ሥልጣን ለሕዝብ ወይስ ለግል ጥቅም?

0
229

ሥልጣን የሕዝብ አደራ እንጂ የግለሰቦች የጉልበት መፈተኛ፣ የዜጎች ማንገላቻ፣ የሰብዓዊ መብታቸው መጣሻ ወይም የሀብት ማከማቻ መሳሪያ አይደለም። በማንኛውም ዴሞክራሲያዊ እና የሕግ የበላይነት በሰፈነበት ማህበረሰብ ውስጥ ስልጣን ሲሰጥ አብሮ የሚመጣ ትልቅ ኃላፊነት አለ፡፡ ይኸውም ዜጎችን በእኩልነት እና በፍትሐዊነት ማገልገል ነው። ሆኖም ይህ የሕዝብ አደራ ተዘንግቶ ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም (Abuse of Power) ሲንሰራፋ የሀገር ምሰሶ የሆኑት ፍትሕ፣ እኩልነት እና ማህበራዊ መተማመን አደጋ ላይ ይወድቃሉ። የሀገር ሀብትም በጥቂቶች እጅ ይከማቻል።

በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ያለው መተማመን ይሸረሸራል። ዜጎች ፍትሕ እንደሌለ ሲሰማቸው ሥርዓቱን መጥላት እና ማመፅ ይጀምራሉ። በዚህ መጣጥፍ ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ምንነት፣ የሚያስከትለው መዘዝ እና የሕግ ተጠያቂነትን እንቃኛለን።

ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ሲባል ምን ማለት ነው?

ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ማለት አንድ ግለሰብ ከተሰጠው ሕጋዊ ኃላፊነት፣ ማዕረግ ወይም የሥራ ድርሻ በላይ በመሄድ የግል ጥቅምን ለማሳደድ ወይም ሌሎችን ለመጉዳት ስልጣኑን ለተገቢው ዓላማ ሳይሆን ለግል ፍላጎቱ ማዋል መሆኑን የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከፍተኛ የሕግ ባለሙያዋ ወ/ሮ ፍቅር በለጠ አብራርተዋል። ይህ ድርጊት በሕግ የሚያስቀጣ እና የአንድን ተቋም ወይም ሀገር መልካም ስም እና አሠራር የሚያበላሽ ከባድ የሙስና ወንጀል መሆኑንም ባለሙያዋ ገልጸዋል።

ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ዋና ዋና መገለጫዎች፡-

የመንግሥት ወይም የሕዝብ ሀብትን ለግል ወይም ለቤተሰብ ጥቅም ማዋል፣ የሥራ ቅጥርን፣ እድገትን፣ ሹመትን ወይም ጥቅማጥቅሞችን በእውቀት፣ በችሎታ እና በብቃት ሳይሆን በዘመድ አዝማድ፣ በጓደኛ ወይም በፖለቲካ ትስስር ሰዎችን መጥቀም፣ የሐሰት መረጃዎችን ወይም ውሳኔዎችን በማሳለፍ የገንዘብ እና የንብረት ዝርፊያ መፈጸም፣ ከተፈቀደው የስልጣን ወሰን ውጭ በመሆን የዜጎች መብት መጋፋት ወይም ያለአግባብ ሰዎችን ማሰር፣ ማንገላታት እና ሐሳባቸውን በነፃነት እንዳይገልፁ ማፈን ዋና ዋናዎቹ መገለጫዎች ናቸው፡፡

ሌላው በሥራው አጋጣሚ ያገኘውን መረጃ ከሕግ ውጭ ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ጥቅም እንዲውል የማድረግ ወንጀል ነው። እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ ይህ ወንጀል ከሌሎች የሙስና አይነቶች (ለምሳሌ ጉቦ) የሚለየው ግለሰቡ የግድ ክፍያ መቀበል የለበትም፤ ስልጣኑን ከሕግ ዓላማ ውጭ መጠቀሙ ብቻ ለወንጀሉ መመስረት በቂ ነው። አንድ ሀገር ስልጣንን ያለአግባብ በሚጠቀሙ ኃላፊዎች እጅ ስትወድቅ መዘዙ የከፋ ነው። ችግሩም ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠባሳዎችን ያስከትላል።

