የስኳር በሽታ መንስኤዎች እና መፍትሄዎቹ?

0
173

የስኳር በሽታ በአሁኑ ወቅት በዓለማችንም ሆነ በሀገራችን በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ያለና የብዙዎችን ሕይወት የሚያሰጋ ሥር የሰደደ የጤና እክል ነው። እንደ ክሊንተን ሄልዝ አክሰስ ኢኒሼቲቭ (Clinton Health Access Initiative) እና የዓለም ጤና ድርጅት መረጃዎች፣ በየዓመቱ በአለም ዙሪያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በዚህ በሽታ ምክንያት ለሞት ይዳረጋሉ። ይሁን እንጂ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን በመከተል የበሽታውን አደጋ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ፣ መከላከል ወይም በሽታው ቢከሰት እንኳን በቁጥጥር ስር በማዋል ረጅም እና ጤናማ ህይወት መኖር ይቻላል።

በሽታውን አስመልክቶ የውስጥ ደዌ እና የስኳር እንዲሁም ኢንዶኮሎጅ ስፔሻሊስት ዶክተር አበረ ገነቱ ለበኩር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ሙያዊ ማብራሪያና አስፈላጊውን የጥንቃቄ መመሪያ በስልክ ሰጥተውናል።

የስኳር በሽታ ምንድነው? የሚለውን ለዶክተር አበረ የመጀመሪያውን ጥያቄያችን አድርገን አንስተንላቸዋል፡፡ ዶክተር አበረ  ስኳር /ጉሉኮስ/ ለሰውነታችን በጣም አስፈላጊ የሆነ ንጥረ ነገር እንደሆነ ያብራራሉ ፡፡ ሆኖም ይህ ጠቃሚ ንጥረ ነገር እንደ በሽታ ሆኖ የሚከሰተው ጉሉኮስ ከሰውነታችን ሴሎች ውስጥ መገኘት ሲገባው በማይገባው መንገድ በደም ስሮቻችን ላይ ከመጠን በላይ ሲገኝ የስኳር በሽታ ተገኘ ወይም ተከሰተ እንላለን፡፡ይህ በሽታ ለረጅም ጊዜ አብሮ የሚቆይ ሥር የሰደደ የጤና እክል መሆኑን ነው ዶክተር አበረ የተናገሩት። በሽታው የሚከሰተው ቆሽት የተባለው የሰውነታችን ክፍል በቂ የሆነ ኢንሱሊን (ምግብንና ስኳርን ወደ ኃይል የሚቀይር ሆርሞን) ሳያመርት ሲቀር ወይም ደግሞ ሰውነታችን የሚመረተውን ኢንሱሊን በአግባቡ መጠቀም ሳይችል ሲቀር ነው።

የስኳር በሽታ ዓይነቶች እና ዋና ዋና መንስኤዎቻቸው ምንድን ናቸው ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ዶክተር አበረ ሙያዊ ማብራሪያዎችን ሰጥተውናል፡፡ የስኳር በሽታ በዋናነት በሦስት ትላልቅ ክፍሎች ይከፈላል ይላሉ፡

1ኛ. ይነት 1 (Type 1 Diabetes)

ይህ ዓይነቱ የስኳር በሽታ አብዛኛውን ጊዜ በልጅነት ወይም በወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚከሰት ነው። መንስኤውም የሰውነታችን የበሽታ መከላከል ስርዓት ቆሽት ውስጥ የሚገኙ ኢንሱሊን አምራች ሴሎችን በስህተት በመደምሰሱ ምክንያት ቆሽት ኢንሱሊን ማምረት ሙሉ በሙሉ ሲያቆም የሚከሰት ነው። እነዚህ ታካሚዎች እድሜ ልካቸውን የኢንሱሊን መርፌ መጠቀም ይኖርባቸዋል ነው ያሉ።

2ኛ. ዓይነት 2 (Type 2 Diabetes)

