ተጠያቂው ማነው?

0
205

የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ወሳኝ ሚና ያላቸውን  ግብዓቶች (ምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያ እና ኬሚካል…) ጥራት እና ሕጋዊ ስርጭት ለማረጋገጥ በ2018 በጀት ዓመት ሰፊ የቁጥጥር እና የሕግ ማስከበር ሥራዎች መከናወናቸውን የአማራ ክልል የግብርና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታውቋል። የምርጥ ዘር እና ችግኝ ጥራት ቁጥጥርን በተመለከተ ከዚህ ቀደም የነበሩ የአሠራር ክፍተቶችን በማረም በዚህ ዓመት ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን የባለሥልጣኑ ኃላፊ አቶ ፈንታሁን ስጦታው ለበኵር ተናግረዋል። ጥራቱ ያልተረጋገጠ ምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እንዳይሰራጭ ጥብቅ ቁጥጥር መደረጉንም አብራርተዋል፡፡

ኃላፊው ይህንን ያሉት ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የ2018  በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡ ሕገ-ወጥ የግብዓት ዝውውርን ከመግታት አኳያ በተለይም በአርሶ አደሩ ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እና የምርት ብክነትን ሲያስከትሉ የነበሩ ሕገ-ወጥ የግብርና ግብዓት አቅራቢዎች ላይ ጥብቅ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል።  በበጀት ዓመቱ በተደረገ ክትትልም  አንድ ሺህ 600 ኩንታል የሚጠጋ ሕገ-ወጥ ማዳበሪያ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ስር በማዋል በፍርድ ቤት ውሳኔ ሕጋዊ እርምጃ ተወስዷል፡፡ በተጨማሪም ጥራታቸው ያልተጠበቀ እና በሕገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የተያዙ ዘጠኝ ሺህ 227 ሊትር የጸረ-ተባይ እና ጸረ-አረም ኬሚካሎች በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል፡፡ ይህን ድርጊት ሲፈፅሙ የነበሩ ድርጅቶችም እንዲታሸጉ ተደርጓል።

የምርጥ ዘር እና የችግኝ ጥራት ቁጥጥር ከዚህ ቀደም የዘር ጥራት ቁጥጥር ሥራው የታችኛውን እርከን ያላካተተ እንደ ነበር ኃላፊው አስታውሰዋል፡፡ በ2018 በጀት ዓመት ግን እስከ ወረዳ እና ቀበሌ ድረስ በመውረድ ከ10 ሺህ 814 ሄክታር በላይ የዘር ብዜት ማሳ ላይ ጥብቅ የጥራት ቁጥጥር መደረጉን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ከ16 ሺህ ኩንታል በላይ ዘር በማሳ ደረጃ እንዲሁም ተጨማሪ 16 ሺህ ኩንታል ዘር በላቦራቶሪ ፍተሻ ተደርጎ ውድቅ ሆኖል፡፡