በአጭሩ የሚያስከትላቸው ጉዳቶችም

ባለሙያዋ እንደሚሉት  ስልጣንን ያለአግባብ ሲውል ንጹሃን ዜጎች መብታቸውን ሲያጡ፣ ጥፋተኞች ደግሞ በስልጣን ከለላ ከቅጣት ያመልጣሉ። ማህበረሰቡ በመንግሥት ተቋማት እና በሕግ የበላይነት ላይ ያለው እምነት ሙሉ በሙሉ ይሸረሸራል፣ የሀገር ሀብት ለልማት መዋል ሲገባው በጥቂት ግለሰቦች እጅ ስለሚከማች ድህነት ይስፋፋል፣ ሥራ አጥነት ይበራከታል።

ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም የሚያስከትለው  የሕግ ተጠያቂነት

አንዳንድ ግለሰብ ከመንግሥታዊ ወይም ከሕዝብ የተሰጠውን ኃላፊነት ከሕግ እና ከስነ-ምግባር ውጪ ለግል ጥቅም፣ ለቤተሰብ፣ ለወዳጅ ዘመድ ወይም ለተወሰነ ቡድን ጥቅም እንዲያገኙ ሲያደርግ ይስተዋላል። ሆኖም ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀምን ለመግታት ጠንካራ የሕግ ተጠያቂነትን ማስፈን ነው። የተጠያቂነት ሥርዓት ማለት አንድ ባለስልጣን ላጠፋው ጥፋት ወይም ላጎደለው ኃላፊነት በሕግ ፊት ቀርቦ መልስ የሚሰጥበት እና ጥፋተኛ ሆኖ ሲገኝም ተመጣጣኝ ቅጣት የሚያገኝበት አሠራር ነው።

በኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ከባድ የወንጀል ድርጊት ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን በዋናነት በ2007 ዓ.ም የወጣው የሙስና ወንጀሎች አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 881/2007) እና በ1996 ዓ.ም የኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ (አንቀጽ 407) ላይ ተደንግጎ እንደሚገኝ ከፍተኛ የሕግ ባለሙያዋ ወ/ሮ ፍቅር በለጠ ጠቁመዋል።

ወንጀሉ የሚፈጸምባቸው መንገዶች

ወ/ሮ ፍቅር እንዳብራሩት ሕጉ ወንጀሉ በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ሊፈጸም እንደሚችል ያስቀምጣል፡፡

በድርጊት (By Commission)፦ ከተሰጠው ስልጣን ውጭ ሕግን በመጣስ ቀጥተኛ እርምጃ መውሰድ።  ለምሳሌ ያለአግባብ ሰነድ መፈረም እና የመንግሥት ንብረትን ለግል ሥራ ማዋል ነው፡፡ ሌላው ሳይፈጽሙ በመቅረት (By Omission) ነው፡፡ ይህም መፈጸም የሚገባውን ሕጋዊ ግዴታ ወይም አሠራር ሆን ብሎ ሳይፈጽም መቅረት ነው። ለምሳሌ የሚገባውን ቀረጥ ወይም ታክስ ሳይሰበስብ መተው እና ወንጀል ሲፈጸም እያየ ዝም ማለት እንደ ሆነ ባለሙያዋ ጠቁመዋል፡፡

ሕጋዊ ቅጣቶች (Penalties)

ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም እንደ ወንጀሉ ክብደት እና እንደሚያስከትለው የጉዳት መጠን የተለያየ የገንዘብ እና የእስራት ቅጣቶችን ያስከትላል። በዚህም ወንጀሉ ከባድ ጉዳት ወይም ከፍተኛ ጥቅም ያላስገኘ ከሆነ ቅጣቱ ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት እና መቀጮ ይሆናል።

