ጉበት ከሰውነታችን ትልቁ እና እጅግ ወሳኝ ከሆኑ አካላት አንዱ ነው። ጉበት መርዛማ ንጥረ ነገሮችን፣ አልኮልን እና አላስፈላጊ ኬሚካሎችን ከደም ውስጥ በማጣራት ከሰውነት ያስወግዳል፡፡ ሀሞትን በማመንጨት ስብን (ቅባትን) ለመፍጨት፣ ቫይታሚኖችን ( ኤ፣ ዲ፣ ኢ፣ኬ እና ቢ12) እንዲሁም እንደ ብረት ያሉ ማዕድናትን በውስጡ ያከማቻል፡፡ ደም በሚጎዳበት ጊዜ እንዲረጋ የሚያደርጉ ፕሮቲኖችንም ያመርታል፡፡ ሆኖም ግን ይህ ወሳኝ አካል በቫይረሶች፣ በአልኮል፣ በአመጋገብ ችግሮች ወይም በሌሎች ምክንያቶች ሲጎዳ የጉበት በሽታ ይከሰታል።
የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚጠቁመው ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት እና አንዳንድ የእስያ ክፍሎች በተለይ በሄፐታይተስ ቢ እና ሲ ከፍተኛ ተጠቂዎች ናቸው። ለዚህም የክትባት ሽፋን ዝቅተኛ መሆን፣ የጤና ተቋማት ንጽሕና ጉድለት፣ ያልተጸዱ ሹል መሳሪያዎችን መጠቀም እና የንጹህ ውኃ እጥረት ዋና ምክንያቶች ተብለው ይጠቀሳሉ።
በኢትዮጵያም በጉበት በሽታ የሚጠቃው የማህበረሰብ ክፍል ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ሪፈራል ሆስፒታል የውስት ደዌ ስፔሻሊስት ሀኪም ዶ/ር ሀና ስመኝ ጋር በስልክ ቆይታ አድርገናል፡፡ እንደ ባለሙያዋ ገለጻ የጉበት በሽታ ማለት የጉበት ሕዋሳት መጎዳት፣ ማበጥ ወይም በጊዜ ሂደት ቋሚ ጠባሳ (Scar tissue) በመፍጠር የጉበትን መደበኛ ሥራ የሚያስተጓጉል የጤና ችግር ነው። በሽታው በድንገት ለአጭር ጊዜ የሚቆይ አጣዳፊ ወይም ከስድስት ወራት በላይ በመቆየት ጉበትን ቀስ በቀስ በመጉዳት ሥር ይሰዳል።
በዓለም ላይ በብዛት የሚገኙት የጉበት በሽታ አይነቶች በሄፐታይተስ ኤ፣ ቢ፣ ሲ፣ ዲ እና ኢ ቫይረሶች ናቸው። የጉበት በሽታን እንደየ ህመም ደረጃቸው አጣዳፊ እና ስር የሰደደ የጉበት በሽታ ተብለው ይከፈላሉ፡፡
እንደ ዶ/ር ሀና ገለጻ የጉበት በሽታ አይነቶች አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ ወደ ሰባት የሚደርሱ ቫይረሶች መኖራቸው ይነገራል፡፡ ከነዚህ ውስጥ በዋነኝነት ትኩረት የሚሰጣቸው ለሦስቱ ነው፡፡ እነዚህም ሄፐታይተስ ኤ ፣ ቢ እና ሲ ናቸው፡፡ በሽታው የሚከሰትባቸው እና የሚተላለፉባቸው መንገዶችም ይለያያሉ።
የሄፐታይተስ ኤ ቫይረሶች ብዙ ጊዜ በልጆች ላይ ይከሰታል፡፡ የመተላለፊያ መንገዱም የተበከለ ምግብ፣ ውኃ እንዲሁም የንጽህና ጉድለት ናቸው። የሄፐታይተስ ኤ ቫይረስ ፈሳሾችን በመውሰድ እና እረፍት በማድረግ መዳን የሚችል መሆኑንም ነው ዶ/ር ሀና የጠቆሙት፡፡
ሄፐታይተስ ቢ እና ሲ ደግሞ ስር የሰደደ የጉበት በሽታ የማምጣት አጋጣሚ አላቸው፡፡ በዚህ ላይ በተበከለ ደም፣ በግብረ ስጋ ግንኙነት፣ ከእናት ወደ ልጅ በእርግዝና እና በወሊድ ጊዜ፣ በመርፌ፣ በምላጭ ወይም በሌሎች ሹል መሳሪያዎች አማካኝነት ሊተላለፉ እንደ ሚችልም ባለሙያዋ ጠቁመዋል።
በእርግዝና እና በወሊድ ወቅት ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፍ የጉበት በሽታ ስር የሰደደ የጉበት ቫይረስ የመሆን እድሉ ሰፊ መሆኑንም ነው ዶ/ር ሀና የተናገሩ፡፡ ከጊዜ በኋላ የመጣ የሄፐታይተስ ቢ በሽታ ከሆነ ደግሞ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ከአምስት በመቶ በታች ለሆኑ ሰዎች ላይ ስር የሰደደ የጉበት በሽታ ሊሆን ይችላል፡፡ 95 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የህክምና ክትትል በማድረግ እና ክትባት በመውሰድ ስር ሳይሰድ የመዳን እድሉም ከፍ ያለ ነው፡፡ በዚህም በሽታው ጨርሶ ሊድን ይችላል ነው ያሉ፡፡ ዶ/ር ሀና አክለውም የጉበት በሽታን መከላከል ከሕክምናው የበለጠ ቀላልና ውጤታማ ነው።
