ከፋሽን ጀርባ

0
260

በ2010 እ.ኤ.አ. ሙዚቀኛዋ ሌዲ ጋጋ በኤምቲቪ የሙዚቃ ሽልማት መድረክ ላይ ጥሬ የከብት ሥጋ በተሰፋበት ልብስ ተሸልማ ስትወጣ ዓለም በድንጋጤ ተዋጠች።

በ2023 እ.ኤ.አ. ደግሞ የቪክቶር እና ሮልፍ የፓሪስ ፋሽን ሳምንት ትርኢት ላይ ሞዴሎች ቁልቁል የተገለበጡ፣ ወደ ጎን የተዛመሙ እና ከአካላቸው ተነጥለው የሚንሳፈፉ የሚመስሉ የጋብቻ ልብሶችን ለብሰው ሲወጡ ታዳሚው አፉን ያዘ።

ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች አብደዋል? ወይስ እኛ ልብስ የሚለውን ጽንሰ-ሐሳብ መረዳት አልቻልንም?

ልብዙዎቻችን ልብስ  ውርጭን መከላከያ፣ ሀፍረተ-ሥጋን መሸፈኛ ወይም ለሰርግና ለበዓል ማጌጫ ብቻ ስለሆነ የፋሽን ዓለም እንቆቅልሽ ይሆንብናል።

በሰለጠነው ዓለም ልብስ ሰው የሚያስብበት፣ የሚያስደነግጥበት እና ማህበረሰባዊ እውነቶችን የሚሞግትበት ህያው የኪነ-ጥበብ መድረክ ሆኗል።

ፈረንሳዊው ፈላስፋ ሮላንድ ባርትስ “ዘ ፋሽን ሲስተም” በተሰኘው  መጽሐፉ ላይ “ፋሽን ቁሳቁስ ብቻ አይደለም፤ ፋሽን የራሱ ቋንቋ፣ ምልክት እና የባህል ኮድ ያለው ውስብስብ የፍልስፍና ሥርዓት ነው” ብሏል።

ይህ መጣጥፍ እንግዳ እና የሚያስደነግጡ በሚባሉ የፋሽን ዲዛይኖች ከጀርባ ያለውን ምስጢራዊ ጥበብ፣ የሆሊዉድ እና የመዝናኛ ኢንዱስትሪውን ድብቅ ፍላጎት፣ የዘመናዊ ውበትን አዲስ ትርጉም እና ታዳጊ ሀገራት በዚህ የሩጫ መድረክ ላይ ያላቸውን ቦታ በጥልቀት ይዳስሳል።

ሰዎች እንግዳ የሚሏቸው የፋሽን ዲዛይኖች በፋሽን ቋንቋ አቫንት-ጋርድ ወይም ላብራቶሪያዊ ፋሽን ይባላሉ። እነዚህ ልብሶች ለዕለታዊ አገልግሎት የተሰፉ አይደሉም። ይልቁንም ልክ እንደ ሥዕል ወይም እንደ ቅርጻ ቅርፅ የሰውን አካል እንደ ሸራ በመጠቀም የተሰሩ የዕይታ ጥበቦች  ናቸው።

በፋሽን ታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራ ያሳረፈው ብሪታንያዊው ዲዛይነር አሌክሳንደር ማክኩዊን በ1999 እ.ኤ.አ. ባቀረበው “ቁጥር 13” በተሰኘው ትርኢቱ ላይ ነጭ ልብስ የለበሰች ሞዴልን በሁለት የኢንዱስትሪ ሮቦቶች መካከል አቁሞ ሮቦቶቹ በልብሷ ላይ ቀለም እንዲረጩ አድርጓል።

ማክኩዊን ስለ ዲዛይኖቹ ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር “ሴቶች ደካማ መስለው እንዲታዩ አልፈልግም። ሰዎች እኔ ባዘጋጀሁላቸው ልብስ የሚያልፉትን ሴቶች እንዲፈሯቸው ነው የምፈልገው!”

