የሰው ልጅ እና ጠፈር

0
205

ጥንታዊ የጠፈር ምርመር በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ረጅም እና ጥልቅ ታሪክ ያለው የሳይንስ ዘርፍ ነው። በጥንቱ ዘመን የዛሬው ዓይነት የረቀቁ የሳተላይት እና የሮኬት ቴክኖሎጂዎች ባይኖሩም ጥንታውያን ስልጣኔዎች አይናቸውን ወደ ሰማይ በመላክ ከዋክብትን እና ፕላኔቶችን በመታዘብ ረቂቅ የጠፈር ምርምሮችን ያካሂዱ ነበር። ይህ ምርምር በዋናነት ለግብርና፣ ለቀን መቁጠሪያ (ካላንደር) መስሪያ፣ ለጉዞ አቅጣጫ መጠቆሚያ እና ለሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶች ያገለግል ነበር።

ጥንታዊት ኢትዮጵያ በከዋክብት ምርምር ቀዳሚ ከሆኑ ሀገራት አንዷ ነች። የታሪክ ተመራማሪዎች እንደሚገልጹት ጥንታውያን ኢትዮጵያውያን የከዋክብትን ሳይንስ በመጀመር እና ለፕላኔቶች እንደ ባህሪያቸው ስም በመስጠት ይታወቃሉ። ለአብነት የቦረና ኦሮሞ የቀን መቁጠሪያ ከዋክብትን እና ጨረቃን መሰረት ያደረገ እጅግ ረቂቅ ባህላዊ የጠፈር ስሌት ነው። የአክሱም ሀውልቶች አቀማመጥ እና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትም ከሰማያዊ አካላት እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ የምህንድስና ጥበብ እንዳላቸው ጥናቶች ያሳያሉ።

ሜሶፖታሚያዊያን (ባቢሎናውያን) በታሪክ የመጀመሪያውን የከዋክብት ካርታ እና የምድብ ስብስቦችን የሠሩ  ናቸው። ጨረቃን መሰረት ያደረገ የቀን መቁጠሪያ ፈጥረዋል። ጥንታዊ ግብፅ የዓባይን ወንዝ ሙላት እና የግብርና ወቅትን ለማወቅ “ሲሪየስ” (Sirius) የተባለችውን ደማቅ ኮከብ በቅርብ ይከታተሉ ነበር። ታዋቂዎቹ ፒራሚዶችም የተገነቡት በቀጥታ ከከዋክብት አቀማመጥ ጋር እንዲገጣጠሙ ተደርጎ ነው። ግሪካውያን እንደ አርስቶትል፣ ቶለሚ እና ሂፓርከስ ያሉ ፈላስፎች እና ሳይንቲስቶች የጠፈርን አካሄድ በሂሳብ እና በጂኦሜትሪ አስደግፈው አጥንተዋል። መሬት ክብ መሆኗን በጥንቱ ዘመን ያረጋገጡትም እነዚሁ ተመራማሪዎች ናቸው። በማዕከላዊ አሜሪካ የነበሩት ማያዎች የቬነስን (የጽዮን ኮከብ) እና የፀሐይን ዑደት በመለካት እጅግ በጣም ትክክለኛ የሆነ ዘመናዊ የቀን መቁጠሪያ አዘጋጅተው ነበር።

በጨረቃ እና በሰው ልጅ ታሪክ መካከል ያለው ግንኙነት እጅግ ጥልቅ ከመሆኑም በላይ ባህላችንን፣ ሳይንስን እና የጠፈር ምርምራችንን ቀርጿል።

በጥንት ዘመን የነበሩ ህዝቦች በምሽት ወደ ሰማይ በመመልከት ጨረቃን ከሃይማኖታዊ ህይወታቸው ጋር አገናኝተዋታል። እንደ ጥንታዊት ግብፅ፣ ግሪክ እና ሮም ያሉ ስልጣኔዎች ለጨረቃ አማልክት አምልኮ ያደርጉ የነበረ ሲሆን የጨረቃን መደበኛ ኡደት በመጠቀምም የዓለምን የመጀመሪያ የቀን መቁጠሪያዎች ፈጥረዋል። እነዚህ የቀን መቁጠሪያዎች ዛሬም ድረስ ለተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓላት በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