በውይይቱ የዘር ጥራት ተቆጣጣሪዎች ወደ አርሶ አደሩ ማሳ በመውረድ በጂፒኤስ (GPS) እና በዳታ ቤዝ የታገዘ የጥራት ቁጥጥር ማድረጋቸው እንደ ትልቅ ስኬት ተነስቷል። በአጠቃላይ በማሳ እና በላቦራቶሪ የዘር ጥራትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ፍተሻ መደረጉን ኃላፊው ተናግረዋል። በተጨማሪም በፍራፍሬ ችግኝ ልማት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ የተሠራ መሆኑን  የገለጹት አቶ ፈንታሁን፤ አሁን ላይም በ866 ሚሊዮን  ችግኞች ላይ የጥራት ቁጥጥር ተደርጎ ለተከላ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ስኬቶችን ቢያስመዘግብም አሁንም ዘመናዊ እና ደረጃውን የጠበቀ የግብርና ላቦራቶሪ አለመኖር ዋነኛ ተግዳሮት መሆኑን አስታውቋል፡፡ ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶችን ጥራት ለማረጋገጥ፣ የማዳበሪያ እና የኬሚካል ፍተሻዎችን በአግባቡ ለማካሄድ ዘመናዊ ላቦራቶሪ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ የጥናት ሰነድ ተዘጋጅቶ ለሚመለከተው የፋይናንስ ቢሮ መቅረቡን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱን የሰው ኃይል፣ ቁሳቁሰስ፣ ተሽከርካሪ እና መሰል ችግሮች ቢፈትኑትም አምስቱን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በመጠቀም ውጤታማ ተግባር መፈፀም መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በአማራ ክልል የግብርና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን በደሴ ከተማ   ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ባከናወነው ዘርፈ-ብዙ ተግባራት በክልል ደረጃ ከአቻ ተቋማት አንደኛ በመውጣት ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡ በውይይት መድረኩ ተነስቷል። ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ለላቀ ውጤት የበቃው በየደረጃው ያሉ አመራሮች እና ባለሙያዎች ያሳዩት ጠንካራ የቡድን ሥራ፣ ከሌሎች ተቋማት ጋር የነበረው ቅንጅት እንዲሁም ጠንካራ የክትትል እና ግምገማ ሥርዓት መሆኑ ተመላክቷል።

የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ብርሐኔ ገብሬ እንዳስታወቁት ጽ/ቤቱ በዋናነት በምርጥ ዘር ብዜት፣ በግብርና ኬሚካሎች ቁጥጥር፣ በማዳበሪያ አቅርቦት ሕጋዊነት እንዲሁም በችግኝ ጥራት ላይ ትኩረት አድርጎ ሠርቷል። አርሶ አደሩ ጥራቱን የጠበቀ ምርጥ ዘር እንዲያገኝ ከ222 ሺህ ኩንታል በላይ ዘር በላቦራቶሪ ተፈትሾ ማረጋገጫ ተሰጥቶታል።

በበጀት ዓመቱ ሌላው ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ሕገ-ወጥ የግብዓት ዝውውር ቁጥጥር ነው። በተለይም በአያያዝ፣ በአጠቃቀም እና በስርጭት ጉድለት ለካንሰር እና ለሌሎች ከባድ የጤና ችግሮች መንስኤ የሆኑ ሕገ-ወጥ የግብርና ኬሚካሎችን በድንበር አካባቢዎች ጭምር ከፖሊስ እና ከፍትሕ አካላት ጋር በመቀናጀት ጥብቅ ቁጥጥር ተደርጓል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም አርሶ አደሩን ከብዝበዛ ለመታደግ በተደረገ ክትትል ከ280 ኩንታል በላይ ሕገ-ወጥ ማዳበሪያ በቁጥጥር ስር ውሎ ወደ አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወደ መንግሥት ካዝና ገቢ መደረጉ የቁጥጥር ሥራው ምን ያህል ጥብቅ እንደነበር ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።

በእፀዋት ጤና እና ኳራንቲን ዘርፍም ፈጣን ስርጭት ያላቸውን አረሞች ለመከላከል በተሠራው ሥራ ከ107 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከአረም የጸዳ እንዲሆን ተደርጓል። በተጨማሪም ከ216 ሚሊዮን በላይ የደን እና የፍራፍሬ ችግኞች የጥራት እና የጤንነት ማረጋገጫ ተሰጥቷቸዋል።

ምንም እንኳን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ይህንን ውጤት ቢያስመዘግብም የሥራው ሂደት ግን አልጋ በአልጋ አልነበረም ነዉ ያሉት። ኃላፊው እንደገለጹት  የትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ እጥረት፣ የላቦራቶሪ ግብዓት ማነስ እንዲሁም የሕገ-ወጥ ደላሎች እና ነጋዴዎች ተፅዕኖ ዋነኛ ተግዳሮቶች ነበሩ። በቀጣይ የበጀት ዓመት ጽ/ቤቱ ያጋጠሙትን ማነቆዎች በመቅረፍ የአርሶ አደሩን የግብዓት ፍላጎትን በበለጠ መጠን ለማሟላት በትኩረት እንደሚሠራ አቶ ብርሐኔ አረጋግጠዋል።