ለማክኩዊን እንግዳ ልብሶቹ የሴቶችን ጥንካሬ፣ የጭካኔን እና የውበትን ውሕደት የሚያሳዩ ፍልስፍናዎች ነበሩ።

በሆሊዉድ፣ በሙዚቃ ቪዲዮዎች፣ በኦስካር እና በተለይም በኒውዮርክ ሜት ጋላ  መድረኮች ላይ የሚታዩ እንግዳ ፋሽኖች ድገተኛ ክስተቶች አይደሉም። ከጀርባቸው ሁለት ትላልቅ ምስጢራዊ ፍላጎቶች አሉ፦

  1. የትርኢት ኢኮኖሚ፦

ፈረንሳዊው ፈላስፋ ጊ ዴቦር በ1967 “ዘሶሳይቲ ኦፍ ዘ ስፔክታክል” በተሰኘው መጽሐፉ እንደተነበየው በዘመናዊው ዓለም እውነተኛው ህይወት በትእይንት ተተክቷል።

በዘመናዊው የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ውስጥ ትኩረት (መታየት) ትልቁ የገንዘብ ምንጭ ነው። አንዲት ኮከብ በተለመደ ውብ ልብስ መድረክ ላይ ብትወጣ በማህበራዊ ሚዲያ ለአንድ ሰዓት እንኳ አታወያይም። ነገር ግን ሜት ጋላ ላይ ዶጃ ካት  ሙሉ አካሏን በ30 ሺህ ክሪስታሎች አሽሞንሙና ድመት መስላ ስትመጣ፣ ወይም ኪም ካርዳሺያን ሙሉ አካሏን በጥቁር ጨርቅ ሸፍና ስትቀርብ አጠቃላይ የዓለም ሚዲያ ስለእሷ ያወራል። ይህ  ትኩረትን ወደ ካፒታል የመቀየር ምስጢር ይባላል።

  1. የማንነት እና የፖለቲካ ማኒፌስቶ፦

ሌዲ ጋጋ የሥጋ ልብስ በለበሰችበት ወቅት ከጀርባው የነበረው ምስጢራዊ መልእክት፡ “ለእምነታችን እና  ለመብታችን ካልታገልን፣ በቅርቡ አጥንት እና ሥጋ ብቻ ሆነን እንቀራለን” የሚል የፖለቲካ ተቃውሞ ነበር። በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥም እንደ ብላክ ፓንተር፣ ደን እና ሀንገር ጌምስ  ባሉ ፊልሞች ውስጥ የሚታዩት እንግዳ አልባሳት የባህል እና የፖለቲካ ቅስቀሳ መግለጫዎች ናቸው።

ቀደም ሲል የፋሽን እና የውበት አረዳድ በጥብቅ ደንቦች የታጠረ ነበር። ቀጫጭን ሞዴሎች፣ ተመጣጣኝ የፊት ቅርጽ፣ እና ባህላዊ የሴትነት/ወንድነት መግለጫዎች። ዛሬ ግን የዓለም መዝናኛ ኢንዱስትሪ ይህንን አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ ሰባብሮታል።

ታዳጊ ሀገራት (በተለይም የአፍሪካ ሀገራት) በዓለም አቀፉ የፋሽን ሩጫ ውስጥ ከቀደመው የጥሬ ዕቃ አቅራቢነት እና የተጣለ ልብስ ተቀባይነት” ሚና ወደ “የፈጠራ ባለቤትነት እየተሸጋገሩ ይገኛሉ።

የአፍሪካ ሀገራት የራሳቸውን ጥንታዊ ባህል፣ አፈ-ታሪክ እና ሽመና ከዘመናዊው የፋሽን ጥበብ ጋር በማቀናጀት አዲስ አብዮት እያካሄዱ ነው። ለምሳሌ የናይጄሪያው ዲዛይነር ኬኔዝ ኢዜ እና የደቡብ አፍሪካው ቴቤ ማጉጉ  የአፍሪካን ባህላዊ ጨርቆች ወደ ፓሪስ የሀውት-ኩቱር መድረክ በማውጣት ትልቅ አድናቆት አግኝተዋል።