የሰው ልጅ ወደ ሳይንሳዊው ዘመን ሲሸጋገር ከጨረቃ ጋር ያለው ግንኙነት ከአምልኮ ወደ ትዝብትና ምርምር ተቀየረ። ጋሊልዮ ጋሊሊ ቴሌስኮፑን ወደ ሰማይ አቅንቶ ጨረቃ ልሙጥና ፍጹም ክብ ሳትሆን ተራራና ጉድጓዶች የበዙባት ሌላ ዓለም መሆኗን ባረጋገጠ ጊዜ ስለ አጽናፈ ሰማይ ያለንን ግንዛቤ ለዘላለም ለወጠው።

ይህ የማወቅ ጉጉት በሃያኛው ክፍለ ዘመን ለተቀሰቀሰው የጠፈር ፉክክር መንስኤ በመሆን የሰውን ልጅ ታላቅ የቴክኖሎጂ ስኬት አስገኝቷል። አሜሪካዊው ጠፈርተኛ ኒል አርምስትሮንግ በጨረቃ ገጽ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በመራመድ ታሪክ የሰራ ሲሆን ይህም የሰው ልጅ ከገዛ ፕላኔቱ ባሻገር መድረስ እንደሚችል ያሳየ ነበር።

የዘመናዊው የጠፈር ምርምር በዋናነት መሠረት የተጣለው በሃያኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ በጀርመናዊው ሳይንቲስት ቨርነር ቮን ብራውን የተሰራው ቪ-2 (V-2) የተሰኘው ሚሳይል ለመጀመሪያ ጊዜ የመሬት ከባቢ አየርን አልፎ በወጣበት ወቅት ነበር። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ ይህ የሮኬት ቴክኖሎጂ ወደ አሜሪካ እና ሶቪየት ህብረት በመሸጋገሩ ለጠፈር ምርምር መፋጠን ትልቁን በር ከፈተ።

የጠፈር ምርምር ታሪክ የሰው ልጅ ከምድር ስበት ወጥቶ የጽንፈ ዓለምን ምስጢራት ለመግለጥ ያረገውን  አስደናቂ ጉዞ ያሳያል። ይህ ታላቅ ጉዞ በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ በዩናይትድ ስቴትስ እና በሶቪየት ህብረት መካከል በነበረው ከፍተኛ የቀዝቃዛ ጦርነት ፉክክር ምክንያት እጅግ በጣም ፈጣን እድገት አሳይቷል።

ዘመናዊው የጠፈር ዘመን በይፋ የጀመረው እ.አ.አ በጥቅምት ወር 1957  ሶቪየት ህብረት ስፑትኒክ 1 የተባለችውን የዓለማችንን የመጀመሪያዋን ሰው ሰራሽ ሳተላይት በተሳካ ሁኔታ ወደ ህዋ ስታመጥቅ ነበር። ይህ ታሪካዊ ስኬት መላውን ዓለም ያስገረመ ሲሆን የጠፈር ውድድር ተብሎ የሚጠራውን ከባድ ፉክክር ቀስቅሷል። ከጥቂት ዓመታት በኋላ እ.አ.አ ሚያዝያ 1961   የሶቪየት ህብረቱ ጠፈርተኛ ዩሪ ጋጋሪ በቫስቶክ 1 መንኮራኩር ምድርን በመዞር የመጀመሪያው የህዋ ተጓዥ በመሆን ታሪክ ሰርቷል። ሶቪየቶች እ.ኤ.አ. በ1963  ቫለንቲና ቴሬሽኮቫን ወደ ህዋ በመላክ የመጀመሪያዋን ሴት የጠፈር ተጓዥ ማድረግ ችለዋል።

