አክራ – የጥቁር ሕዝብ ማንነት ምልክት

0
293

የአትላንቲክ ውቅያኖስ ሞቃት እና ጨዋማ ነፋስ ፊትን እየዳበሰ፣ የጊኒ ባሕረ ሰላጤ ማዕበል ከዳርቻው አሸዋ ጋር ሲላተም የሚፈጥረው ዜማ የጋና መዲና የሆነችውን የአክራን ከተማ የዕለት ተዕለት ሕይወት ይገልጣል። ፀሐይዋ በምዕራብ አፍሪካ ሰማይ ላይ ደምቃ መውጣት ስትጀምር ይህች ታሪካዊት ከተማ በማይነጥፍ እና አስገራሚ ኃይል ትነቃለች። ወደ ታዋቂው ማኮላ ገበያ  ብቅ ሲሉ በቀለማት ያሸበረቁትን እና የዓይን ማረፊያ የሆኑትን ባህላዊ የኬንቴ እና የአንካራ ልብሶችን የለበሱ እናቶች በጭንቅላታቸው ላይ ከባድ ሸቀጦችን ተሸክመው በሚያስገርም ሚዛን እና ቅልጥፍና ሲራመዱ ይታያሉ። በከተማዋ አውራ ጎዳናዎች ላይ የትሮትሮ (የሕዝብ ማመላለሻ ሚኒባሶች) ረዳቶች ተሳፋሪ ለመጥራት የሚያሰሙት ጩኸት፣ ከጎዳና ዳር ከሚጠበሰው የቹባ (ዓሳ) እና በርበሬ በዛ ተደርጎበት ከሚሰራው የጆሎፍ ራይስ ጠረን ጋር ተደባልቆ አእምሮን ይስባል፣ ሆድንም ያስርባል።

በአንድ በኩል ከዘመነ ቅኝ ግዛት የተረፉ ጥንታዊ ግንቦች ከዘመናት ብልሽት ጋር ሲታገሉ በሌላ በኩል ደግሞ የሰማይ ጠቀስ ዘመናዊ ሕንፃዎች መስታዎቶች የፀሐይዋን ብርሃን ያንፀባርቃሉ። ይችው የድሮው እና የአዲሱ፣ የባህላዊው እና የዘመናዊው ሥልጣኔ አስደናቂ ውህደት በጉልህ የሚታይባት የጋና የልብ ትርታ የሆነችው ከተማ አክራ ናት።

የአክራ አመሰራረት

አክራ የጋና ሪፐብሊክ ዋና ከተማ ትልቋ የንግድ ማዕከል እና ብዙ ሕዝብ  የሚገኝባት ዋነኛ ስፍራ ናት። የከተማዋ ስም አመጣጥ ንክራን  ከሚለው የጥንታዊው የአካን ቋንቋ ቃል የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም “ጉንዳኖች” ማለት ነው። ይህ ስያሜ የተሰጠው ባካባቢው መጀመሪያ ለሰፈሩት እና የከተማዋ መሥራች ለሆኑት የ”ጋ” (Ga) ብሔረሰብ አባላት ሲሆን ስያሜው የተሰጣቸውም በብዛታቸው እና በጦርነት ጊዜ በነበራቸው ሰፊ የስምሪት ጥበብ ምክንያት ነው።

አክራ እንደ ከተማ መመስረት የጀመረችው በ15ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ነው። ሆኖም የከተማዋን ዕጣ ፈንታ በቀየረው የ17ኛው ክፍለ ዘመን የአውሮፓውያን መምጣት ምክንያት ፖርቱጋሎች፣ ደቾች፣ ዴንማርካውያን እና እንግሊዞች በባሕር ዳርቻዋ ላይ የንግድ እና የባሪያ ፍንገላ ምሽጎችን ገነቡ። በዴንማርካውያን የተገነባው ኦሱ ካስል እና በእንግሊዞች የተገነባው ጀምስ ፎርት የታሪኩ አካል ናቸው። ከጊዜ በኋላ የብሪታንያ ተፅዕኖ ጎልቶ እ.አ.አ በ1877 እንግሊዞች ዋና ከተማቸውን ከኬፕ ኮስት ወደ አክራ አዛወሩ። ከዚህ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ጀምሮ አክራ በከፍተኛ ፍጥነት ማደግ ጀመረች።

