የድህረ ወሊድ ድባቴ

0
144

እናትነት አስደሳች ቢሆንም፣ በውስጡ ከባድ ፈተናዎችንም የያዘ ነው። ህፃናት ወደዚህች ምድር ሲቀላቀሉ ቤተሰብ በደስታ ይሞላል፤ ከወዳጅ ዘመድ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክቶችም ይጎርፋሉ።

ነገር ግን ከዚህ የቤተዘመድ የጋራ ደስታ በስተጀርባ፣ ብዙ እናቶች ዝምታና ብቸኝነት እንዲያጠቃቸው ስለሚያደርገው የድህረ ወሊድ ድባቴ (Postpartum Depression – PPD) ለተባለው የጤና እክል ብዙ ጊዜ አስፈላጊው ትኩረት ሲሰጠው አይስተዋልም።

ችገሩ ጊዜያዊ ከሆነውና አብዛኛውን ጊዜ በራሱ ጊዜ ከሚጠፋው “የቀናት ድብርት” (Baby Blues) ይለያል። የድህረ ወሊድ ድባቴ ከባድ፣ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ እና አስቸኳይ የባለሙያ ትኩረት የሚሻ የጤና እክል መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል።

እንደ ድርጅቱ መረጃ ልጅ ከተወለደ በኋላ በእናትየው አካል ላይ የሚከሰተው ድንገተኛ ለውጥ በአንጎል መዋቅር ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል።

በእርግዝና ወቅት ኤስትሮጂን እና ፕሮጂስትሮን የተባሉ ሆርሞኖች በከፍተኛ መጠን ይጨምራሉ፤ ወሊድ እንደተጠናቀቀ ባሉት 24 ሰዓታት ውስጥ ደግሞ በከፍተኛ ፍጥነት ይቀንሳሉ።

ይህንን ለውጥ አስመልክቶ የሥነ ልቦና ምሁሩ ጌል በሠሩት ጥናት ላይ እንደገለጹት፣ ይህ ድንገተኛ የሆርሞን መውረድ በአንጎል ውስጥ ስሜትን የሚቆጣጠሩትን የነርቭ አስተላላፊዎች (Neurotransmitters) ሚዛን ያናጋዋል። በተጨማሪም ከወሊድ በኋላ የሚከሰተው የታይሮይድ ሆርሞን መቀነስ ለከፍተኛ ድካምና ለድብርት ስሜት መፈጠር ሥነ – ሕይወታዊ ምክንያት ይሆናል።

እናቶች ከወሊድ በኋላ የሚገጥማቸው አዲስ ኃላፊነት እና የማንነት ሽግግር ቀላል የሚባል አይደለም። “ጥሩ እናት መሆን እችል ይሆን?” የሚል ስጋት፣ የሰውነት ቅርጽ መለወጥ፣ እና የቀድሞውን ነፃነት ማጣት የሚፈጥሩት የስነ – ልቦና ጫና ለድባቴ መፈጠር ምክኒያት የሚሆንበት አጋጣሚም አለ።

በእርግዝና ወቅት ወይም ከዚያ በፊት የአዕምሮ ጤና እክል ወይም የድብርት ታሪክ የነበረባቸው እናቶች ላይ የድህረ ወሊድ ድባቴ የመከሰት ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑንም ጥናቱ ያሳያል።

የድህረ ወሊድ ድባቴ የአካልና የስነ – ልቦና ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ማሕበራዊም ነው። አንዲት አራስ እናት ከባሏ፣ ከቤተሰቧ ወይም ከማሕበረሰቡ በቂ እንክብካቤ እና ስነ – ልቦናዊ እገዛ ካላገኘች ለድባቴ የመጋለጥ ዕድሏ በእጅጉ ይጨምራል። ሃልብሬሽ እና ካርኩን የተባሉት የሥነ ልቦና ምሁራን ባደረጉት የምርምር ሥራ ላይ እንዳመለከቱት፣ የድህረ ወሊድ ድባቴ ስርጭት በተለያዩ ባሕሎችና ማሕበረሰቦች ውስጥ ይለያያል። ጠንካራ የማሕበራዊ ድጋፍ ሥርዓት ባላቸው ማሕበረሰቦች ውስጥ የሚኖሩ እናቶች ለዚህ ድባቴ የመጋለጥ ዕድላቸው አነስተኛ ሲሆን፣ ማሕበራዊ ድጋፍ ባነሰበት ሁኔታ ውስጥ ግን ስርጭቱ በከፍተኛ መጠን ይጨምራል።