በዚህ ውድድር ለመቀደም ያልፈለገችው አሜሪካ በአፖሎ ፕሮግራም አማካኝነት ጨረቃ ላይ ለመድረስ ትኩረት አድርጋ ሰርታለች። ይህ ምኞት እ.አ.አ ሐምሌ 20 ቀን 1969  አፖሎ 11 መንኮራኩር በጨረቃ ላይ በተሳካ ሁኔታ ሲያርፍ እውን ሆኗል። በዚህም ኒል አርምስትሮንግ እና ባዝ ኦልድሪን ጨረቃ ላይ ለመራመድ በቅተዋል። አርምስትሮንግ ይህንን ታሪካዊ ወቅት ለአንድ ሰው ትንሽ እርምጃ ለሰው ልጅ ግን ግዙፍ ዝላይ በማለት ገልጾታል።

ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ያ የነበረው ከባድ ፉክክር በህዋ ላይ ረጅም ጊዜ የመቆየት ጥናት እና ዓለም አቀፍ ትብብር ወደማድረግ ተቀየረ። ሶቪየት ህብረት ሳሊዩት እና ሚር የተባሉ የመጀመሪያዎቹን የጠፈር ጣቢያዎች የገነባች ሲሆን አሜሪካ ደግሞ ስካይላብን መሰረተች። ይህ ዘመን እ.አ.አ. በ1998  ለተመሰረተው ዓለም አቀፍ የጠፈር ጣቢያ መፈጠር መንገድ የከፈተ ሲሆን የቀድሞ ተቀናቃኞችን በጋራ ለሳይንሳዊ ምርምር እንዲሠሩ አድርጓል።

በታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያ ከዘመናዊ የጨረቃ ላይ ጉዞ ጋር በቀጥታ ስም ባይኖራትም ከጨረቃ ጥናት እና ከጠፈር ምርምር ታሪክ ጋር የሚያገናኟት በርካታ ትኩረት የሚስቡ ሁነቶች አሉ። የመጀመሪያውና ዋናው ናሳ (NASA) ከዓለም መሪዎች የተላኩ የሰላም መልዕክቶችን በትንሽ የፕላቲኒየም ዲስክ ላይ ቀርጾ ከጠፈርተኞቹ ጋር ወደ ጨረቃ ልኳል። በወቅቱ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሤ ያስተላለፉት መልዕክት በጥንታዊው የግዕዝ ቋንቋ ተጽፎ ከዲስኩ ጋር ጨረቃ ላይ  አርፏል፤ መልዕክቱም የሰው ልጅ በሰላም እና በወንድማማችነት እንዲኖር የሚማጸን ነበር። ይህም ግዕዝን ጨረቃ ላይ ከደረሱ ጥቂት የዓለም ቋንቋዎች አንዱ ያደርገዋል።

ይህ ታሪካዊ ጉዞ ከተሳካ በኋላ በዚያው ዓመት እ.አ.አ በጥቅምት ወር 1962  ጨረቃን የረገጡት ጠፈርተኞች ኒል አርምስትሮንግ፣ ባዝ ኦልድሪን እና ማይክል ኮሊንስ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር። ጠፈርተኞቹ አዲስ አበባ ሲገቡ በሺህ በሚቆጠሩ ሰዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ ዐፄ ኃይለ ሥላሤም የክብር ሜዳሊያ ሸልመዋቸዋል። በተጨማሪም ጠፈርተኞቹ ከጨረቃ ያመጡትን አነስተኛ የጨረቃ አፈር እና ድንጋይ ናሙና ከኢትዮጵያ ባንዲራ ጋር ለዐፄ ኃይለ ሥላሴ በስጦታ አበርክተዋል። ይህ “የአፖሎ 11 የጨረቃ ድንጋይ” (Apollo 11 Moon Rock) ዛሬም ድረስ በአዲስ አበባ በሚገኘው ብሔራዊ ሙዚየም ውስጥ ለጉብኝት ተቀምጦ ይገኛል።

