የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት

0
212

ኢትዮጵያ ያሉባትን የፖለቲካ፣ የታሪክ፣ የኢኮኖሚ፣ የማሕበራዊ እና ሌሎች የሀገሪቱን ዜጎች ለግጭት የሚዳርጉ ችግሮቿን በምክክር ለመፍታት በማለም ሥራዎቿን ከጀመረች አራት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሐምሌ 8 /2018 ዓ.ም ከሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች እና ከሁለት የከተማ አስተዳደሮች፣ ከዲያስፖራ ተወካዮች እና ከሲቪክ ማሕበራት እንዲሁም ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጡ አራት ሺህ ሰዎች አዲስ አበባ ከከተሙ ሳምንት አልፏቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር የሀገራዊ ምክክር ጉባኤውን አሁናዊ ሂደት አስመልክተው ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫም ተመካካሪዎች ከሐምሌ 13 ቀን ጅምሮ በንዑስ ቡድኖች ተከፋፍለው በተመደቡባቸው አጀንዳዎች ላይ መመካከር ጀምረዋል፡፡ እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ ለእያንዳንዱ አጀንዳ 500 ተመካካሪዎችን ያካተተ ዐቢይ የሥራ ቡድን ተደራጅቷል፡፡

እያንዳንዱ ዐቢይ ቡድን ደግሞ 50 ተመካካሪዎች ያሉባቸው 10 ንዑስ ቡድኖችን የያዘ ሲሆን በአጠቃላይ 80 ንዑስ ቡድኖች በተመደቡላቸው አጀንዳዎች ላይ ውይይት እያካሄዱ ነው፡፡

ከሐምሌ 8/2018 ዓ.ም. ጀምሮ ተመካካሪዎቹ በኮሚሽኑ ይፋ በተደረጉት ስምንት አጀንዳዎች ላይ ተመድበው ቅድመ ምክክር ውይይቶችን፣ ትውውቆችን እና በምክክሩ የአሠራር ሥርዓቶች ላይ ግንዛቤ ሲወስዱ ቆይተዋል፡፡

ኮሚሽነሩ እንደገለጹት የተጀመረው የንዑስ ቡድን ውይይት የሀገራዊ ምክክሩ ቁልፍ ምዕራፍ ሲሆን ተመካካሪዎች በተመደቡባቸው አጀንዳዎች ላይ ሐሳባቸውን የሚያቀርቡበት እና አንዱ የሌላውን ሐሳብ በማዳመጥ የሚመካከሩበት ሂደት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የንዑስ ቡድን ውይይቶች ልዩነቶች የሚደመጡበት፣ ሐሳቦች የሚፈተኑበት፣ ጥያቄዎች በጥልቀት የሚመረመሩበት እና መግባባት በትዕግሥት የሚገነባበት ወሳኝ መድረክ ነው፡፡ እያንዳንዱ ተሳታፊ ድምፁን በነፃነት ያሰማል፤ የሌሎችን ሀሳብ በአክብሮት ያዳምጣል፤ የተለያዩ እይታዎችም  በምክንያትና  በማስረጃ ይመዘናሉ፡፡

በዚህ ሂደት የሚፈጠረው መግባባት ለጋራ ራዕይ መገንባት እና ለዘላቂ ሰላም ጠንካራ መሠረት  መሆኑን የኢትዮጵያ የምክክር ኮሚሽን በድረገጹ ያሰፈረው መረጃ ያስረዳል፡፡

የምክከር ኮሞሽኑ እንደገለጸው በንዑስ ቡድኖች  ላይ የሚቀርብ እያንዳንዱ ሀሳብ ዋጋ አለው፤ እያንዳንዱ ድምፅ ይደመጣል፤ እያንዳንዱ ውይይት የጋራ ነገን ለመገንባት አንድ ተጨማሪ ርምጃ ነው፡፡ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ውስጥ የንዑስ ቡድን ውይይቶች ከመደበኛ ውይይት በላይ የሆነ ትርጉም አላቸው፡፡ እነዚህ መድረኮች የተለያዩ ልምዶች፣ እይታዎች፣ እሴቶች እና ተሞክሮዎች በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስበው በጥልቀት የሚመክሩባቸው ወሳኝ የሀሳብ ማንሸራሸሪያ ማዕከላት ናቸው፡፡