ችግር የሩቅ አገር እናቶች ስቃይ ብቻ አይደለም፤ በሀገራችንም በዝምታ የሚሰቃዩ እናቶች ቁጥር ከምናስበው በላይ ከፍተኛ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ በሀገራችን የተሠሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ በኢትዮጵያ የድህረ ወሊድ ድባቴ ስርጭት በአማካይ ከ15 እስከ 22 በመቶ ይደርሳል። ይህም ከአምስት እናቶች መካከል አንዷ በዚህ ችግር ትጠቃለች ማለት ነው።

ይህ ስርጭት እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ እንደሚለያይ ልብ ይሏል።

በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ እናቶችን ለዚህ የአዕምሮ ጤና ቀውስ ይበልጥ ተጋላጭ የሚያደርጓቸው ማሕበራዊ፣ ባሕላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ናቸው፤ ያልታቀደ እርግዝና፣ የቤት ውስጥ ጥቃት (Intimate Partner Violence)፣ በእርግዝና ወቅት ወይም ከወሊድ በኋላ ከትዳር አጋር የሚደርስ ጥቃት ለድባቴ የመጋለጥ ዕድልን ይጨምራል።

የምግብ ዋስትና እጥረት ደግሞ ሌላው ምክንያት ነው፤ በቂ እና የተመጣጠነ ምግብ አለማግኘት የሚፈጥረው አካላዊ ችግር ለድባቴ ቀጥተኛ መንስኤ ነው።

የአካባቢያዊ ልማዶች ተጽዕኖ ደግሞ ሌላው ተጠቃሽ ምክንያት ነው። በኢትዮጵያውያን ዘንድ አራስ እናት እንክብካቤ የሚደረግላት ቢሆንም፣ የአዕምሮ ጤና ጉዳይ ግን አሁንም በትኩረት አይታይም።

የድህረ ወሊድ ድባቴ ምልክቶች (ያለምክንያት ማልቀስ፣ ራስን ማግለል፣ ፍርሃት) ብዙ ጊዜ ከሳይንሳዊ እውነታው ይልቅ ከባሕላዊ ወይም ከመንፈሳዊ ዕምነቶች ጋር ይያያዛሉ። ችግሩን “የአጋንንት ጥቃት”፣ “የአራስ ቁራኛ” ወይም “ክፉ ዓይን” ተደርጎ ስለሚወሰድ ሳይንሳዊ ሕክምና እንዳያገኙ ያደርጋል።

ሌላው ስቴይን የተባሉት የሥነ ልቦና ምሁር እንደገለጹት ደግሞ፣ የእናቶች የአዕምሮ ጤና መረበሽ በሕፃናት የዕውቀት (cognitive)፣ የስነ – ባሕርይ እና የስሜት ዕድገት ላይ ዘላቂ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ስለዚህ እናትን ማከም ሕፃኑን መታደግ መሆኑንም ምሁሩ ያስገነዝባሉ።

የድህረ ወሊድ ድባቴ ሕክምና የሚፈልግ ሥነ – ሕይወታዊ እክል ነው። ጉዳዩን በሚመለከት ሃሳባቸውን ያጋሩን በዳባት ጤና ጣቢያ የሕክምና ክትትል ሲያደርጉ ያገኘናቸው ወ/ሮ በለጠች መስፍን ከድህረ ወሊድ ድባቴ ጋር ተያይዞ በቂ እንቅልፍ ያለማግኘት እና መጠነኛ የድካም ስሜት አጋጥሟቸው እንደነበር ያነሳሉ። እነዚህን ስሜቶች ልብ ያለማለት እና የተለመደ የስሜት ለውጥ አድርገው መቁጠራቸው ችግሩን እንዳባባሰው አክለዋል።

ወ/ሮ በለጠች በወቅቱ የባለሙያ ምክር ማግኘታቸው እና ከቤተሰብ አባላት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ምክክር ማድረጋቸው መፍትሔ እንዲያገኙ እንደረዳቸው ገልጸዋል። ሌሎች እናቶችም ይህን ስሜት ሲያስተናግዱ መረበሽ እንደሌለባቸው ነው የነገሩን፤ በአቅራቢያቸው ወዳለ የሕክምና ማዕከል በመሄድ ክትትል እና ድጋፍ ማግኘት እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኤልያስ ገብሩ በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የስነ ልቦና ትምህርት ክፍል መምህር ናቸው፤ ጉዳዩን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት መምህሩ ድህረ ወሊድ ድባቴ የደካማነት ወይም የእናትነት ብቃት ማነስ ምልክት አለመሆኑን ያብራራሉ። ይልቁንም እንደ ማንኛውም አካላዊ ሕመም የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልገው የጤና እክል መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በድህረ ወሊድ ወቅት በቂ እንቅልፍ እና ረፍት ማግኘት፣ አመጋገብን ማስተካከል እና የቤተሰብ ድጋፍ መጠየቅ ከችግሩ ለመላቀቅ መፍትሔዎች መሆናቸውን ነው ያነሱት።

