የማንኛውም ሀገር የልማት ጉዞ የሚሳካው የዜጎች ንቁ ተሳትፎ፣ የጋራ ኃላፊነት ስሜትና ለማህበረሰብ የመስጠት ባህል ሲጎለብት ነው። በተለይም ወጣቶች በፈቃደኝነት የሚያከናውኗቸው ተግባራት ከቀጥተኛ ማህበራዊ ጥቅም ባሻገር የዜግነት እሴቶችን፣ መተሳሰብን፣ መተባበርንና የሀገር ባለቤትነት ስሜትን የሚያጎለብቱ በመሆናቸው ለዘላቂ ልማት የሚጣል ጠንካራ መሠረት ይሆናሉ።
በኢትዮጵያ በየዓመቱ በክረምት ወቅት የሚካሄደው የወጣቶች የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴም ይህንን ዓላማ የሚያንጸባርቅ ነው። ከአካባቢ ጽዳትና ከአረንጓዴ ልማት ጀምሮ በትምህርትና ጤና ተቋማት ድጋፍ፣ አቅመ ደካሞችን መርዳት፣ የደም ልገሳ፣ የአካባቢ ጤና ጥበቃና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን በማከናወን የወጣቶች አቅም ለሀገር ግንባታ እየዋለ ይገኛል። እነዚህ ተግባራት የአንድ ወቅት እርዳታ ብቻ ሳይሆኑ በማህበረሰቡ ውስጥ የመተባበርና የመረዳዳት ባህልን የሚያጠናክሩ ናቸው።
የዓለም አገራት ተሞክሮም ይህንን እውነታ ያረጋግጣል። ደቡብ ኮሪያ ከኮሪያ ጦርነት በኋላ በነበረው የመልሶ ግንባታ ሂደት ወጣቶችን በመንደር ልማት፣ በትምህርት፣ በአካባቢ ጽዳትና በማህበረሰብ አገልግሎት በስፋት አሳትፋ ፈጣን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጥ ማስመዝገብ ችላለች። በተለይም የ«ሳኤማኡል ኡንዶንግ» (Saemaul Undong) የመንደር ልማት እንቅስቃሴ በራስ አቅም መተማመን፣ መረዳዳትና በጎ ፈቃደኝነትን ወደ ማህበራዊ ባህል በመቀየር ለሀገሪቱ ዘላቂ ልማት መሠረት ጥሏል። እንዲሁም በሩዋንዳ የሚካሄደው “ኡሙጋንዳ” የማህበረሰብ አገልግሎት መርሃ ግብር ዜጎችን በወር አንድ ጊዜ በጋራ በማሰማራት በአካባቢ ጽዳት፣ በመንገድ ጥገናና በሌሎች የልማት ሥራዎች ተሳትፎ እንዲያደርጉ በማድረግ ማህበራዊ ትስስርን አጠናክሯል። እነዚህ ተሞክሮዎች የፈቃደኝነት ባህል ወደ ቋሚ አገራዊ እሴት ሲቀየር ልማትን ማፋጠን እንደሚቻል ያሳያሉ።
በአማራ ክልልም የ2018 ዓ.ም የክረምት የበጎ ፈቃድ ሥራ በሰፊ ዕቅድ ተጀምሯል።
ወጣት አብዱ ሞላ በሰሜን ወሎ ዞን ሀራ ከተማ ነዋሪ ነው፡፡ ወጣት አብዱ በማኔጅመንት የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን ተምሮ ተመርቋል፡፡ ወጣቱ ከተመረቀ ጊዜ ጀምሮ በበጎ ፈቃድ ስራ ዙሪያ የሰራዉን ተግባራት እንዲህ በማለት ይገልጻል።’’በክረምት የበጎ ፈቃድ ስራ ተሳታፊ በመሆን በተለያዩ የስራ ዘርፎች ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የክረምት ዕረፍቴን በቤት ውስጥ ብቻ ከማሳለፍ ይልቅ ለማኅበረሰቤ የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት ወስኜ ተሰማራሁ። ከጓደኞቼ ጋር በመሆንም የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ፣ የአካባቢ ጽዳት በማከናወን፣ አረንጓዴ ልማትን በማገዝ እና ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ በማድረግ ተሳትፈናል’’።