ወንጀሉ የተፈጸመው ከባድ የወንጀል ደረጃ  ከሆነ እና ከፍተኛ ጥቅም ለማግኘት፣ በሰው ሕይወት፣ አካል ወይም በሀገር ደህንነት ላይ ከባድ ጉዳት ለማድረስ ታስቦ ከሆነ የተፈፀመው ቅጣቱ ከ10 ዓመት እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና የገንዘብ መቀጮ ያስቀጣል። ወንጀሉ የተፈጸመው ለምሳሌ በሙስና ድርጊት ከሆነ ተከሳሹ ያለአግባብ ያገኘው ማንኛውም ንብረት ወይም ገንዘብ ተወርሶ ለተበዳዩ አካል ወይም ለመንግሥት እንዲመለስ ይደረጋል።

የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣ አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 (1) መሰረት ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት ወይም በሌላ ሰው ጥቅም ወይም መብት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ለማድረግ በማሰብ የተሰጠውን ሹመት፣ ስልጣን ወይም ኃላፊነት ያለአግባብ የተገለገለበት እንደሆነ፣ በግልጽ ከተሰጠው ስልጣን ወይም ኃላፊነት አሳልፎ የሠራ እንደሆነ ወይም ስልጣኑ ወይም ኃላፊነቱ የማይፈቅድለትን ጉዳይ በተለይ ስልጣን ወይም ኃላፊነት ሳይኖረው ወይም ከሥራው ከታገደ፣ ከተዛወረ፣ ከተሻረ ወይም ስልጣኑን ወይም ኃላፊነቱን ከተወ በኋላ ስልጣኑን ወይም ኃላፊነቱን የሠራበት እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እስራት እና ከሦስት ሺህ  ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ከ10 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እና 10 ሺ ብር መቀጮ ይቀጣል፡፡

አንቀጽ 9 (2) -ኃላፊነቱ ወይም ግዴታው እንዲጣስ የተፈለገበት ዓላማ፣ የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት፣ የጥፋተኛው የኃላፊነት ወይም የስልጣን ደረጃ ወይም በግለሰብ፣ በመንግሥት ወይም በሕዝባዊ ድርጅት ጥቅም ወይም በሕዝብ ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛነት በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) መሰረት የተፈጸመ ወንጀል ከባድ አድርጎት እንደሆነ ቅጣቱ ከሰባት ዓመት እስከ 15 ዓመት መድረስ የሚችል ጽኑ እስራት እና ከ10 ሺህ ብር እስከ 100 ሺህ ብር የሚደርስ መቀጮ ይሆናል፡፡

አንቀጽ 9(3) በንዑስ አንቀጽ (2) ከተዘረዘሩት ምክንያቶች ሁለቱ ወይም ከዚያ በላይ ተደራርበው ሲገኙ ቅጣቱ ከ10 ዓመት እስከ 25 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከ20 ሺህ ብር እስከ 200 ሺህ ብር የሚደርስ መቀጮ ይሆናል፡፡

አንቀጽ 9 (4) – በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) እና (2) የተገለጸው ቢኖርም በሕዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ የሚፈጸም ከሰው ኃይል አስተዳደር ጋር የተያያዘ ጥፋት ጉቦ የመስጠት እና የመቀበል ሁኔታ መኖሩ ካልተረጋገጠ በስተቀር በሙስና ወንጀል አያስከስስም፡፡

አንቀጽ 10 (1)  ማንኛውም የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ በኃላፊነቱ ወይም በሥራ ግዴታው ማድረግ የማይገባውን ለማድረግ ወይም ማድረግ የሚገባውን ላለማድረግ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ጥቅም እንዲሰጥ የጠየቀ፣ የተቀበለ ወይም የተስፋ ቃል የተቀበለ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ ከአንድ  ዓመት በማያንስ ቀላል እስራት እና ከሦስት ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ከ10 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እና ከ40 ሺህ በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡

አንቀጽ 10 (2) ኃላፊነቱ ወይም ግዴታው እንዲጣስ የተፈለገበት ዓላማ፣ የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት፣ የጥፋተኛው የኃላፊነት ወይም የስልጣን ደረጃ ወይም በግለሰብ ወይም በመንግሥት ወይም በሕዝባዊ ድርጅት ጥቅም ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛነት በዚህ አንቀጽ ንዑስ 1 መሰረት የተፈጸመውን ወንጀል ከባድ አድርጎት እንደሆነ ቅጣቱ ከሰባት ዓመት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከ10 ሺህ ብር የማያንስ፣ ከ100 ሺህ ብር የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል፡፡

አንቀጽ 10 (3) ወንጀሉን የፈጸመው በዚህ አንቀጽ በንዑስ አንቀጽ (2) ከተዘረዘሩት ምክንያቶች ሁለቱ ወይም ከዚያ በላይ ተደራርበው ሲገኙ ቅጣቱ ከ10 ዓመት እስከ 25 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከ20 ሺህ ብር እስከ 200 ሺህ ብር  ይሆናል፡፡

አንቀጽ 10 (4) ማንኛውም የመንግሥት ወይም ሕዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) በተገለጸው መሰረት ወንጀሉን የፈጸመው ከዓለም አቀፍ ግብይት ወይም ግንኙነት ጋር በተያያዘ የሥራ ግዴታ ድንበር ዘለል ኮርፖሬሽንን ጨምሮ ከማንኛውም ከሌላ ሀገር መንግሥት፣ ድርጅት፣ ሰው ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅት ጥቅም ወይም ስጦታ የጠየቀ፣ የተቀበለ፣ ወይም ለመቀበል የተስማማ  እንደነገሩ ሁኔታ በዚህ አንቀጽ (1)፣ (2)፣ ወይም (3) ከተመለከቱት ቅጣቶች በአንዱ ይቀጣል፡፡

አንቀጽ 18 ማንኛውም የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ በኃላፊነቱ ወይም በሥራው ምክንያት በቀረበለት ጉዳይ ላይ ጥቅም ካለው ማንኛውም ሰው በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ጥቅም ለማግኘት፣ በጉዳዩ ላይ ጥቅም ያለውን ማንኛውንም ወገን ለመጥቀም ወይም ለመጉዳት ሲል ከሕግ ወይም ከሥራ ደንብ፣ ወይም ከመመሪያ ወይም ከተለመደው አሠራር ውጪ ያለበቂ ምክንያት ያልወሰነ፣ ያዘገየ፣ ወይም ባለጉዳይን ያጉላላ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ በመቀጮ ወይም በቀላል እስራት ወይም ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እና ከአምስት ሺህ ብር በማይበልጥ እንደሚቀጣ ባለሙያዋ በሰጡት ማብራሪያ አስገንዝበዋል፡፡

ሕጋዊ ትርጋሜ

በሕጉ መሰረት ማንኛውም የመንግሥት ወይም በሕዝብ ተመርጦ የተሾመ ወይም የተቀጠረ ሠራተኛ የሥራ ድርሻውን ወይም ኃላፊነቱን ወደ ጎን በመተው ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ያለአግባብ ጥቅም ወይም ብልጽግና ለማስገኘት ካሰበ ወይም በሌላ ሰው መብት ወይም ጥቅም ላይ ጉዳት ለማድረስ አስቦ የሥራ ኃላፊነቱን ካላከበረ፣ ሕግ እና መመሪያን ከጣሰ ወይም ካልተገበረ ስልጣንን ያለአግባብ የመጠቀም ወንጀል ፈጽሟል ይባላል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የሐምሌ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here