የአክራ ሕዝብ

አክራ የሰዎችን ብዝሃነት እና የቁጥር ግዝፈት በሚገባ የምታሳይ ከተማ ናት። የከተማዋ መስተዳድር (City Proper) በ225.67 ካሬ ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ላይ ያረፈ ሲሆን ታላቋ አክራ (Greater Accra Region) ተብሎ የሚጠራው ሰፊው የሜትሮፖሊታን ክልል ደግሞ 3ሺህ245 ካሬ ኪሎ ሜትር ይሸፍናል። እ.አ.አ በ2021 በተደረገው ብሔራዊ የሕዝብ ቆጠራ እና በቅርብ ጊዜ ግምቶች መሠረት የታላቋ አክራ ነዋሪዎች ቁጥር ከ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ደርሷል። ከዚህ ግዙፍ የሕዝብ ቁጥር ውስጥ የከተማዋ ነዋሪ ከሞላ ጎደል (ከ99 በመቶ በላይ) ጥቁር አፍሪካውያን ናቸው። ይህ ፍፁም የሆነ የጥቁር ሕዝብ ስብጥር ከተማዋን የእውነተኛ አፍሪካዊ ማንነት፣ የነፃነት እና የፓን-አፍሪካኒዝም ማዕከል ያደርጋታል። በብሔረሰብ ስብጥር ረገድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የአካን (Akan) ብሔረሰብ አባላት የከተማዋን ሕዝብ 39 በመቶ፣ የመጀመሪያዎቹ ሰፋሪዎች የሆኑት የጋ-ዳንግሜ (Ga-Dangme) ሕዝቦች 27 በመቶ፣ እንዲሁም የኤዌ (Ewe) ብሔረሰብ 16 በመቶ ያህሉን ይሸፍናሉ። ቀሪው 18 በመቶ ሌሎች የጋና ብሔረሰቦችን እና ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ ጥቁር ዜጎችን ያካትታል። አክራ እጅግ ወጣት የሆነ የሕዝብ ስብጥር ያላት ስትሆን ከነዋሪዎቿ ውስጥ 56 በመቶ ያህሉ ከ24 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች ናቸው።

የከተማዋ መዋቅር የታሪክ አሻራዎችን እና የፈጣን የከተሜነት ዕድገትን ያሳያል። ጀምስታውን እና ኡሸርታውን በመባል የሚታወቁት የከተማዋ ጥንታዊ ክፍሎች ጠባብ መንገዶች እና ጥንታዊ የድንጋይ ቤቶች ያሉባቸው ሲሆኑ የሀብታሞች እና የዲፕሎማቶች መኖሪያ የሆኑት ካንቶንመንትስ እና ሪጅ ደግሞ በዘመናዊ ቪላዎች እና ኤምባሲዎች የተሞሉ ናቸው። የከተማዋ የንግድ እና የመዝናኛ ልብ የሆነው ኦሱ ሰፈር በተለይም ኦክስፎርድ ስትሪት በምሽት ህይወቱ እጅግ የደመቀ ነው። በቅርብ ዓመታት አክራ ሞል እና ኤርፖርት ሲቲ የመሳሰሉ ግዙፍ የንግድ ማዕከላት ብቅ ብቅ በማለት ከተማዋን ወደ ዘመናዊ ሜትሮፖሊታን ቀይረዋታል።

ታሪካዊ መስህቦች

ይህች ደማቅ ከተማ የአፍሪካን የነፃነት ትግል ታሪክ የሚዘክሩ ታላላቅ መስህቦችን አቅፋለች። የጋና የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ክዋሜ ንክሩማህ የተቀበሩበት የክዋሜ ንክሩማህ መታሰቢያ ፓርክ እንዲሁም ጋና በ1957 ነፃ መውጣቷን ለማሰብ የተገነባውና 30 ሺህ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችለው የነፃነት አደባባይ ዋነኞቹ ናቸው። በ1930ዎቹ የተገነባው ጀምስታውን ላይትሀውስ እና ታዋቂው አሜሪካዊ የሰብአዊ መብት ታጋይ ያረፉበት የደብሊው ኢ ቢ ዱቦይስ ማዕከል ለታሪክ ተመራማሪዎች ታላቅ ቤተመዘክር ናቸው። ለመዝናኛ ደግሞ ላባዲ የባህር ዳርቻ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በባህላዊ ከበሮዎች እና የፈረስ ግልቢያ ጥበቦች ደምቆ ይውላል።

የአክራ ሕዝብ ባህል እና አኗኗር በከፍተኛ ማሕበራዊ ትስስር የተሞላ ነው። በየዓመቱ ነሐሴ ወር ላይ በከፍተኛ ድምቀት የሚከበረው የሆሞዎ  በዓል የከተማዋ አንጋፋ ባህላዊ ክዋኔ ነው። ሆሞዎ ማለት “ረሀብን ማባረር” ማለት ሲሆን የጋ ሕዝቦች በጥንት ዘመን የነበረውን አስከፊ ረሀብ በአንድነት ማለፋቸውን በማሰብ ክፖክፖይ የተባለ ባህላዊ ምግብ አዘጋጅተው ይበላሉ። በሙዚቃው ዓለም አክራ የሀይላይፍ እና የአፍሮቢት ሪትም ማዕከል ናት። በምግብ ባህላቸውም ዋክዬ፣ ባንኩ እና የጋና ጆሎፍ ራይስን በስፋት ይመገባሉ። ከሁሉም በላይ የነዋሪው ትህትና ወደር የሌለው ሲሆን አክዋባ (እንኳን ደህና መጣችሁ) ብለው በሚያቀርቡት ፈገግታ ይታወቃሉ።