ችግሩ ከተከሰተ በኋላም አለመረበሽ፣ የባለሙያ ድጋፍ ማግኘት፣ በሐኪም የታዘዙ መድኃኒቶችን መጠቀም እና ምክሮችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ችግሩ እንዳይከሰት ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እና ከተከሰተም በኋላ ሳይረበሹ የባለሙያ ድጋፍ በማግኘት ከችግሩ ነጻ መሆን እንደሚቻል አክለዋል።

ማናት

ልዕልት ፀሐይ

ልዕልት ፀሐይ ኃይለ ሥላሴ የቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ እና የእቴጌ መነን አስፋው አራተኛ ልጅ ሲሆኑ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በቁርጠኝነታቸው፣ በበጎ አድራጎታቸው እና ለሕክምና ሙያ በነበራቸው ፍቅር የሚታወቁ ድንቅ ልዕልት ነበሩ።

ልዕልት ፀሐይ የተወለዱት ነሐሴ 16 ቀን 1912 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ነው:: ያደጉት በቤተመንግሥት ውስጥ ቢሆንም የፋሺስት ጣሊያን ጦር በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ሲወር ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ እንግሊዝ ሀገር ለመሰደድ ተገደዱ:: በስደት ላይ እያሉ አብዛኞቹ የንጉሣዊ ቤተሰብ አባላት በፖለቲካ እና ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ሲያተኩሩ ልዕልት ፀሐይ ግን ትኩረታቸውን በሰብአዊ አገልግሎት ላይ አደረጉ::

በለንደን ታዋቂ በነበረ ሆስፒታል ገብተው የሕክምና እና የነርስነት ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ:: በዚህም የመጀመሪያዋ ሰልጣኝ ኢትዮጵያዊት ነርስ ለመሆን በቁ:: በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለንደን በጀርመን አውሮፕላኖች በቦምብ ስትደበደብ ልዕልት ፀሐይ በሆስፒታል ውስጥ ሌሊት እና ቀን የተጎዱ ሰዎችን በመንከባከብ እና በማከም ከፍተኛ የጀግንነት እና የርህራሄ አገልግሎት አሳይተዋል::

በ1933 ዓ.ም የጣሊያን ጦር ተሸንፎ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ልዕልት ፀሐይም አብረዋቸው ተመለሱ:: ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሱም በጦርነቱ ምክንያት የወደመውን የሕክምና ዘርፍ ለማንሰራራት ትልቅ ጥረት ማድረግ ጀመሩ::

በወቅቱ የነበረውን የህፃናት እና እናቶች ሞት ለመቀነስ፣ ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎት ለማስፋፋት እና የቀይ መስቀል ማህበርን በኢትዮጵያ ለማጠናከር ሌት ከቀን ይደክሙ ነበር:: የሕክምና ሙያ ክብር እንዲኖረው እና በርካታ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ወደ ሙያው እንዲገቡ ትልቅ መንገድ ከፍተዋል::

ልዕልት ፀሐይ በ1934 ዓ.ም ከታዋቂው ወታደራዊ እና ፖለቲከኛ ከብርጋዴር ጄኔራል አቢይ አበበ ጋር ጋብቻ ፈጸሙ:: ነገር ግን ደስታቸው ብዙ አልዘለቀም:: ጋብቻ በፈጸሙ በዓመቱ በወሊድ ምክንያት በተፈጠረ ድገተኛ የጤና መታወክ በነሐሴ 22 ቀን 1934 ዓ.ም በ22 ዓመታቸው በወጣትነታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ::

ልዕልት ፀሐይ በሕይወት በነበሩበት ወቅት በኢትዮጵያ ትልቅና ዘመናዊ ሆስፒታል የመገንባት ትልቅ ሕልም ነበራቸው:: ዐፄ ኃይለ ሥላሴ የልጃቸውን አሳዛኝ ህልፈት እና የነበራቸውን በጎ ፍላጎት ለማስታወስ ከዓለም አቀፍ ረዳቶች ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ «ልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል»ን አስገነቡ:: ይህ ሆስፒታል በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘመናዊ ሆስፒታል ሲሆን በአሁኑ ወቅት ጦር ኃይሎች ሆስፒታል በመባል ይታወቃል::

ምንጭ፡- “ሕይወቴ እና የኢትዮጵያ እርምጃ” – ዐፄ ኃይለ ሥላሴ

 

 

(ደረጀ ደርበው)

በኲር የሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here