ለሄፐታይተስ ቢ ክትባት በመውሰድ፣ የግል ንጽህናን መጠበቅ፣ ንጹህ ውኃና ጤናማ ምግብ መጠቀም፣ የምላጭ፣ የጥርስ ብሩሽ እና መርፌን አለመጋራት እንዲሁም የአልኮል መጠጥን መቀነስ ወይም ማቆም በሽታውን የመከላከያ መንገዶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሄፐታይተስ ሲ ደግሞ ምንም አይነት ምልክት ሳያሳይ እና ሳይታወቅ ስር የመስደድ አጋጣሚው በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ነው ባለሙያዋ ያስገነዘቡት፡፡ ሄፒታይተስ ሲ የመተላለፊያ መንገዶቹ ከሄፐታይተስ B ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ሆኖም ሄፒታይተስ ሲ በሽታውን የሚከላከል ክትባት የለውም፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን መድኃኒት ስለተገኘለት ከሦስት ወር እስከ ስድስት ወር ጊዜ ውስጥ በመውሰድ በሰውነት ያለውን ቫይረስ ከደም ማስወገድ እንደሚቻልም ነው ዶ/ር ሀና የተናገሩት፡፡
በአጠቃላይ የጉበት በሽታ ሕክምና እንደ በሽታው ዓይነት ይለያያል። በቫይረስ የሚመጡ በሽታዎች በሐኪም ምክር የፀረ-ቫይረስ መድኃኒቶች ይታከማሉ። በአኗኗር ዘይቤ የሚመጡ ችግሮች ደግሞ አመጋገብን በማስተካከል፣ ክብደትን በመቆጣጠር እና አልኮልን በማቆም ሊቀንሱ ይችላሉ። በሽታው ወደ ከፍተኛ ደረጃ ከደረሰ ደግሞ የጉበት ንቅለ ተከላ ብቸኛው የሕክምና አማራጭ ሊሆን ይችላል።
እንደ ዶ/ር ሃና ማብራሪያ ብዙ ጊዜ በሀገራችን ሰዎች የምግብ ፍላጎታቸው ሲቀንስ እና ዐይናቸው ቢጫ ሲሆን የወፍ በሽታ በሚል ወደ ባህላዊ ህክምና በመሄድ የተለያዩ ባህላዊ መድኃኒቶችን ወስደው ወደ ጤና ተቋማት ይመጣሉ፡፡ ሆኖም የምግብ ፍላጎትን የሚቀንስ እና ዐይንን ቢጫ የሚያደርግ የጉበት በሽታ ብቻ አለመሆኑን እና ሌሎች በሽታዎችም እንደነዚህ አይነት ምልክቶችን ሊያሳዩ እንደሚችሉ በመረዳት በሽታው መኖሩን ለማወቅ የግድ በህክምና ምርመራ መደረግ እንዳለበት ነው በአጽንኦት የመከሩት፡፡
ዶ/ር ሀና አክለውም የጉበት በሽታን በባህላዊ ህክምና ዘዴ ለመታከም መሞከር የለበትም፤ ምክንያቱም የሚወሰደው የባህላዊ መድኃኒት በአፍ የሚወሰድ ከሆነ በሽታውን ሊያባብስ ስለሚችል ህብረተሰቡ ወደ ህክምና ተቋም በመምጣት ጤንነቱን በምርመራ ማረጋገጥ ይገባዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ የጉበት ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ መኖሩ በምርመራ ከታወቀም ህክምና እንዳለው መረዳት እና መተላለፊያ መንገዶችንም መገንዘብ ሌላውን የቤተሰብ አባል መታደግ መሆኑንም ነው የተናሩት፡፡
ጉበት ለሰውነታችን የሕይወት መሠረት ከሆኑ አካላት አንዱ በመሆኑ ጤንነቱን መጠበቅ የሁላችንም ኃላፊነት ነው። የጉበት በሽታዎች ብዙዎቹ በቀላል የንጽሕና ልምዶች፣ በክትባት፣ በጤናማ የአኗኗር ዘይቤ እና በወቅታዊ የሕክምና ምርመራ ሊከላከሉ ይችላሉ። እንደሚባለው ከመታመም መከላከል ስለሚሻል ለጉበታችን ጤንነት ዛሬውኑ ትኩረት መስጠት ለነገው ጤናማ ሕይወት መሠረት መሆኑን አስገንዝበዋል።
ጤና አዳም
የተለመዱ የጉበት ካንሰር ምልክቶች
ያልታወቀ ክብደት መቀነስ
የምግብ ፍላጎት ማጣት ወይም ቀደም ብሎ የመርካት ስሜት
ድካም እና አጠቃላይ ድክመት
በላይኛው የሆድ ክፍል ውስጥ ህመም ወይም ምቾት ማጣት
በቀኝ የላይኛው የሆድ ክፍል ውስጥ እብጠት መኖር
በፈሳሽ ክምችት ምክንያት የሆድ እብጠት
የቆዳ እና የዓይን ቢጫ ቀለም መሆን
ማቅለሽለሽ ወይም ማስታወክ
በእግሮች ላይ እብጠት መኖር
ትኩሳት መኖር
(ሰናይት በየነ)
በኲር የሐምሌ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


