ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!

0
199

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማእከል መካሄድ ጀምሯል፡፡ በመላ ሀገሪቱ የተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ አጀንዳዎችን የመሰብሰብ ሥራን ያጠናቀቀው ኮሚሽኑ ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም አራት ሺህ ተሳታፊዎች በተገኙበት ዋናውን ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በይፋ ጀምሯል፡፡

በምክክር ጉባኤው ማስጀመሪያ ሥነ ስርዓት ላይ ከሀገር ውስጥ ታዳሚዎች በተጨማሪ የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ)፣ ኤምባሲዎች፣ የውጭ ሀገር የተለያዩ ዲፕሎማቶች እና  ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡ ከአራት ዓመታት በፊት የተቋቋመው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ ውስጥ አወዛጋቢ ናቸው የተባሉ ጉዳዮችን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እና በውጭ ሀገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን አጀንዳዎችን ማሰባሰቡን ልብ ይሏል፡፡

በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እየተፈጠረ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ልዩነት ለመፍታት በሚል ታኅሣሥ 20 ቀን 2014 ዓ.ም የተመሠረተው ኮሚሽኑ የጀመረው የምክክር መድረክ  ከሦስት እስከ አራት ሳምንታት የሚቆይ ይሆናል፡፡

 

ለመሆኑ ሀገራዊ  ምክክር ምንድን ነው?  መቼ ያስፈልጋል?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ  ሀገራዊ ምክክር ማለት በአዋጁና የኮሚሽነሮች ምክር ቤት በሚያወጣው መመሪያ መሠረት በሚለዩ አጀንዳዎች ላይ በተለያዩ አካላት ውይይት እንዲደረግባቸው የኮሚሽኑ ምክር ቤት በፌዴራልና በክልሎች የሚያመቻቸው ውይይቶች እንደሆኑ አብራርቷል፡፡

ሀገራዊ ምክክር በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል የሀሳብ ልዩነቶች ሲፈጠሩ፣ በከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ወቅት፣ ከጦርነት በኋላ በተከሰቱ ሁኔታዎች ወይም ሰፊ የፖለቲካ ሽግግሮች ውስጥ ባሉ በርካታ ባለድርሻ አካላት መካከል መግባባት ለመፍጠር ሲታሰብም ይካሄዳል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጭር ጉዞ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞ ውስጥ የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ተስፋ የተጣለበት ተቋም ነው፡፡ ኮሚሽኑ የካቲት 2014 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኮሚሽነሮች ከተሾሙለት ጊዜ ጀምሮ ሀገራዊ ምክክሩን ለማድረግ የሚያስፈልጉ በርካታ ዝግጅቶችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ አካታችነት፣ ግልጸኝነት፣ ተአማኒነት፣ ብሔራዊ ጥቅም፣ ገለልተኛ አመቻችነትን ጨምሮ 11 መርሆችን በመያዝ ሥራውን ጀምሯል፡፡

ኮሚሽኑ ባሳለፈው የአራት ዓመታት ጉዞ በአራት ዋና ዋና ምዕራፎች ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ የመጀመሪያው የኮሚሽኑ የጉዞ ምዕራፍ የቅድመ ዝግጅት ወቅት ነበር፡፡ በዚህ ወቅት በአዋጁ መሠረት አስራ አንዱ ኮሚሽነሮች በየካቲት 14 2014 ዓ.ም እንደተሰየሙለት ከሁለት ቀናት በኋላ  ስራዉን ጀምሯል፡፡ ከዚሁ በተጓዳኝም ኮሚሽኑ የተቋቋመበትን ዓላማ፣ የተሰጡትን ተግባራትና ኃላፊነቶች እንዲሁም የሚጠበቁበትን ውጤቶች በተመለከተ የአዋጁን ይዘትና አውድ በአግባቡ ለመረዳት ሰፊ ጥረት ተደርጓል፡፡ በዚህም አዋጁን በማርቀቅና በማጽደቅ ሂደት ዋነኛ ተዋናይ ከነበሩ የፍትህ ሚኒስቴር የሥራ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ምክክር ተደርጓል፡፡

ሁለተኛው ምዕራፍ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የነበረ ሲሆን ኮሚሽኑ አጀንዳዎችን ለመሰብሰብ በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሲቪክ ማሕበራት፣ ከአካባቢ ሽማግሌዎች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከዲያስፖራዎች ጋር ባደረገው ውይይትም ለምክክር ጉባኤው የሚቀርቡ አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡

በአጀንዳ ማሰባሰቡ ሂደት ላይ የተሳተፉት ባለድርሻ አካላት ስብጥርና ብዛት  21 የክልልና ከተማ መስተዳደር፣ 38 የፌዴራል እና ስምንት የዲያስፖራ ባለድርሻ አካላት ተለይተው ተሳትፈዋል፡፡ በተለይም 19 ሺህ 624 የኅብረተሰብ ክፍል ወኪሎች፣ 673 የፖለቲካ ፓርቲ ወኪሎች፣ 2ሺህ649 ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እና 1ሚሊዮን 165 የዲያስፖራ ማኅበረሰብ ወኪሎች መሳተፋቸው የተገፋ ወይም ድምፅ አልባ የተደረገ የኅብረተሰብ ክፍል እንዳይኖር የተደረገው ከፍተኛ ጥረት ነው፡፡ 673 የፖለቲካ ፓርቲ ወኪሎች መገኘታቸው ደግሞ የሐሳብ ብዝኃነትን ከማረጋገጡም በላይ ፖለቲካዊ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ባህል እየተለመደ መምጣቱን ያበስራል፡፡