ይህ በጣም የተለመደውና ከ90% በላይ የሚሆነውን የስኳር ህመምተኞች የሚሸፍን አይነት ነው። የሚከሰተውም የሰውነት ሴሎች ኢንሱሊንን መቋቋም (Insulin Resistance) ሲጀምሩ ወይም ቆሽት በቂ የሆነ ኢንሱሊን ማምረት ሲያቅተው ነው። ዶክተር አበረ እንደሚሉት፣ ለዚህ አይነቱ በሽታ ዋነኞቹ አጋላጭ መንስኤዎች ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ እና ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ስርአት ናቸው።

3ኛ. የእርግዝና ስኳር (Gestational Diabetes)

ይህ የስኳር በሽታ አይነት በአንዳንድ እርጉዝ ሴቶች ላይ ብቻ በሚከሰት ጊዜያዊ የስኳር አይነት ሲሆን፣ ከወሊድ በኋላ የሚጠፋ ቢሆንም፤ ወደፊት በእናትየው እና በልጁ ላይ ለዓይነት 2 ስኳር በሽታ የመጋለጥ እድልን ይጨምራል።

የስኳር በሽታ በዘር ይተላለፋል ወይ ብለንም ላነሳንላቸው ጥያቄ ዶክተር አበረ ሲያብራሩት ብዙ ሕመምተኞች ከሚያነሱት ጥያቄ አንዱ በሽታው በዘር መተላለፍ አለመተላለፉን ነው፡፡በሽታው  “አዎን፣  በዘር የመተላለፍ ባህሪ አለው” ብለዋል።በቤተሰብ (በወላጆች፣ በአያቶች ወይም በቅርብ የደም ዘመዶች) የስኳር በሽታ ታሪክ ካለ፣ በተለይም ዓይነት 2 የስኳር በሽታ የመያዝ ዕድሉ በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል። ሆኖም ግን፣ የዘር ስጋት ቢኖርብንም እንኳን ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን በመከተል በሽታው እንዳይከሰት ማድረግ ወይም እንዳይባባስ ማዘግየት እንደሚቻል ዶክተር አበረ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።ዶክተር አበረ አክለውም ህብረተሰቡ ራሱን ከዚህ በሽታ እንዲጠብቅ የሚከተሉትን ሶስት ወሳኝ መመሪያዎች እንዲተገብር ይመክራሉ።

በሳምንት ቢያንስ ለአምስት ቀናት ከ30 ደቂቃ እስከ 1 ሰዓት የሚደርስ መጠነኛ የሰውነት እንቅስቃሴ (እንደ ፈጣን እርምጃ፣ ሩጫ፣ ዋና ወይም ብስክሌት መጋለብ) ማድረግ የደም ስኳርን በእጅጉ ይቀንሳል ነው ያሉ። ከዚህ በተጨማሪም ከመጠን ያለፈ ውፍረትን ማስወገድ እና የሰውነትን ክብደት መቀነስ፣ አልኮል መጠጦችን መቀነስ እንዲሁም ሲጋራ ማጨስን ሙሉ በሙሉ መተው እንደሚኖርብንም ነው ያብራሩት።

እንደ ዶክተር አበረ ገለጻ በስኳር በሽታ ቁጥጥር ውስጥ የአመጋገብ ሚና ከምንም በላይ ወሳኝ መሆኑን ያስረዳሉ። ለዚህም የምግብ አይነቶችን በሁለት ከፍለው አብራርተዋል፡

  1. ከምግብ ገበታችን ልናስወግዳቸው የሚገቡ (የሚከለከሉ ምግቦች)