በቅርብ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ በዘርፉ የራሷን አሻራ ማሳረፍ ጀምራለች። በኢትዮጵያ የጠፈር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና በእንጦጦ ማስተማሪያ እና ምርምር ማዕከል የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች በቴሌስኮፕ አማካኝነት የጨረቃን ገጽታና ከዋክብትን የማጥናት ሥራ ይሠራሉ። ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን ሳተላይት (ET-RSS1) በ2019 እ.አ.አ ወደ ጠፈር ማምጠቋም ለወደፊቱ የጨረቃ እና የጠፈር ጥናቶች የሀገር ውስጥ አቅምን ለመገንባት ትልቅ መሠረት ጥሏል።

በአሁኑ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የጠፈር ምርምር እንደ ስፔስ ኤክስ እና ብሉ ኦሪጅን (SpaceX እና Blue Origin) ያሉ የግል ኩባንያዎች በመሳተፋቸው አዲስ ምዕራፍ ላይ ደርሷል። እነዚህ ኩባንያዎች ወደ ጠፈር የመጓዣ ወጪን በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሱት ይገኛሉ። በአሁኑ ጊዜ ትኩረቱ ወደ ጥልቁ ህዋ የዞረ ሲሆን ሮቦቶች ማርስ ላይ የቀደመ ህይወት መኖር አለመኖሩን እያጠኑ ይገኛሉ፤ እንዲሁም እንደ ጄምስ ዌብ ያሉ የጠፈር ቴሌስኮፖች ስለ ጽንፈ ዓለም አጀማመር አዳዲስ መረጃዎችን እያቀረቡ ነው። ምንጮቻችን ናሳ ሂስትሪ፣ ዓለም አቀፉ ኤሮኖቲክስ ፌደሬሽን እና ናሽናል ጂኦግራፊክ ናቸው፡፡

ሳምንቱ በታሪክ

የአቡነ ጴጥሮስ መስዋዕትነት

አቡነ ጼጥሮስ ሐምሌ 21 ቀን 1928 ዓ.ም በጣሊያች ጥይት በግፍ ተደብድበው መሰዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ የአቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ወቅት የኢትዮጵያን ነፃነት እና ክብር ያስጠበቀ ታላቅ ታሪካዊ ክስተት ነው። የምሥራቅ ኢትዮጵያ ጳጳስ የነበሩት አቡነ ጴጥሮስ ጠላት ሀገርን በወረረበት ወቅት ወደ አርበኞች ዘንድ በመሄድ ህዝቡ ለነፃነቱ እንዲታገል መንፈሳዊ ማበረታቻ ሲሰጡ የቆዩ ሲሆን በአዲስ አበባ በተደረገው የአርበኞች ማጥቃት ወቅት በጠላት እጅ ተማረኩ። የጣሊያን ባለሥልጣናት የህዝብ ተሰሚነታቸውን በመጠቀም አርበኞች እጃቸውን እንዲሰጡ እንዲያደርጉ ቢጠይቋቸውም እሳቸው ግን ለጠላት ለመገዛት ፈቃደኛ ባለመሆን የኢትዮጵያ ምድርና ህዝብ ለፋሽስት እንዳይገዛ በሥልጣነ ክህነታቸው አወገዙ።

በዚህ ፅናታቸው ምክንያት የሞት ፍርድ ተፈረደባቸው፤ በአዲስ አበባ ከተማ እምብርት ላይ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ በተሰበሰበበት ፊት በጥይት ተደብድበው ሰማዕትነትን ተቀበሉ። ከመገደላቸው በፊት ዐይናቸውን እዲሸፈኑ ሲጠየቁ “የአገሬን መሬት እና የህዝቤን ፊት እያየሁ መሞት እፈልጋለሁ” በማለት ውድቅ ማድረጋቸው እና ያሳዩት ታላቅ ፅናት የኢትዮጵያውያንን የአርበኝነት ስሜት በከፍተኛ ደረጃ በማቀጣጠል ለአምስት ዓመቱ የነፃነት ትግል ትልቅ መንፈሳዊ ጉልበት ሆኗል።

ምንጭ፡ “የኢትዮጵያ ታሪክ”- ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የሐምሌ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here