በተመሳሳይ የአማራ ክልል የግብርና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን የደብረ ማርቆስ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ባደረገው ጥብቅ ክትትል ጥራቱን የጠበቀ ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ ከማድረጉም ባሻገር ሕገ-ወጥ የግብርና ግብዓቶች ዝውውርን በከፍተኛ ደረጃ መቆጣጠር መቻሉን አስታውቋል። የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ አለልኝ ነጮ ለበኩር እንደተናገሩት በበጀት ዓመቱ በተከናወነው የዘር ብዜት ማሳ የጥራት ቁጥጥር ሁለት ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ ፍተሻ አድርጓል። ከተፈተሸው ማሳ ውስጥ የጥራት ደረጃውን ያላሟላው 116 ሄክታር መሬት ውድቅ ተደርጓል፡፡ መመዘኛውን ካለፈው ማሳ ላይ የተሰበሰበ ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ደግሞ የላቦራቶሪ ፍተሻን አልፎ በወቅቱ ለአርሶ አደሩ እንዲሰራጭ ተደርጓል።

በማዳበሪያ ስርጭት ዙሪያም በምዕራብ እና በምሥራቅ ጎጃም ዞኖች ጥብቅ የቁጥጥር ሥራ መሠራቱን የተናገሩት ኃላፊው፤ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ የአፈር ማዳበሪያ ቦታዉ ድረስ በመገኘት ፍተሻ ተካሂዶ የጥራት ደረጃቸውን ያልጠበቁትን የመለየት ሥራ ተሠርቷል። በተለይም ክብደታቸው ያነሰ እና በእርጥበት ምክንያት የረጋ አንድ ሺህ ኩንታል  የአፈር ማዳበሪያ በቀጥታ ወደ አርሶ አደሩ እንዳይገባ ተከልክሎ ነበር፤ ይሁን እንጅ  የክብደት ማስተካከያ እና የማለስለስ ሥራ ከተሠራ በኋላ  ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተደርጓል።

ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ከሠራባቸው ጉዳዮች መካከል ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የተከናወነው ሕገ-ወጥ የግብርና ግብዓት ዝውውር ቁጥጥር ዋነኛው ነው። በበጀት ዓመቱ እስከ አንድ ሺህ 200 ኩንታል ምርጥ ዘር እንዲሁም እስከ አንድ ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር መያዙን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ዘንድሮ ሕገ-ወጥ የግብዓት ዝውውርን ለማስቀረት የተጠናከረ ቅንጅታዊ አሠራር ተግባራዊ ማድረግ በመቻሉ ነው፡፡ በቀጣይም ጽ/ቤቱ ከወረዳዎች ጋር ያለውን ቅንጅት በማጠናከር እና ባለሙያዎችን በተጠና የጊዜ ሰሌዳ ወደ ሥራ በማሰማራት አርሶ አደሩ ጥራቱን የጠበቀ ግብዓት ብቻ እንዲያገኝ ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ በበኩሉ በግብርናው ዘርፍ በሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ አሠራሮች ላይ ጥብቅ የቁጥጥር እና የእርምት እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን  የቢሮው ኃላፊ አቶ ብርሐኑ ጎሽም ለበኩር ጠቁመዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ማብራሪያ  የቢሮው ዋነኛ ተልዕኮ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ ሕገ-ወጥነትን መከላከል እና ጥፋተኞችን ተጠያቂ ማድረግ ነው፡፡ በዚህም መሰረት በነዳጅ፣ በንግድ እና በግብርና ዘርፎች ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም ቢሮው ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡

በግብርናው ዘርፍ በተለይም በምርጥ በዘር እና በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ላይ አሳሳቢ የሆኑ ሕገ-ወጥ ተግባራት እየተፈጸሙ መሆኑን ኃላፊው  ጠቁመዋል፡፡ ድርጊቱ ምርት እና ምርታማነትን ከመቀነስ ባሻገር በሰው ልጅ ጤና ላይ ከፍተኛ አደጋ እያስከተሉ በመሆኑ ቢሮው በመቅንጅት እየሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በተለይም በአፈር ማዳበሪያ ስርጭት ላይ በሕገ-ወጥ መንገድ ማጓጓዝ እና ዋጋን ያለአግባብ መጨመር እንደሚስተዋል የገለጹት አቶ ብርሐኑ፤ ከዚህም ባሻገር የአገልግሎት ጊዜው ያለፈበትን ማዳበሪያ ለገበያ ማቅረብ አርሶ አደሩን ለጉዳት መዳረግ  መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ፍትሕ ቢሮው በሁለት ዋና ዋና መንገዶች እየሠራ መሆኑ አሳውቀዋል።

ሕብረተሰቡ ከሕገ-ወጥ የግብርና ግብዓት (በተለይም የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ካለፈባቸው ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር) ግዥ ራሱን እንዲጠብቅ እና ከሕገ-ወጦች ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት እንዲያቋርጥ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን እና በማሕበራዊ ሚዲያዎች ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑንም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

ሌላው ሕገ-ወጥ ድርጊት በሚፈጽሙ አካላት ላይ ሕጋዊ ተጠያቂነትን የማስፈን ሥራ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ገልጸዋል፡፡ በዚህም  ጊዜው  ያለፈበትን ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ  በሚሸጡ ግለሰቦች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ሲሆን  ጥቅም ላይ ስለማይውሉም  እንዲወገዱ እየተደረገ ነው፡፡ በቀጣይም ይህን የመከላከል እና ተጠያቂነትን የማስፈን ሥራ ቢሮው አጠናክሮ እንደሚቀጥል ኃላፊው አስረድተዋል።

  መረጃ

የግብርና ግብዓት ቁጥጥሩ እንዴት ይከናወናል?

  • ምዝገባ እና ፈቃድ፦ ማንኛውም የግብርና ግብዓት ወደ ሀገር ከመግባቱ ወይም ከመመረቱ በፊት በኢትዮጵያ የግብርና ባለሥልጣን እና በሚመለከታቸው አካላት ይመዘገባል።
  • የላቦራቶሪ ፍተሻ፦ምርቶቹ ወደ ገበያ ከመሰራጨታቸው በፊት የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ መሆናቸው በላቦራቶሪ ይረጋገጣል።
  • የድንበር ቁጥጥር፦በጉምሩክ ኬላዎች በኩል ሕገ-ወጥ እና ያልተፈቀዱ ኬሚካሎች እና ዘሮች እንዳይገቡ ቁጥጥር ይደረጋል።
  • የገበያ ላይ ድንገተኛ ፍተሻ፦በየሱቆቹ፣ በመጋዘኖች እና በአከፋፋዮች በመዘዋወር የተበላሹ፣ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ወይም የተጭበረበሩ ምርቶች መኖራቸው ቁጥጥር ይደረግባቸዋል።

በአጠቃላይ የግብርና ግብዓት ቁጥጥር ከማሳ እስከ ላቦራቶሪ እና ከላቦራቶሪ ወደ ገበያ የሚደረግ ያልተቋረጠ ሰንሰላታዊ የጥንቃቄ እና የክትትል ስርዓት ነው። ጠንካራ የግብርና ግብዓት ቁጥጥር ሥርዓት መገንባት የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ፣ አርሶ አደሩን ለመደገፍ እና የዜጎችን ጤና ለመጠበቅ አይተኬ ሚና አለው።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here