በታዳጊ ሀገራት  ከፍተኛ የፈጠራ አቅም ቢኖርም፣ ልብሶችን በከፍተኛ ጥራት የሚያመርቱ ፋብሪካዎች እና የካፒታል እጥረት አለ። የሆሊዉድ እና የፓሪስ ትልልቅ ኩባንያዎች የአፍሪካን ጥንታዊ ቅርሶች እና ዲዛይኖች ወስደው ያለ እውቅና እና ክፍያ ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። ምዕራባውያን አምርተው የተዋቸውን ርካሽ ልብሶች ታዳጊ ሀገራት ላይ በመድፋት የሀገር ውስጥ የሽመና እና የልብስ ጥበብ እንዲሞት ያደርጋሉ።

አሁኑ ትውልድ እንግዳ የፋሽን ዲዛይኖችን ለመረዳት የሚከተሉትን ሶስት የአስተሳሰብ መነጽሮች መጠቀም አለበት።

  1. ልብስን ከቁሳዊ አገልግሎት ነጥሎ ማየት፦

አንድን ሥዕል በሙዚየም ውስጥ አይተን “ይህ ሥዕል ለምግብ መሸፈኛ ይሆናል?” ብለን አንጠይቅም። አቫንት-ጋርድ ፋሽንም ልብስ የለበሰ ሙዚየም ነው። ልብሱን እንደ ልብስ ሳይሆን እንደ ሀሳብ መመልከት ይገባል።

  1. ታሪኩን መፈለግ፦

ዲዛይነሩ በዚህ ልብስ ምን እያለ ነው? ስለ አየር ንብረት ለውጥ እያወራ ነው? ስለ ፆታ እኩልነት? ወይስ ስለ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የበላይነት? ከጀርባው ያለውን ፍልስፍና መመርመር ያስፈልጋል።

  1. የውበትን ወሰን መፈተሽ፦

ውበት ማለት ምን ማለት ነው?” የሚለውን ማህበረሰቡ የሰጠንን ትርጉም መጠራጠር ተገቢ ነው። እንግዳ ፋሽኖች የተፈጠሩት አእምሯችንን ከለመደው ለማውጣት እና አዲስ ነገሮችን እንድንቀበል ለማሰልጠን ነው።

ፋሽን የሰው ልጅ የውስጥ ነፍስ፣ የፍርሃት፣ የህልም እና የፖለቲካ ነጸብራቅ ነው። እንግዳ የሚባሉ የፋሽን ዲዛይኖች ዓለምን ለማስደሰት ሳይሆን ዓለምን ለማሳሰብ የተፈጠሩ ጥበቦች ናቸው።

በመዝናኛ እና በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥ የምናያቸው እብደት የሚመስሉ ልብሶች ከጀርባቸዉ የብዙ ቢሊዮን ዶላር ኢኮኖሚ፣ የፍልስፍና ተቃውሞ እና የባህል ማኒፌስቶ ይዘዋል። ታዳጊ ሀገራትም የራሳቸውን ጥንታዊ ማንነት ከዚህ አቫንት-ጋርድ አስተሳሰብ ጋር በማቀናጀት የዓለምን ፋሽን የመምራት ትልቅ አቅም አላቸው።

ፋሽን የነገዋን ዓለም ዛሬ ላይ ሆኖ የሚያሳይ ህያው የሀሳብ መስታወት ነው!

 

ማረፊያ

በ2022 እ.ኤ.አ በፓሪስ የፋሽን ሳምንት ላይ ድምጻዊ ካንዬ ዌስት “White Lives Matter” የሚል ጽሑፍ ያለበትን ቲሸርት ለብሶ በመቅረቡ ሰፊ ተቃውሞ አስነስቷል፡፡

ጽሑፉ የጥቁሮችን መብት እንቅስቃሴ (Black Lives Matter) የሚያንኳስስ እና ነጭ የበላይነት አናፋሾች የሚጠቀሙበት ነው በሚል ከደጋፊዎቹ፣ ከተከታዮቹ እና በትልልቅ የፋሽን ኩባንያዎች (እንደ አዲዳስ ያሉ) ዘንድ ማዕቀብ እና የውል ማቋረጥ ደርሶበታል፡፡

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሐምሌ 27  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here