የዓለም ዋንጫ “አጤሬራ”

0
204

ስፔን ከአሥራ ስድስት ዓመት በኋላ የዓለም ዋንጫ ባለቤት ሆናለች፡፡ ግላዲያተሮቹ-    ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር የተዘጋጀውን የደቡብ አፍሪካ የ2010 (እ.አ.አ) ዓለም ዋንጫ ካነሱ በኋላ በ2026 ካናዳ፣ ሜክሲኮ እና አሜሪካ በጥምረት ባዘጋጁት የዓለም ዋንጫ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ አሸናፊ ሆነዋል፡፡

አርጀንቲና በተከታታይ ለሁለት ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት የብራዚልን ስኬት ለመድገም ብትሞክርም ለስፔን ወጣቶች ስብስብ እጇን ሰጥታለች፡፡ አርጀንቲና ሦስት የዓለም ዋንጫዎችን የሳመች ሲሆን የ2022ቱን የኳታር የዓለም ዋንጫ በአምበሏ ሊዮኔል ሜሲ እየተመራች ብታነሳም አራተኛውን የዓለም ዋንጫን ግን ማንሳት ሳትችል ውድድሩን በሁለተኛነት አጠናቃለች፡፡

አፍሪካዊቷ ሞሮኮ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫም እስከ ሩብ ፍጻሜው ድረስ በመጓዝ አፍሪካን በመድረኩ ከወከሉት 10 ሀገራት ውስጥ የተሻለውን ውጤት አስመዝግባለች፡፡ ሞሮኮ በ2022ቱ የኳታሩ ዓለም ዋንጫ ለግማሽ ፍጻሜ በመድረስ በአፍሪካ ትልቁን ውጤት ያስመዘገበች ሀገር ናት፤ ሞሮኮ በኳታሩ የዓለም ዋንጫ በግማሽ ፍጻሜ የተሸነፈችው በፈረንሳይ ሲሆን በዘንድሮው የዓለም ዋንጫም ከሩብ ፍጻሜው የተሰናበተችው በፈረንሳይ መሆኑ አስገራሚ ገጠመኝ ሆኖ አልፏል፡፡

ኖርዌይ የአምስት ጊዜ የዓለም ዋንጫ ባለ ክብረ ወሰኗን ብራዚልን በ16 ቡድኖች ውስጥ ከውድድር ማሰናበቷም የዘንድሮው ዓለም ዋንጫ አስገራሚ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ኖርዌይ ከ28 ዓመታት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫው ተመልሳ ለዋንጫው ከፍተኛ ግምት የተሰጣትን ብራዚልን በ16 ቡድኖች ውስጥ ጥላት ማለፏ የዓለም እግር ኳስ ምን ያህል ተቀራራቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ማሳያም ሆኗል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ 48 ሀገራት በተሳተፉበት የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ አስገራሚ ውጤቶች ከተባሉት ውስጥ ፓራጓይ ጀርመንን በመለያ ምቶች አሸንፋ 16 ቡድኖችን መቀላቀሏ ይጠቀሳል፡፡ የዓለም ዋንጫን አራት ጊዜ በመውሰድ ከብራዚል ቀጥላ የምትገኘው ጀርመን በፓራጓይ መሸነፏ አስገራሚ ክስተት ከመሆኑ ባሻገር ፓራጓይም ይህንኑ ድሏን ለአንድ ቀን ብሔራዊ ክብረ በዓል አድርጋ አሳልፋዋለች፡፡

በ2026 የውድድር ዓመት በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግና በላሊጋው ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ያጠናቀቀው ፈረንሳዊው ኪሊያን ምባፔ በዓለም ዋንጫውም 10 ግቦችን በማስቆጠር በውድድር ዓመቱ ሦስተኛ የወርቅ ጫማውን ተሸልሟል፡፡ የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ 48 ሀገራትን ማሳተፉ ብቻ ሳይሆን ለብሔራዊ ቡድኖቹ የሰጠው ሽልማትም ከእስካሁኑ የላቀና ክብረ ወሰን ሆኖ የተመዘገበ ነው፡፡

ስፔን የዋንጫው ባለቤት በመሆኗ 50 ሚሊዮን ዶላር እና ለ30 የቡድኑ አባላት ደግሞ በከፊል ከዳይመንድ የተሠራ ቀለበት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ፊፋ በ2018 የሩሲያው ዓለም ዋንጫ አሸናፊ ለነበረችው ፈረንሳይ 38 ሚሊዮን ዶላር የሸለመ ሲሆን በ2022 የኳታሩ ዓለም ዋንጫ አሸናፊ ለነበረችው አርጀንቲና ደግሞ 42 ሚሊዮን ዶላር መሸለሙ ይታወሳል፡፡

ስፔን በዓለም ዋንጫው ከተዘጋጁት አራት ሽልማቶች ውስጥ ሦስቱን ጠቅልላ በመውሰድም ታሪክ ሠርታለች፡፡ በወጣት ተጨዋች ሽልማት ፓዉ ኩባርሲ፣ በግብ ጠባቂ ኡናይ ሲሞን እና በኮከብ ተጨዋችነት ሮድሪን ተሸላሚ ያደረገችው ስፔን የኮከብ ግብ አግቢነቱን ብቻ ለፈረንሳዩ ኪሊያን ምባፔ ትታለታለች፡፡

ስፔን ከ16 ዓመት በፊት ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ ኔዘርላንድስን በጭማሪ ሰዓት 1 ለ 0  ያሸነፈችበትን ታሪክ ከ16 ዓመት በኋላ በጭማሪ ሰዓት ፌራን ቶሬስ ባስቆጠራት ግብ አርጀንቲናን 1 ለ 0 ማሸነፏ  ከዓለም ዋንጫው አስገራሚ ትዕይንቶች ውስጥ አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

