በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የአንድ ታላቅ መሪ፣ የንጉሥ ወይም የፕሬዝዳንት ውሳኔ የሀገርን ታሪክ ሲቀይር ማየት የተለመደ ነው። ነገር ግን እ.አ.አ በመስከረም ወር 1983 ዓለምን ከአጠቃላይ የኑክሌር እልቂት ያዳናት የአንድ ሀገር መሪ ሳይሆን በሚስጥራዊ ወታደራዊ ማዕከል ውስጥ በሌሊት ፈረቃ ተረኛ የነበረ “ስታኒስላቭ ፔትሮቭ” የተባለ የሶቪየት ህብረት መካከለኛ መኮንን ነበር። ይህ ታሪክ ወታደራዊ መመሪያን በዕውር ድንብሩ ከመከተል ይልቅ አመክንዮን እና የሰከነ ሰብአዊ አእምሮን ያስቀደመ የአንድ ጀግና እውነተኛ ታሪክ ነው።
ስታኒስላቭ ዬቭግራፎቪች ፔትሮቭ እ.አ.አ. መስከረም 7 ቀን 1939 በሶቪየት ህብረት (በአሁኗ ሩሲያ) ቭላዲቮስቶክ ከተማ አቅራቢያ ተወለደ። አባቱ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጦር አውሮፕላን አብራሪ ነበሩ፤ እናቱ ደግሞ ነርስ ነበረች። ይህ የቤተሰብ ታሪክ ፔትሮቭ ወደ ወታደራዊ ሳይንስ እንዲሳብ አደረገው።
ኪየቭ በሚገኘው ከፍተኛ የሶቪየት አየር ኃይል ምህንድስና ኮሌጅ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ በሶቪየት ህብረት የአየር መከላከያ ኃይል ውስጥ ተቀጠረ። ፔትሮቭ በተለይ በኮምፒውተር ሳይንስ፣ በሳተላይት ቴክኖሎጂ እና በቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓቶች ላይ ከፍተኛ ክህሎት የነበረው መሀንዲስ እና ወታደር ነበር። በታማኝነቱ እና በስራ ትጉነቱ ምክንያት በፍጥነት በማደግ የሌተናል ኮሎኔልነት ማዕረግን ማግኘት ችሏል።
የፔትሮቭ ታሪክ የተከሰተበት ወቅት እ.አ.አ. በ1983 “ቀዝቃዛው ጦርነት” እጅግ አስፈሪ ምዕራፍ ላይ በደረሰበት ጊዜ ነበር። በወቅቱ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬገን የሶቪየት ህብረትን “ክፉው ኢምፓየር (ግዛት)” በማለት የጠሩበት እና ሁለቱም ሀገራት የኑክሌር ጦር መሳሪያቸውን እያዘመኑ የነበረበት ወቅት ነበር።
ይህ ውጥረት ይበልጥ የናረው የፔትሮቭ ታሪክ ከመከሰቱ ከሶስት ሳምንታት በፊት (በመስከረም 1 ቀን 1983) ነበር። የሶቪየት ህብረት የጦር አውሮፕላኖች የአየር ክልሌን ጥሳለች በሚል የደቡብ ኮሪያን መንገደኞች አውሮፕላን (KAL 007) መትተው ጣሉ። በአደጋው 61 አሜሪካውያንን ጨምሮ 269 ንጹሃን ተሳፋሪዎች ህይወታቸው አለፈ። አሜሪካ እና አጋሮቿ በሶቪየት ህብረት ላይ ከፍተኛ ቁጣ ሰነዘሩ። የሶቪየት ጦር ሰራዊትም አሜሪካ ወዲያውኑ የኑክሌር ጥቃት ልትሰነዝርብኝ ትችላለች በሚል ከፍተኛ ዝግጅት ላይ ነበር።
በዚህ በተወጠረ የፖለቲካ ከባቢ አየር ውስጥ ሌተናል ኮሎኔል ስታኒስላቭ ፔትሮቭ ከሞስኮ በስተደቡብ 100 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው “ሰርፑክሆቭ-15” በተባለች ሚስጥራዊ የቅድመ-ማስጠንቀቂያ ማዕከል ውስጥ በፈረቃ ኃላፊነት ተረኛ ነበር። የእሱ ዋና ተግባር “ኦኮ” የተሰኘውን የሶቪየት ህብረት የሳተላይት መቆጣጠሪያ ስርዓት መከታተል ነበር። ይህ ስርዓት አሜሪካ የምታስወነጭፋቸውን ሚሳይሎች እሳት እና ሙቀት አይቶ ለሞስኮ መረጃ የመስጠት አላማ ነበረው።
ከሌሊቱ 6፡15 ሲል በማዕከሉ ውስጥ የነበሩት ሳይረኖች በከፍተኛ ድምፅ መጮህ ጀመሩ። የመቆጣጠሪያ ክፍሉ ኮምፒውተሮች በትላልቅ ቀይ ፊደላት “ሚሳይል ተተኩሷል)” የሚል ማስጠንቀቂያ አሳዩ። ሳተላይቱ ዩናይትድ ስቴትስ ከአንደኛው ወታደራዊ ሰፈሯ አህጉር አቋራጭ የባለስቲክ ሚሳይል ወደ ሶቪየት ህብረት እንዳስወነጨፈች አመለከተ።