ሦስተኛው ምዕራፍ የዝግጅት ወቅት ደግሞ የመረጃ ትንተና እና የአደረጃጀት ሥራዎችን በመሥራት፣ የተሰበሰቡት አጀንዳዎችን በመመርመር እና በመለየት የሀገር አቀፍ የምክክር አጀንዳዎች እንዲሆኑ የማድረግ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡ የተሰበሰቡት አጀንዳዎች የሀገሪቱን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እንዲሁም  የማሕበራዊ ጥያቄዎችን ያካተቱ ሲሆን፤ የጸጥታ ጉዳይ እና መሰል አጀንዳዎችንም  ሰብስቧል፡፡

በዚህ  ምዕራፍ ለጉባኤው መካሄድ አስፈላጊ የሆኑ ዋና ዋና ተግባራትን ኮሚሽኑ ያከናወነበት ሲሆን በዋናነትም ከመላ ሀገሪቱ የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን በማጣመር እና በማግባባት  ስምንት አጀንዳዎችን ይፋ አድጓል፡፡ በዚህም የሀገር ግንባታ ጉዳይ፣ የመንግሥት አደረጃጀትና ስርአት ጉዳይ፣ የፌዴራል ከተሞች ማለትም የአዲስ አበባ እና ድሬድዋ ጉዳይ፣ የሃይማኖት ጉዳዮች፣ የተቋማት ግንባታ፣ የሕግ የበላይነት እና ሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ፣ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደር ጉዳዮች፣ ሙስና እና የመልካም አስተዳዳር ጉዳዮች እንዲሁም የሰላም ግንባታ ጉዳዮች የሚመከርባቸው አጀንዳዎች እንደሚሆኑ ገልጿል፡፡

አራተኛው አሁን ላይ የተጀመረው የመጨረሻው ምዕራፍ የምክክር ጉባኤው መካሄድ ነው፡፡ ምክክሩ ከ150 በላይ አማካሪዎችና ከ70 በላይ የባለድርሻ አካላት ወኪሎች የሚገኙበት ትልቁ የዴሞክራሲያዊ ውይይት መድረክ ነው፡፡ የውይይቱን ውጤታማነትና ትኩረት ለመጠበቅ ሲባል እያንዳንዳቸው 500 ተመካካሪዎቹ የያዙ ስምንት ንዑስ ቡድኖች  ተዋቅረዋል፡፡

ስለ ሀገራዊ ምክክሩ ማን ምን አለ?

ጠቅላይ ሚኒሥትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀገራዊ  የምክክር ሂደቱን አስመልክተው ለመላው ኢትዮጵያውያን ባስተላለፉት መልእክት ምክክሩ ፍቱን የፖለቲካ መድረክ ብቻ ሳይሆን የአሁን እና የመጪውን ትውልድ እጣ ፈንታና የወደፊት ተስፋ ሙሉ በሙሉ የሚወስን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ነው፡፡   “ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋትና ሁለንተናዊ ብልጽግና የምትተጉ፣ የኢትዮጵያ ታላቅነት ግድ የሚላችሁ ሁሉ ፈረሱም ሜዳውም ይኸው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒሥትሩ ሕዝቡ ኃላፊነት ስላለበት የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ “ትናንት አባቶቻችንና እናቶቻችን በዓድዋ ለሀገር ነጻነት፣ ለሉዓላዊነትና ለክብር ሲሉ በደማቸውና በአጥንታቸው እንደተዋደቁላት ሁሉ ዛሬም ኢትዮጵያ የታሪክ አደራ የሚሸከሙ የቁርጥ ቀን ልጆቿን ትፈልጋለች” ሲሉም በማሕበራዊ የትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

“አዲሱ የኢትዮጵያ ታሪክ በውይይትና በንግግር ተጽፎ ዘላቂ ሰላም እንደሚያመጣ ሙሉ እምነት አለኝ፤ ኢትዮጵያ የራሷን ቁስል የምታክምበት ቁልፍ በእጇ ላይ ነው በማለት ንግግር ያደረጉት ደግሞ የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ክቡር ወርቅነህ ገበየሁ በሀገራዊ ምክክር መክፈቻ ሥነ ስርዓት ላይ ባስተላለፉት መልእክት በዓለም ታሪክ ውስጥ በግጭት የተገነባ ወይም ያተረፈ ሀገር አለመኖሩን አስገንዝበዋል፡፡ ዋና ፀሐፊው በፖለቲካ ባህል ውስጥ ልዩነቶች መኖራቸው ተፈጥሮአዊ ቢሆንም፤ ትልቁና መሰረታዊው ስህተት ግን እነዚህን ልዩነቶች በኃይል ለመፍታት መሞከር እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ ከሁሉ በላይ ልዩነቶችን መፍታት የሚቻለው በሰላማዊ መንገድ፣ በመነጋገርና በተለያዩ ሰላማዊ መድረኮች መሆኑን ዋና ፀሐፊው አብራርተዋል ፤ ኢትዮጵያም ለዚህ የሚሆኑ በርካታ ባህላዊ የምክክር መንገዶች ያሏት ሀገር መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡

የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት እና የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልክተኛ ክቡር ቺፍ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በሀገራዊ ምክክር ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ የህዝቦቿን ብዝሃነትና ታታሪነት በመጥቀስ ይህ ህዝብ የሰነቀውን ብሩህ ተስፋ ለማሳካት ደግሞ አሁን የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ስኬት ቁልፍ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በአጠቃላይ ሀገራዊ ምክክሩ አሁን ያለውን የኢትዮጵያዊያንን ችግር ይቀርፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here