በዓለም ዋንጫው አስገራሚ ከነበሩት ጉዳዮች ውስጥ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አንዱ ናቸው፡፡ የዓለም ዋንጫውን በጥምረት ያዘጋጁት ካናዳ፣ ሜክሲኮ እና አሜሪካ ቢሆኑም የካናዳ እና የሜክሲኮ መሪዎች በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ልክ የውድድሩ ድምቀት ወይም መነጋገሪያ አልሆኑም፡፡

ትራምፕ እና ሀገራቸው ሶማሊያዊው ዳኛ ኦማር አርታር ወደ ሀገራቸው ገብተው እንዳይዳኙ ከማገዳቸውም በተጨማሪ አሜሪካዊው አጥቂ ፍሎረን ባሎገን በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቶ የሦስት ጨዋታዎች ቅጣት ቢጣልበትም ትራምፕ በፊፋው ፕሬዚዳንት ኢንፋንቲኖ ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ተጨዋቹ ያለምንም የጨዋታ ቅጣት ከቤልጅየም ጋር እንዲጫወት አድርገዋል፡፡

በዚህ ጨዋታ ላይ የቤልጅየሙን አሠልጣኝ ጨምሮ በርካታ የእግር ኳስ ተንታኞች የትራምፕን ጣልቃ ገብነት እና የፊፋን የውሳኔ ብቃት ማነስ ያወገዙ ቢሆንም በጨዋታው ቤልጅየም አሜሪካንን 4 ለ1  አሸንፋታለች፡፡  በዓለም እግር ኳስ ውስጥ የዘወትር መነጋገሪያ የሆኑት የ41 ዓመቱ ፖርቱጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶና የ39 ዓመቱ አርጀንቲናዊ ሊዮኔል ሜሲ የመጨረሻቸውን የዓለም ዋንጫ በ2026 ማድረጋቸውም ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ነበር፡፡

የስምንት ጊዜ የባላንዶር አሸናፊው እና የዓለም ዋንጫን በ2022 ኳታር ላይ የሳመው ሊዮኔል ሜሲ በእግር ኳስ አሉ የተባሉ ክብሮችን በሙሉ ተቀዳጅቶ ከዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች በእንባ ተሰናብቷል፡፡ የአምስት ጊዜ የባላንዶር አሸናፊው እና በእግር ኳሱ ዓለም የብዙዎች ተምሳሌት የሆነው ፖርቱጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶም ምንም እንኳን ሀገሩን በአምበልነት እየመራ ለዓለም ዋንጫው ባይታደልም ከዚያ በመለስ ያሉ ክብሮችን በሙሉ ተቀዳጅቶ ከዓለም ዋንጫ ጨዋታ በክብር ተሰናብቷል፡፡

እነዚህ ሁለት የእግር ኳስ ዕንቁዎች በየራሳቸው መንገድ እና ክህሎት ለዓመታት በእግር ኳሱ መድረክ ደምቀው ኖረዋል፡፡ ሁለቱም ባለ ተሰጥኦዎች የየራሳቸውን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደጋፊዎች አፍርተው የእግር ኳሱ ዓለም መከራከሪያ ሆነው ኖረዋል፡፡ ሁለቱም በአንድ ዘመን ላይ የተፈጠሩ የእግር ኳስ ውበትና ምልክቶች ሆነው ዘልቀዋል፡፡

ላሚን ያማል (ስፔን)፣ ፓዉ ኩባሲ (ስፔን)፣ አዩብ ቡአዲ (ሞሮኮ)፣ አንቶኒ ኑሳ (ኖርዌይ)፣ አርዳ ጉለር (ተርኪዬ) እና ሌሎችም ወጣቶች በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ያሳዩት እንቅስቃሴ የሜሲና የሮናልዶ ተተኪዎች በየትኛውም ዘመን የማይነጥፉ መሆኑን ነው፡፡

ኪሊያን ምባፔ እና ኸርሊንግ ሃላንድ ደግሞ በቅርቡ የሁለቱ ኮከቦች አልጋ ወራሽነትን ለመረከብ በመንገዱ ላይ የሚገኙ መሆኑን በዓለም ዋንጫው ላይ ያሳዩት ብቃት ምስክር ሆኖላቸዋል፡፡

በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ከተመለከትናቸው ሌሎች አስገራሚ ነገሮች ውስጥ አንዱ በጀርመናዊው ሚሮስላቭ ክሎስ ተይዞ የነበረው የዓለም ዋንጫ የ16 ግብ ክብረ ወሰን በሜሲ እና በምባፔ መሻሻሉ ነው፡፡

የዘንድሮው ዓለም ዋንጫ ከመጀመሩ በፊት ሊዮኔል ሜሲ በ13 ግቦች እና ኪሊያን ምባፔ ደግሞ በ12 ግቦች የክብረ ወሰኑ ተፎካካሪ ነበሩ። ሜሲ ስምንት እና ምባፔ ደግሞ 10 ግቦችን አስቆጥረው የዓለም ዋንጫውን ክብረ ወሰን ምባፔ በ22፣ ሜሲ ደግሞ በ21 ግቦች የውድሩን የምንጊዜም ግብ አስቆጣሪነት በአንደኛ እና በሁለተኛ ደረጃ ይዘውታል፡፡

ፈረንሳዊው ምባፔ ዕድሜው ገና 29 ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወደፊት ክብረ ወሰኑን በተሻለ የግብ መጠንሊያሻሽለው እንደሚችል ይገመታል፡፡

 

(እሱባለው ይርጋ)

በኲር የሐምሌ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here