ምጣኔ ሀብት

አክራ የጋና የፖለቲካ ማዕከል ብቻ ሳትሆን የሀገሪቱ ዋነኛ የምጣኔ ሀብት ሞተር ናት። የከተማዋ ምጣኔ ሀብት እጅግ የተለያየ ሲሆን አሀዛዊ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ታላቋ አክራ ብቻዋን ከጋና አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ከ25 እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን ታመነጫለች። አብዛኛዎቹ የፋይናንስ ተቋማት እና የቴሌኮሙኒኬሽን ኩባንያዎች እዚሁ ይገኛሉ። የማምረቻው ዘርፍ በከተማዋ ዳርቻዎች ከ800 በላይ መካከለኛ እና ግዙፍ ፋብሪካዎችን (የምግብ ማቀነባበሪያ፣ ጨርቃ ጨርቅ እና ኬሚካል) አቅፎ ይገኛል። መደበኛ ያልሆነው የንግድ እንቅስቃሴ ደግሞ የአክራ የጀርባ አጥንት ነው። ለምሳሌ በማኮላ እና ካኔሺ ገበያዎች ውስጥ ከ70ሺህ በላይ ማርኬት ዉሜን (የገበያ እናቶች) በየቀኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የገንዘብ ልውውጥ ያካሂዳሉ። ከዚህም በተጨማሪ አክራ የምዕራብ አፍሪካ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ማዕከል በመሆን ላይ ስትሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ የቴክኖሎጂ ጀማሪ ኩባንያዎች  በከተማዋ ተመስርተዋል።

ለማጠቃለል ያህል አክራ የትናንትናውን የባርነት እና የቅኝ ግዛት ጠባሳን አሽቀንጥራ የጣለች፣ የነፃነትን ጮራ ለአፍሪካ ያበሰረች እና ዛሬ ደግሞ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የምትገኝ ድንቅ የጥቁር ሕዝቦች ከተማ ናት። የ”ጋ” ሕዝቦች ባህላዊ የከበሮ ድምፅ ከዘመናዊው አፍሮቢት ጋር የሚዋሀድባት፣ የድሮው ታሪክ ከአዲሱ ስልጣኔ ጋር የተዛመደባት መዲና ናት።

አክራ የጋና ብቻ ሳትሆን፣ የታሪካዊው ፓን-አፍሪካኒዝም ማዕከል እንደመሆኗ መጠን አሁንም የመላው ዓለም ጥቁር ሕዝብ ተስፋ ነች። “አክዋባ” የሚለው ሞቅ ያለ ሰላምታዋ፣ ከተማዋ ጎብኚን አቅፋ የምትይዝ፣ ማለቂያ የሌለው የሕይወት ዜማ የምትጫወት ታላቅ እና ቁልፍ የአፍሪካ መዲና መሆኗን ያረጋግጣል።

 

አጫጭር እውነታዎች

ስለ ጋና አጫጭር መረጃዎች

  • ጋና በምዕራብ አፍሪካ የምትገኝ ሀገር ናት።
  • ዋና ከተማዋ አክራ (Accra) ናት።
  • በምዕራብ ከኮትዲቯር፣ በሰሜን ከቡርኪና ፋሶ፣ በምስራቅ ከቶጎ እና በደቡብ ከጊኒ ባሕረ ሰላጤ ትዋሰናለች።
  • የመንግሥት ቋንቋ እንግሊዝኛ ሲሆን፣ ትዊ (Twi)፣ ኤዌ (Ewe)፣ ጋ (Ga) እና ሌሎች አካባቢያዊ ቋንቋዎችም በስፋት ይነገራሉ።
  • የሕዝቧ ብዛት ከ35 ሚሊዮን በላይ ነው።
  • የገንዘብ አሃዷ ጋና ሴዲ (Ghanaian Cedi) ይባላል።
  • ጋና እ.አ.አ በ1957 ዓ.ም ከብሪታንያ ነፃነቷን ያገኘች ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት መካከል የመጀመሪያዋ ነች።
  • የመጀመሪያው ፕሬዚዳንቷ Kwame Nkrumah ነበሩ።
  • የኢኮኖሚዋ ዋና መሠረቶች ወርቅ፣ ካካዋ ፣ ዘይት እና ግብርና ናቸው።
  • ጋና በዓለም ላይ ከትልቁ የካካዋ አምራች ሀገራት አንዷ ናት።
  • ብሔራዊ ቡድኗ በእግር ኳስ ታዋቂ ሲሆን Black Stars በመባል ይታወቃል።
  • ታዋቂ የቱሪስት መዳረሻዎች የባህር ዳርቻ ቤተመንግስቶች፣ Cape Coast Castle እና Kakum National Park ናቸው።
  • በአጠቃላይ ጋና በአፍሪካ ውስጥ በአንፃራዊነት የተረጋጋ ዴሞክራሲ እና ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በማድረግ የምትታወቅ ሀገር ናት።

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የሐምሌ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here