በክፍሉ ውስጥ የነበሩት 200 የሚሆኑ ወታደሮች በሙሉ ደነገጡ። ፔትሮቭ ሁኔታውን ለመገምገም ጥቂት ሰኮንዶች ብቻ ነበሩት። የሶቪየት ወታደራዊ መመሪያ “ማስጠንቀቂያ ሲመጣ ወዲያውኑ ለበላዮች ሪፖርት ይደረጋል” ይላል። ሪፖርት ከተደረገ ደግሞ የሶቪየት ህብረት መሪዎች የአጸፋ ጥቃት ለመሰንዘር ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ስለሚኖራቸው ወዲያውኑ የኑክሌር ሚሳይሎችን ወደ አሜሪካ ይተኩሳሉ።
ፔትሮቭ ግን የራሱን ወታደራዊ እውቀት እና ህሊና አስቀደመ። “አሜሪካ የዓለም ጦርነት መጀመር ብትፈልግ በኦፕሬሽኑ መጀመሪያ ላይ በአንድ ሚሳይል ብቻ አትመጣም፤ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝቧን ለሞት ለሚዳርግ አጸፋዊ እርምጃ ራሷን አጋልጣ በአንድ ሚሳይል አታጠቃም” የሚል አመክንዮአዊ ጥርጣሬ አደረበት። ስለዚህ ማስጠንቀቂያው የኮምፒውተር ስህተት መሆን አለበት ብሎ ወሰነ።
ነገር ግን ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሳይረኑ በድጋሚ ጮኸ። ኮምፒውተሩ ሁለተኛ፣ ሦስተኛ፣ አራተኛ እና አምስተኛ ሚሳይሎች ከአሜሪካ መነሳታቸውን አሳየ። አጠቃላይ ማስጠንቀቂያው ወደ የሚሳይል ጥቃት ተቀየረ። በክፍሉ ውስጥ የነበሩት 200 የሚሆኑ ወታደሮች ፔትሮቭ ትዕዛዝ እንዲሰጥ በትኩረት ይጠባበቁ ነበር። ፔትሮቭ በግራ እጁ ስልኩን ይዞ በቀኝ እጁ የመገናኛ መስመሩን ዘርግቶ ነበር። ለበላዮቹ “ጥቃት እየተሰነዘርብን ነው” ብሎ ከተናገረ ጦርነቱ ይጀምራል።
ፔትሮቭ ግን የራሱን ወታደራዊ እውቀት እና ህሊና አስቀደመ። አሁንም ቢሆን አምስት ሚሳይሎች ለአንድ ታላቅ ሀገር ማጥፊያ በጣም ጥቂት መሆናቸውን በመገመት ለሶቪየት ጦር ዋና መሥሪያ ቤት ስልክ ደውሎ “መረጃው የኮምፒውተር እና የሳተላይት ስህተት ነው” የሚል ሪፖርት አስተላለፈ።
ከጥቂት አስጨናቂ ደቂቃዎች በኋላ የአሜሪካ ሚሳይሎች ሶቪየት ህብረት መሬት ላይ መድረስ በሚገባቸው ሰዓት ምንም የተፈጠረ ነገር አልነበረም። የፔትሮቭ ግምት ትክክል ነበር። ከወራት በኋላ በተደረገ ምርመራ የሶቪየት ሳተላይት በዩናይትድ ስቴትስ የደመና ክምችቶች ላይ ያረፈውን የፀሐይ ብርሃን ነጸብራቅ ተሳስታ የሚሳይል እሳት አድርጋ መተርጎሟ ተደረሰበት።
ፔትሮቭ ዓለምን ከጥፋት ቢያድንም የሶቪየት ህብረት ባለስልጣናት ግን እንደ ጀግና አልቆጠሩትም። ይልቁኑ ወታደራዊ መመሪያን ባለመከተሉ እና በወቅቱ የተፈጠረውን የደቂቃዎች ማስታወሻ ደብተር ላይ በአግባቡ ባለመመዝገቡ ተወቀሰ። የሶቪየት የጦር መሪዎች የኮምፒውተር ስርዓታቸው ስህተት መስራቱን ለዓለም ማሳወቅ ስለማይፈልጉ ታሪኩ በሚስጥር እንዲያዝ ተደረገ።
ፔትሮቭ ምንም አይነት ሽልማት ወይም ማዕረግ አላገኘም። ከጥቂት ጊዜ በኋላም ከከፍተኛ ሥራው ተነስቶ ዝቅተኛ ቦታ ላይ እንዲሠራ ከተደረገ በኋላ በገዛ ፈቃዱ ከጦር ሰራዊቱ ተገለለ።
የስታኒስላቭ ፔትሮቭ ታሪክ ለዓለም ይፋ የሆነው ከ15 ዓመታት በኋላ እ.አ.አ. በ1998 የሶቪየት ህብረት የቅድመ-ማስጠንቀቂያ ሚሳይል ክፍል አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ዩሪ ቮቲንትሴቭ የህይወት ታሪክ መጽሐፋቸውን ሲያትሙ ነበር። ይህ ታሪክ ይፋ ሲሆን ዓለም በከፍተኛ ድንጋጤ እና አድናቆት ውስጥ ወደቀች።
የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የፔትሮቭን ውሳኔ ማድነቅ ጀመሩ። እ.አ.አ. በ2006 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት በተካሄደ ስነ-ስርዓት “ዓለምን ላዳነ ሰው” የሚል ልዩ የሰላም ሽልማት ተሰጠው። እ.ኤ.አ. በ2013 የጀርመኑን ታዋቂ “የድሬስደንን የሰላም ሽልማት” (Dresden Peace Prize) አሸነፈ። ስለ ህይወቱ የሚያወሳ “The Man Who Saved the World” የተሰኘ ታዋቂ የሰነድ ፊልም (Documentary) ተሰርቶለታል።
ስታኒስላቭ ፔትሮቭ በቀሪው የህይወት ዘመኑ በሞስኮ አቅራቢያ በምትገኝ ፍሪያዚኖ በተባለች ትንሽ ከተማ ውስጥ በጣም ቀላል እና የድሃ ህይወት ነው የኖረው። ሚስቱ ራኢሳ በካንሰር በሽታ ቀድማው የሞተች ሲሆን እሱም በጡረታ አበል ብቻ እየተደገፈ በብቸኝነት ኖሯል። ፔትሮቭ እ.አ.አ. ግንቦት 19 ቀን 2017 በ77 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
ፔትሮቭ ሁልጊዜ ስለራሱ ሲናገር፦ “እኔ ጀግና አይደለሁም፤ በሰዓቱ ተረኛ የነበርኩ እና ስራዬን በአግባቡ የሰራሁ መኮንን ነኝ” ይል ነበር። ነገር ግን የእሱ “ስራዬን በአግባቡ ሰራሁ” የሚለው ውሳኔ ዛሬ የሰው ልጅ በምድር ላይ እንዲኖር ያደረገ ታላቅ የሰብአዊነት ታሪክ ነው።
የፔትሮቭ ታሪክ የቴክኖሎጂ ውጤቶች (እንደ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም ኮምፒውተሮች) ምንም ያህል ቢራቀቁ የመጨረሻውን ወሳኝ ውሳኔ ለመስጠት የሰው ልጅ የሰከነ አእምሮ እና ህሊና ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ትልቅ ማሳያ ነው።
ምንጭ፡- የተባበሩት መንግሥታ ይፋዊ ድረ ገጽ፣ ብሪታኒካ፣ ቢቢሲ እና ታይም መጽሔት
ሳምንቱ በታሪክ
የኢትዮጵያ እና ጣሊያን የሠላም ሰምምነት
የኢታሎ-ኢትዮጵያ የሰላም እና የወዳጅነት ስምምነት ነሐሴ 2 ቀን 1920 ዓ.ም በሮም ከተማ በአልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን (በኋላ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ) እና በጣሊያኑ ፋሺስት መሪ ቤኒቶ ሙሶሊኒ መካከል የተፈረመ የ20 ዓመት ውል ነበር።
የስምምነቱ ዋና ዓላማ በሁለቱ ሀገራት መካከል ዘላቂ ሰላምን ማስፈን፣ ማናቸውንም ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ መፍታት፣ እና ኢትዮጵያ በአሰብ ወደብ በኩል የነፃ ንግድ ቀጠና እንድታገኝ የሚያስችል የኢኮኖሚ ትብብር መፍጠር ነበር ። ራስ ተፈሪ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለማጠናከር ሲሉ ስምምነቱን ቢፈርሙም ሙሶሊኒ ግን ውሉን የተጠቀመው የፋሺስትን የጥፋት ዕቅድ ለመሸሸግ እና ለወረራ ጊዜ ለመግዛት ነበር።
ይህ የሰላም ስምምነት በተግባር የቆየው ለስድስት ዓመታት ብቻ ሲሆን እ.አ.አ. በ1934 የፈነዳውን የወልወል የድንበር ግጭት ተከትሎ ጣሊያን ውሉን ሙሉ በሙሉ በመጣስ ጉዳዩን በሰላም ለመፍታት ፈቃደኛ ሳትሆን ቀረች።
በመጨረሻም ጥቅምት 1935 የፋሺስት ጣሊያን ጦር ስምምነቱን ወደ ጎን በመተው ኢትዮጵያን በግፍ ወሯል፡፡ ይህም ክስተት በታሪክ የሙሶሊኒን ዲፕሎማሲያዊ ማታለል እና የዓለም መንግስታት ማኅበርን ደካማነት በጉልህ ያሳየ ታሪካዊ ምዕራፍ ሆኖ ተመዝግቧል።
ምንጭ፡- “የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1848 እስከ 1966” -በፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