በእነዚህ ውይይቶች ውስጥ እያንዳንዱ ተሳታፊ ሀሳቡን በነፃነትና በኃላፊነት ያቀርባል፡፡

የሌሎችን ሀሳብ በትዕግሥት ያዳምጣል፣ ጥያቄዎችን ያነሳል፣ ማብራሪያዎችን ይጠይቃል፣ እንዲሁም በማስረጃና በምክንያት የተደገፉ አስተያየቶችን ያቀርባል፡፡ ይህ ሂደት ልዩነቶችን እንደ ግጭት ሳይሆን እንደ የመማማሪያና የመግባቢያ ዕድል እንዲታዩ ያግዛል፡፡ ተመካካሪዎች  ሀሳቦችን በአንድ ጊዜ አያፀድቁም፡፡

ይወያዩባቸዋል፣ ይመረምራሉ፣ ይሻሻላሉ፣ ይጠናከራሉ፡፡ በዚህም የተለያዩ እይታዎችን ያካተቱና ሰፊ ድጋፍ ሊያገኙ የሚችሉ ምክረ ሀሳቦች ይፈጠራሉ፡፡

የንዑስ ቡድን ውይይቶች አስፈላጊነታቸው በሐሳብ ልውውጥ ብቻ አይወሰንም፡፡ እርስ በርስ የመተማመን ባሕልን፣ የመደማመጥ ልምድን እና የጋራ መፍትሔ ፍለጋን ያጠናክራሉ፡፡

ሀገራዊ ጉዳዮች በአንድ ወገን እይታ ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሲታዩ የተሻሉ መፍትሔዎች ሊገኙ እንደሚችሉ ይህ ሂደት ያሳያል፡፡

በመጨረሻም የንዑስ ቡድን ውይይቶች የሀገራዊ ምክክር ልብ እነደሆኑ ነው የምክክር ኮሚሽኑ ያሳወቀው፡፡ በነዚህ ቡድኖች የሚነሳ ሀሳብ የነገን አቅጣጫ ሊቀይር እንደሚችል እና በውይይቱ የሚፈጠር መግባባትም የጋራ የወደፊት ጉዞን ሊያጠናክር እንደሚችል ጠቁሟል፡፡

የውይይቱን ሂደት ለማስተባበር ኮሚሽኑ በሥራ ልምድና በትምህርት ዝግጅት ብቃት ያላቸው 160 አመካካሪዎች እና 156 የቃለ ጉባኤ ጸሐፊዎች የምክክሩን ሂደት በመመዝገብና በመደገፍ እየሠሩ ነው፡፡ እንደሚታወቀው  አመካካሪዎች የምክክር ሂደቶች ከአድልዎ ነፃ በሆነ እና ሙያዊ በሆነ መንገድ ይመራሉ፤ አክብሮት የተሞላበት እና ሁሉንም ያካተተ ተሳትፎን ያበረታታሉ፤ የምክክር ሂደቶቹ በአጀንዳው ነጥቦች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ያደርጋሉ፤ የሃሳብ መስጫ ጊዜንም በፍትሐዊነት ያስተዳድራሉ፡፡

ኮሚሽምኑ የገለልተኛ መሪነት ሚናን በመጫወት የምክክር ሂደቱን በበላይነት እየተቆጣጠረ ነው፡፡ የምክክር ሂደቶቹ ከኮሚሽኑ ተልዕኮ  ጋር መጣጣማቸውንም እያረጋገጠ ነው፡፡

ለምክክር  ሂደቱ ነፃና ምቹ አካባቢን ፈጥሯል፡፡ በተጨማሪም ለምክክር ሂደቱ አስተዳደራዊና ቴክኒካዊ መመሪያ እየሰጠ እንደሚገኝ የመክክር ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

ቴክኒካዊ ባለሙያዎችም በአጀንዳ ነጥቦች ላይ ለሚፈጠሩ ብዥታዎች እና ማብራሪያዎች ተጨማሪ ማብራሪያ እየሰጡ ተገቢ የሆኑ ምርምሮችን እና ማስረጃዎችን በመጥቀስ የምክክር ሂደቱን የሚደግፉ ሃሳቦችን እያቀረቡ ነው፡፡

ታዛቢዎችም የምክክር ሂደቱን አሳታፊነት፣ አካታችነት ወዘተ በተለያዩ መመዘኛዎች በገለልተኝነት እየተከታተሉ ነው፡፡ የእነሱ መገኘት ለምክክሩ ግልጽነት እና ተዓማኒነት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ልብ ይሏል፡፡