ጣፋጭ ምግቦችና መጠጦች፡ ስኳር፣ ማር፣ ኬክ፣ ብስኩት፣ ለስላሳ መጠጦች እና የታሸጉ የፍራፍሬ ጭማቂዎች።

የተጣራ ካርቦሃይድሬት ነጭ ሩዝ፣ ነጭ ዱቄት እና ከነሱ የተዘጋጁ ምግቦች (ነጭ እንጀራ፣ ፓስታ፣ ፒዛ)።

የተጠበሱና ቅባት የበዛባቸው ፈጣን ምግቦች (Fast foods) እና በፋብሪካ የተዘጋጁ ከፍተኛ ቅባት ያላቸው ምግቦች።

  1. በሰፊው ልንመገባቸው የሚገቡ (የሚፈቀዱ ምግቦች) አትክልትና ፍራፍሬ፡ ቅጠላማ አትክልቶች (ሰላጣ፣ ቆስጣ)፣ ካሮት፣ ጎመን እና ትኩስ ያልተቀነሱ ፍራፍሬዎች።ሙሉ እህሎች፡ ገብስ፣ አጃ፣ ጤፍ፣ እና ቡናማ ሩዝ (Brown rice)።

ጥራጥሬዎች፡ ባቄላ፣ አተር፣ ምስር፣ ሽምብራ እና አኩሪ አተር።

ጤናማ ፕሮቲኖች፡ አሳ፣ ቆዳው የተገፈፈ የዶሮ ስጋ፣ እና እንቁላል መመገብ ይኖርብናል። በመጨረሻም ዶክተር አበረ ህብረተሰቡ የራሱንና የቤተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ሶስት ዋና ዋና ነገሮችን ማከናወን እንዳለበት አሳስበዋል።

መደበኛ የደም ምርመራ ማድረግ፡ በሽታው በቅድመ-ደረጃ ላይ እያለ ምንም አይነት ምልክት ላያሳይ ስለሚችል፣ በዓመት ቢያንስ አንድ ጊዜ በአቅራቢያ በሚገኝ ጤና ጣቢያ የደም ስኳር መጠንን መመርመር ያስፈልጋል። የመድኃኒት አጠቃቀም መመሪያን መከተል፡ የታመሙ ሰዎች ከሐኪም የታዘዘላቸውን መድኃኒት ወይም የኢንሱሊን መርፌ በሰዓቱና ያለማቋረጥ መውሰድ አለባቸው።

እውቀትን ማዳበር፡ ስለ በሽታው የተሟላ መረጃ ለማግኘት እንደ የጤና ባለሙያዎችን ማማከር እና ስለስኳር በሽታ የሚወጡ  ትምህርታዊ መረጃዎችን መከታተል ተገቢ ነው።

በመጨረሻም የስኳር በሽታ ምልክቶች (እንደ ጥም፣ ተደጋጋሚ ሽንት፣ የክብደት መቀነስ) ካለብዎ ወይም የቤተሰብ ታሪክ ካለዎት፣ ዕድሜዎን፣ የክብደት ሁኔታዎን እና የምግብ ፍላጎትዎን ለህክምና ባለሙያ በማጋራት ተገቢውን ክትትል ያድርጉ። ጤናዎን በመጠበቅ ረጅም እና ጤነኛ ህይወት ይኑሩ ሲሉ ዶክተር አበረ ሙያዊ የማጠቃለያ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

 

መረጃ

በዓለም ላይ የስኳር በሽታ በፍጥነት እያደገ ከመጣ የጤና እክሎች አንዱ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከ 589 ሚሊዮን በላይ አዋቂዎች (ወይም 1 ከ 9 ሰዎች) በበሽታው እየተሰቃዩ ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ህመሙ እንዳለባቸው አያውቁም። 81 በመቶ የሚሆኑት የታማሚዎች ቁጥር በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ይገኛሉ።

እንደ የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) መረጃ ከ1990 ጀምሮ የስኳር በሽታ በዓለም ላይ በአራት እጥፍ አድጓል።

  • ከተያዙት አዋቂዎች ውስጥ ወደ 43 በመቶ የሚሆኑት (ወይም 252 ሚሊዮን ሰዎች) በሽታው እንዳለባቸው ያላወቁ ወይም ምርመራ ያላደረጉ ናቸው።
  • የስኳር በሽታ በዓለም ዙሪያ ለትልቅ የጤና ወጪ የሚዳርግ ሲሆን፣ በዓመቱ ከ አንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ይጠይቃል።

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here