃ ትንተና እንደጠቆመው በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ሀገራት አዲስ ብድር ከማግኘት ይልቅ ለቻይና የሚከፍሉት የዕዳ ክፍያ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ይህ ማለት አፍሪካውያን ወደ ቻይና የሚልኩት ገንዘብ ከቻይና ወደ አፍሪካ ከሚመጣው ይበልጣል።

አልጀዚራ ባወጣው ዘገባ ደግሞ አፍሪካን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ያሉ 75 ደሃ ሀገራት ባለፉት አስርት ዓመታት ከቤልት ኤንድ ሮድ (Belt and Road) ፕሮጀክት የወሰዱት ብድር የመክፈያ ጊዜው በመድረሱ ከፍተኛ የክፍያ ጫና ውስጥ መውደቃቸውን ዘግቧል። ይህ ጫና ሀገራቱ ለትምህርት እና ለጤና የሚመድቡትን በጀት ለቻይና እዳ ክፍያ እንዲያውሉ እያስገደዳቸው መሆኑን ሚዲያዎቹ አስገንዝበዋል።

የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ትንተና እንደሚያሳየው ቻይና አሁን ላይ ለአዳዲስ እና ሰፋፊ መሠረተ-ልማት ለመገንባት ምትሰጠውን ብድር በመቀነስ  ለአረንጓዴ ኢነርጂ ወሳኝ የሆኑ እንደ ኮባልት፣ ሊቲየም እና ክሮሚየም ያሉ  የአፍሪካ ማዕድናትን በቀጥታ የማግኘት መብት  ላይ ማተኮሯን ዘግበዋል።

ሞደርን ጋና እና መሰል ሚዲያዎች እንደዘገቡት አሜሪካ እና አውሮፓ የአፍሪካ ሀገራትን የብድር እዳ እንደ ፖለቲካዊ መሣሪያ በመጠቀም የቻይናን የማዕድን የበላይነት ለመስበር አዳዲስ ስትራቴጂካዊ የማዕድን ጥምረት ለመፍጠር እየሞከሩ ነው። በዚኅም አፍሪካ በሁለቱ ኀያላን (ቻይና እና ምዕራባውያን) ፉክክር መካከል መዳከሟን ይተነትናሉ።

የኬንያን ዎልስትሪት  እና ሮይተርስ እንደዘገቡት አይኤምኤፍ (IMF) ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የ468 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ቢፈቅድም ይህ የተደረገው ግን ሀገሪቱ በምዕራባውያን ተቋማት ግፊት ያደረገችውን የማክሮ-ኢኮኖሚ ሪፎርም (የገንዘብ ተመን በገበያ እንዲወሰን የማድረግ ፖሊሲ) ተከትሎ የመጣውን የሀገር ውስጥ የኑሮ ውድነት ተቋቁማ መሆኑን ሚዲያዎቹ ይገልጻሉ። ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አፍሪካን እንደ “ካፒታል ላኪ” መመልከት የጀመሩ ሲሆን አበዳሪዎች የሰጡትን ብድር መልሰው እየሰበሰቡ እንጂ ለአፍሪካ አዲስ የልማት ፈንድ እያቀረቡ እንዳልሆነ በስፋት እየተነተኑት ይገኛሉ።

ሴሸልስ እ.አ.አ በ2008 የውጭ ዕዳዋ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ምርት (GDP) በላይ 175 በመቶ ደርሶ ከነበረበት የኢኮኖሚ ውድቀት ያገገመችው ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ጋር በመሆን የሀገሪቱን ገንዘብ ዋጋ በገበያ እንዲወሰን በማድረጓ እና ጠንካራ መዋቅራዊ ሪፎርም በመተግበሯ ነው። ሀገሪቱ ከፓሪስ ክለብ የ45 በመቶ የብድር ስረዛ ከማግኘቷም በላይ የውጭ ዕዳዋን በከፊል ለአካባቢ ጥበቃ ፈንድ የሚሆን የገንዘብ ሽግሽግ በማድረግ  ወደ 50 በመቶ ዝቅ ማድረግ ችላለች፤ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ከፍተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢ ካላቸው ግንባር ቀደም ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ አድርጓታል።

ጋና በበኩሏ እ.አ.አ በ2022 የውጭ ዕዳዋ 70 ቢሊዮን ዶላር ደርሶባት የዋጋ ግሽበቱ 50 በመቶ አልፎ ዕዳ መክፈል አቁማ ነበረ፤ የሀገር ውስጥ የቦንድ ልውውጥ በማድረግ እና በጂ20 (G20) መዋቅር ሥር በመግባት ቀውሱን ተቋቁማለች። ጋና ከሁለትዮሽ አበዳሪዎቿ (ከፓሪስ ክለብ እና ቻይና) የአምስት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር የብድር ሽግሽግ ስምምነት አግኝታለች፡፡ ከግል ዩሮቦንድ ባለቤቶች ጋርም የ13 ቢሊዮን ዶላር ዕዳዋን በ37 በመቶ ቅናሽ ለማሻሻል በመስማማቷ ምንም እንኳ ማሻሻያው በሕዝቡ ላይ የኑሮ ውድነት ቢያስከትልም ሀገሪቱን ከፍጹም ውድቀት አድኖ የኢኮኖሚ ጥንካሬዋ እንዲመለስ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ማሳያ

የኢትዮጵያ መንግሥት ከፈረንሳይ (የፓሪስ ክለብ ሰብሳቢ) እና ከቻይና ጋር የሁለትዮሽ የብድር ሽግሽግ ስምምነቶችን መፈራረሟን ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሚዲያዎች በሰፊው ዘግበውታል። ይህ ስምምነት በጂ20 መዋቅር ሥር እንደ ትልቅ ምዕራፍ ተወስዷል። ኢትዮጵያ ከቻይና፣ ከፈረንሳይ (የፓሪስ ክለብ ሰብሳቢ) እና ከግል አበዳሪዎች ጋር ያደረገችው የብድር ሽግሽግ ሂደት የዚህ ማሳያ ነው። በቅርቡ በ2026 ዓ.ም ኢትዮጵያ ከፈረንሳይ እና ከቻይና ጋር የሁለትዮሽ የብድር ማሻሻያ ስምምነቶችን የተፈራረመች ሲሆን ከተበደረችው አንድ ቢሊዮን ዶላር የዩሮቦንድ ባለቤቶች ጋርም መሠረታዊ ስምምነት ላይ መድረስ ችላለች።

ይህን የብድር ስምምነት እንድታገኝ ግን ሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ማሻሻያ (የማክሮ-ኢኮኖሚ ሪፎርም) እንድታደርግ በምዕራባውያን ተቋማት በኩል ግፊት ተደርጎባታል። በተጨማሪም በጥናት እንደተጠቆመው ኢትዮጵያ ከቻይና ያገኘችውን ብድር  ከዶላር ወደ ቻይናውያን ገንዘብ (ዩዋን) በመቀየር እስከ 778 ሚሊዮን ዶላር ማዳን የምትችልበትን ዕድል ለመጠቀም እየገፋችበት ይገኛል፤ ይህም የቻይና ገንዘብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ተቀባይነት ከፍ ለማድረግ ይረዳል።

የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ብድርን ለመሠረተ-ልማት ግንባታ ቢጠቀሙበትም በአሁኑ ወቅት ግን ብድሩ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታቸውን የሚጋፋ እና አበዳሪዎች የራሳቸውን ስትራቴጂካዊ ጥቅም የሚያስከብሩበት ዋነኛ መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የሐምሌ 13  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here