‘’በተለይ ያንዲት አቅመ ደካማ እናት ቤትን በጠገንሁበት ጊዜ የተሰማኝን ደስታ በቃላት ለመግለጽ አልችልም። ቤታቸው በዝናብ ወቅት ውኃ እያስገባ ሳይ አዝን ነበር ነገር ግን ግንባታው ከተጀመረ በኋላ በፊታቸው ላይ የሚታየው ደስታ ለሠራነው ሥራ ትልቁ ሽልማት ነበርና በጣም ተደስቻለሁ።የበጎ ፈቃድ ተግባር ገንዘብን መስጠት ብቻ አይደለም፤ ጊዜን፣ ጉልበትን፣ እውቀትን እና ፍቅርን ለሌሎች ማካፈል ነው። ይህ ተግባር የመተሳሰብን ባህል ያጠናክራል፤ ወጣቶችንም ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች እንዲሆኑ ያግዛል።በመሆኑም ሁሉም ወጣቶች በሚችሉት መጠን በበጎ ፈቃድ እንዲሳተፉ እጋብዛለሁ። አንድ ሰው የሚያደርገው ትንሽ በጎ ሥራ የሌላን ሰው ሕይወት ሙሉ በሙሉ ሊቀይር ይችላል።”በማለት የበጎ ስራ ተሳታፊ መሆን ስለሚሰጠዉ እርካታ ተናግሯል።
የሃራ ከተማ ነዋሪ የሆኑት እና በበጎ ፈቃድ ስራ ተሳታፊ ወጣቶች ቤታቸው የታደሰላቸው አቅመ ደካማ እናት ወ/ሮ አልማዝ በላይ በወጣቶች ስለተደረገላቸዉ ድጋፍ እንዲህ በማለት ተናግረዋል፡፡’’ለብዙ ዓመታት በዝናብ ወቅት ቤቴ ውኃ ያስገባ ነበር፤ ሌሊቱን በሙሉ ውኃ ስናፈስ እናድር ነበር። አቅሜ ውስን በመሆኑ ቤቴን ለማደስ አልቻልኩም ዛሬ ግን በእነዚህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እና በአጋር አካላቶች አማካኝነት አሁን ቤቴ በብሎኬት እየተገነባልኝ ነው።
ወጣቶቹ ለእኔ ቤት ብቻ አይደለም የሰጡኝ ይልቁንም ተስፋና የመኖር ጉልበትም መልሰውልኛል። ይህን የመሰለ ተግባር የሚፈጽሙ ወጣቶችን ሳይ የሀገራችን የወደፊት ተስፋ ብሩህ መሆኑን አምናለሁ።
ለሁሉም በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ ለድጋፉ ተባባሪ ለሆኑ አካላት እና ይህን መልካም ሥራ ላስተባበሩ ሁሉ ከልብ አመሰግናለሁ። እግዚአብሔር የሠሩትን መልካም ሥራ ይባርክላቸው። እንደ እኔ ያሉ ሌሎች አቅመ ደካሞችም በእነዚህ ዓይነት የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምኞቴ ነው ‘’ሲሉ ደስታቸውን ለበኩር በስልክ ተናግረዋል።
አቶ ጥላሁን አሰፋ የሰሜን ወሎ ዞን ወጣት ማህበራት አስተባባሪ ናቸዉ ፡አስተባባሪዉ እንደተናገሩት በዞኑ በአስራ ሰባት የተለያዩ የስራ ዘርፎች የክረምት በጎ ፈቃድ ወጣቶችን በማሰባሰብ ወደ ስራ ገብተናል ብለዋል፡፡
ከነዚህ ውስጥ በዋናነት የአቅመ ደካማ ቤቶችን እድሳት እና ግንባታ፣የማዕድ ማጋራት ስራ ፣የደም ልገሳ፣አቅም ለሌላቸው አርሶአ ደሮች የእርሻ ስራ መስራት እና ለችግረኛ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሶችን አሰባስቦ ተደራሽ የማድረግ ስራዎች ይሰራሉ፡፡በዚህ ስራ ላይ በዞኑ ባሉ ወረዳዎች ከ24 ሺህ በላይ ወጣቶች እንደሚሳተፉ ነው አቶ ጥላሁን የተናገሩት፡፡ይህ የበጎ አድራጎት ስራ በክልሉ ላሉ ወጣቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በመስራት በስፋት እየተተገበረ ይገኛል፡፡ የአማራ ወጣቶች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ በድር ወንድሙ እንደገለጹት፣ ለ22 ዞኖች የዕቅድ ኦሬንቴሽን ተሰጥቶ በ16 የተለያዩ የሥራ መስኮች 784 ሺህ 716 የበጎ አድራጎት ፍቃደኛ ወጣቶችን ለማሳተፍ ታቅዷል። በአጭር ጊዜም ከ345 ሺህ በላይ ወጣቶች በፈቃደኝነት ሥራውን መሳተፋቸው የወጣቶች ተነሳሽነት እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል።