ሽማግሌዎችም በየትኛውም የምክክር ምዕራፍ በተለያዩ የምክክሩ ተሳታፊ አካላት መካከል ጥልቅ አለመተማመን፣ የማይታረቁ ፍላጎቶች ወይም ሁከት በሚያጋጥሙበት ጊዜ ወደ መግባባት መንገድ እንዲመጡ እገዛ እያደረጉ ነው፡፡ በተለይ ተሳታፊዎቹ ባለመግባባታቸው ምክንያት የምክክር ሂደቱ ሲቋረጥ ወይም ቅርቃር (deadlock) ውስጥ ሲገባ ሽምግልና (mediation) ተግባራዊ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያን ችግር በምክክር ለመፍታት አዲስ አበባ ከከተሙት ተሳታፊዎች መካከል ለአሚኮ አስተያየታቸውን የሰጡ ተወያዮች እንዳሉት ግጭት በቤተሰብም ይኖራል፤ በፖለቲካ ፓርቲም ይኖራል፣ በተለያዩ አጋጣሚዎችም ይከሰታል፡፡ ግጭት በተከሰተ ቁጥር ግን ኃይል እና ጉልበት ከመጠቀም  በምክክር እና በውይይት በመመካከር መፍታ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ተወያዮች እንዳሉት እስካሁን ባለው የምክክር ሂደት ሀሳባቸውን በነፃነት እየገለጹ ነው፡፡ ሴቶች እና አካል ጉዳተኞችም በምክክሩ እኩል እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ መግባባትን የሚፈጥር ግልጽ እና ተስፋ ሰጪ ምክክሮች እየተካሄዱ መሆናቸውን ነው ያሳወቁት፡፡

አቶ ሲሳይ ዘለቀ የተባሉ ተሳታፊ እንዳሉት ውይይቱ አሳታፊ ነው፡፡ ሁሉም በገባው ልክ ሀገርን ለማዳን ይበጃል ያለውን ሀሳብ እያቀረበ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

መምህር ሞገስ ፍስሀ እንዳሉት  ከብሔር ብሔረሰቦች ጋር በአንድ ተገናኝቶ መነጋገር እና መከባበር ትልቅ ነገር ነው፡፡ አሁን እየተካሄደ የሚገኘው የምክክር ሂደትም አዲስቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር እድል የሚሰጥ ነው፡፡

ናሰር አብደላ የተባሉ ተመካካሪ በሰጡት እስተያየት ምክክር አንዱ የሌላውን ሀሳብ በማዳመጥ መግባባት ለመፍጠር ያስችላል፡፡ የምክክር ጉባኤውም ሀሳብን በነጻነት ለመግለጽ እድል የሰጠ ነው፡፡

በባሕር ዳር ከተማ ክምክክር ኮሚሽኑ ምን ትጠብቃላችሁ ብለን  ያነጋገርናቸው ሰዎች  በሰጡት አስተያየት ደግሞ  በሀገራዊ ምክክሩ ከዚህ በፊት ለግጭት እና ለቅራኔ ይጋብዙ የነበሩ የተሳሳቱ ትርክቶች ይቀረፋሉ ብለው እንደሚያስቡ  እንዲሁም  ከምክክሩ በኋላ ኢትዮጵያዊያን ያሉባቸውን ችግሮች ሁሉ ቀርፈው የሰላም አየር እንደሚተነፍሱ ተስፋቸው እንደሆነ ነግረውናል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በመክፈቻው ጊዜ ባካሄዱት ንግግር የሃሳብ ልዩነቶች ለመከፋፈል መንስኤ ተደርገው ሊወሰዱ እንደማይገባ ማስገንዘባቸው ይታወሳል፡፡ ይልቁንም ልዩነቶች አንዱ ሌላውን እንዲያውቅ መንገድ በመክፈት፣ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር እና ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች በጋራ መፍትሔ ለመፈለግ እንደ መልካም አጋጣሚ ሊቆጠሩ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ይህ የሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከመላው ሀገሪቱ የተወጣጡ ተሳታፊዎችን በማሳተፍ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለዩ አጀንዳዎች ላይ ሁሉንም ባካተተ መልኩ ለመጪዎቹ ሳምንታት እየተካሄደ ይቀጥላል፡፡

 

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሐምሌ  20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here