ልብን የሚያድሰው

0
58

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ልብን ማጠንከር ብቻ ሳይሆን የነርቭ አውታር መረብን በማደስ ለተለያዩ የልብ የጤና ችግሮች በተናጠል መድኃኒት ለመሻት በር ከፋች መሆኑን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል፡፡

በእንግሊዝ የብሪስቶል ዩኒቨርስቲ በመረጃ ምንጭነት ለንባብ እንዳበቃው የተቋሙ ተመራማሪዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የልብና የደም ቧንቧ ጤናን ከማሻሻል ባሻገር የልብን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠሩ ነርቮችን እንደሚያድስ ደርሰውበታል፡፡ይህም ለየችግሮቹ በተናጠል መድኃኒት ለመሻት እንደሚያግዛቸውም ነው ያረጋገጡት ፡፡

በዩኒቨርሲቲው በመምህርነት የበርካታ ዓመታት ልምድ ያካባቱት የምርምሩ መሪ ዶ/ር አውግስቶ ኮፒ ግኝቱ ቀደም ሲል በሰውነት “አውቶፓይለት” ስርዓት  ውስጥ ድብቅ የሆኑን የግራ እና ቀኝ ክፍሎችን በወጉ ለማሰራት እንደሚያስችልም ነው ያሰመሩበት፡፡

ተመራማሪዎቹ በብራዚል ከሳኦፓሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር በመቀናጀት ለ10 ሳምንታት በአይጥ ላይ ባደረጉት ምርመራ በግራ እና በቀኝ የልብ ክፍል ያለው የነርቭ መጠን መለያየቱን ተገንዝበዋል፡፡ ይህ ማለት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የነርቭ ብዛትንም ሆነ ጥንካሬን በማሻሻል ማደስ ማስቻሉን አመላክቷል፡፡

ዶ/ር አውግስቶ ኮፒ እንዳብራሩት በቀጣይ ያልተለመደ የልብ ምት ወይም የልብ ምት መዛባት፣ በተለምዶ የደረት ህመም በመባል የሚታወቁትን ችግሮች በተናጠል ማከም ያስችላል ነው ያሉት፤ ግኝቱ፡፡ ተመራማው ወደፊት   የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዴት የነርቭ አገዳዎችን (መነሻዎችን) እንደሚቀይር ወይም ተፅእኖ እንደሚያሳርፍ በመገንዘብ ማስተካከል እንደሚቻል ፍንጭ እንደሰጠ ተዘግቧል፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሐምሌ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here