በእቅዱ ውስጥ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በቀዳሚነት ተካቷል። ለችግኝ መትከያ ጉድጓዶችን መቆፈር፣ ችግኞችን መትከልና መንከባከብ የአካባቢ ጥበቃን ከማጠናከር ባለፈ የወደፊት ትውልድ የተሻለ አካባቢ እንዲወርስ ያግዛል። በተመሳሳይ ሁኔታ አቅመ ደካሞችን በእርሻ ሥራ፣ በቤት ግንባታና ጥገና፣ በምግብና በአልባሳት ድጋፍ ማገዝ የማህበረሰብ አንድነትን የሚያጠናክር ተግባር ነው።
በጤናው ዘርፍ የደም ልገሳ፣ የወባ መከላከል፣ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምርመራ ፣ የኤች አይ ቪ/ኤድስ እና ሌሎች የጤና ጉዳዮች ላይ የግንዛቤ ሥራዎች እንደሚሰሩም በእቅዱ ተካትተዋል። በትምህርት ዘርፍም የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት፣ ለችግረኛ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ማቅረብ፣ ትምህርት ቤቶችን መጠገንና ማደስ ይገኙበታል። ለ5 ሺህ 100 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ለማቅረብ መታቀዱም የበጎ ፈቃድ ሥራው በትውልድ ግንባታ ላይ ያለውን አስተዋፅኦ ያሳያል።
ከዚህ በተጨማሪ ወጣቶችን በዲጂታል ክህሎት፣ በኢትዮ ኮደርስ፣ በስፖርት፣ በትራፊክ ደህንነት፣ በአደንዛዥ እጾች መከላከል፣ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር እና በፋይዳ መታወቂያ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮች መዘጋጀታቸውን ነው ምክትል ፕሬዜዳንቱ የተናገሩ። ይህ ደግሞ ፈቃደኝነት በአካላዊ ሥራ ብቻ ሳይወሰን የወጣቶችን እውቀት፣ ሙያና የቴክኖሎጂ ብቃት ለሀገር ግንባታ እንዲውል መንገድ እየከፈተ መሆኑን ያሳያል።
በአጠቃላይ የክረምት የበጎ ፈቃድ ሥራ የወቅታዊ ዘመቻ ብቻ አይደለም፤ የወጣቶችን አቅም ለልማት የሚያሰባስብ፣ የዜግነት እሴቶችን የሚያጎለብት፣ የማህበራዊ ትስስርን የሚያጠናክርና በትውልድ ግንባታ ላይ ዘላቂ አሻራ የሚያሳርፍ ስትራቴጂያዊ እንቅስቃሴ ነው። ባሳለፍናቸው ሁለት ሳምንታት ውስጥ በተገኙ ውጤቶች 10 ቤቶች መጠገናቸውና 8 አዳዲስ ቤቶች መገንባታቸው የወጣቶች ተሳትፎ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚችል ያረጋግጣል ነው ያሉ ። ይህንን ባህል በማጎልበት እና በየዓመቱን በማስቀጠል የዜግነት እንቅስቃሴ ማድረግ ከተቻለ፣ የክልላችን የልማት ጉዞ ይበልጥ የተፋጠነና የተሳካ ሆናል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።
መረጃ
የበጎ ፈቃደኝነት ዋና ዋና መገለጫዎች
- ነፃነት፡- ከማንም አስገዳጅነት ውጪ በራስ ፍላጎትና ውሳኔ የሚከናወን
- ከክፍያ ነፃ መሆን፡- ዓላማው ትርፍ ማግኘት ወይም ቋሚ ደመወዝ መጠበቅ ሳይሆን ሌላውን መጥቀም
- አብሮነትን ማጠናከር፡- ማህበራዊ ትስስርን የሚገነባና ችግር ላይ ላሉት አጋርነትን ማሳየት
(ሰናይት በየነ)
በኲር በኲር የሐምሌ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


